ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ትሻል?
አድማጭ ተመልካቾቼ እንደምን ከረማችሁ? ቸሩ መደኅኒዓለም ይመስገነውና እኔ ደህና ነኝ።
ዛሬ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን መውቀሴን ስለማቆሜ እንዲሁም በካውንስሉ ስለገባኝ ሥጋቴ አካፍላችኋለሁ። ሐሳቡ የግሌ ነው። ወንጌል አማኞችን በአጠቃላይ ሆነም ፣ አባል የሆንኩባትን ቤተክርስቲያን አይወክልም። ወቀሳዬን በመተዌ ለኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሚጨምርላት ነገር የለም። ባልተወውም የሚያጎድልባት ነገር የለም። ምናልባትም ነገሩን በማንሳቴ ሊቆጡብኝ የሚችሉ ይኖራሉ። ስለወቀሳው የማወጋው በጓዳዬ የማወጣውንና የማወርደውን ወደ ብርሃን ለማውጣት ያህል ነው። ስለ"ወንጌላዊ አማኞች ካውንስሉ" ለመጻፍ የተነሳሁት ደግሞ የካውንስሉ ቦርድ በ13ኛ መደበኛ ስብሰባው ያሳለፈው ውሳኔ አሳስቦኝ ነው። ሁለቱን አንድ ላይ ማቅረቤ ግን ተገጣጥሞብኝ ነው። እንደተለመደው በትዕግሥት ተከታተሉኝ!
አሁን
ወደ ሐሳቡ እገባለሁ።
ከቀደሙትና
ዛሬ በሕይወት ከሚገኙት የወንጌል አማኞች መኻል የምቆጠር ነኝ።ታዲያ በዚያ በወጣትነት ዘመኔ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስደት
አድርሳብን እንደነበር አስታውሳለሁ።በግሌ እንኳ ወላጆቼ እንዲቆጣጠሩኝ ክቤተክርስቲያኒቷ ተመክረው ነበር። በተለይም አባቴ ደብተራ
በመሆኑ “የቤተክርስቲያን አገልጋይ ልጅ ሆኖ እንዴት የመጤ ሃይማኖት ተከታይ ይሆናል” የሚል ጫና ነበረበት።በጊዜው አብሬው (ማለትም
ከወላጆቼ ጋር) የማልኖር ስለነበር ሊያደርግ የቻለው ነገር አልነበረም። ይሁን እንጂ በግል ከማውቃቸው የሥጋ ዘመዶቼና የሥጋ ዘመዶቼ
ባልሆኑ በአጠቃላይ ጥቂት በማይባሉ የኢትዮዽያ ወንጌል አማኞች የደረሰውን ፈተና አስታውሳለሁ። ቁጥራችን ትንሽ ከመሆኑና ብዙም የምንፈናፈንበት
መንገድ ያልነበረ በመሆኑ እነዚህ ሁኔታዎች ክፉኛ አልተመቹንም ነበር።ይሁን እንጂ ስለ እምነታችን የተቀበልነው መከራ አድርገን በመቁጠር
ተጽናንተናል፣ ደስ ተሰኝተናል።እርስ በእርስ ተደጋግፈን ተወጥተነዋል።
ታዲያ እንደዚያ ከነበረ “ዛሬ ላይ ወቀሳህን ለምን ተውከው ?” ያላችሁኝ እንደሆን መልሴ "ያስተዋልኳቸው ነገሮች በመኖራቸው ነው" ይሆናል።
