Skip to main content

ከቄስ ( ዶ/ር ) ቶሎሳ ይልቅ


 አድማጭ ተመልካቾቼ አንደምን ከረማችሁ? የአብርሃም አምላክና አምላካችን የተመሰገነ ይሁንና እኔ ደህና ነኝ።"ከቄስ (ዶ/ር ) ቶሎሳ ይልቅ" በሚል ርዕስ ያዘጋጀሁትን  የሚከተለውን መልዕክቴን እንድትከታተሉልኝ በታላቅ አክብሮት እጠይቃችኋለሁ።

ባንቱ ገብረማርያም ነኝ

ከቄስ (ዶ/ር) ቶሎሳ ይልቅ

          ቄስ (ፓስተር) ዶ/ር ቶሎሳ  ጉዲና የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን በአትላንታ/ጆርጂያ ፓስተር መሆናቸው በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ይመስለኛል። በበኩሌ የማከብራቸውም ሰው ናቸው። በወንጌላውያን መኻል ለበርካታ ዐመታት ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የተናገሩ፣ ያሳሰቡና የጸለዩ መሆናቸውን ሰምቼአለሁ።በነገዳቸው የተደራጁትን የወንዛቸው ልጆችን ወቀሳ ተቋቁመው ለመላው ኢትዮጵያዊ ሲጮኹ የኖሩ ናቸው።

          ስለ እሬቻ የሰጡት ትምህርት እስከዛሬ እንደሞዴል የማየው ነው። እሬቻን እንዳይከተሉና እንዳያስፋፉ የአሁኖቹን የመንግሥት ዐላፊዎች የመከሩበትንም ጊዜ አስታውሳለሁ።

          የወንጌላውያን ሽማግሌ ብቻ ሳይሆኑ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌ አድርጌ አያቸዋለሁ። ይህን መደላድል የማስቀምጠው ስለእርሳቸው ያለኝን አስተያየት ለማስታወቅና ይኸው ሐሳቤ የጸና መሆኑን ለማስጮህ ነው።አስተያየቴን አልጠየቁኝም፣ የሚጨምርላቸውም ሆነ የሚቀንስባቸው ነገር እንደማይኖርም ጠንቅቄ አውቃለሁ። መደላድሉን አስቀድሜ  ማስቀመጤ ወንድሞችንና እህቶችን “አይዟችሁ አትደንግጡ” ለማለት ያህል ነው።

           ከዚህ በታች ያለውን  የማቀርበው ከጥቂት ቀናት በፊት በአንደኛው ዩ-ትዩብ መልዕክታቸው ሲናገሩ የሰማሁት መነሻ ሆኖኝ ነው። ንግግራቸውን በትክክል ያልተረዳሁት ከሆነ ለመታረም ፈቃደኛ ነኝ። በዚህ በአርቲፊሺል ኢንተልጀንስ ዘመን አይታወቅምና ያልተናገሩት ከሆነም ይቅርታ ለመጠየቅ አይተናነቀኝም።

 በንግግራቸው ያነሷቸው አራት ነጥቦች ናቸው።እያንዳንዳቸውን በራሴ አገላለጥ እያስቀመጥሁ ተያያዡን አስተያየቴን አስከትላለሁ። ትንሽ ረዘም ስለሚል በትዕግሥት እንድትከታተሉልኝ ላስቸግራችሁ እወዳለሁ። አሁን ወደ ሐተታዬ እንድገባ ይፈቀድልኝ።

1.    ቄስ (ዶ/ር ) ቶሎሳ  የተናገሩት አንዱ ነጥብ "ለሕዝብ አንድነትና ሰላም አይበጅምና መንግሥትና ፓርላማው የክልል አስተደደሩን ያፍርስ/ይለውጥ" የሚል ነው።

