Skip to main content

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ


የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ

(1)  ድንግል ማርያምን ስለማክበር

(2) ለጥያቄዎች መልስ

(ሀ) ድንግሊትን ‘የወይን ግንድ (ተክል)’ና የ ‘ሕይወት በር’ የሚል ማዕረግ  ለምን እንሰጣታለን?

(ለ) ወደ ድንግል ማርያም መጸለይ ትክክል ነው ወይ?

(3) የድንግል ማርያም ድንግልና ዘላለማዊነት

(4) ለተቃራኒ አስተያየቶች መልስ

(ሀ) “የመጀመሪያ ልጇን” የሚለው ሐረግ

(ለ) “ሚስትህ” የሚለው ሐረግ

(ሐ) “አብረው ከመሆናቸው በፊት ጸንሳ ተገኘች”

(መ) “የመጀመሪያ ልጇን እስክትወልድ አላወቃትም”

(ሠ)  “ወንድሞቹ” የሚለው ሐረግ


የቅድስት ድንግል ማርያም  ክብሯ

(1) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ድንግል እመቤታችንን አያከብሩም፤ ደግሞም እንድታማልድላቸውም (እንድትማልድላቸውም)  አይጠይቋትም።ከእነርሱ ወገኖች አንዳንዶቹ እንዲያውም ጫጩቱ ከተፈለፈለ በኋላ ዋጋ ከሌለው የዶሮ እንቁላል ቅርፊት ጋር እስከሚያመሳስሏት ይደርሳሉ።ይህ የተጋነነ ማቃለል የመጣው ምናልባት ሮሜዋውያን ካቶሊኮች የተጋነነ ማክበር ስለሚያከብሯት ለዛ ተቃርኖ ከማሳየት አዝማሚያ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን አንዱንም የእርሷን በዓል አያከብሩም። 

(2) አንዳንዶቹ የፕሮቴስታንት ወገኖች ድንግል ማርያምን “እህታችን” ይሏታል።

(3) በተጨማሪ አንዳንዶቹ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ጌታ ኢየሱስን በድንግልና ከወለደች በኋላ ከዮሴፍ ጋር ጋብቻዋን ፈጽማለች፤ የ‘ኢየሱስ ወንድሞች’  ወይም የ’ጌታ ወንድሞች’ ተብለው የተጠሩ ልጆችን ወልዳለች ይላሉ። 

(4) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ቤተክርስቲያናችን ለድንግል እመቤታችን የሰጠቻቸውን አንዳንድ የማዕረግ ስሞችም ይቃወማሉ። 

(5) ድንግልን ያለማክበራቸው አንዱ ማሳያ  መልአኩ የሰጣትን  “ጸጋ የሞላሽ”፣  “ከሴቶች--- የተባረክሽ”  የሚሉት የማዕረግ ስሞች በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉማቸው  መቀየራቸው (መለወጣቸው)  ነው።  

(6) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ድንግል እመቤታችንን የ‘አምላክ እናት’ (እመ-አምላክ Theotokos) በማለት ፈንታ አዘውትረው የ‘ኢየሱስ እናት’ ይሏታል።

ድንግል ማርያምን ማክበር

ለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቦ የሚገኘውን የራሷን የድንግልን ቃል መጥቀስ ይበቃል። “እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” (ሉቃ 1÷48) ። “ትውልድ ሁሉ” የሚለው ሐረግ ድንግልን ማክበር ክርስቶስ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ በየትምና በሁሉም ዘንዳ የሚኖር ዶግማ ነው ማለት ነው። 

አንዳንዶቹ የድንግል ማርያም የአክብሮት ቃሎች በመጽሐፍ ቅዱስ በራሱ ውስጥ ተመዝግበዋል። ለምሳሌ በእድሜ ከቅድስት ማርያም  እናት  እኵያ የምትሆነዋ ኤልሳቤጥ እንዲህ አለች፦“የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?  እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና” (ሉቃ 1÷43፣ 44) ። በዚህ ላይ ስለድንግል ታላቅነት የሚገርመን ኤልሳቤጥ የሰላምታዋን ድምጽ በጆሮዋ በሰማች ጊዜ “በመንፈስ ቅዱስ መሞላቷ” (ሉቃ 1÷41) ነው። የድንግልን ድምጽ መስማቷ ብቻ ኤልሳቤጥን መንፈስ ቅዱስ እንድትሞላ አደረጋት። 

ድንግል ክብርን የተቀበለችው ከሰው ዘር ብቻ ሳይሆን ከመላእክትም ነበር። ይህም “ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት” (ሉቃ 1÷28) በማለት መልአኩ ገብርኤል ከሰጣት ሰላምታ በግልጽ የሚያታይ ነው። “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ” (ሉቃ 1:42) የሚለው ሐረግ ኤልሳቤጥ ለድንግል በሰጠቻት ሰላምታ ላይም ተደግሟል። ሊቀ መልአኩ ገብርኤል ካህኑን ዘካርያስን ካነጋገረበት ይልቅ እጅግ በገዘፈ ሞገስና ክብር ነበር ድንግል ማርያምን ያነጋገራት (ሉቃ 11÷3) ።

ድንግል ማርያምን የሚያመለክቱ በርካታ ትንቢቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ይገኛሉ። ከነዚህ መካከል “ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” (መዝ 45÷9) የሚለውን እንጠቅሳለን። መለኮታዊው እስትንፋስም ስለ እርሷ ይላል÷“ለሐሴቦን ንጉሥ ልጅ ሁሉ ክብርዋ ነው” (መዝ 45÷13) ይላል።ስለዚህ ድንግል ማርያም ንግስትም የንጉሡ ልጅም ናት።ለዚህ ነው የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን በድንግል ማርያም አርማዎቿ (ሥዕሎቿ) ሁሉ ላይ አክሊል የጫነች ንግስትና በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀኝ የተቀመጠች አድርጋ የምትስላት፤ ክብር ለእርሱ ይሁን።

ቤተ ክርስቲያን በቅዳሴዋ ድንግልን እንዲህ በማለት ታደንቃታለች። “መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ፥ አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ” (ምሳ 31÷29) ።

ቅድስት ድንግል ማርያም ትውልድ ሁሉ የተጠባበቃት ናት። እርሷ ናት ዘሯ “የእባቡን ራስ ሊቀጠቅጥ” (ዘፍ 31÷5) የቻለው። በዚህም እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን የገባው የመጀመሪያ ቃል በእርሷ ተፈጽሟል። 

ድንግል የጌታ ኢየሱስ እናት እንደመሆኗ መጠን የክርስቶስ ማዕረግ የሆነው ሁሉ በእናትነቷ ለእርሷም የሚውልበት አግባብ አለው። 

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነተኛው ብርሃን” (ዮሐ 1÷9) ነው። ጌታ ኢየሱስ ስለ ራሱ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” (ዮሐ 8÷12) ። ስለዚህ ድንግል እናቱ ደግሞ የ‘ብርሃን እናት’ (እመ ብርሃን) ወይም የ‘እውነተኛው ብርሃን እናት’ ናት። 

ክርስቶስ ቅዱስ ስለሆነ (ሉቃ 1÷35) ድንግል የ’ቅዱሱ እናት’ ናት። 

ለበግ እረኞቹ “ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና” (ሉቃ 2÷11) እንዲለ ክርስቶስ ኢየሱስ አዳኝ ነው። አዳኝ ለመሆኑ ምክንያቱ  ያም ብቻ አይደለም።  “ሕዝቡንም ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል” (ማቴ 1÷21) ስሙም ኢየሱስ ማለትም ‘አዳኝ’ ነው ይላልም። ። ስለዚህ ድንግል የ‘አዳኙ እናት’ ትባላለች። 

በ1ኛ ዮሐ 1 ፤ በሮሜ 9÷5ና በዮሐ 20÷28 መሠረት ክርስቶስ አምላክ ስለሆነ ድንግልም የ‘አምላክ እናት’ (እመ አምላክ፣ ወላዲተ አምላክ) ናት። 

ክርስቶስ ጌታ ስለሆነ ኤልሳቤጥ በአንደበቷ “የጌታዬ እናት” (ሉቃ 1÷43) በማለቷ ድንግል የ‘ጌታ እናት’ ናት። በተመሳሳይ ሁኔታ የ‘አማኑኤል እናት’ (ማቴ 1÷24)ና ‘ወላዲተ ቃል’ (ዮሐ 1÷14) ናት።