በቤተክርስቲያኒቷ ደረጃ የሚታወቁ ነበሩ የምላቸውን አራቱን ድርጊቶች አንስቼ በእያንዳንዳቸው ሥር አስተውዬአቸዋለሁ የምላቸውን አሰፍራለሁ። ሁሉም ዐይነት መከራዎች፣ በሁሉም ሥፍራ፣ በሁሉም የወንጌል አማኝ ላይ ደርሰው ነበር ለማለት እንዳልሆነ ግን ልብ ይሏል። መከራው ያነጣጠረው በወንጌላዊ እምነት ላይ ስለሆነ ነው በሁላችንም ላይ እንደደረሰ አድርጌ የምጽፈው።
1.ስም
ማጥፋት።
“ከኮርኒስ ሳንቲም እያወረዱ ያታልላሉ፣ ክርስቶስ ከእኛ ይወለዳል እያሉ ልጃገረዶችን ያማግጣሉ” የሚል ወሬ ተነዛብን።
ማስተዋል አንድ
ከአንድ ማሠሮ ባቄላ ውስጥ አንድ ያልበሰለ ሊገኝ እንደሚቻለው ዝሙትን ያደረጉ ሊገኙ ቢችልም ይህ ወሬ ግን ውሸት መሆኑን ማኅበረሰቡ ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደበትም። ኦርቶዶክሳውያኑን ወደ እኛ እምነት እንዳይመጡ ለማድረግ ውጤታማ የነበረም አይመስለኝም።በእኛ ላይም ያመጣው መጨናነቅ እምብዛም አልነበረም ማለት ይቻላል።
2.መለየት/ማግለል
የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ሃይማኖታቸውና ሃይማኖታችን ነበር። የእነርሱ ማኅበርተኞች ነበርን።እንደዚህ ሳለ እኛ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት የምንለው - እነርሱ ግን ለዶግማቸውና ለቀኖናቸው እንግዳ በመሆኑ- መጤ የሚሉትን እምነት ተቀበልን። ያንን የተቀበልን ጊዜ ከዚያ ማኅበር ራሳችንን ለይተናል ማለት ነው።ነገር ግን ከእነርሱ መኻል አልወጣንም። እንዳውም መኻከላቸው ቆይተን ከምዕመናኖቻቸው ተጨማሪ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ የምንለውን ትምህርት እንዲከተሉ ሠራን። እነርሱ ደግሞ "እንግዳ ትምህርታችሁን ለምዕመኖቻችን አታስተምሩ /አትበክሏቸው - ከእኛ ወገን እስካልሆናችሁ ድረስ ከእኛ መኻል ምን ታደርጋላችሁ? ውጡልን" አሉ። አሻፈረን ባልንበት አንዳንድ ሥፍራ ዱላም ተከትሎብናል። ምዕመናኖቻቸው ከመሠረቱት ዕድርም አስወጡን፣ እንዳንገባም ከለከሉን። አንዳንድ ወላጆችም ልጆቻቸውን ከቤት ያስወጡ ይገኛሉ።
ማስተዋል ሁለት
ቅሬታን ለመቋጠር ይህ አንዱ ምክንያቴ ነበር። ያው ልጅ ሳሉ እንደልጅ ማሰብ ያለ ነገር አይደል? ታዲያ
አሁን ከጥንት የቤተክርስቲያን ታሪክ ስረዳው “ምን ማድረግ ነበረባቸው?” ብዬአለሁ።
ታሪክ
እንዳመለከተኝ ከሆነ ከኦርቶዶክስ እምነት የወጣ ሲኖር ፤ ማውገዝና መለየት ከአባቶቻቸው የተላለፈላቸው ትምህርት ነው። ታዲያ “ሃይማኖቱን
እንደሚያከብር ሰው ከዚያ የተለየ ምን ማድረግ ነበረባቸው?”