    የክልል አስተዳደር ጉዳይ ከዚህ ቀደም ሲተችበት  የቆየ ነው። የእርሳቸው ንግግር ይኸንኑ  ያጸናል። ያንን ሰሚ ጆሮ  በመጥፋቱ የብሔርተኝነት አስተሳሰብ ሥር እየሰደደ እንደመጣ በብዙዎች ሲተነተን ሰምቼአለሁ።እርሳቸው መድገማቸው ለጉዳዩ ትኩረት ማግኘት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጥርጥር የለኝም። በጎሳና በነገድ መቧደንና መሥራት  ያደገባቸውና የለመደባቸው ሰዎች ፥ የትኛው ጠበል በአብ ፥በወልድ፥ በመንፈቅ ቅዱስ ስም ቢረጭባቸው እንደሚለቃቸው ባይነግሩንም፣ ክልል ይፍረስ ማለታቸው ገምቢ አቅጣጫን ማመልከታቸው እንደሆነ ተሰምቶኛል። ጉዳዩን በድፍረት በማንሳታቸውም አመሰግናቸዋለሁ።ለዚህ ግንዛቤ ማደግ ‘ለአማራ ብሔርተኝነት መነቃቃት’ ምሥጋና ይግባውም እላለሁ። ክልል ይፍረስ ብለው አማራጩን በተጨማሪ ጠቁመውን ቢሆን ኖሮ የተሟላ ሐሳባቸውን ባገኘነው ነበር። ዋይ ነዶ!

2.    ቄስ (ዶ/ር) ቶሎሳ ከተናገሩት ሁለተኛው ነጥብ "ኢትዮጵያን ለዘመናት ወደ ኋላ አስቀርቷት ከነበረ ማነቆ እያላቀቃት ስለሆነ በአሁኑ መንግሥት የተያዘውን የእድገት ጉዞ አንጎትት" የሚል ነው።

ይኸንን በጸሎት ለሚተጉ ወገኖች የጸሎት ጥያቄን በማቅረብ አልፈዋለሁ። ጸልዩልን፡- እግዚአብሔር

        Ø 1. በኢትዮጵያ የተገኘውንና የሚገኘውን ዕድገትና ፍሬውን  የኢትዮጵያውያን እንዲያደርግልን/እንዲሆንልን

        Ø 2. የሸገር ከተማ ሥራውን፥ እንዲሁም የኮሪደሩ ልማቱን በመሠሪነትና በኅይል ሥራ ለተፈናቀሉ፣ ብትንትናቸው እንዲወጣ ለተደረጉና ለድህነት  ለተወረወሩ እንዲሁም ታሪካቸው ለተሰረዘባቸው ወገኖች መታወሺያቸው እንዲያደርግልን/ እንዲሆንልን። አሜን!

3.    ከቄስ (ዶ/ር ) ቶሎሳ ከተናገሩት ሦስተኛው ነጥብ  "ነፍሳት ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዙ። በተዋረድ ያሉ አስተዳዳሪዎችን ጨምሮ ሕዝብ የማያከብር ከሆነ እግዚአብሔር ሕዝቡን ይቀጠዋል" የሚል ነው።ይህ የእግዚአብሔር የዘላለም መመሪያ እንደሆነም አስምረውበታል።

በሌላ አነጋገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይና በተዋረዳቸው ላሉ ባለሥልጣኖች ይገዛ፣ ያክብራቸው። አለበለዚያም እግዚአብሔር ይቀጣቸዋል ማለታቸው ሆኖ ታይቶኛል።

          በመጀመሪያ ደረጃ አንድ የፕሮቴስንት (ወይም መሠረቱ ፕሮቴስታንት የሆነ) ሰባኪ/አስተማሪ "በማናቸውም ሁኔታ ለበላይ ባለሥልጣናት ተገዙ” ብሎ ሲናገር መስማት ግር ይለኛል። ሊለወጥ የሚያስፈልገውን ሥርዓት እምቢ ማለትና መቃወም የፕሮቴስታንት ጀማሪ መሪዎች በሥራቸውና በቃላቸው ያስተማሩን መስሎኛልና። ያንን ስላደረጉ ነው ዛሬ እርሳቸውን ጨምሮ ፕሮቴስታንቶች የሚያስተምሩትን ያገኙት። "በማናቸውም ሁኔታ ለበላይ ባለሥልጣን ተገዙ” ሲባል ያንን “የአባቶችን ትምህርታቸውንና አካሃዳቸውን” አለመከተል ይሆን? የሚል ጥያቄ ያጭርብኛል።

          የእኛ ሥርዐት በቆመበት ጊዜ፥ ይህ ትምህርት በአጽንኦት መሰጠት አለበት ካልተባለ በስተቀር፥ ሊለወጥ የሚገባው እየታየ “እምቢ አትበሉ” ማለት ለበረከት የሚሆን አይመስለኝም።