ድንግል ማርያም የክርስቶስ እናት ከሆነች ያለምንም ጥርጥር የሁሉም ክርስቲያን ‘መንፈሳዊ እናት’ ናት ማለት ነው። ለዚህም ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በዋለ ጊዜ ለተወዳጁ ሐዋርያ  ለቅዱስ ዮሐንስ “እናትህ እነኋት”  (ዮሐ 19÷27) ያለው ይበቃል።  እኛን “ልጆቼ” (1 ዮሐ 2÷1)  እያለ ለሚጠራን ለዮሐንስ ድንግል ማርያም እናት ከሆነች ለእኛ ለሁላችን እናት (እምዬ) ናት ማለት ነው። ስለዚህ ‘እህታችን’ የሚለው አጠራር ተቀባይነት የለውም። እንደዚህ ዓይነቱ ነገር መልስም ሊሰጠው አይገባም፣ ምክንያቱም ተቀባይነት የሌለው ከትክክለኛው ሃሳብ ያፈነገጠ ነውና። እኛ በስሙ ያመንን ልጆቹ ሆነን ሳለ ለእርሱ እናት እኛ ተመልሰን እህት ልንሆን አንችልም።

ድንግልን የሚያከብር ማንም ሰው ያው ራሱን ክርስቶስን ማክበሩ ነው። “ተስፋ ያላት የፊተኛዋ ትዕዛዝ እናትን ማክበር” ከሆነች እናታችን የሆነችውን ድንግል ማርያምን የጌታ ኢየሱስ እናትን፣ የሐዋርያት እናትን ልናከብር አይገባንምን [(ኤፌ 6÷2) (ዘዳ 20÷ 12) (ዘዳ 5÷16)]? ለድንግሊቱ ነው መልአኩ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል" (ሉቃ 1÷35) በማለት የተናገራት። እርሷ ነበረች “ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት” (ሉቃ 1÷45) በማለት በኤልሳቤጥ የተወደሰችው። 

“ከሴቶቹ ሁሉ አንቺ የተባረክሽ ነሽ” የሚለው  በመልአኩ ገብርኤልና በቅድስት ኤልሳቤጥ የተነገረው ሐረግ ድንግሊቷ በዓለም ላይ ከሚገኙ ሴቶች ሁሉ ጋር ብትወዳደር ብጽዕት የምትሆነው እርሷ ናት፤ ምክንያቱም በመለኮት “ሥግው መሆን” እርሷ የተቀበለችውን ክብር በዓለም ካሉት ሴቶች መካከል አንዳቸውም  የተቀበሉ አይደሉምና። ያለጥርጥር እግዚአብሔር ድንግል እመቤታችንን ከሴቶች ሁሉ የመረጠበት ምክንያት እንደ እርሷ ዓይነት ሌላ አንዲትም ሴት አልነበረችምና ነው። ይህ የመወደሷንና ከፍ የማለቷን ልክ ያሳያል።  ለዚህ ነው በኢሳያስ ላይ ወደ ግብጽ መሰደዷን በተነበየው ትንቢት ላይ ነቢዩ ኢሳያስ ‘ደመና’ በማለት የጠራት (ኢሳ 19÷1)።

አምላክ ‘ሥግው’ ሲሆን በድንግል ማርያም ማደሩን በተመለከተ ቤተ ክርስቲያን  ‘ሁለተኛ ሰማይ’፣ ‘መገናኛ ድንኳን’ (‘ደብተራ ሙሴ’)ና የ’ሙሴ ጽላት’ ትላታለች። 

መዝሙረኛው “ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፣ በውስጥዋም ሰው ተወለደ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት“(መዝ 87) እንደሚል ቤተ ክርስቲያን ድንግልን የ‘እግዚአብሔር ከተማ’ ወይም ‘ጽዮን’ ብላም ትጠራታለች። 

ጌታ ኢየሱስ ከሰማይ የመጣ ሕያው እንጀራ በመሆኑ ራሱን ከሰማይ መና ጋር ስላመሳሰለ (ዮሐ 6÷58) ቤተ ክርስቲያን ድንግልን “የ’መና መሶብ” ብላ ትጠራታለች። ፡

የቅድስት ማርያምን ድንግልና በተመለከተ ቤተ ክርስቲያን ‘ያቆጠቆጠችው የ’አሮን በትር’ ብላም ትጠራታለች።ዘኁ 17 

የምስክሩ ታቦት (ዘጸ25÷10-22) የድንግል ማርያም ምስያ ነው። ምክንያቱም መጀመሪያ ታቦቱ ውስጡንም ውጭውንም በወርቅ የተለበጠ መሆኑ ንጽሕናዋንና ክብሯን ይመስለዋል። በሁለተኛ ደረጃ ታቦቱ ከማይበሰብሰው ከግራር እንጨት ስለተሠራ ቅድስናዋን ይመስላታል። በሦስተኛ ደረጃ ታቦቱ ከሰማይ የወረደውን የሕይወት እንጀራ የክርስቶስ ምሳሌ የሆነውን መናውን በመያዙ፤ በመጨረሻም ታቦቱ የእግዚአብሔር ቃል ማለትም የክርስቶስ (ዮሐ 1÷1) ምሳሌ የሆነውን ሁለቱን የሕጉን ሰሌዳዎች (ጽላቶች) በመያዙ ይመስላታል።ያዕቆብ በህልሙ ያየው ከምድር ወደ ሰማይ የተዘረጋው መሰላል የድንግል ማርያም አምሳል ነው (መመሳሰል አለው) ። በክርስቶስ ሥግው መሆን ጊዜ የዚህ የምድርና የሰማይ መገናኛ በመሆን እርሷ ሰማይ ያደረባት ምድር ነበረች፤ በምድር ሆና ሳለ ሰማይን በውስጧ ተሸከመች (ዘፍ 28÷ 12) ። 

ሙሴ ያየው በ”እሳት ሲነድ የነበረው ነገር ግን ያልተቃጠለው ቁጥቋጦ” (ዘጸ 3) መንፈስ ቅዱስ በመለኮታዊ እሳቱ ወርዶባት ያልተቃጠለችው የድንግል ማርያም አምሳሏ (ምሳሌዋ) ነው። 

የክርስቶስ መለኮትነትና ትስብእት (ሰውነት) መዋሐድ የእሳትና የከሰል መዋሐድ ጋር ይመሳሰላል። ስለዚህ ቅድስት ድንግል ማርያም  ያንን መዋሐድ በውስጧ መሸከሟ ጥናውን ትመስላለች። ስለዚህም የ’አሮን ጥና’ (‘የአሮን ማዕጠንት’) ወይም የ’ወርቅ ጥና’ ትባላለች። ይህም ክብሯን  ያጎለዋል። 

ቤተ ክርስቲያን ድንግልን ‘መልካም (ውብ) ርግብ’ የሚል ማዕረግም ሰጥታታለች። ምክንያቱም 

1.  በየዋህነቷ ርግብን ትመስላለች

2. በርግብ አምሳል የታየው መንፈስ ቅዱስ (ማቴ 3÷ 16) በእርሷ ላይ ወርዷል።  

3. በኖኅ መርከብ የነበረችው ርግብ ከጥፋት ውኃ በኋላ የሕይወትን መመለስ መልእክት እንዳመጣችው ለሰዎች የድኅነትን መልእክት አምጥታለች (ዘፍ 8÷10-11) ።   

ድንግል በቤተ ክርስቲያን ተመስላለች እናም በርካታ ትንቢቶች የቤተ ክርስቲያንም የእርሷም ሆነው ይገኛሉ። 

በቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶችና በቅዱሳት መጻሕፍት ያሉ የድንግል ማርያም ምልክቶችና ተምሳሌቶች በርካታ ናቸው። እርሷ (ድንግል ማርያም)  ትከበራለች፤ ምክንያቱም

1.  መንፈስ ቅዱስ ወርዶባታል

2. የአምላክ እናት ናት

3.  ዘላለማዊ ድንግልና አላት

4. ቅድስት ናት

5. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እርሷ ይመሰክራል

6. ጌታ ራሱ አክብሯታል እና

7. በታምራታዊ ምልክቷና በተቀደሰው መታየቷ 

ይህ አክብሮት በተለያዩ የቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓቶች፣ቅዳሴዎች፣ዝማሬዎች፣ ምልጃዋን በሚጠይቁ የቤተ ክርስቲያናችን ጸሎቶች በተለያዩ በዓሎቿና ከአጽዋማቱ አንዱን በእርሷ ስም በመሰየም ተገልጧል።  

