Skip to main content

ኢትዮጵያ ወንጌላውያን ለአቅመ አሳዳጅነት መድረሳችን ይሆን?

 

ኢትዮጵያ ወንጌላውያን ለአቅመ አሳዳጅነት መድረሳችን ይሆን?

ቀዳሚ ማስታወሻ፡

  1. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያንና በኢትዮጵያ ወንጌላውያን መኻከል ድልድይ እንድንሠራ ለማመልከት የሞከረ ሀቲቴ ነው(መደምደሚያውን ይመለከቷል)።

  2. ለመጻፍ ያነሳሳኝ ”ካውንስሉ” መቋቋም አንደኛ ዓመት ልደት ሲሆን የቅርብ ጊዜውን የወንጌላውያን ስደት በሰፊው አትቼአለሁ። ለካውንስሉ መቋቋም ዋና ገፊ ምክንያት ያ ስደት ሳይሆን አልቀረም ብዬ ገምቼአለሁና።

  3. በግርጌ ማስታወሻ ሊገባ ይችል የነበረን ሃሳብ በሀቲቱ ውስጥ በቅንፍ አስቀምጬአለሁ። በግርጌና በጽሑፉ መኻከል በመመላለስ የአንባቢዬ ሃሳብ እንዳይበተንብኝ ጠንቃቃ መሆኔ ነው ።

በመግቢያዬ እንዳገራችን ወግና ልማድ የእግዚአብሔር ሰላምታዬ ይድረስዎት እላለሁ።


የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት ሲፈነዳ ሊመራው የተዘጋጀ ኅይል በወቅቱ አልነበረም።ከዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመራበትን አስተዳደር መምረጥ እንዲችል የተለያዩ አማራጮች እየቀረቡ ነጻ የሕዝብ ውይይት ይደረግባቸው ተጀምሮ ነበር። ይሁን እንጂ ሶሺያሊዝምን ለኢትዮጵያ ብቸኛው መድኅን አድርገው ብዙ ወገኖች ስለተቀበሉት ሌሎች አማራጮች ከቁምነገር ሳይጣፉ ቀርተዋል።

ደርግ

በትረ መንግሥቱን ለመጨበጥ “ታሪክ የጣለብኝ አደራ ነው” (እግዚአብሔር ያሸከመኝ ኃላፊነት አይል ነገር)* ያለው ደርግም (ሙሉ ስሙ ጊዚያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ነበር) ይኸንኑ ርዕዮተ ዓለም ተከትሎ ነበር አገዛዙን የዘረጋው። ሙት ወቃሽ አያድርገኝና ያ መንግሥት ነበር በአነሳሱ ገራም መስሎ በኋላ ላይ ወንጌላውያንን በጭቃ ጅራፉ የገረፈን። እንደ አንድ ወገን አስጨነቀን፤ አዋከበን። የመከራው ጥልቀት ከአንዱ ቤተ እምነት ሌላው ቤተ እምነት፤ ከአንዱ ክፍለሀገር ሌላው ክፍለ ሀገር ይለያይ ነበር (በሥፍራው እንደሚሠራው አለቃና ካድሬ ጨካኝነት የተወሰነ ሳይሆን አልቀረም)።


መከራ ማብዛቱን ክርስትና ተስፋፍቶ አብዮቱን ወደ ፊት የሚያራምደው ሕዝብ ቁጥር እንዳይቀንስ ወይም ለሚቀለብሰው ወገን ሚዛን እንዳይደፋለት መቆጣጠሪያ አደረገው።“ሃይማኖት የሰፊው ሕዝብ አደንዛዥ ዕፅ ነው” ይል አልነበር?


ከወሰዳቸው የማዋከብ እርምጃዎች የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፦

  1. መፈክር አሰሙ፦የመፈክርን ነገር ካነሳሁ አይቀር ሦስቱን ላስታውሳችሁ

    • “አድሃሪያን/ ፀረ አብዮተኖች ይውደሙ” የሚለው አንዱ ሲሆን የራስን ወገን ይጥፋ ማለት እንደሆነ የገባኝ ዘግይቶ ነበር።

    • “ኢምፐሪያሊዝም ይውደም” የሚለው ሌላው ሲሆን “ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ” ደርግ ላይ ጥርስ ያስነከሰበት፤ እንደ አገር በሁላችንም ላይ ያስነከሰብን ሳይሆን አይቀርም

    • “ከሁሉም በላይ አብዮቱ” የሚለው ሦስተኛው ሲሆን ለእኛ የሚመቸን አልነበረም። እንዴት ሆኖ? እኛ የምናምነው ከሁሉም በላይ እግዚአብሔር መሆኑን ስለሆነ ልንል የምንችለው መፈክር አልሆነም።

  2. ኪነት ጓድ ውስጥ ገብታችሁ ዝፈኑ (ያን ጊዜ ዘፈን ኃጢአት ነው በሚለው ላይ ልዩነት የነበረ አይመስልም)።

  3. ከቤተክርስቲያን አገልግሎት ጋር በሚጋጭ ሰዓት በየቀበሌው ተሰብስባችሁ ንቁ (አእምሮ አጠባ መሆኑ ነበር)

