አድማጭ ተመልካቾቼ አንደምን ከረማችሁ? የአብርሃም አምላክና አምላካችን የተመሰገነ ይሁንና እኔ ደህና ነኝ።"ከቄስ (ዶ/ር ) ቶሎሳ ይልቅ" በሚል ርዕስ ያዘጋጀሁትን የሚከተለውን መልዕክቴን እንድትከታተሉልኝ በታላቅ አክብሮት እጠይቃችኋለሁ። ባንቱ ገብረማርያም ነኝ ከቄስ (ዶ/ር) ቶሎሳ ይልቅ ቄስ (ፓስተር) ዶ/ር ቶሎሳ ጉዲና በበኩሌ የማከብራቸው ሰው ናቸው። በወንጌል አማኞች መኻል ለበርካታ ዐመታት ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የተናገሩ፣ ያሳሰቡና የጸለዩ መሆናቸውን ተከታትዪአለሁ። በነገዳቸው የተደራጁትን የወንዛቸው ልጆችን ወጥሬ ወቀሳ ተቋቁመው ለመላው ኢትዮጵያዊ ሲጮኹ የኖሩ ናቸው።ዛሬም ድረስ ለወንዛቸው ልጆች በማድላት አይታሙም። በተለያዩ ጊዜያት ስለ እሬቻ ያሰሙትን መልዕክትም እንደ ሞዴል የማየው ነው። እሬቻን እንዳይከተሉና እንዳያስፋፉ የአሁኖቹን የመንግሥት ዐላፊዎች የመከሩበትንም ጊዜ አስታውሳለሁ። ዛሬም ይኸንኑ ለማድረግ አልታከቱም። የወንጌላውያን ሽማግሌ ብቻ ሳይሆኑ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌ አድርጌ አያቸዋለሁ። ይህን መደላድል የማስቀምጠው ስለእርሳቸው ያለኝን በጎ አስተያየት ለማስታወቅና ይኸው ሐሳቤ የጸና መሆኑን ለማስጮህ ነው። አስተያየቱን አልጠየቁኝም፣ የሚጨምርላቸውም ሆነ የሚቀንስባቸው ነገር እንደማይኖርም ጠንቅቄ አውቃለሁ። መደላድሉን አስቀድሜ ማስቀመጤ በተናገሩት ላይ ጥያቄ ሳነሳ ወንድሞችንና እህቶችን “አይዟችሁ አትደንግጡ” ለማለት ያህል ነው። ...