የድንግል በዓላት 

1. ዕለተ ዕረፍቷን ጥር 21 ። ከዚህ በተጨማሪ በቅብጥ ኦርቶዶክስ ወር አቆጣጣር በየወሩ 21 ኛው ቀን

2. ልደቷን ግንቦት 1 

3. የመወለድ ብሥራቷን ነሐሴ 1

4. ለቤተ መቅደስ መሰጠቷን (በአታ ማርያም) ታህሳስ 3

5. ቅብጥ (ግብጽ) ምድር መግባቷን ግንቦት 24

6. በዓለ ዕርገቷን ነሐሴ 16

7. በፊሊጵስዩስ ያለች ቤተ ክርስቲያኗ ምረቃውን ሰኔ 21

8. በካይሮ በ‘ዜይቶን’ ቤተ ክርስቲያን በገጽታዋ መታየቷን መጋቢት 24 እናስታውሳለን።

ስለድንግል ማዕረግ ስም ሁለት ጥያቄዎች

ስለ “ወይን ግንድነቷ (ተክልነቷ)”

(1) የወይን ግንዱ (ተክሉ) ጌታችን ኢየሱስ  ክርስቶስ ሆኖ ሳለ፣  ክርስቶስ ስለራሱ በግልጽ እንዲህ እንዳለ፦  “እውነተኛ የወይን ግንድ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው።”---“እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ” (ዮሐ 15÷ 1፣ 5)  ለምንድነው በ3ኛው ሰዓት ጸሎታችን  “እመ አምላክ ሆይ አንቺ  እውነተኛዋ የወይን ግንድ (ተክል) የሕይወትን ፍሬ ያፈራሽ (ያቀፍሽ)” በማለት ድንግልን ‘የወይን ተክል’ እያልን የምንጠራት?  

ስለ “የሕይወት በርነቷ” 

(2) ስለራሱ “እኔ የበጎች በር ነኝ” (ዮሐ 10÷7) እንዳለው በሩ ራሱ ክርስቶስ ሆኖ ሳለ፤ ለምንድነው ድንግልን በ3ኛው ክፍል የመንፈቀ ሌሊት ጸሎታችን “የሕይወት በር" እያልን የምንጠራት?

(1) ድንግል እውነተኛ የወይን ግንድ (ተክል) ናት

‘እውነተኛ የወይን ግንድ (ተክል)’ የሚለውን ማዕረግ ለድንግል ማርያም መስጠት የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ‘የወይን ግንድ (ተክል)’ ማዕረግነት አያፋልሰውም። ጌታ በአንድ መልክ የ’ወይን ግንድ’ ሲሆን ማርያም ደግሞ በሌላ መልክ ‘የወይን ግንድ (ተክል)’ ናት። 

ጌታ የወይን ግንድ ሲሆን እኛ ቅርንጫፎቹ ነን። እርሱ መጀመሪያው ነው፤ እኛ ሁላችን ደግሞ ከእርሱ ተገኝተናል። እርሱ ራስ እኛ ሁላችን ደግሞ የአካሉ ብልቶች ነን። 

ድንግልን በተመለከተ እንደ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴው የ”ሕይወት ፍሬ”ን ማለትም ‘የእግዚአብሔርን ልጅ’ የወለደችው እርሷ ናት።  እርሷ መጠውለግን ያላወቀች በማንም ያልተቀጠፈች የወይን ተክል (ወይን) ናት።

ጌታ ኢየሱስ አንዳንድ የራሱ የሆኑ ስያሜዎችን እንድንጠራባቸው ቸሮናል 

(1)ጌታ እንዲህ ይላል፦ “መልካም እረኛ እኔ ነኝ” (ዮሐ 10÷11፣14) ። “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው” (መዝ 23÷1) ያለ ጊዜ ይህን ማዕረግ ለእግዚአብሔር በመዝሙሩ የሰጠው ዳዊት ነበር። በትንቢተ ሕዝቅኤል መጽሐፍም ላይ እንደዚሁ ለእርሱ ተሰጥቶታል (ሕዝ 34÷11-16) ። 

ይሁን እንጂ  ጌታ አንዳንድ ልጆቹን እረኛ አድርጎ ይሾማል።  ቤተ ክርስቲያን “አንድ መንጋ  በአንድ እረኛ” (ዮሐ 101÷6) እንድትሆን የገደደው ጌታ ለሐዋርያው ለጴጥሮስ “ጠቦቶቼን ጠብቅ” “በጎቼን አሰማራ” (ዮሐ 21÷15፣ 16) ብሎታል። በብሉይ ኪዳንም ጌታ “እንደ ልቤም በግ ጠባቆችን እሰጣችኋለሁ” (ኤር 3÷15) ብሏል። ‘እረኛ’ የሚለው ማዕረግ ለሐዋርያቱ ተተኪዎች  ለኤጲስ ቆጶሳቱ ማዕረግ ሆኗል። እንደዚህ ለሚያደርጉት፦ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት (እረኛ ትሆኗት) ዘንድ ----ተጠንቀቁ” (ሐዋ 20÷28)። ቅዱስ ጴጥሮስ ይላል፦ “በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ (እረኛ ሁኑት) እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት” (1 ጴጥ 5÷2)። 

(2)ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” (ዮሐ 8÷12ና ዮሐ 9÷5) በማለት ራሱን ‘ብርሃን’ ብሎ ጠርቷል። ይሁን እንጂ ለደቀመዛሙርቱም “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ” ና(ማቴ 5÷14) “ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” (ማቴ 5÷16) ይላል። 

በትክክል ቃሉ እንደሚያመለክተው ጌታ ፍጹም ብርሃን ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ደቀ መዛሙርቱ ብርሃን ናቸው ፤ ምክንያቱም ብርሃናቸውን  ከእርሱ ያገኙና የእርሱን ብርሃን በሰው ፊት ያበራሉ። እንደዚሁም ሁሉ እንደ ቃሉ ሙሉ ትርጉም (የቃል በቃል ትርጉም) ከተሄደ እርሱ ‘እረኛ’ ነው፤ነገር ግን እነርሱም የእግዚአብሔር ባለ አደራ በመሆን መንጋውን እንዲጠብቁ በእርሱ  የተሾሙ በመሆናቸው እረኞች ናቸው።

(3) “--- ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ--” (1ኛ ጴጥ 2÷25) ተብሎ በተጻፈው በሙሉ ስሜቱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ እረኛ (ኤጲስ ቆጶስ) ነው። ይሁን እንጂ የሐዋርያቱ ደቀመዛሙርት ‘ኤጲስ ቆጶሳት’ (እረኞች) እንዲሆኑ በመንፈስ ቅዱስ ተሾመዋል [(ዮሐ 20÷20-23) (ሐዋ 20÷28) (1 ተሰ 3÷2) (ፊል 1÷1) (ቲቶ 1÷7)] ።

(4) ስለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” [(መዝ 110÷4) (ዕብ 5÷6)] ተብሎ ተጽፏል። ይሁን እንጂ ስለ ሊቀ ካህንነት፣ ስለ ካህናት አለቃና ስለ ካህን የሚናገሩ በርካታ ጥቅሶች በመጽሐፍ ቅዱስ ይገኛሉ። እነዚሁ ጥቅሶች የክህነት ማዕረግ ለዘላለም እስከ ልጅ ልጅ መሰጠቱንም ያመለክታሉ (ዘጸ 40÷15) ።

በብሉይ ኪዳን “ካህናቶችህ ጽድቅን ይልበሱ” (መዝ 132÷9፣16) “ከቅብዓቱም ዘይት በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰ፥ ይቀድሰውም ዘንድ ቀባው።” (ዘሌ 8÷12) “የተቀደሰውንም ልብስ ለክብርና ለጌጥ እንዲሆን ለወንድምህ ለአሮን ሥራለት” (ዘጸ 28÷2) የሚል ተጽፏል። በአዲስ ኪዳን ቅዱስ ጳውሎስ “እንደ ካህን እያገለገልሁ” (ሮሜ 15÷16) በማለት ራሱን ካህን ብሎ ይጠራል።

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእኛ ራስን መስዋዕት አድርጎ ከማቅረቡ አኳያ ካህን ነው። ነገር ግን ከሰው ዘር የሆኑቱ ካህናት አገልጋዮችና የእግዚአብሔር ምስጢር ባለ አደራዎች ናቸው። የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን መስዋዕት ያቀርባሉ። በብሉይ ኪዳን ደግሞ  የክርስቶስን መስዋዕት  ተምሳሌት የሆነውን መስዋዕት ያቀርቡ ነበር።  