  4. አምልኳችሁን አቋርጣችሁ ቤተክርስቲያኑን ለቀበሌ ስብሰባ ክፍት አድርጉ አለን

  5. በኋላ ላይ መሰብሰባችን እንዲቋረጥ በርካታ ቤተክርስቲያኖችን (የአምልኮ ሥፍራዎችን) ዘጋ። የሙዚቃ መሣሪያዎቻችንን ወረሰ።ጥሬ ገንዘባቸውን የወሰደባቸውም ነበሩ።

  6. ለወንጌል ሥርጭት ዓይነተኛ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያን ወረሰ፤ እምነታችንን ለሚዋጋ ዓላማ አዋለ

  7. ከዚህ በተረፈ የአካል ቅጣት ያደረሰባቸው፣ በእሥር ቤት የወረወራቸውና እንዲሁም ከአገር በስደት እንዲወጡ ምክንያት የሆናቸው ጥቂት አልነበሩም።

ለዓመታት በእስር ቤት የተረሱትና የተሰደዱት ትምህርትን በመግፋት ወይም በማጠናቀቅ፣ ትዳር በመመሥረት፣ የሥራ ዕድልና ልምድ በማግኘት ከእኩዮቻቸው ጋር ሲነጻጸር ወደ ኋላ ቀርተዋል። እህቶች የመውለጃ ዕድሜያቸው ባክኖባቸዋል። በእስር የተወረወሩት ወንጌልን የመንገር ዕድላቸው በእስር ቤቱ ተገድቧል። እነዚህ ሁሉ ዕድሎች አምልጠዋቸዋል። በእርግጥ «አንበጣና ደጎብያ ኩብኩባና ተምች የበላቸውን ዓመታት እመልስላችኋለሁ።» ኢዮ 2:25 እንደሚለው እግዚአብሔር ያደረገላቸው አልጠፉም።


ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች


ደርግን የሚወጉ ነገር ግን ለሶሺያሊዝም/ለኮሚኒዝም እንሞታለን የሚሉቱ ሌሎቹም ቢሆኑ ዝም አላሉንም። በስድብ፣ በማስፈራራትና በዛቻ ተገዳድረርውናል። አዲስ ኪዳናችንን/መጽሐፍ ቅዱሳችንን ቀዳደውብናል። “አሳምነኝ ላሳምነህ ብለው ግግም የሚሏት ነገር ግን ለእኛም ወንጌልን ልንመሰክርላቸው መልካም አጋጣሚ ሆናልን ነበር። “ አንዳንዶች ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፥ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ” (ይሁዳ 1፣22) የሚለውን ቃሉን ለመታዘዝ በር ከፈተችልን።

ጦርነት በነበሩባቸው አካባቢዎች የነበሩ ቤተክርስቲያኖች ደግሞ በጦርነቱ ሁኔታ ተወስነዋል።

በዚህ የሶሺያሊዝም ማዕበል የተወሰዱና (የኮበለሉ) እንዳውም ለሶሺያሊዝም ሲታገሉ በሞት ያጣናቸው ወንድሞች በመኖራቸው በጊዜው አዝነናል።በኋላ ላይ በሕይወት ከተረፉት የተመለሱ እንዲሁም ከእሳቱ የነጠቅናቸው በማግኘታችን ግን ደስ ተሰኝተናል። የተመለሱትንና ከእሳቱ የተነጠቁትን ተከትሎ ግን “ኢሕአፓ መጽሐፍ ቅዱስን ይዛ ጴንጤ መኻል ገብታለች” በማለት ደርግ ክትትሉን አከበደው። ቢሆንም የመመለሳቸውና ከእሳት የመነጠቃቸው ጉዳይ ለእግዚአብሔ ክብር ነበረና የክትትሉ ብርታት ደስታችንን አልቀነሰውም።


በዚህ ሁሉ ውስጥ ብዙዎች የእግዚአብሔር ጸጋ በዝቶልን (ፍጹም ነበርን ባይባልም) በክርስትናችን ጸንተን ቆምን። የሃይማኖት ነጻነትንም ሆነ እኩልነትን ለመጠየቅ ሳይቃጣን የወንጌል ሥራችንን በመሥራት ላይ ብቻ አተኮርን።