          ለማንኛውም የነገረ መለኮቱን ትንተና ለመስጠት የበቃሁ አይደለሁም። ወንበር ላይ ተቀምጬ መማርን ስለለመድኩ እንጂ በዶ/ር ቶሎሳ እግር ሥር ተቀምጬ መማር የሚገባኝ ነኝ። ያም ሲሆን እንደ ተማሪ ጥያቄዎችን እጠይቃለሁ።

          1.     በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሞና በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያለው ጦርነቱ፣ መፈናቀሉ፣ ውድመቱ፣እገታው፣ የታወቁ ግለሰቦች እየተመረጡ መገደላቸው፥ አንድን ብሔር በሌላው ላይ ማነሳሳቱ  ሁሉ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ትዕዛዝ ወይም በእርሳቸው አውቅና የሚደረግ እንደሆነ በክቡር አቶ ታዬ ደንደአ ተገልጦ ፥ በኋላም በሁለተኛና በሦስተኛም ሌሎች ምስክሮች ዝርዝሩ ተብራርቷል። ይህንን “ያጣ ወሬ ነው” ብለው ያጣጣሉ አሉ። ቄስ (ዶ/ር) ቶሎሳ እንደዚህ ዐይነቱን ሰው በሕይወቱ ችግር ያለበት ሊሆን ስለሚችል መደመጥ እንደሌለበት የሚመክሩ ይመስላል።እኔ ግን ክርስቶስ ከሙታን መነሳቱን ባመንኩበት መከራከሪያ አኳያ ሳየው የታዬ ደንድአን ምስክርነት እውነትነት አምኛለሁ። ("አንበሶቼ! አጠፋሁ እንዴ?")[i] በሚለው መጣጥፌ ሰፋ አድርጌ ጽፌበታለሁ፤ በነገራችን ላይ ከዚያ ቀደም ሲል ወሬዎቹን ሰምቼአለሁ። እነዚያን ያደረጉትና  ያስደረጉት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ብዬ ግን አስቤ አላውቅም)። ታዲያ በእነ ታዬ እማኝነት ሲመዘን  ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ክፉ የሚባልን የበላይ ባለሥልጣን መስፈርት"ን እንኳ  ያሟላሉ ወይ? ከእማኝነት ቃሉ መገንዘብ እንደሚቻሉው (ያው እውነት ነው ብዬ ተቀብያለሁ) ጠቅላይ ሚኒስትር ቀድሞውኑ የሚፈልጉት ማጥፋት እንጅ መግዛት አይመስልምና

          2.    እንዳው ለነገሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ነፍስ “በሰው እንጂ በእግዚአብሔር የተሾምኩ ነኝ ብላ እርፍ ብላለች? ያረፈች አትመስልም።ብትልማ ኖሮ ይኸን ሁሉ የሚዘገንን ግፍ ለምን ይፈጽማሉ/ያስፈጽማሉ? የእርሳቸው ነፍስ በእግዚአብሔር ተሾሜያለሁ ብላ ካላረፈች ሌላው በእግዚአብሔር ተሾመዋል የሚለው የምን ቤት ነው?

          3.    እሺ በእግዚአብሔር ተሾመዋል ብለን እንቀበል።ታዲያ በሮሜ ምዕራፍ 13 መሠረት መንግሥትን ከመታዘዝና አስተዳዳሪዎችን ከማክበር ውጭ ምንም መፈናፈኛ የለም ማለት ነው?

          4.    አሁን ባለው ሁኔታ የክልሎች መንግሥታት ከማዕከላዊ መንግሥት በማይስማሙበት ጊዜ በሮሜ 13 መሠረት ነፍሳት ለማንኛው ነው መገዛት ያለባቸው

          5.    ሮሜ ምዕራፍ 13ን የተናገሩት/የጻፉት ሄሮድስና መሰሎቹ ማለትም የገዢ ወገኖች እንዳልነበሩ ይታወቃል። ዛሬ ላይ ሄሮድስ ወይም የገዢ ወገኖች ሲጠቀሙበት እንደ ሄሮድስ መሆናቸውን መጠርጠር አይቻልም? ሄሮድስ እንዲህ አለ፦ «ወደ ቤተ ልሔምም እነርሱን ሰድዶ፦ ሂዱ፥ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ አላቸው።ማቴ 2፥8» (እውነት ሄሮድስ ለሕጻኑ ኢየሱስ ሊሰግድለት ኖሯልን?)