(5) ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ ተጽፏል (1ዮሐ 4÷14፣ 15) ። እኛም የእርሱ ልጆች ነን (1 ዮሐ 3÷1) ። ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ሲል ከመሠረቱ ማለትም በባህርዩና በመለኮትነቱ ነው። እኛ ግን ልጆቹ የሆንነው በፍቅሩና በማደጎነት ስለተቀበለን ነው። ስለዚህ ነው ጌታ ኢየሱስ ‘አንድያ ልጅ’ የተባለው (ዮሐ 31÷6) ።

‘የወይን ግንድ (ተክል)’ የሚለው ስያሜም እንደዚሁ ነው

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የወይን ግንድ ነው።መላዋ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ የወይኑ ቦታ ተብላ ተጠርታለች (ኢሳ 5÷3፣7) ። ጌታ የወይኑ ቦታ ቅኔን ስለቤተ ክርስቲያን ተቀኝቷል እንዲህ ሲል፦ “አሁንም እናንተ በኢየሩሳሌም የምትኖሩ የይሁዳ ሰዎች ሆይ፥ በእኔና በወይኑ ቦታዬ መካከል እስኪ ፍረዱ” (ኢሳ 5÷ 3) “የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ወይን ቦታ እርሱ የእስራኤል ቤት ነው” (ኢሳ 5 ÷7) ።

በማቲዎስ ጌታ የተናገረው የወይን አትክልትና የባለቤቱ ምሳሌም ተመሳሳይ ትርጉም ነው ያለው (ማቴ 21÷33-41) ። በዚህ ሥፍራ የወይን አትክልቱ ቤተ ክርስቲያን ናት፤ ገበሬዎቹ ካህናት ናቸው፤ የአትክልቱ ባለቤትም እግዚአብሔር ነው። 

ቤተ ክርስቲያንን የወይን ግንድ ብለን ለመጥራት የመለኮት እስትንፋስ የሆነውን መዝሙረ ዳዊትን እንጠቅሳለን። “የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ እንግዲህ ተመለስ፤ ከሰማይ ተመልከት፥ እይም፥ ይህችንም የወይን ግንድ ጐብኝ። በሰው ልጅ ለአንተ ያጸናኸውን ቀኝህ የተከላትን አንሣ” (መዝ 80÷14፣ 15) ።

ክርስቶስ ራሱ ይህንኑ ማዕረግ ሰጥቷት ሳለ ቤተ ክርስቲያንን የወይን ግንድ ብንላት የእግዚአብሔርን ክብር መስረቃችን ነውን?  የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንድናደርግ አዞን ሳለ ሕዝቡን የወይን ቦታ ብንል የእግዚአብሔርን ክብር መስረቃችን ነውን? “በዚያም ቀን ለተወደደው የወይን ቦታ ተቀኙለት፤ እኔ እግዚአብሔር ጠባቂው ነኝ፤ ሁልጊዜ አጠጣዋለሁ፤ ማንም እንዳይጐዳው በሌሊትና በቀን እጠብቀዋለሁ” (ኢሳ 27÷2፣ 3) ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ በተናገረላት በቤተ ክርስቲያን ላይ ጥቃትን ማድረሳችን ነውን? 

ከዚህም በላይ በመዝ 128÷3 “ሚስትህ በቤትህ እልፍኝ ውስጥ እንደሚያፈራ ወይን ናት” በማለት ወይን የሚለውን ስም ለየትኛዋም የተባረከች እናት አውሎታል። 

ስለዚህ ቅድስት ድንግል ማርያምን  ‘የወይን ግንድ (ተክል) ’ ብሎ መጥራት የሚያስደንቅ አይደለም። 

(2) ድንግል የ‘ሕይወት በር’ና የ‘ድኅነት በር’ ናት።

በመጽሐፍ ቅዱስ ድንግል ማርያም ‘በር’ ተብላለች። በትንቢተ ሕዝቅኤል መጽሐፍ ወደ ምሥራቅ የሚመለከተው በር መሆኗና ጌታ እግዚአብሔር በዚያ እንደገባና ተመልሶ እንደወጣ ተጽፏል (ሕዝ 44÷2) ። 

ጌታ ሕይወት እንደሆነ እርሷ ደግሞ ‘የሕይወት በር’ ናት። ጌታ ሕይወት መሆኑን ገልጿል እንዲህ በማለት፦ “ኢየሱስም። ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” (ዮሐ 11÷25) ። ድንግል ክርስቶስ የመጣበት በር ስለሆነች ስለዚህ የሕይወት በር ናት። 

በተመሳሳይ ሁኔታ ቅድስት ማርያም የድኅነት በር ናት። ምክንያቱም ጌታ ‘አዳኝ’ ነውና። እርሱ ዓለምን ሊያድን መጣ፤ ጠፍተው የነበሩትን ሊያድን ተገለጠ (ሉቃ 19÷10) ። 

ድንግልን ‘በር’ ብሎ መጥራት አያስደንቅም፤ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ‘በር’ (‘ደጅ’) ተብላ ከዘመናት በፊት ተጠርታለችና። አባታችን ያዕቆብ ቤተ ክርስቲያን አድርጎ የቀባውን ቅዱሱን ሥፍራ ‘ቤቴል’  ማለትም የ’እግዚአብሔር ቤት’ ብሎ ሲሰይመው “ይህ ስፍራ እንዴት ያስፈራ፤ ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህም የሰማይ ደጅ ነው” (ዘፍ 28÷1) ብሏል።

 ለድንግል መጸለይ ትክክል ነው ወይ?

ለድንግል አንጸልይም፤ ነገር ግን ስንጸልይና ልመና ስናቀርብ እንድትማልድልን እንነግራታለን። ድንግልን ብቻ ሳይሆን መላእክትን፣ ተፈጥሮን፣ ሰዎችን፣ እራሳችንን ሌላው ቀርቶ ለሰይጣናትም እንናገራለን። ይህም በእግዚአብሔር እስትንፋስ በተጻፈው ቃል (ጥቅስ) መሠረት ሲሆን ይህ ከጸሎት አልተቆጠረም። ስለምንድነው ከሌሎች ለይተን ድንግል እናታችንን ብቻ የማንነግራት? 

(1) “ቃሉን የምትፈጽሙ፥ ብርቱዎችና ኃያላን፥ የቃሉንም ድምፅ የምትሰሙ መላእክቱ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ። ሠራዊቱ ሁሉ፥ ፈቃዱን የምታደርጉ አገልጋዮቹ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ” (መዝ 103÷20፣21)ና “እግዚአብሔርን ከሰማያት አመስግኑት፤ በአርያም አመስግኑት።መላእክቱ ሁሉ፥ አመስግኑት፤ ሠራዊቱ ሁሉ፥ አመስግኑት” (መዝ 148:1፣ 2) በማለት ስንጸልይ ለመላእክት መንገራችን ነው። 

(2) በጸሎታችን ለተፈጥሮ መንገራችን ነው እንዲህ ስንል፦“ፀሐይና ጨረቃ፥ አመስግኑት፤ ከዋክብትና ብርሃን ሁሉ፥ አመስግኑት። ሰማየ ሰማያት፥ አመስግኑት የሰማያት በላይም ውኃ። እርሱ ብሎአልና፥ ሆኑም፤ እርሱም አዝዞአልና፥ ተፈጠሩም፤ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑት።ለዘላለም ዓለም አቆማቸው፤ ትእዛዝን ሰጠ፥ አያልፉምም። እባቦች ጥልቆችም ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ከምድር አመስግኑት፤ እሳትና በረዶ አመዳይና ውርጭ፥ ቃሉን የሚያደርግ ዐውሎ ነፋስም፤ ተራሮች ኰረብቶችም ሁሉ፥ የሚያፈራም ዛፍ ዝግባም ሁሉ” (መዝ 148÷3-9) ። 

(3) ለእግዚአብሔር ቅድስት ከተማ እግዚአብሔርን እንድታመሰግን መንገራችንና መጠየቃችን ነው፤ እንደዚህ ስንል፦“ኢየሩሳሌም ሆይ፥ እግዚአብሔርን አመስግኚ፥ ጽዮንም ሆይ፥ ለአምላክሽ እልል በዪ፤ የደጆችሽን መወርወሪያ አጽንቶአልና፥ ልጆችንም በውስጥሽ ባርኮአልና” (መዝ 147÷ 12፣ 13) ። በሌላ መዝሙር እንዲህ እንላለን፦ “የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ፥ በአንቺ የተከበረ ነገር ይባላል” (መዝ 87÷3) ። 