እኛ ካደረግነውም ጋር አነጻጸርኩት።በመኻከላችን ገብተው ትምህርታችንን
በሚገለብጡት ላይ (ማለትም የሐሰት ትምህርት አስተማሪዎች ባልናቸው ላይ) ምን የተለየ ነገር አደረግን? ያደረግነው ማውገዝና (መቃወምና)
መለየት አልነበረምን? በእኛ ዘንድ እንዳያስተምሩ መድረኩን መከልከልስ አልነበርምን? ለኦርቶዶክሳውያንስ ቢሆን እንዲሰብኩበት መድረካችንን
እንሰጣቸዋለን? ኦርቶዶክሳውያኑ
ተመሳሳይ ነገር ሲያደርጉ ስደት ይባላልን?እነርሱም የከለከሉን እኮ እነርሱጋና ለእነርሱ እንጂ ለሌሎች እንዳንሰብክ እልነበረም።
አሁን ላይ ምዕመናቸውን ከቸውና ቀኖናቸው እንዳይወጣ ለመከላከልና
አንድነታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ የራሳቸው ምዕመን በነበርነው በእኛ ላይ የወሰዱት የዲስፕሊን ርምጃ ብቻ አድርጌ አየዋለሁ
3.የቀብር
ሥፍራ ተከልከለናል
በመቆየት ብዛት እኛም ከመኻከላችን በሞት የሚለዩ ኖሩና ኦርቶዶክስ ለምዕመኖቿ ከምትሰጠው አገልግሎት መኻል የቀብር ሥፍራን ጠየቅን። የቀብር ሥፍራውም "ለእኛ ምዕመናን የተቀደሰ ሥፍራ ነው እንጂ ለተለያችሁቱ ለእናንተ አይደለም" በማለት እምቢ አሉን። ይህ መቼም እጅግ የሚያም ትዝታ አለው።ከዚህ ጋር በተያያዘ ብዙ የሚያሳዝኑ ታሪኮች ሆነዋል።የሚያሙ ይገኙበታል። በተለይ በአምነት ከእኛ ይልቅ ለሚርቋቸው ለ“ደርጎች” ፈቅደው እኛን እንዴት ይከለክሉናል በሚል ቅሬታዬን ምክንያታዊ አድርጌ አየው ነበር። በአርግጥ ለማወዳደር ትንሽ ይከብዳል። ደርጎቹ ሲጀመር የኦርቶዶክስን ፈቃድ አልጠየቁም፣ ነጠቋቸው እንጂ። እዚያ ላይ ይልቁንም ኦርቶዶክስ ተሰዳለች ማለቱ የበለጠ እውነትነት አለው።
ማስተዋል ሦስት
ይሁን እንጂ አሁን ላይ አስተያየቴ ተለውጧል።ሳስበው እንዳው
ለመሆኑ የቀብር ሥፍራ ከእነርሱ መጠየቃችን ስለ ምን ነበር? ስለ ምን ከሌላ ሃይማኖት የቀብር ሥፍራ አልጠየቅንም? ደግሞስ የቀብር
ሥፍራ መጠየቅ መንግሥትን እንጂ ሌላ ማንን መሆን ነበረበት? ይህንን ስል ቤተሰባዊ ትሥሥራችንና የጊዜው ሁኔታ ኦርቶዶክስን እንድንጠይቅ
ያስገደደ መሆኑን አልሳትኩትም። “ሃዘኑ የራሳቸውም ሆኖ ሳለ ሃዘኔታንና ሰብዓዊነትን አሳይተው ቢሆን ኖሮ መልካም ነበር” ከማለት
በስተቀር መብት ነበረን ወይ ለማለት ነው?
አሁን የቀብር ሥፍራ አግኝተናል። አንድ ሰው ቢጠይቀን ከእኛ ሃይማኖት
ውጭ ለሆነ ሰው የቀብር ሥፍራ እንሰጣለን? ሊያውም የተቀደሰ ለማንለው ሥፍራ።
ይህን
አስተያየቴን ያጸናው ደግሞ ከዓለማዊ ሥርዓትም ልብ ያልኩት ጉዳይ ነው።በዓለማዊ አሠራርስ ቢሆን ደምብና መመሪያ ባልተከተለ አባል
የሚደረገው ከማኀበሩ ማስወጣትና ከማኀበሩ የሚገኘውን ጥቅም መከልከል አይደለምን? ታዲያ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከዚያ የተለየ
ምን ነገር አደረገች?