የሚሲዮናውያን መውጣት


የአንዳንድ ሚሲዮናውያን መውጣት (አገሪቷን ለቀው የወጡ ነበሩ) ሳይታሰብ መልካም አጋጣሚ የሆነላቸው ወንጌላውያንም ነበሩ። ኃላፊነትን ወስደው በራሳቸው ቆመው ማገልገልን እንዲለምዱ በር ከፈተላቸው።እርስ በእርሳችን እንዳንገፋፋም ሆንን።አንድነት በልዩነት የሚለውን መርኅ ተቀብለን በመተባበር ተግተን ሠራን ። በየቤተ እምነታችን የሚከልለን ድንበርም በጴንጤ ቆስጤ ንቅናቄ መስፋፋት ሽንቁር ስላበጀ ተደባለቅን።የገጠመን የጋራ ፈተና ለመቀላቀላችን ውጤታማነት ግፊት እንዳደረገም አይካድም። እግዚአብሔር በዝማሬዎች ፣ በስብከቶች፣ በምናነባቸው መጽሐፍት፣ በቡድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች፣ በአዳር ጸሎት ፣ በጽሞና ጊዜያችን በኮንፈረንሶች (ባልተዘጉ ቤተክርስቲያኖች)፣ በሱባኤያችን (ሪትሪት) እየተገኘ ጌታ ኢየሱስን ለመመስከር (በቃልና በሥራ) ፣ ለኅብረትና በመከራ ለመጽናት አስጨከነን።እርስ በእርስ እየተጽናናን እየተደጋገፍን በተቀበልነው የመንፈስ ቅዱስ ኃይልና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ደስታ ያንን ዘመን ዘለቅን።

በአጭሩ የደርግ ዘመን መከራን ለመቀበል ሁልጊዜ ተዘጋጅቶ የመውጣትና የመግባት ዘመን ነበር። ያዋከቡን ግን እነዚህ ብቻ አልነበሩም።


ቤተሰብና ጎረቤት


    በእምነታችን የተለየናቸው ማለትም ያልመሰልናቸው የቅርብ ቤተሰቦቻችንና ጎረቤቶቻችንም አሳደውናል። የእነዚህ ወገኖቻችን የሃይማኖት ድርጅቶች (ኦርቶዶክስና እስላምና) መክረውና ዘክረው በመዋቅር ያወረዱት ትዕዛዝ መሆኑን እርግጠኛ አይደለሁም። ሆኖም ዋንኞቻቸው "ልጆቻችን ናቸው ተዉ አታሳዷቸው” ማለታቸውንም አልሰማሁም። ከእስልምና በመጡት ላይ የመግደል ሙከራ ፣ ድብደባና የልጅነት ውርስን መካድ የገጠማቸው ነበሩ።


    ብዙዎቻችን ከኦርቶዶክስ የተገኘን እንደመሆናችን መጠን የዛኑ ያህል መከራውም የሰፋው ከኦርቶዶክሳውያኑ ነበር። የአምልኮ ሥርዓታችን ሲያዩትና ዶክትሪናችንን ሲመለከቱት ለዘመናት ከለመዱትና ከሚያውቁት የተለየ ሆነባቸው። ስለዚህ ሳይሆን አይቀርም እምነታችንን መጤ ሃይማኖት አሉት። ተንኮለኛ ባዕዳን አገሮች ኢትዮጵያን ለመጉዳት ያመጡት አድርገውም ቆጠሩት። የእናት አባት ሃይማኖትን መተዋችንን ተጠየፉት። እንደ ክህደት አዩት። ይባስ ብለን ሌሎችንም እንዳናስኮበልል ሠጉብን። ልጆቹ «እምነቱንና አካሄዱን» እንዲተው የሚፈልግ ስለዚህ ፍላጎታቸው ይውገራቸውና በእኔ በኩል ኦርቶዶክስ ሆነን እንድንቀጥል በመፈለጋቸው አልፈረድኩባቸውም። እዚያ ግብ ላይ ለመድረስ የመረጡትና የተከተሉት ዘዴ ግን ከማሳደድ የሚመደብ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።


  1. የያዙት ጫፍ ምን እንደሆነ ባላውቅም ሲጀምር ስማችንን አጠፉት። እንዲህ እያሉ፦

    • ሣንቲም ከኮርኒስ በመወርወር ገንዘብ ከሰማይ ይወርድላችኋል እያሉ ያታልላሉ

    • ክርስቶስ ከእኛ ይወለዳል በማለት ልጃገረዶችን ያማግጣሉ

በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ» ማቴ 5:11 በሚለው ቃል ተጽናናን እንጂ በዚህ ስም ማጥፋት አልታወክንም።ከስም ማጥፋት አልፈው የደበደቧቸውም ነበሩ።

  1. ሲቀጥል ከዕድር ያስወጧቸው፣ የቀብር ሥፍራ የከለከሏቸው፣በዘመድ ቀብር ላይ እንዳይገኙ ያገዷቸው ነበሩ። እንዳውም አስከሬን ከተቀበረበት ሥፍራ አውጥተው ሜዳ ላይ የተውበት አጋጣሚም ነበር(ሰምቼአለሁ)።