(4) በጸሎታችን ለሕዝቡ መናገራችን ነው እንዲህ ስንል፦ “አሕዛብ ሁላችሁ፥ እጆቻችሁን አጨብጭቡ፥ በደስታ ቃልም ለእግዚአብሔር እልል በሉ” (መዝ 47÷1) ። “የእግዚአብሔርን ሥራ፥ በምድር ያደረገውንም ተኣምራት እንድታዩ ኑ” (መዝ 46÷8) ።  “ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች አትታመኑ” (መዝ 146÷3) ። “ፍጥረቶቹ ሁሉ በግዛቱ ስፍራ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ” (መዝ 103÷22)። በሌላ መዝሙር እንዲህ እንላለን። “ሃሌ ሉያ። የእግዚአብሔር ባሪያዎች ሆይ፥ አመስግኑት፥ የእግዚአብሔርንም ስም አመስግኑ።” (መዝ 113÷1) ደግሞም እንዲህ እንላለን። የ“አምላክ ልጆች ሆይ፥ ለእግዚአብሔር አምጡ። ክብርንና ምስጋናን ለእግዚአብሔር አምጡ። የስሙን ክብር ለእግዚአብሔር አምጡ፥ በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ” (መዝ 29÷1፣ 2) ።

(5) አምላኪው ደግሞ እንዲህ ሲል ለራሱ ይናገራል፦“ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፥ አጥንቶቼም ሁሉ፥ የተቀደሰ ስሙን፣ ነፍሴ ሆይ፥ እግዚአብሔርን ባርኪ፥ ምስጋናውንም ሁሉ አትርሺ፤ ኃጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል፥ ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ፥ሕይወትሽን ከጥፋት የሚያድናት፥ በምሕረቱና በቸርነቱ የሚከልልሽ፥ ምኞትሽን ከበረከቱ የሚያጠግባት፥ ጕልማስነትሽን እንደ ንስር ያድሳል።” (መዝ 102÷1-5) ። በሌላ መዝሙር ደግሞ አምላኪው ሲጸልይ እንዲህ ይላል፦ “ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ” (መዝ 42÷5) ። በ12ኛው ሰዓት ጸሎት አምላኪው ለራሱ እንዲህ ይላል፦ “በምድር ላይ እስካለሽ ድረስ ነፍሴ ሆይ ንስሐ ግቢ”። 

(6) በተጨማሪ በጸሎታችን ለክፉ መናፍስትና ለኃይላቸው እንናገረለን፤ እንዲህ በማለት፦ “ዓመፃን የምታደርጉ ሁሉ፥ ከእኔ ራቁ፥ እግዚአብሔር የልቅሶዬን ቃል ሰምቶአልና። እግዚአብሔር ልመናዬን ሰማኝ፤ እግዚአብሔር ጸሎቴን ተቀበለ። ጠላቶቼ ሁሉ ይፈሩ እጅግም ይጐስቍሉ፤ ወደ ኋላቸው ይመለሱ፥ በፍጥነትም ይፈሩ” (መዝ 6÷8-10) እንላቸዋለን።

ለእነዚህ ሁሉ እንጸልያለን ማለት ነውን? ለመላእክት እንጸልያለንን?  ለተፈጥሮ ፣ ለሰዎችና ለሰይጣናት እንጸልያለንን? ይህን እግዚአብሔር ያርቀው! በጸሎታችን እንነግራቸዋለን። ይህ ተቀባይነት ያለው ነገር ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርትና ከመዝሙሩ መንፈስ የተወሰደ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ እንዲህ አለ፦“እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ምንድር ነው? በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለእያንዳንዱ መዝሙር አለው” (1ኛ ቆሮ 14÷26) “በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ” (ኤፌ 5÷19)ና “እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ። በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ” (ቆላ 3÷16) ።

በመለኮት እስትንፋስ በተሰጠው ትምህርት መሠረት ለመላእክት ፣ ለተፈጥሮ ፣ ለሰዎች፣ ለራሳችንና ለሰይጣን በጸሎታችን እስከተናገርን ድረስ ለእናታችን ድንግል በጸሎታችን ብንነግራት ስህተት አይደለም።ይህ ወደ እርሷ መጸለይ ተደርጎ ሊወሰድም አይገባውም። 

ድንግል ማርያም በድንግልናዋ የጸናች ለመሆኑ

የብፅዕት ድንግል ማርያም የጸና (የማያቋርጥ) ድንግልና የጥንት ርዕሰ ጉዳይ ነው።በሁለተኛው፣ በሦስተኛው ፣ በአራተኛውና በአምስተኛው ምዕተ ዓመት የነበሩ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ተነጋግረውበታል። ስለ ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና ‘ሄልቪዲየስ  የተባለን ሰው የተሳሳተ ትምህርት ለመመከት በ383 ዓ.ም በቅዱስ  ‘የሮም (ጀሮም) የተጻፈውን የመልስ ውይይት ትንታኔ ጽሑፍ በ1962 ዓ.ም ተርጉመናል። የፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን የሚያቀርቡት ክርክር የ‘ሄልቪዲየስ’ን ይመስላል። 

የማርያምን ዘላለማዊ ድንግልና የሚቃወሙ አስተያየቶች ማጠቃለያቸው

(1) የማያቋርጥ ድንግልናዋን የሚክዱቱ በሉቃ 2÷7ና ማቴ 1÷25 የሚነበበውን “የበኵር ልጅ” የሚለውን ሐረግ ከሌሎች ወንድሞቹና እህቶቹ መካከል በኵር ማለት ነው ብለው ያስባሉ።

(2) ስለድንግል ለዮሴፍ የተነገረው ‘ሚስትህን’ የሚለው ሐረግ (ማቴ 1÷20)ና ባጠቃላይ ስለማርያም ሲጻፍ ‘ሴት’ እየተባለ መጻፉ ነው (ማቴ 1÷24) ። 

(3) “የበኵር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም” ና(ማቴ1÷25)ና “ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች” (ማቴ 1÷18) የሚሉት ዓረፍተ ነገሮች

(4) ‘ወንድሞቹ’ የሚለው ቃል የተጠቀሱባቸው ክፍሎች (ማቴ 12÷46) ፣ (ማቴ 13÷ 54-56) ፣ (ሐዋ 1÷14) ፣ (ገላ 1÷ 18፣ 19) ናቸው። 

በእግዚአብሔር እርዳታ ለነዚህ ተቃውሞዎች በሚቀጥሉት ገጾች መልስ እንሰጣለን

(1) የ”በኵር ልጇ”ን የሚለው ሐረግ÷

መጽሐፍ ቅዱስ የ‘በኵር ልጅ’ የሚለውን (ሐረግ) በግልጽ ተርጉሞታል። አሮናዊ ክህነት ከመመስረቱ በፊት መለኮታዊ እስትንፋስ እንዲህ ብሏል፦ “በእስራኤል ልጆች ዘንድ ከሰውም ከእንስሳም ማሕፀንን የሚከፈት በኵር ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ፤ የእኔ ነው” (ዘዳ 13÷2)። በኋላ (በላዩ) ወንድም ቢወለድለትም ባይወለድለትም የበኵር ልጅ ለእግዚአብሔር ይቀደሳል፤ ለእግዚአብሔር ይሰጣል። በኵሩን ለጌታ ለመቀደስ ወይም ለመሰዋት ወላጆች ሌላ ወንድም እስኪወለድለት አይጠብቁም ነበር ወይም የእንስሳው ባለቤት ሌላ ጥጃ እስኪወለድ ድረስ አይጠብቅም ነበር። ነገር ግን እንደተወለደ ነው ለእግዚአብሔር የሚቀደሰው ምክንያቱም የመጀመሪያ የማህጸን ፍሬ መሆኑ ነውና የሚፈለገው። ስለዚህ የበኵር  ልጅ ብቸኛ ልጅ የመሆን ትልቅ ዕድል ነበረው። 

እንደዚሁ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የበኵርም ብቸኛም ልጅ ነው። ቅዱስ የሮም “ብቸኛ ልጅ ሁሉ የበኵር ልጅ ነው የበኵር ልጅ ሁሉ ግን ብቸኛ አይደለም” ያለው ትክክል ነው። የ’በኵር ልጅ’ የሚለው አገላለጥ በፊት የተወለዱ ወንድሞችና እህቶች የሉም ማለት እንጂ በኋላ (ቀጥሎ) ልጆች ተወልደዋል ማለት አይደለም። ለዚህ ነበር ንጹህ ያልሆነውን የእንስሳ በኵር  እድሜው አንድ ወር ከሆነው ጀምሮ መቤዠት የሚቻለው (ዘኁ 18:16፣ 17)። የሚቀጥል “የእንስሳ ልጅ” መወለዱን መጠበቅ ሳያስፈልግ የንጹህ እንስሳ በኵር ግን ለእግዚአብሔር በመስዋዕትነት ይሰጣል ምክንያቱም የማሕጸን  ከፋች ነውና።