          6.    ለመሆኑ ሕዝብ መገዛት ያለበት የራሱ ላልሆነም ጠቅላይ ሚኒስቴር ነው? (ይኸን የምጠይቀው ፣ ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ አገር ዜጋ ማደጎ ናቸው ፣ ኢትዮጵያዊ መሪ አይደሉም የሚል ወሬ ስለተሰማ ነው)። ይህ ወሬ የሚሲዮናዊውን  የዶ/ር ላምቤን ታሪክ አስታወሰኝ። ዶ/ር ላምቤ የጃንሆይ ወዳጃቸው ነበሩ ይባላል። ጃንሆይ በስደት ላይ በነበሩበት ጊዜ ላምቤ ከኢጣልያን ጋር በመተባበራቸው ግን እንዳዘኑባቸው ከታሪክ መጽሐፍ  ያነበብኩትን አስታውሳለሁ። ለላምቤ ከኢጣልያን ጋር መተባበር አንዱ ምክንያታቸው  ሮሜ ምዕራፍ 13 ነበር ይባላል[ii]።የመተባበራቸው ልክ ኢጣልያን የኢትዮጵያን ሕዝብ በመርዛማ ጭስ ደብድባለች ብለው አውጥተው ከነበረው ዘገባ እስከማፈግፈግ አድርሷቸው ነበ[iii]

          7.    እግዚአብሔር የሚቀጣው ያልታዘዙትን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ያልታዘዙትን መሪዎችም ይመስለኛል። ከግራ ከቀኝ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩና አስተዳደራቸው ቅሬታ እየተሰማ ነው። ይሁን እንጂ የሕዝብ ቅሬታን ካልሰማችሁ እግዚአብሔር ይቀጣችኋል ብለው እርሳቸውንና መንግሥታቸውን ለማስጠንቀቅ ግድ የሰጣቸው አይመስልም።መሪዎችን ማስጠንቀቁንስ ለማን መተዋቸው ይሆን? ብቻ ሲቀጣ በምርጫ ይቀጣል ብለው  እግዚአብሔርን አሳንሰውትና ወስነውት እንዳይሆን?

          8.    የቅጣት ነገር ከተነሳ፣ ለመሆኑ የውስጥ ሥጋታቸው ወይም ሃዘኔታቸው ሕዝብ እንዳይቀጣ ነው? ነው ወይስ መሪዎች እምቢ እንዳይባሉ ለመሪዎቹ ሳስተውላቸው ነው?

          9.    ቅጣትን ማሳየት ብቻ ሳይሆን ምህረትን መጠየቅም አለ። ልገልብጠውና ቢያጠፋም ለሕዝቡ ወይስ ለመንግሥት ባለሥልጣኖቹ ነው እግዚአብሔር ምህረት እንዲያደርግ የሚፈልጉት?

          10.    ክርስቲያን ማን ነው የሚለው ክርክር እንዳለ ሆኖ በኢትዮጵያ ክርስቲያን ያልሆኑ አሉ። ስለዚህ መታዘዙም ቅጣቱም ወንጌላውያኑንና ጴስጤቆስጤውያኑን ብቻ የሚመለከት ነው? ነው ወይስ ነፍሳት ሁሉ በሚለው መሠረት ከነዚህ በስተቀር የሚል ነገር አይኖርም?   

ያው እንግዲህ የሚመረምር ተማሪ ጥያቄ ያበዛል።

         ቀደም ብዬ ከሌላ መምህር የተማርኩት ደግሞ ከቄስ ቶሎሳ ጉዲና ትምህርት ለየት ያለ ነው። እኒያ መምህር R.C Sproul ይባላሉ።  ከእርሳቸው የተማርኩት "በማናቸውም ሁኔታ ነፍሳት ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዙ” ከሚለው ትምህርት ይልቅ ሰፋ ያለ ሆኖ ታይቶኛል። (ያው ተማሪ ብዙ አስተማሪዎች አይደል ያሉት?) ስፕሮል  እንዲህ ይላሉ፦