በሃዘን ተመትቶ ድድቅ ጨለማ በገባ እንዲሁም ለመጽናናት የመጨረሻ ስንብት ማድረግ በሚያስፈልገው ሰው ይህን ማድረግ ያለ ጥርጥር ጭካኔ ነበር። ለሃዘንተኛው ሸክሙ የከበደ፣ ሕማሙም ታላቅ የነበረ መሆኑ የሚሸሸግ አይደለም።የቀብር ሥፍራ መስጠት ግዴታ ነበረባቸው ለማለት ሳይሆን ርኅራኄ ተሰምቷቸው ባይከለክሉ ኖሮ ግን እጅግ ለበረከት በሆነ ነበር-ሊያውም ለሚጋሩት ሃዘን ለማለት ነው። በእኛ በኩል የጣልናትን ቤተክርስቲያን እንደባለ መብት የቀብር ሥፍራ መጠየቃችንም የሚያስደንቅ ሊመስል ይችላል።ነገር ግን ከኦርቶዶክስ ጋር እትብታችን የማይቆረጥ መሆኑን የሚያመለክት ሳይሆን ይቀራል ትላላችሁ?


የቀብር ሥፍራ ከኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ማግኘት መብታችን እንዳልነበረ የሚያሳይ ታሪክ ልጥቀስ፦ በቅርቡ ለወንጌላውያን የተለየ የቀብር ሥፍራ እንደተሰጠ የሚታወቅ ነው። ታዲያ አንዱን የቤተክርስቲያን ሽማግሌ (ወዳጄ ነው)፦ “ የቀብር ሥፍራ ለይሖዋ ምስክሮች ትሰጣላችሁ ወይ?" ብዬ ጠየቅሁት። እርሱም “እንዴት ተደርጎ? እኛ የወሰድነው ለወንጌላውያን አባላት ነው” ብሎ መልሶልኛል። ስለዚህ መከልከል በእኛ ሲሆን ያምርብናል በኦርቶዶስክ ግን አያምርባትም ለማለት ካልሆነ በስተቀር የቀብር ሥፍራ ባለመስጠታቸው አያስፈርድባቸውም እላለሁ። ሃዘኔታቸውን ለሃዘንተኛው ሊያሳዩ በቻሉ መልካም በሆነ ነበር ማለት ግን የሚያስኬድ ይመስለኛል።


በነገራችን ላይ ቢያሳድዱንም ያለ ኦርቶዶክሳውያን ወንጌልን ማድረስ እንቸገር እንደነበር እገነዘባለሁ። የአንበሳውን ድርሻ ወስደው የአገሩን ሰላም ጠብቀዋል።በመሆኑም እንደልብ ተዘዋውረን አገለገልን።በየትኛውም ሥፍራ በመገኘታቸው ከማኅበረሰቡ መገናኛ (Contact Point) ሥፍራ ሆነውልናል።ለወንጌል እዳሪ አውጥተውልናል። ሃይማኖታቸውንና ሃይማኖታችንን በመተዋችን ደስ ባልተሰኙ ዘመዶቻችንን ላይ እየኖርን ማለትም ምግባቸውን እየበላን፣ በጎጇቸው እየኖርን፣ የቀንና የሌሊት ልብስ እየገዙልን (ብዙዎቹ ተበድረው ተለቅተው ነበር) ፣ የኪስ ገንዘብ እየሰጡን መሆኑ ይታወሳል። በእርግጥ ይኸንን ዕድል ያልሰጡና ልጆቻቸውን ከቤታቸው ያባረሩ፤ ልጅነታቸውንም የካዱ ይገኛሉ። አብዛኞቹ ግን ተሸክመውናል (አሁን ላይ ኦርቶዶክስ ካልሆኑ ወላጆች የተወለዱ ብዙ ወንጌላውያን ስላሉ ከኦርቶዶክሳውያን ያገኘነውን በረከት እንዲገነዘቡ ቢያግዝ ለማለት ነው ይህን ሃሳብ እዚህ ላይ የሸነቀርኩት)።


    ይኸን ስጽፍ ያየ አንድ ጓደኛዬ “ኧረ ይኸን ሁሉ ተወው፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ቀደም ብላ ወደ አማርኛ ባትተረጉመው ኖሮ ወንጌላዊ እምነትን ይኸን ያህል ማሰራጨት ቀርቶ ኢትዮጵያ እንደ መኻከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሆና ታርፈው ነበር” በማለት ሞግቶኛል። እነዚህ ታሪኮች ከኦርቶዶክሳውያን ጋር የአንድ ወገንነት ስሜት እንዲሰማን አያደርጉም ትላላችሁ?