በተመሳሳይ ሁኔታ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያው የድንግል ልጅ ነበር። ድንግል ማርያምና ዮሴፍ በተወለደ በ40 ቀኑ መስዋዕትን ሲያቀርቡ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።“እንደ ሙሴም ሕግ የመንጻታቸው ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥ በጌታ ሕግ። የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ወንድ ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል ተብሎ እንደ ተጻፈ በጌታ ፊት ሊያቆሙት፥ በጌታም ሕግ። ሁለት ዋሊያ ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደ ተባለ፥ መሥዋዕት ሊያቀርቡ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት” (ሉቃ 2÷22-24) ።

ስለበኵር ልጅ የነበረው ሕግ ክርስቶስ በተወለደ በ40 ቀኑ እንደ ተፈጸመ ግልጽ ነው።በእርግጥ የመጀመሪያው ልጅ መወለድ ከሚቀጥሉት ወንድም-እህት መወለድ ጋር አይዛመድም። 

በዚህ ላይ ቅዱስ ‘የሮም’ እግዚአብሔር በግብጽ በኵርን ሁሉ ሲመታ ታናሽ ወንድም-እህት ያላቸውን ብቻ ነውን የመታቸው? ወይስ ማሕጸን የከፈተውን ልጅ ሁሉ ታናሽ  ወንድም-እህት ቢኖራቸውም ባይኖራቸውም ነበር? በማለት ጠይቆ ነበር።

(2) ‘ሚስትህን’ ስለሚለው ሐረግ ‘

ሚስት ወይም ‘ሴት’ የሚለው ቃል ልጃገረድ እንደታጨች ወዲያውኑ የሚሰጣት ስያሜ ነው። “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን  ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ” (ማቴ 1÷20) በማለት መላእኩ ለዮሴፍ ለተናገረው  ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሰጠውን ትርጉም ማንሳት ይቻላል። መልአኩ ‘የታጨችን ‘ሚስት’ ብሎ ጠርቷል ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ሁል ጊዜም የተጫጩ (ወጣት) ጥንዶችን ከመጋባታቸው በፊት ‘ሰው’ና ‘ሚስት’ ብሎ ይጠራቸዋልና። ደግሞም አለ፦ ‘ለመውሰድ’ የሚለው ቃል ትርጉምስ ምንድነው? ይህ ማለት “በኣደራ ተሰጥሃለች ከእግዚአብሔር እንጂ ከወላጆቿ ስላልሆነ በቤትህ አስቀምጣት። ምክንያቱም እንድትወስዳት አደራ የተሰጠችህም እንድትጠብቃት እንጂ ጋብቻ እንዲፈጸም አይደለም” ማለት ነው። “ልክ በዚሁ መልክ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ድንግል ማርያምን ለደቀመዝሙሩ ለዮሐንስ አደራ ሰጥቷታል” (“የቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል ድርሳን”) ።

ቅዱስ የሮም ‘ሴት’፣ ‘ሚስት’ የሚለው ስያሜ ለታጨች ልጃገረድ ጭምር የሚሰጥ ነው ብሏል። ለዚህም የመጽሐፍ ቅዱስ የጥቅስ ማረጋገጫዎቹ መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል። “ማናቸውም ሰው ድንግልና ያላትን ልጃገረድ ቢያጭ፥ ሌላ ሰውም በከተማ ውስጥ አግኝቶ ከእርስዋ ጋር ቢተኛ፥ ሁለቱን ወደዚያች ከተማ በር አውጡአቸው፤ ብላቴናይቱ በከተማ ውስጥ ሳለች አልጮኸችምና፥ ሰውዮውም የባልንጀራውን ‘ሚስት’ አስነውሮአልና እስኪሞቱ ድረስ በድንጋይ ውገሩአቸው፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታስወግዳለህ” (ዘዳ 22÷23፣ 24) ።‘ሚስት’ም አጭቶ ያላገባትም ሰው ቢኖር”  (ዘዳ 20÷7) 

ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሴት’ ወይም ‘ሚስት’ የሚሉትን ቃላት የታጨች ድንግልን ለመግለጥ ይጠቀምባቸዋል። ጾታን ለማመልከት እንጂ መሠረግን (ማግባትን) ለማመልከት የሚሰጡ አይደሉም።  

በእርግጥ ሔዋን በመጀመሪያ ‘ሴት’ ተባለች ምክንያቱም ከወንድ ተገኝታለችና (ዘፍ 3÷20) ። ስለዚህ ‘ሴት’ የሚለው ቃል ፍጥረቷንና ጾታዋን፣ ‘ሔዋን’ የሚለው ቃል እናትነቷን የሚያመለክቱ ናቸው።

ድንግል ማርያምን በተመለከተ ‘ሚስት’ የሚለው ቃል የታጨች እንጂ ያገባች አለመሆኑን ማረጋገጫው የወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ቃሎች ናቸው። “ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተ ልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ፀንሳ ከነበረች ከ’እጮኛው’ ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ” (ሉቃ 2÷4፣ 5) ።ስለዚህ ‘ሚስትህ የሚለው ሐረግ እጮኛህ ማለት ነው።

ስለዚህ ድንግል ማርያም ‘ሚስት’ መባሏ ድንግልናዋን ያጣች መሆኗን አያመለክትም። እግዚአብሔር ያርቀው፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ዮሴፍ እንዳላወቃት ይመሰክራልና። ይሁን እንጂ እንደዛ ተብላ የተጠራችበት ምክንያት በአይሁድ የተለምዶ ቋንቋ የታጨች ልጃገረድ ‘ሚስት’ ትባል፣ ያላገባች ልጃገረድ ደግሞ ‘ሴት’ ትባል ስለነበር ነው።ለዚህም ግልጽ ማስረጃው እንደተፈጠረች ወዲያውኑ፣ ኃጢአትን ከመሥራት በፊት ፣  ከኤደን ገነት ከመባረራቸው በፊት ፣ ልጅንም ከመውለዷ በፊት ሔዋን ‘ሴት’ ተብላ ነበር።

መልአኩ ‘ሚስት’ የሚለውን ቃል ድንግል ጌታ ኢየሱስን ከወለደች በኋላ  ያልተጠቀመበት መሆኑን ልብ ማለት እንችላለን። ዮሴፍን ግን እንዲህ ነው ያለው፦ “ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥” (ማቴ 2÷13) ። ዮሴፍ ወደ ግብጽ ሲሄድና ሲመለስ መልአኩ÷-“ተነሣ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ” አለው (ማቴ 2÷20) ። ዮሴፍም እንደተነገረው አደረገ። “እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና --- በዚያ ኖረ።”“እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ያዘና ወደ እስራኤል አገር ገባ።” (ማቴ 2÷14 ፣ 21) ። እዚህ ላይ ቅዱስ መጽሐፍ ‘ሚስቱን’ የሚል ሐረግ አልተጠቀመም።

‘ሚስቱ’ የሚለው ቃል አይሁድ ድንግል ማርያምን እንዳይወግሯት ከማርገዟ በፊትና እንዳረገዘች ተጠቀመበት። ምክንያቱም ድንግል ማርያም ያረገዘችው የሰው ሚስት ሳትሆን (ወንድ ሳታውቅ) ነበርና። ክርስቶስን ከወለደች በኋላ ግን መለኮታዊ እስትንፋስ ያንን ቃል አልተጠቀመም። ዮሴፍ በተነገረው በመልአኩ ቃል ወይም ዮሴፍ ያደረገውን በሚናገርበት ጊዜ ወይም ስለ ሰብአ ሰገል በተናገረበት ውስጥ እንኳ አልተጠቀመም።“ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥” (ማቴ 2÷11)፣ ስለእረኞቹ በሚያወራበት ጊዜም “ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ” (ሉቃ 2÷16) ነበር ያለው። ሚስት የሚለው ቃል በነዚህ ውስጥ ጥቅም ላይ አልዋለም።

(3) “ሳይገናኙ ----ፀንሳ ተገኘች።” (ሉቃ 1÷18) ስለሚለው ዓረፍተ ነገር 

ወንጌላዊ ቅዱስ ሉቃስ ክርስቶስ ወንድ ካላወቀች ከድንግል መወለዱን በማረጋገጥ ላይ ትኩረት ያደረገበት የሚከተሉት ሁለት ምክንያቶች አሉ።