4.የሁለተኛ
ዜግነት ስሜት ተሰምቶናል፡
ከጓደኞቼ ጋር ስናወራ የሚነሳው ነገር ደግሞ የሁለተኛ ዜጋ ስሜት እንዲሰማን ተደርገናል የሚለው ነው።ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖች እኩል ተደርገን እንደተቆጠርን አልተሰማንም ።ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኦርቶዶክሰኣውያኑን ይሰሙ እንደነበር የሚታወስ ነው። ከእነርሱ ጋር ተደርበው በእኛ ላይ ጫና ያበዙ ነበር። ከዚያም ወዲህ አጠቃላይ መገለላችን የሁለተኛ የዜግነት ስሜት አሳድሮብናል ማለት ይቻላል።
ማስተዋል አራት
ነገር ግን ቆም ብዬ ሳስበው ኦርቶዶክሶች ከእምነት ጋር በተገናኘ ከራሳቸው ቤት አገለሉን እንጂ አትማሩ፣ አትነግዱ፣
አትግዙ፣አትሽጡ፣ አትለውጡ ፣ ሥራ አትቀጠሩ፣ ከሥራ ተባረሩ፣ ንብረት አታፍሩ፣ ክሥፍራ ሥፍራ አትዘዋወሩ አላሉንም። እንዳውም ያለሥጋት መዘዋወርና ወንጌልን መስበክ
እንድንችል አብዩን ሥራ የሠሩ እነርሱ ነበሩ። ለእኛ ያደላል የሚባለው የአሁኑ መንግሥት የሚሠራውን ከዚያ ጋር በማነጻጸር የቀደመ
ሐሳብን መከለስ አይገባምን? ብቻ ሁልጊዜም የሚሰማ የራስ ህመም ሆነና ነው መሰለኝ ይኸኛውን ልብ አንለውም።
ከራሴ ጋር እንዲህ በመሟገት ብዛት ነው ቅሬታዬን ለማንሳት የመረጥኩት።
አሁን ወንጌል አማኞች በራሳችን ቤት ደርጅተን አለን። ከእነርሱ
በወጣነው ላይ ሌሎችንም አክለን ራሳችንን ችለን እየሠራን ነው። መቼም እንደቀድሞው ዛሬ ኦርቶዶክሶቹ ከእኛ ተለዩ አይሉም። ቢሉም ትርጉም ያለው
አይመስለኝም። ምናልባት ሊሉን የሚችሉት “ቀጥተኛዋን ትምህርት ተከተሉ፣ ይህን ወደ ምናስተምረው ወደ እኛ ተመለሱ“ሊሆን ይችላል። ተመለሱ ማለት ብቻ ሳይሆን ለምን እንደወጣን ይመረምሩና ከእኛ ውጤታማ አሠራር
ለመማርም ያስቡ ይሆናል። ለማንኛውም የሚያደርጉትን እነርሱ ያውቃሉ።
እኔ
ግን አሁን ወደ ራሴ ወገኖች ልምጣ። የባሰው እየመጣብን ያለ ይመስላል። ያውም ከእኛ ወገን አይደላችሁም ከሚለን ሳይሆን የእኛ ወገን
ናችሁ ከሚለን- ከ"ወንግሌል አማኞች ካውንስሉ"።
ካውንስሉ ሲቋቋም አንስቶ እስካሁን ድረስ ቅይጥነቱና ያስከተለውን ጭቅጭቅ አቃልዬ አላየውም። ይህንን ለጊዜው ልተወውና ፤ ቦርዱ በ13ኛ መደበኛ ስብሰባው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ለምን እንዳሳሰበኝ ላስረዳ።
የካውንስሉ ቦርድ በዚያ ስብሰባው የብዙሃን መገናኛውን መደበኛና ማኅበራዊ
ሚዲያ በማለት በሁለት ከፍሎታል። የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን ደግሞ የሚታወቁና የማይታወቁ ግለሰቦች በሚል ሁለት ሥፍራ ከመደበ
በኋላ መደበኞቹን ስለመደገፍ ፥ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ግን ስለመቆጣጠር ይናገራል።በአገራችን ነጻነትን ከመገደብና ግፍን ከመሥራት ጋር
ተያይዞ ስለሚታወስ “ቁጥጥር” ሲባል ከደጉ ይልቅ ክፉው ነው የሚያቃጭል። ስለዚህ ሐሳቤ ክፉውን ወደ መጠርጠር አድልቶብኛልና አትፍረዱብኝ። ልቀጥል፡-
ሥጋት 1. ማኅበራዊ ሚዲያን መረበሽ
“መደበኛ