የኢህአዴግ መንግሥት


    ለማንኛውም ያ የስደት ዘመን አለፈና የኢህአዴግ ጊዜ መጣ። ለወንጌላውያንም ጸሐይ ወጣችልን። ጥርሱን በማርክሲዝም ሌኒንዝም የነቀለው ኢህአዴግ ለእኛ የሃይማኖት ነጻነትን ሰጠን። ኦርቶዶክሶያውያንና ሙስሊሞችን በመከፋፈል ቢወቀስም እኛን በተመለከተ ግን ያለምንም ፍርሃት የተቀበልነውን ወንጌል እንድንሰብክ ፈቀደልን ወይም አልከለከለንም። ትልቁ ችግራችን የነበረውን የቀብር ሥፍራ አለማግኘትንም አቃለለልን። በአንዳንድ አካባቢዎች ቦታ ለይቶ ሰጠን (ቀድሞውንም ቢሆን የቀብር ሥፍራን ሊያዘጋጅንል ይገባው የነበረ መንግሥት ነበር እላለሁ)። ከአዲስ አበባ ውጭ ለሚገኙ ለአንዳንድ ቤተክርስቲያኖች ደርግ ወስዶባቸው የነበሩን ንብረቶችም መለሰላቸው። ይደነቃል አይደል? አዎ በዚህ ሥራው አንዳንዶች ኢህአዴግን አድንቀዋል።


ይህን ሲያደርግ ኢህአዴግ ምክንያቶች ነበሩት ይባላል። በተባራሪ ወሬ የሠማኋቸው እነሆኝ፦


  1. አሁን በሕይወት የሌሉት የተከበሩ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር (አቶ መለስ ዜናዊ) “ፖለቲካ ውስጥ አትግቡ እንጂ ማንም አይነካችሁም። እምነታችሁን ማስተማር ትችላላችሁ” ብለው ነበር ይባላል። (እውነት ተናግረው ከነበረ ሲደርስብን የነበረውን ወከባ ተረድተው አዝነውልን ሳይሆን አይቀርም እላለሁ።)

  2. በቀ.ኃ.ሥ. ዩኒቨርስቲ (የኋላው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ) ይማሩ በነበረበት ጊዜ የመኝታ ክፍል (ዶርም- የያን ጊዜ አጠራሩ) ጴንጤ ጓደኛቸው የመንግሥትን ሥልጣን እንደሚይዙ ትንቢት ተናገሮላቸው ነበር ይባላል። ይኸው ትንቢት በመፈጸሙ አቶ መለስ ስለወንጌላውያን በጎ አስተያየት ስለነበራቸው ነው የሚል ወሬም ሰምቼአለሁ (ማንነቱን ስላላወቅሁ የታሪኩን እውነተኝነት ከራሱ ማጣራት አልቻልኩም)።

  3. በኢህአዴግ ዘመን ስላገኘነው ነጻነት ሲነሳ ተደጋግሞ ሲወራ ጆሮዬ ጥልቅ ይል የነበረም የይሆናል ምክንያትም አለ። ያም “ተዋሕዶችንና ሙስሊሞችን በቁጥር እንድናሳንስለት  እንዲሁም እምነታቸውን እንድናጣጥልለት በውጤቱም የኢህአዴግ ወዳጅ ወይም ገለልተኛ ሕዝብን ለማብዛት ነው” የሚለው ነው። (እኛ ግን የነፍሳት መጥፋት ግድ ብሎን እንደምንሰብክ የታወቀ ነው።)


የኢህአዴግ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምንም ነጻነትን አልነፈገንም። እኛም ይኸንኑ ለመጠቀም ቸል አላልንም። በውጭ አገርም በአገር ቤትም እየተዘዋወርን ያለመሳቀቅ ወንጌልን ሰበክን። በቁጥርም በዛን።በተለይ ከኦርቶዶክሳውያን ብዙዎች ወደ እኛ መጡ። “በጥጃዬ ባላረሳችሁ የእንቈቅልሼን ትርጓሜ ባላወቃችሁ ነበር” (መሳ 14:18) እንዳለው የተሠራው በአገር ልጅ ሆነና በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ሥርጭቱ ፈጠነ። 


ይህን የተመለከተ ከእስልምና ከመጡ ወንድሞቼ አንዱ “ወንጌል ማድረስ ማለት ጨርሶ ላልሰሙት መናገር እንጂ ለኦርቶዶክሶች መናገርማ ክርስቲያንን ከአንዱ ኪስ ወደ ሌላው ማዛወር ነው” ብሎኛል። ይህን ያለው እንኳ ለኦርቶዶክሶች አንናገር ማለቱ ሳይሆን የሙስሊም ወገኖቹን/ወገኖቻችንን መጥፋት አሳስቦት ትኩረታችንን ወደዛ እንድናዞርለት መማለዱ ነበር።እኛ ግን የምንሰብከው ሰዎች በየግላቸው ስለ ድኅነታቸው (መዳናቸው) እርግጠኛ እንዲሆኑ ለመርዳት እንጂ እከሌ ሙስሊም ነው ወይም ኦርቶዶክስ ነው እያልን እንዳልሆነ ይታወቃል።