          «ከእግዚአብሔር ውክልና ከተሰጠው ማዕቀፍ ዐልፎ ትእዛዝ ቢያወጣ ፣ መንግሥትን ቤተ ክርስቲያን (ክርስቲያኖች ማለት ነው) ላትታዘዝ ትችላለች። እንዲያውም እንዳትታዘዝ ብቻ ሳይሆን ፣ ከማዕቀፉ ወጥቶ ስላወጣው ትእዛዙ መንግሥትን እንድትወቅስ ግዴታ አለባት።»[iv] (ትርጉም የራሴ)

          ክልል አስተዳደርንና እሬቻን በተመለከተ ቄስ ቶሎሳ የመንግሥት ዐላፊዎችን መውቀሳቸው ከስፕሮል ማስገንዘቢያ የሚስማማ ነው።ለጠቅላይ ሚኒስትርና ለተዋረዳቸው በማናቸውም ሁኔታ ተገዙ የሚለው ግን ከዚያ ጋር አይገጥምም።

4,  ከቄስ (ዶ/ር ) ቶሎሳ ንግግር  አራተኛውና የመጨረሻው "ውጭ በሚመች ሥፍራ የተቀመጣችሁ፣ ልጆቻችሁንም እዛው ያስቀምጣችሁ የዋሁን የኢትዮጵያ ገበሬ  በመቀስቀስ በጦርነት አትማግዱት/ በዚያም አታድቅቁት" ይላል።

እውነት ነው፥ መቼም በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ጦርነት ባለበት ሁኔታ እንደማይኖር ይታወቃል። ምናልባትም ጥቂት የማይባለው ዲያስፖራ በተመቻቸ ሁኔታ ይኖራል ማለትም ይቻላል። ታዲያ ከብዛት በዲያስፖራው መኻል በክፋት ጦርነት የሚቀሰቅስ አይኖርበትም አይባልም። ተለይቶ በታወቀ ቁጥር እንዲህ ዐይነቱን መውቀስ ተገቢ ነው።

 ነገር ግን በእውነት በደል መኖሩ ተሰምቷቸው፥ ሕዝቡ ይኸንን ለመለወጥ፥ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለበት በሐቅ የሚያስገነዝቡ የሉምን?

ይልቁንስ አገር ቤት ገባ ወጣ እያሉ (አንዳንዶቹም ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ቢሮ  ጎራ እንደሚሉ ይታማሉ) በሕዝብ ላይ የሚደርስ በደልን መግለጥ የማይፈቅዱ፥ የሚደባብቁና የሚሸፋፍኑ እንዲያውም የሕዝብ ሰቆቃ ጉዳይ ሲነሳባቸው ወሬውን የሚያስቀይሱ የሉምን? እነርሱስ ሊወቀሱ አይገባቸውምን? በግሌ ጦርነት ቀስቃሽ አይደለሁም።ጦርነት ውስጥ ባይገባ ኖሮ ምርጫዪ ነበር።አሁንም ቢሆን የሕዝብ እሮሮ መልስ ያገኛል። ሰላምም ይወርዳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እመኛለሁም።ጦርነት ውስጥ የገባው እንደ በጎ ወታደር ሲጋደል ለማድነቅ ግን የምሰንፍ አይደለሁም።

          አዎን ከቄስ (ዶ/ር) ቶሎሳ ይልቅ የታዬ ደንደአና የምስክሮቹ ቃል የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰቆቃ ምንጭ በሐቅ አሳይቷል። የኢትዮጵያን ሕዝብ የተሻለ አስጠንቅቋል። የሚሠራ ስለመሆኑ ወይም የራሱ ችግር እንደሌለው በእርግጠኝነት መናገር ባልችልም የመፍትሔ ሐሳብንም አመልክቷል።

          ይህን መሰናዶ በማቅረቤ ያሳዘንኳቸው ብሆን በዚህ ጥቂት ሞኝነቴ ቄስ (ዶ/ር) ቶሎሳን ይቅርታ ያድርጉልኝ እላለሁ። እርግጠኛ ነኝ ሣሩን (ኮሪደር ልማቱን ወዘተረፈ ማለት ነው) አይተው እንጂ፣ እንደ እነ ታዬ ገደሉን (በንድፍና በእቅድ የሚሠራውን የጥፋት ሥራ ማለት ነው) ለማየት ዕድል አግኝተው ቢሆን ኖሮ፣ ቄስ ቶሎሳ እንዲጠፋ በተፈረደበት ሕዝብ ጫማ  ውስጥ እግራቸውን አስገብተው፣ ሕመሙን ያዩለት ነበር። ሕዝቡ ሕልውናውን በመንግሥትና በተባባሪዎቹ  ላለማጣት  የሚያደርገውን ጥንቅንቅም ያደንቁ ነበር።

ኧረ እንዳውም 'ቦንኾፈርን’[v] ሆነው ይነሱ ነበር።ታዲያ ምን ያደርጋል?