ሚዲያዎች ስህተት ይሠራሉ። የሚሠሯቸው ስህተቶቹ ግን ጥቃቅን ናቸው። በሂደትም ይታረማሉ። ለስህተታቸው ጥቃቅን መሆን ምክንያቱም
ሕግና ደምብን ተከትለው መሥራታቸው ነው ይላል” (የሕዝብ ግንኙነቱ ጥናት በራሴ አገላለጽ)።
ሀ) ያው መግለጫው አጭር ከመሆኑ የተነሳ ሊሆን ይችላል ብዙ ነገር
ግልጽ አልተደረገም። ጥቃቅን የሚላቸው ስህተቶቹ ምንድናቸው? አሁን የሌለ፣ ነገር ግን ጥቃቅን የሚላቸው ስህተቶች ሲታረሙ የሚገኘው
ውጤት ምንድነው? ስላልተገለጡ አድማጭ የራሱን ቅን ፍርድ ለመስጠት አያመቸውም። ያ ውጤት ክፉ አይሆንም ብሎ ማመን ግን ይቸግራል።
ለ) ለመደበኛ ሚዲያዎች ድጋፍ ለማድረግ መርጧልም፣ወስኗልም። ስለዚህ
መደበኛ ሚዲያዎች ቁጥጥር የሚያደረግባቸው አይደሉም ማለት ነው። ምናልባትም ማኅበራዊ ሚዲያውን በመቆጣጠሩ የሚተባበሩትም ሊሆኑ ይችላሉ።
በዚህ ዐይነት ማኀበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎቹን የመድፈቅ ወይም የማስደንበር ሥራ ለመሥራት አይተባበሩም ለማለት ያዳግታል።
ሐ) በመቀጠልም “የሚታወቁትም፣ የማይታወቁትም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ
ግለሰቦች ግን ትልቅ ስህተት ይሠራሉ። የቤተክርስቲያን ሰላም እያወኩ ነው።ሌሎቹም ስህተቶች አሉባቸውና እነዚያ ተጠንተው ይቅረቡ”
ይላልም ጥናቱ (አሁንም በራሴ አገላለጽ)
ምን መልዕክት ስላስተላለፉ ሰላም እንደደፈረሰ አልገለጸም። በእነዚህ
ሰዎች መልዕክት የየትኛው ወይም የየትኞቹ ቤተክርስቲያን ሰላም እንደተናጋም አልተነፈሰም። በወንጌላዊ አማኝ ቤት አንድ ቤተክርስቲያን
ብሎ ነገር የለምና ይህን ግልጽ ማድረግ ለግንዛቤ ይረዳ ነበር።መቼም ሰላም ከነሳ መልዕክታቸው እንጂ ግለሰቦቹ እንደማይሆኑ ግልጽ
ነው። የትኛው መልዕክት ወይም የትኞቹ መልዕክቶች ሰላም ነሣ/ነሡ? የማኅበራዊ ሚዲያ ለረዥም ጊዜ ተከታትዬአለሁ።ወንጌላዊ አማኞችን
በተመለከተ የሚተላለፉት መልዕክቶች
- የበርካታ አጥቢያ ቤተክርስቲያኖች የአምልኮና የቃል ጊዜያቸው
- መዝሙሮች፣ ቅኔዎች፣ ግጥሞችና ምስክርነቶች
- ነቢያትና ሐዋርያት ነን የሚሉት ትንቢታቸውና መልዕክታቸው፣ እነዚህኑ የሚሞግቱ ሐሳቦችና የ”ነቢያቱና የሐዋርያቱ” ምላሽ
- የአገልጋዮች ብልሹ አኗኗራቸው እንዲለውጡ ውትወታ (በዚህ ስማቸው የሚነሱትን ማለት ነው
- የነገረ መለኮት ክርክር
- የካውንስሉን ሥራ የሚደግፉ ፣ የሚተቹም አስተያያቶች
- ግለ ታሪክና ሌሎች የቅዱሳን ጽሑፎችም
- የአባቶችና መንፈሳዊ ዕውቀት ያላችው የሌሎችም ልምዳቸውና እውቀታቸው
- ትዳርን ለማጽናት ለማበልጸግም የሚጠቅሙ ምክሮች
- ከትዳር ጋር ተያይዥነት አለው ስለሚባለው ስስ ግብረ ሰዶማዊነት ( ቀላጤነት)
- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የወንጌል አማኝ ወጣቶች ከኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ጋር የሚያደርጉት ውይይት
የመሳሰሉት ናቸው። ከአነዚህ የትኛው ወይም የትኞቹ የሰላም መደፍረስ ምክንያት ሆነዋል? “በሚዲያ ሰበብ ሰላም ጠፋ” የሚለው “በሰላም
ሰበብ ማኅበራዊ ሚዲያ ይጥፋ” ለማለት ይሆን?