የመደመሩ መንግሥት

   (ይህ የተጻፈበትን ዘመን ያጤኗል) የአሁኑ መንግሥት ደግሞ ከኢህአዴግ ይልቅ ልዩ ሆኗል። ከመሪዎቹ በርካቶቹ ወንጌላውያን እንደሆኑ ይነገራል። ”ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ” ማለታቸውን ትተው አንዳንድ ወንጌላውያን በፖለቲካው (የኢትዮጵያውያንን ችግር ለመፍታት እንደመረጡት ዘዴ ጎራ ለይተው) ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ አነቃቅቷቸዋል። በተለይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በወንጌላውያን ዘንድ ልዩ ሰው ሆነው ታይተዋል።እንደ እኛው አንድ ሰው ሆነው በመኻከላችን ለመገኘት የማያፍሩብን እንደሆኑ፣ ለመቅረብ የማይከብዱ፣ በሥልጣናቸው የማይኮፈሱና ደማሪ-አቃፊ መሆናቸው በስፋት ይወሳል። “ከባለሥልጣንና ከሰይፍ ፊት ዞር ማለት ነው” የሚሉ ባይጠጓቸው የእርሳቸው ጥፋት አይመስልም። ለወንጌላውያን ማኅበረሰብ ድጋፍ የሚያደርጉ እንደሆነም ተሰምቷል።ለማሳያነት ያህል ለመልካም ወጣቶች (ስለአገልጋዩ ያለው ውዝግብ እንዳለ ሆኖ) ያደረጉት ይፋዊ ድጋፍ ይገኛል።መጽሐፍ ሲጽፉ ኤዲት ከማድረግ አንስቶ ማሳተሚያ ገንዘብ እስከ መለገስ የደረሰ ውለታ የዋሉላቸው ወንድሞችና እህቶች አሉ ይባላል (ለምሳሌ በምኒልክ ቴሌቪዥን ስመጥሩ ጋዜጠኛ አቶ አዲሱ አበበ ለአርቲስት አስቴር በዳኔ [ስመ ጥር አርቲስት መሆኗን ሰምቼአለሁ]— “አንዳንድ ነገሮችን”ያዳምጧል)። ይህን የመሳሰሉ ድርጊቶቻቸው ብቻ በወንጌላውያን ተወዳጅ ሊያደርጓቸው ይችላሉ።ታሪክ የሠሩት ግን “ካውንስል” በማቋቋሙ ባደረጉት ተጋድሎ ነው።

ለመቋቋሙ ገፊ ምክንያት እንደሆነ የገመትኩትንና ከላይ የጠቀስኩትን ጨምሮ የጋራ ችግሮች ሲገጥሙን መፍታት የሚያስችለን ሕጋዊ “ካውንስል” እንዲኖረን አድርገዋል:: ይኸንን ያደረጉት ያለተቃውሞ አልነበረም። “ከመሠረታዊ ትምህርታችን ጋር የማይገጥምን ትምህርት ከሚያስተምሩ ጋር ማኅበርተኛ አይኮንም” የሚሉ ወገኖች አምርረው ተቃውመዋቸው ነበር። እርሳቸው ግን ወይ ፍንክች! ልባቸውን አጸኑ፣ ዋንኞቻችንን የወንድምነት ልመና ለመኗቸው፤ አግባቧቸው። በሕግ እስኪቋቋም እስከመጨረሻው ገፉበት።


በደርግ ዘመን እንደሆነው የምንጋደልበት መሣሪያ “እምነት” ብቻ እንዳይሆን የሕግና የፖለቲካ መሣሪያም (በእምነት ብቻ መጋደላቸውን እሚቀጥሉ ወይም እሚመርጡ እንደሚኖሩ አምናለሁ) በእጃችን አስገቡልን ማለት ነው። መቼም እንዲህ እንዲያደርጉ ግድ ያላቸው ክርስትናቸው የምር መሆኑና ለወንጌላውያን ያላቸው ቀረቤታ ይመስለኛል።የኢሃዴግን መንግሥት ላገለገሉበት ሥራ ያገኙት ሥልጠናና ልምምድም አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችል ይሆናል።


    ታዲያ ስለኢትዮጵያ ከገለጹት ራዕይ በተጨማሪ በእነዚህ ድርጊቶቻቸው ጥቂት የማይባሉ ወንጌላውያን ክርስቲያኖች ለእርሳቸው አስተዳደር ድጋፍ የመስጠት አዝማሚያ ያሳያሉ።ከማዝመም አልፈው አፍቃሪዎችም ያሉ ይመስላል። በሌላ በኩል