ቸር እንሰንብት

 በነገራችን ላይ መልዕክቱ ፓስተር ለሆኑባት ቤተክርስቲያን አባላት ብቻ ቢሆን ኖሮ አስተያየቴን ከመስጠት እታቀብ ነበር

 

 

 

 

 

 

 



[ii]  Lambie, Thomas Alexander (C) - Dictionary of African Christian Biography

In his interview with General Graziani, Lambie indicated that as Italy was now the power in charge in Abyssinia, and the Haile Selassie government had departed Ethiopia, he would submit to the Italian rulers as admonished in Romans 13:1, “Be subject unto the higher powers.”(KJV) 

[iii] Thomas Lambie - Wikipedia

After Italy occupied Addis Ababa in 1935, Lambie at first submitted to the Italian regime in order to continue his work, going as far as to retract his reports about Italian use of mustard gas in the Second Italo-Abyssinian War

[iv] Sproul, R.C. (2014) What is the Relationship between Church and State? (First edition, Vol. 19.). Orlando, FL: Reformation Trust: Ligonier Ministries. (በነገራችን ላይ ስመጥር የነገረ መለኮት አዋቂ እንደነበሩ ይታወቃል። እንዳናዳምጣቸው ምክንያት የሚሆን በሕይወታቸው ችግር እንዳለባቸውም አላውቅም)

[v] For Love of the World; Bonhoeffer's Resistance to Hitler and the Nazis.pdf This article explores Bonhoeffer’s transformation from nonviolent resistance to active conspiracy, his theological wrestling with truth and responsibility, and his deep conviction that God’s love for the world demanded costly action—even at the risk of being labeled a traitor.

 

Comments

Popular posts from this blog

Comparative Theology የነገረ መለኮት ንጽጽር (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት)/ በብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሲኖዳ ሳልሳዊ

 የነገረ መለኮት ንጽጽር  (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት): የወደደ  ሁሉ በነጻ እንዲጠቀምበት ተፖስቷል። ይሁን እንጂ መብቱ በሕግ የተጠበቀ ስለሆነ በየትኛውም መልኩ ለንግድ እንዲውል አልተፈቀድም። ልዩ ልዩ መግቢያ የሚለውን መጀመሪያ ካነበቡ በኋላ የተቀረውን በተመረጠው ቅደም ተከተል ማንበብ ይቻላል። ልዩ ልዩ መግቢያ   ጥምቀት   ትውፊት (ወግና ልማድ)   መካከለኝነት   ጾም የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ መንፈሳዊ ስጦታዎችና በልሳኖች የመናገር ስጦታ   ሥርዐት ንስሐ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ (1)  ድንግል ማርያምን ስለማክበር (2) ለጥያቄዎች መልስ (ሀ) ድንግሊትን ‘የወይን ግንድ (ተክል)’ና የ ‘ሕይወት በር’ የሚል ማዕረግ  ለምን እንሰጣታለን? (ለ) ወደ ድንግል ማርያም መጸለይ ትክክል ነው ወይ? (3) የድንግል ማርያም ድንግልና ዘላለማዊነት (4) ለተቃራኒ አስተያየቶች መልስ (ሀ) “የመጀመሪያ ልጇን” የሚለው ሐረግ (ለ) “ሚስትህ” የሚለው ሐረግ (ሐ) “አብረው ከመሆናቸው በፊት ጸንሳ ተገኘች” (መ) “የመጀመሪያ ልጇን እስክትወልድ አላወቃትም” (ሠ)  “ወንድሞቹ” የሚለው ሐረግ   የቅድስት ድንግል ማርያም  ክብሯ (1) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ድንግል እመቤታችንን አያከብሩም፤ ደግሞም እንድታማልድላቸውም (እንድትማልድላቸውም)  አይጠይቋትም።ከእነርሱ ወገኖች አንዳንዶቹ እንዲያውም ጫጩቱ ከተፈለፈለ በኋላ ዋጋ ከሌለው የዶሮ እንቁላል ቅርፊት ጋር እስከሚያመሳስሏት ይደርሳሉ።ይህ የተጋነነ ማቃለል የመጣው ምናልባት ሮሜዋውያን ካቶሊኮች የተጋነነ ማክበር ስለሚያከብሯት ለዛ ተቃርኖ ከማሳየት አዝማሚያ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን አንዱንም የእርሷን በዓል አያከብሩም።  (2) አንዳንዶቹ የፕሮቴስታንት ወገኖች ድንግል ማርያምን “እህታችን” ይሏታል። (3) በተጨማሪ አንዳንዶቹ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ጌታ ኢየሱስን በድንግልና ከወለደች በኋላ ከዮሴፍ ጋር ጋብቻዋን ፈጽማለች፤ የ‘ኢየሱስ ወንድሞች’  ወይም የ’ጌታ ወንድሞች’ ተብለው የተጠሩ ልጆችን ወልዳለች ይላሉ።  (4) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ቤተክርስቲያናችን ለድንግል እመቤታችን የሰጠቻቸውን አንዳንድ የማዕረግ ስሞችም ይቃወማሉ።  (5) ድንግልን ያለማክበራቸው አንዱ...

