ኢትዮጵያ ወንጌላውያን ለአቅመ አሳዳጅነት መድረሳችን ይሆን? ቀዳሚ ማስታወሻ፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያንና በኢትዮጵያ ወንጌላውያን መኻከል ድልድይ እንድንሠራ ለማመልከት የሞከረ ሀቲቴ ነው(መደምደሚያውን ይመለከቷል)። ለመጻፍ ያነሳሳኝ የ ”ካውንስሉ” መቋቋም አንደኛ ዓመት ልደት ሲሆን የቅርብ ጊዜውን የወንጌላውያን ስደት በሰፊው አትቼአለሁ። ለካውንስሉ መቋቋም ዋና ገፊ ምክንያት ያ ስደት ሳይሆን አልቀረም ብዬ ገምቼአለሁና። በግርጌ ማስታወሻ ሊገባ ይችል የነበረን ሃሳብ በሀቲቱ ውስጥ በቅንፍ አስቀምጬአለሁ። በግርጌና በጽሑፉ መኻከል በመመላለስ የአንባቢዬ ሃሳብ እንዳይበተንብኝ ጠንቃቃ መሆኔ ነው ። በመግቢያዬ እንዳገራችን ወግና ልማድ የእግዚአብሔር ሰላምታዬ ይድረስዎት እላለሁ። የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት ሲፈነዳ ሊመራው የተዘጋጀ ኅይል በወቅቱ አልነበረም።ከዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመራበትን አስተዳደር መምረጥ እንዲችል የተለያዩ አማራጮች እየቀረቡ ነጻ የሕዝብ ውይይት ይደረግባቸው ተጀምሮ ነበር። ይሁን እንጂ ሶሺያሊዝምን ለኢትዮጵያ ብቸኛው መድኅን አድርገው ብዙ ወገኖች ስለተቀበሉት ሌሎች አማራጮች ከቁምነገር ሳይጣፉ ቀርተዋል። ደርግ በትረ መንግሥቱን ለመጨበጥ “ታሪክ የጣለብኝ አደራ ነው” (እግዚአብሔር ያሸከመኝ ኃላፊነት አይል ነገር)* ያለው ደርግም (ሙሉ ስሙ ጊዚያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ነበር) ይኸንኑ ርዕዮተ ዓለም ተከትሎ ነበር አገዛዙን የዘረጋው። ሙት ወቃሽ አያድርገኝና ያ መንግሥት ነበር በአነሳሱ ገራም መስሎ በኋላ ላይ ወንጌላውያንን በጭቃ ጅራፉ የገረፈን። እንደ አንድ ወገን አስጨነቀን፤ አዋከበን። የመከራው ጥልቀ ት ከአንዱ ቤተ እምነት ሌላው ቤተ እምነት፤ ከአንዱ ክፍለሀገር ሌላው ክፍለ ሀገር ይለያይ ነበር ( በሥፍራው እንደሚሠ...