  1. የወሰዷቸውን የአንዳንድ እርምጃዎች ትክክለኛነት ያልተቀበሉ

  2. ይወስዷቸዋል ብለው የጠበቋቸውን እርምጃዎች ባለመውሰዳቸው ቅር የተሰኙ

  3. ከተረኞች ጋር ማኅበረኝነት እንደሌላቸው ማረጋገጫ አልሰጡንም የሚሉ

እንደሚቃውሟቸው የማላውቅና የእነዚህን ስሜትም የማልረዳ አይደለሁም።


በእጃችን ወዳስገቡት ሕጋዊና ፖለቲካዊ መሣሪያ ልመለስና ይህ መሣሪያ ለመከላከል ብቻ ሳይሆን በክፉዎች እጅ ሲገባ ለማጥቃትም ሊያገለግል የሚችል መሣሪያ ነው።ለዚህም ነው ለ”አቅመ አሳዳጅነት መድረሳችን ይሆን?” የሚለውን ጥያቄ ርዕስ አድርጌ የመረጥኩት። አሳዳጅነት ሊኖር የሚችለው (የግድ ይኖራል እያልኩ አይደለም) እኛና እነርሱ የሚል ነገር ሲኖር ነው። እኛና እነርሱ የሚልን ሃሳብ መቀየር አሳዳጅና ተሳዳጅ እንዳይኖር መንገድ ይጠርጋል ማለት ነው። የተነሳሁበት ዓላማ በኦርቶዶክሳውያንና በወንጌላውያን መኻከል ድልድይ እንሥራ ለማለት ስለሆነ በመኻከላችን እኛና እነርሱ የሚልን ሃሳብ ማስቀረት አይቻልም ወይ? ለማለት ነው። ይህ እንደሚቻል የፈነጠቀ ታሪክ በቅርቡ ሆኖ ነበር ።በባሌ፣ በአርሲና በሐረር ኦርቶዶክሳውያን የተገደሉ ጊዜና በአዲስ አበባ አካባቢ ሁለት የወንጌላውያን አገልጋዮች የተገደሉ ጊዜ (ሳይወለድ ጨነገፈ እንጂ) በሁለቱ መኻል የአንድ ወገንነት ስሜት ተረግዞ ነበር። ዶግማን (ዶክትሪንን) እና ቀኖናን (ሥርዓትን) አንድ ማድረግ ይቻላል፣ ይደረግም የምል አይደለሁም። ሆኖም ይህ የሕግና የፖለቲካ አቅም ወደ አሳዳጅነት ሳይቀየር በፊት ከኦርቶዶክሳውያን ጋር አንድ ወገን የምንሆንበት አወቃቀር አይኖርም ወይ? ለማለት ነው።


 ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ዘዴ አያጡምና ይልቁንም በነካ እጃቸው ይኸንን እውን ቢያድርጉት ብዬ ተመኘሁ።

እርሳቸው ለማድረግ ባይመቻቸው እንኳ ኦርቶዶክሳውያንና ወንጌላውያን ግን እንደ አንድ ወገን የምንሆንበትን ብልሃት ልናፈላልግ ይገባል እላለሁ።እኛና እነርሱ ብለን መተያየታችን ውሎ አድሮ ለበረከት የሚሆን አይመስለኝም። «እርሱ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁሉ ትጠፋላች፤ ቤትም በቤት ላይ ይወድቃል (ሉቃ 11:17) እንዳለው እንዳይሆንብን እንጠንቀቅ እላለሁ። እንደ አንድ ወገን ስንሆን ለቤተክርስቲያን የሰምረና የአማረ ዘመን እንደሚመጣ አስባለሁም።

ለዘለቄታው እኛና እነርሱ የሚለው ሃሳብ ቀርቶ ኦርቶዶክሳውያንም “እመን ተጠመቅም ትድናለህ”፣ ወንጌላውያንም «ኢየሱስን ጌታህና አዳኝህ አድርገህ ተቀበል ትድናለህ» እያልን እንደ አንድ ወገን የአፍሪካን፣ የኤስያንና የኦሺኤኒያን ሰዎች የክርስቶስ ደቀመዛሙርት በማድረግ ተልእኮ እንደንካፈል ተስፋ አደርጋለሁ። መቼም ጠያቂ አይጠፋም። “አውሮጳ፣ ሰሜን አሜሪካና ደቡብ አሜሪካስ?” የሚል።

በትዕግሥት ስላነበቡልኝ አመሰግንዎታለሁ! እባክዎ ይመርቁኝ/ይባርኩኝ!

.


Comments

Popular posts from this blog

Comparative Theology የነገረ መለኮት ንጽጽር (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት)/ በብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሲኖዳ ሳልሳዊ