(ሀ) ሰዎች በተፈጥሮያዊ መዋለድ እንደሚዋለዱት ክርስቶስ ከሁለት ወላጆች አለመወለዱ፣ ነገር ግን ያለ አባት ከድንግል መወለዱ የእርሱን መለኮትነት ያረጋግጣል። መልአኩ“ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና” (ማቴ 1÷20) ያለውም ከመንፈስ ቅዱስ ለመወለዱ ማረጋገጫ ነው።

(ለ) በድንግልና መወለዱ የአዳምን ኃጢአት አለመውረሱን ያስረግጥልናል። በዚህም ሊያድነን ይችላል፤ ኃጢአትን ያላደረገ ስለ ኃጢአተኞች መሞት ይችላልና።  

ስለዚህ ድንግል ክርስቶስን ከመውለዷ በፊት ወንድ እንዳላወቀች ሐዋርያው ትኩረት የሰጠበት ምክንያቱ የጌታን በድንግል መወለድ ለማረጋገጥ ሲል ነው። ክርስቶስን ከወለደች በኋላ ድንግል ማርያም ወንድ ያላወቃት መሆኑ ግን  በራሱ በቂ ማስረጃ ነው።

(4) “የበኵር ልጅዋንም እስከምትወልድ ድረስ አላወቃትም” ስለሚለው ዓረፍተ ነገር 

እስከ የሚለው ቃል የሚጠቅሰው ቀዳሚ ሐረጉን ብቻ ነው ፤ የሚያስከተለው ጥገኛ ሐረግ ከቀዳሚ ሐረጉ ተቃራኒ ትርጉም እንደሚያመጣ አይናገርም። 

ይህን የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎች  

(ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ “የሳኦልም ልጅ ሚልኮል “‘እስከ’ ሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም” (2 ሳሙ 62÷3) ይላል። መቼም ከሞተች በኋላ እንዳልወለደች የታወቀ ነው።

(ለ) ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “እነሆም እኔ እስከ’ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ 28÷20) አለ። በእርግጥ ከዘመን ፍጻሜ በኋላም ማለት ነው። 

(ሐ) ጌታ ለክርስቶስ እንዲህ አለው፦“እግዚአብሔር ጌታዬን። ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ ‘እስከ’ አደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው” (መዝ 110 ÷1) ። በእርግጥ ክርስቶስ ለዘላለም በአብ ቀኝ መቀመጡን ይቀጥላል።

ለዚህ ነጥብ አያሌ ምሳሌዎች አሉ። ስለዚህ ‘እስከ’ የሚለው ቃል ከዚያ በኋላ የሚከተለው የግድ የፊተኛውን ተቃራኒ ይሆናል ማለትን አያስከትልም። 

ዮሴፍ ድንግል ማርያም የበኵር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም። የመጀመሪያ ልጇን ከወለደችም በኋላ ቢሆን አላወቃትም። ክርስቶስን ከመውለዷ በፊት ከታቀበ ከወለደችስ በኋላ ምን ይሰማዋል? ታምራዊ ምልክቶቹን ፣ መላእክቱንና ጠቢባኑን ካየ በኋላ  ሕጻኑ ቅዱሱ፣ አማኑኤልና አዳኝ  መሆኑን ካወቀ በኋላ  ዮሴፍ ምን ይሰማው? 

ሕጻኑ የነቢዩ ኢሳያስ ትንቢትን የፈጸመው ‘ክርስቶስ’ እንደነበር ዮሴፍ ተገንዝቧል። ትንቢቱም፦ “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” (ኢሳ 7÷14) ። “ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። ከዚያሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፥ ለሰላሙም ፍፃሜ የለውም።” (ኢሳ 9÷ 6፣ 7)። ለማርያም በታያት ጊዜ መልአኩ የጠቀሰው የዚህን ክፍል የመጨረሻውን ጥቅስ መሆን አለበት (ሉቃ 1÷31-33 ) ።

(5) ‘‘ወንድሞቹ’ ስለሚለው ሐረግ

በዕብራይስጥ አባባል ‘ወንድሞቹ’ የሚለው ቃል የቅርብ ዝምድናን ወይም የእንጀራ አባት (እናት) ልጆች መሆንን ሊያመለክት ይችላል። ለዚህ ከመጽሐፍ ቅዱስ በርካታ ምሳሌዎች አሉን። 

(i) ‘ያዕቆብ’ና አጎቱ ‘ላባ’

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ያዕቆብና ራሔል መገናኘት እንዲህ ይላል፦ “ያዕቆብም የእናቱን ወንድም የላባን ልጅ ራሔልንና የአጎቱን የላባን በጎች ባየ ጊዜ፥ ቀረበ ከጕድጓዱም አፍ ድንጋዩን ገለበጠ፥ የ’አጎቱ’ን የላባን በጎችንም አጠጣ።ያዕቆብም ራሔልን ሳማት፥ ቃሉንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ። ያዕቆብም የ ‘አባትዋ ዘመድ’ና  የርብቃ ልጅ መሆኑን ለራሔል አስታወቃት፤ እርስዋም ሮጣ ሄዳ ለአባትዋ ይህን ነገር ነገረችው” (ዘፍ 29÷10-12) ። ምንም እንኳ የእናቱ ወንድም ቢሆንም ያዕቆብ የራሔል አባትን ወንድሜ አለው። የ‘እናቱ ወንድም’ የሚለው ሐረግ በምዕራፉ ተደጋግሞ ተጠቅሷል። ወንድም የሚለው ቃል የቅርብ ዘመድ መሆኑን ለማመልከት ነው።  

“ላባም ያዕቆብን። ወንድሜ ስለሆንህ በከንቱ ታገለግለኛለህን? ምንዳህ ምንድር ነው? ንገረኝ አለው።” (ዘፍ 29÷ 15) ። ላባም ያዕቆብን ወንድሜ አለው ምንም እንኳ የእህቱ ልጅ ቢሆንም። 

(ii) አብርሃምና ሎጥ

ሎጥ የአብርሃም የወንድሙ የ‘ሐራን’ ልጅ ነው (ዘፍ 11÷31) ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “አብራምም ወንድሙ እንደ ተማረከ በሰማ ጊዜ በቤቱ የተወለዱትን ሦስት መቶ አሥራ ስምንት ብላቴኖቹን አሰለፈ፥ ፍለጋቸውንም ተከትሎ እስከ ዳን ድረስ ሄደ” (ዘፍ 14÷14) ይላል። ምንም እንኳ የወንድሙ ልጅ ቢሆንም ከቅርብ ዝምድናው የተነሳ እዚህ ላይ ‘አብርሃም’ ‘ሎጥ’ን ወንድሜ ብሎታል። 

እንደዚሁ የኢየሱስ ‘ወንድሞቹ’ የሚለው ሐረግ የክርስቶስን ያክስቱን ልጆች ለመጥቀስ ጥቅም ላይ የዋለ ነው

የጌታ ወንድሞቹ እነማናቸው? 

ጌታ ወደ ራሱ አገር በሄደ ጊዜ ሕዝቡ በመገረም እንዲህም አሉ፦“ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን? እንኪያስ ይህን ሁሉ ከወዴት አገኘው? ተሰናከሉበትም” (ማቴ 13 ÷55፣ 56) ፣ (ማር 6÷1-3)።

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ  የጌታን ወንድም ያዕቆብን ማየቱን ገልጿል። “ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር ከሐዋርያት ሌላ አላየሁም” (ገላ 1÷19)። ከ‘ዘብዴዎስ ልጅ’ ያዕቆብ ለመለየት ይኸኛው ‘ታናሹ’ ያዕቆብ ተብሎ ይጠራል (ማር 15÷40)። የ’እልፍዮስ ልጅ’ም ይባላል (ማቴ 10÷ 3) ፤ ከሐዋርያቱ መካከል አንዱ ነው (ገላ 1÷19)። 

ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ በዕለተ ስቅለት“ኢየሱስን እያገለገሉ ከገሊላ የተከተሉት ብዙ ሴቶች በሩቅ ሆነው ሲመለከቱ በዚያ ነበሩ፤ ከእነርሱም መግደላዊት ማርያምና የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ነበሩ” (ማቴ 27÷55:56) ይላል ።

ታዲያ ማርያም ተብላ የተጠራችው የያዕቆብና የዮሳ እናት ማን ነበረች? ድንግል ማርያም ነበረችን? ድንግል እነዚህን ሁሉ ወልዳለች የሚል ግምት የሚመስል ነገር ነውን?  

የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም ነበረች፤ እርሷም የ’ሐልፋ’ ወይም የ’ቀለዮጳም’ ሚስት ነበረች። ቅዱስ ዮሐንስ “በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር” (ዮሐ 19÷25) ብሎ የተናገረላት ማርያም ማለት ናት። ይህንን ጥቅስ ከቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል 27÷ 55፣ 56 ጋር አነጻጽሩ። 

እንደ ማቴ 27÷55፣56 የያዕቆብና የዮና እናት የነበረችው ማርያም ከመግደላዊት ማርያም ጋር በክርስቶስ መስቀል አጠገብ ነበረች። በጌታ ቀብር ላይ የተገኙት፣ ወዴት እንዳኖሩትም ያዩት፣ ሰንበትም እንዳለፈ ሽቶ ለመቀባት ያመጡለትም እነዚሁ ሁለት ሴቶች ነበሩ (ማር 16÷1) ።“በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር” (ዮሐ 19÷25) በማለት ቅዱስ ዮሐንስ የተናገረውም ስለነዚሁ ነበር። 

ስለዚህ የኢየሱስ ወንድሞች የተባሉት የአክስቱ ልጆች ናቸው። የድንግል እህት፣የቀለዮጳም ወይም የሐልፋ ሚስት፣ የያዕቆብ የዮሳና የሌሎች ወንድሞቹ እናት የሆነችው የማርያም ልጆች ናቸው።  

ቀለዮጳምና ሐልፋን በተመለከተ ያለው ልዩነት የቃላት አነባበብ ልዩነት ሊሆን ይችላል ወይም ቅዱስ ‘የሮም’ እንዳለው ለአንድ ሰው ካንድ በላይ ስም መስጠት  በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተለመደ አልነበረምና ሁለቱም ያንድ ሰው ስም ሊሆኑ ይችላሉ።ለምሳሌ፦ የሙሴ አማች‘ራጉኤል’ (ዘጸ 2÷18) ተብሏል። በሌላ ሥፍራ ደግሞ ‘ዮቶር’ (ዘጸ 4÷18) ተብሏል። ‘ግዴዎን’ ’ይሩበኣል’ (መሳ 6÷32)  ‘ጴጥሮስ’ ‘ስምዖን’ና ‘ኬፋ’ ይባል ነበር። ቀነናዊው ‘ስምዖን’ ‘ታዴዎስ’ ይባል ነበር (ማቴ 10 ÷ 3)። 

የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም ድንግል ማርያም አለመሆኗ ግልጽ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ድንግል ማርያም በዚያ ስም ተጠርታ አታውቅም። 

አስተያየት÷

(1) እነዚያ ሁሉ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ኖረዋት ቢሆን ኖሮ በመስቀል ላይ በሆነበት ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱን ድንግል ማርያምን ለሐዋርያው ዮሐንስ አደራ ማለቱ የማይመስል ነው። ልጆች ኖረዋት ቢሆን ኖሮ ያለጥርጥር የሚንከባከቧት እነርሱ በሆኑ ነበር። 

(2) ዮሴፍና ማርያም ወደ ግብጽ በሄዱበት ጊዜም ሆነ ከግብጽ በወጡበት ጊዜ ከክርስቶስ በስተቀር የድንግል ማርያም ሌሎች ልጆች እንዳልተጠቀሱ ልብ እንላለን (ማቴ 2÷14፣ 20፣ 21) ። ጌታ ኢየሱስ ዕድሜው 12 ዓመት በነበረበት ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌምና ከኢየሩሳሌም ባደረጉት ጉዞም እንዲህ ዓይነት ነገር አልተጠቀሰም (ሉቃ 2÷43) ። 

(3) አንዳንዶች “የ’ኢየሱስ ወንድሞች’ የተባሉት ዮሴፍ ከሌላ ሚስት የወለዳቸው ልጆች ናቸው።ይህችው ሚስቱ በሞት በመለየቷ ያለ ሚስት ይኖር ነበር”ይላሉ። ይህ ግን የማይመስል ነገር ነው። ምክንያቱም ከላይ እንደጠቀስነው የያዕቆብና የዮና እናት ክርስቶስ በመስቀል ላይ በተሰቀለበት ጊዜም በቀብሩ ሥፍራም ተገኝታ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ገልጧልና።

ማርያም ለዘላለም ድንግል ስለመሆኗ ግልጽ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አለ። ነቢዩ ሕዝቅኤል በትንቢቱ የተዘጋውን በር በምሥራቅ በኩል አየ። እንዲህም ተነገረው፦ “እግዚአብሔርም፦ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፥ ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል” (ሕዝ 44÷2) ። ይህ በር የድንግል ማህጸን ነው። ጌታ ኢየሱስ የገባበትና ተዘግቶ የሚኖር በሌላ ልጅም ያልተከፈተ ነው። 


Comments

Popular posts from this blog

Comparative Theology የነገረ መለኮት ንጽጽር (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት)/ በብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሲኖዳ ሳልሳዊ

 የነገረ መለኮት ንጽጽር  (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት): የወደደ  ሁሉ በነጻ እንዲጠቀምበት ተፖስቷል። ይሁን እንጂ መብቱ በሕግ የተጠበቀ ስለሆነ በየትኛውም መልኩ ለንግድ እንዲውል አልተፈቀድም። ልዩ ልዩ መግቢያ የሚለውን መጀመሪያ ካነበቡ በኋላ የተቀረውን በተመረጠው ቅደም ተከተል ማንበብ ይቻላል። ልዩ ልዩ መግቢያ   ጥምቀት   ትውፊት (ወግና ልማድ)   መካከለኝነት   ጾም የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ መንፈሳዊ ስጦታዎችና በልሳኖች የመናገር ስጦታ   ሥርዐት ንስሐ

ስለ "አስታዋሽ ጾምና በዐሉ" ጥያቄና መልስ

 ስለ "አስታዋሽ ጾምና በዐሉ" ጥያቄና መልስ  ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ፦ ሕልውናችንን-ነጻነትችንን የማረጋገጥና የማስቀጠል አንድነታችንን የመጠበቅና የማጠንከር  በእሴቶቻችን የመደሰት፣ እነርሱን የመንከባከብና የማስተዋወቅ  በረከታችንን የማብዛትና የማካፈል  ኃላፊነቶቻችንን በማኅበር ፣ በማስተዋልና በትጋት እንድንወጣ “ጾሙና በዐሉ" አስታዋሽ ባሕላዊ ምልክታችን ይሁንልን   ጥያቄ 1 ፡ አድማጭ ተመልካቾቻችን እንኳን ደህና መጣችሁ።የከበረ ሰላምታችን ይድረሳችሁ። ዛሬ የምንወያየው ከአቶ ባንቱ ገብረማርያም ጋር ይሆናል። አቶ ባንቱ በሙያው ፋርማሲት ነው። እንደነገረኝ በእምነቱ ደግሞ ባፕቲስት ነው።ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ባሕላዊ ምልክት የሚሆን “ጾምና በዐልን” በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል። የምንወያየውም ስለዚሁ "ጾሙና በዐሉ" ምልክትነት ይሆናል።  አቶ ባንቱ ለመወያየት  ወደ እኛ በመምጣትህ አመሰግንሃለሁ። እንኳን ደህና መጣህ። አንተ እያልኩ ልቀጥል ወይስ አንቱ? መልስ 1፡ ዎገኔ፡   እንኳን ደህና ቆየኸኝ። ለአድማጭ ተመልካቾቻችሁም ሰላምታዬ ይድረስልኝ። አንተ በለኝ። የሚያውቀኝ ሁሉ አንተ ነው የሚለኝ።  ጥያቄ 2 ፡ እሺ  አንተ እያልኩ እቀጥላለሁ። አቶ ባንቱ፣ ምናልባትም ብዙ ሰው ስለማያውቅህ  እስቲ ስለራስህ በአጭሩ ንገረን። ወዲያውም መክፈቻ ይሆነናል መልስ 2 ዎገኔ ፦ አስቀድሜ ይኸን ዕድል ስለሰጠኸኝ ላመሰግንህ እወዳለሁ። አድማጭ ተመልካቾችህንም ጊዜ ወስደው  ውይይቱን  ስለሚከታተሉ ላመሰግናቸው እወዳለሁ።አዎን፣ ባንቱ ገብረማርያም እባላለሁ።እንደነገሩኝ የተወለድኩት ሽርካ በዛሬ አጠራሩ በአርሲ ዞን ነው።ነፍስ ያወቅሁትና ትምህርት ...