ስለ "አስታዋሽ ጾምና በዐሉ" ጥያቄና መልስ

 ስለ "አስታዋሽ ጾምና በዐሉ" ጥያቄና መልስ  ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ፦ ሕልውናችንን-ነጻነትችንን የማረጋገጥና የማስቀጠል አንድነታችንን የመጠበቅና የማጠንከር  በእሴቶቻችን የመደሰት፣ እነርሱን የመንከባከብና የማስተዋወቅ  በረከታችንን የማብዛትና የማካፈል  ኃላፊነቶቻችንን በማኅበር ፣ በማስተዋልና በትጋት እንድንወጣ “ጾሙና በዐሉ" አስታዋሽ ባሕላዊ ምልክታችን ይሁንልን   ጥያቄ 1 ፡ አድማጭ ተመልካቾቻችን እንኳን ደህና መጣችሁ።የከበረ ሰላምታችን ይድረሳችሁ። ዛሬ የምንወያየው ከአቶ ባንቱ ገብረማርያም ጋር ይሆናል። አቶ ባንቱ በሙያው ፋርማሲት ነው። እንደነገረኝ በእምነቱ ደግሞ ባፕቲስት ነው።ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ባሕላዊ ምልክት የሚሆን “ጾምና በዐልን” በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል። የምንወያየውም ስለዚሁ "ጾሙና በዐሉ" ምልክትነት ይሆናል።  አቶ ባንቱ ለመወያየት  ወደ እኛ በመምጣትህ አመሰግንሃለሁ። እንኳን ደህና መጣህ። አንተ እያልኩ ልቀጥል ወይስ አንቱ? መልስ 1፡ ዎገኔ፡   እንኳን ደህና ቆየኸኝ። ለአድማጭ ተመልካቾቻችሁም ሰላምታዬ ይድረስልኝ። አንተ በለኝ። የሚያውቀኝ ሁሉ አንተ ነው የሚለኝ።  ጥያቄ 2 ፡ እሺ  አንተ እያልኩ እቀጥላለሁ። አቶ ባንቱ፣ ምናልባትም ብዙ ሰው ስለማያውቅህ  እስቲ ስለራስህ በአጭሩ ንገረን። ወዲያውም መክፈቻ ይሆነናል መልስ 2 ዎገኔ ፦ አስቀድሜ ይኸን ዕድል ስለሰጠኸኝ ላመሰግንህ እወዳለሁ። አድማጭ ተመልካቾችህንም ጊዜ ወስደው  ውይይቱን  ስለሚከታተሉ ላመሰግናቸው እወዳለሁ።አዎን፣ ባንቱ ገብረማርያም እባላለሁ።እንደነገሩኝ የተወለድኩት ሽርካ በዛሬ አጠራሩ በአርሲ ዞን ነው።ነፍስ ያወቅሁትና ትምህርት ...