 የነገረ መለኮት ንጽጽር  (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት): የወደደ  ሁሉ በነጻ እንዲጠቀምበት ተፖስቷል። ይሁን እንጂ መብቱ በሕግ የተጠበቀ ስለሆነ በየትኛውም መልኩ ለንግድ እንዲውል አልተፈቀድም። ልዩ ልዩ መግቢያ የሚለውን መጀመሪያ ካነበቡ በኋላ የተቀረውን በተመረጠው ቅደም ተከተል ማንበብ ይቻላል። ልዩ ልዩ መግቢያ   ጥምቀት   ትውፊት (ወግና ልማድ)   መካከለኝነት   ጾም የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ መንፈሳዊ ስጦታዎችና በልሳኖች የመናገር ስጦታ   ሥርዐት ንስሐ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ (1)  ድንግል ማርያምን ስለማክበር (2) ለጥያቄዎች መልስ (ሀ) ድንግሊትን ‘የወይን ግንድ (ተክል)’ና የ ‘ሕይወት በር’ የሚል ማዕረግ  ለምን እንሰጣታለን? (ለ) ወደ ድንግል ማርያም መጸለይ ትክክል ነው ወይ? (3) የድንግል ማርያም ድንግልና ዘላለማዊነት (4) ለተቃራኒ አስተያየቶች መልስ (ሀ) “የመጀመሪያ ልጇን” የሚለው ሐረግ (ለ) “ሚስትህ” የሚለው ሐረግ (ሐ) “አብረው ከመሆናቸው በፊት ጸንሳ ተገኘች” (መ) “የመጀመሪያ ልጇን እስክትወልድ አላወቃትም” (ሠ)  “ወንድሞቹ” የሚለው ሐረግ   የቅድስት ድንግል ማርያም  ክብሯ (1) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ድንግል እመቤታችንን አያከብሩም፤ ደግሞም እንድታማልድላቸውም (እንድትማልድላቸውም)  አይጠይቋትም።ከእነርሱ ወገኖች አንዳንዶቹ እንዲያውም ጫጩቱ ከተፈለፈለ በኋላ ዋጋ ከሌለው የዶሮ እንቁላል ቅርፊት ጋር እስከሚያመሳስሏት ይደርሳሉ።ይህ የተጋነነ ማቃለል የመጣው ምናልባት ሮሜዋውያን ካቶሊኮች የተጋነነ ማክበር ስለሚያከብሯት ለዛ ተቃርኖ ከማሳየት አዝማሚያ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን አንዱንም የእርሷን በዓል አያከብሩም።  (2) አንዳንዶቹ የፕሮቴስታንት ወገኖች ድንግል ማርያምን “እህታችን” ይሏታል። (3) በተጨማሪ አንዳንዶቹ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ጌታ ኢየሱስን በድንግልና ከወለደች በኋላ ከዮሴፍ ጋር ጋብቻዋን ፈጽማለች፤ የ‘ኢየሱስ ወንድሞች’  ወይም የ’ጌታ ወንድሞች’ ተብለው የተጠሩ ልጆችን ወልዳለች ይላሉ።  (4) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ቤተክርስቲያናችን ለድንግል እመቤታችን የሰጠቻቸውን አንዳንድ የማዕረግ ስሞችም ይቃወማሉ።  (5) ድንግልን ያለማክበራቸው አንዱ...

ስለ "አስታዋሽ ጾምና በዐሉ" ጥያቄና መልስ

 ስለ "አስታዋሽ ጾምና በዐሉ" ጥያቄና መልስ  ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ፦ ሕልውናችንን-ነጻነትችንን የማረጋገጥና የማስቀጠል አንድነታችንን የመጠበቅና የማጠንከር  በእሴቶቻችን የመደሰት፣ እነርሱን የመንከባከብና የማስተዋወቅ  በረከታችንን የማብዛትና የማካፈል  ኃላፊነቶቻችንን በማኅበር ፣ በማስተዋልና በትጋት እንድንወጣ “ጾሙና በዐሉ" አስታዋሽ ባሕላዊ ምልክታችን ይሁንልን   ጥያቄ 1 ፡ አድማጭ ተመልካቾቻችን እንኳን ደህና መጣችሁ።የከበረ ሰላምታችን ይድረሳችሁ። ዛሬ የምንወያየው ከአቶ ባንቱ ገብረማርያም ጋር ይሆናል። አቶ ባንቱ በሙያው ፋርማሲት ነው። እንደነገረኝ በእምነቱ ደግሞ ባፕቲስት ነው።ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ባሕላዊ ምልክት የሚሆን “ጾምና በዐልን” በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል። የምንወያየውም ስለዚሁ "ጾሙና በዐሉ" ምልክትነት ይሆናል።  አቶ ባንቱ ለመወያየት  ወደ እኛ በመምጣትህ አመሰግንሃለሁ። እንኳን ደህና መጣህ። አንተ እያልኩ ልቀጥል ወይስ አንቱ? መልስ 1፡ ዎገኔ፡   እንኳን ደህና ቆየኸኝ። ለአድማጭ ተመልካቾቻችሁም ሰላምታዬ ይድረስልኝ። አንተ በለኝ። የሚያውቀኝ ሁሉ አንተ ነው የሚለኝ።  ጥያቄ 2 ፡ እሺ  አንተ እያልኩ እቀጥላለሁ። አቶ ባንቱ፣ ምናልባትም ብዙ ሰው ስለማያውቅህ  እስቲ ስለራስህ በአጭሩ ንገረን። ወዲያውም መክፈቻ ይሆነናል መልስ 2 ዎገኔ ፦ አስቀድሜ ይኸን ዕድል ስለሰጠኸኝ ላመሰግንህ እወዳለሁ። አድማጭ ተመልካቾችህንም ጊዜ ወስደው  ውይይቱን  ስለሚከታተሉ ላመሰግናቸው እወዳለሁ።አዎን፣ ባንቱ ገብረማርያም እባላለሁ።እንደነገሩኝ የተወለድኩት ሽርካ በዛሬ አጠራሩ በአርሲ ዞን ነው።ነፍስ ያወቅሁትና ትምህርት ...