ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ትሻል? አድማጭ ተመልካቾቼ እንደምን ከረማችሁ? ቸሩ መደኅኒዓለም ይመስገነውና እኔ ደህና ነኝ። ዛሬ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን መውቀሴን ስለማቆሜ እን ዲሁም በካውንስሉ ስለገባኝ ሥጋቴ አካፍላችኋለሁ። ሐሳቡ የግሌ ነው። ወንጌል አማኞችን በአጠቃላይ ሆነም ፣ አባል የሆንኩባትን ቤተክርስቲያን አይወክልም። ወቀሳዬን በመተዌ ለኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሚጨምርላት ነገር የለም። ባልተወውም የሚያጎድልባት ነገር የለም። ምናልባትም ነገሩን በማንሳቴ ሊቆጡብኝ የሚችሉ ይኖራሉ። ስለወቀሳው የማወጋው በጓዳዬ የማወጣውንና የማወርደውን ወደ ብርሃን ለማውጣት ያህል ነው። ስለ"ወንጌላዊ አማኞች ካውንስሉ" ለመጻፍ የተነሳሁት ደግሞ የካውንስሉ ቦርድ በ13ኛ መደበኛ ስብሰባው ያሳለፈው ውሳኔ አሳስቦኝ ነው። ሁለቱን አንድ ላይ ማቅረቤ ግን ተገጣጥሞብኝ ነው። እንደተለመደው በትዕግሥት ተከታተሉኝ! አሁን ወደ ሐሳቡ እገባለሁ። ከቀደሙትና ዛሬ በሕይወት ከሚገኙት የወንጌል አማኞች መኻል የምቆጠር ነኝ።ታዲያ በዚያ በወጣትነት ዘመኔ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስደት አድርሳብን እንደነበር አስታውሳለሁ።በግሌ እንኳ ወላጆቼ እንዲቆጣጠሩኝ ክቤተክርስቲያኒቷ ተመክረው ነበር። በተለይም አባቴ ደብተራ በመሆኑ “የቤተክርስቲያን አገልጋይ ልጅ ሆኖ እንዴት የመጤ ሃይማኖት ተከታይ ይሆናል” የሚል ጫና ነበረበት።በጊዜው አብሬው (ማለትም ከወላጆቼ ጋር) የማልኖር ስለነበር ሊያደርግ የቻለው ነገር አልነበረም። ይሁን እንጂ በግል ከማውቃቸው የሥጋ ዘመዶቼና ...