መ) በእርግጥ የግራም የቀኝም ፖለቲካ መልዕክት የሚያስተላልፉም ወንድሞችና እህቶች አሉ። ምናልባት ከእነዚያ እንዲከለከሉ የሚፈልጋቸው ኖረውት በቀጥታ ከመናገር መቆጠብን መርጦ ይሆን?
በፖለቲካ በኩል ያለውን ለሚመለከታቸው አካላት ቢተው ይሻላል ባይ ነኝ። በፖለቲካው
ገለልተኛ ቢሆንና ፖለቲከኞቹ እንደ ፍጥርጥራቸው እንዲሆኑ ቢተዋቸው ይመረጥ ይመስለኛል። የካውንስሉ ምርጫው በፖለቲካው መሳተፍና
ማዳላት ከሆነ ግን የቤተክርስቲያን ሰላም ለመደፍረሱ ሌሎችን መክሰስ አይገባውም እላለሁ።
ምን አደከማትሁ! የዐላማው እምብርት ቁጥጥር በመሆኑ፥ ተያያዥና ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮች በመኖራቸው በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ማኅበራዊ ሚዲያን የመረበሽና የማፈን አዝማሚያ ወይም ምኞት እንዳለው እንድጠራጠር አድርጎኛል። የመጀመሪያው ሥጋቴ ይህ ነው፡
ሥጋት 2. አስፈላጊ እርምጃ መውሰድ
ሁለተኛውና ዋናው ሥጋቴ ግን የመቆጣጠር ዐላማውን ለመፈጸም ሊከተል ያሰበው ዘዴ ነው።ዜናው ሲቀርብና ቦርዱ አመራራ ሲሰጥ የተጠቀመባቸው ኃይለ
ቃላት ነጎድጓዳማ ናቸው።
“ወሳኝ ውሳኔ፣ ቁጥጥር ፣ ሰላም አዋኪዎች፣ እርምጃ መውሰድ፣
አስፈላጊ- ሕጋዊ- ተገቢ እርምጃ” የሚሉ ይገኙበታል። በእነዚህ ቃላት መንፈሳዊ ቃና አላየሁባቸውም።ካውንስሉ በራሱ እርምጃ መውሰድ ቢያቅተው
እንኳ ማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎችን ለመንግሥት አሳልፎ ሊሰጥም ዝግጁ ነው። በመንግሥት ላይ መተማመን ይታይበታል።በመንግሥት የመተማመን ነገር ደግሞ ለኢትዮጵያ
ወንጌል አማኞች እንግዳ ነገር ነው።
እንደ መግለጫው ከተሄደ እርምጃው በማይታወቁ ተጠቃሚዎች ላይም ነው። እነዚያን ለማወቅ
ምን ሊያደርግ ነው? ከሚተባበሩት ጋር በመሆን የሚያደርገው ነገር ይኖራል? አስፈላጊ የሚለው ቃል ማንኛውንም እርምጃ ለመውሰድ ሽፋን
የሚሰጥ አነጋገር ነውና አደገኛ ነው። ሁለተኛውና ዋናው ሥጋቴ ይኼ ነው።
ለማጠቃለል፦
ጥርጣሬዬንና ሥጋቴን የሚጋራ አላገኝ ይሆናል። እኔ ግን አደገኛ አዝማሚያ ታይቶኛል። የራሳችን ወገን የምንለው፣ እርሱም ወገናችን
የሚለን በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ በመሆናችን ፣ “በቤተክርስቲያን ሰላም
ጠፋ ሰበብ” ሊከፋብንና ሊያስጨንቀን ነውን? እንደ ፕሮቴስታንት አስተሳሰብ ማንኛውም ሰው መጽሐፍ ቅዱስ እንደገባው ወይም መንፈስ
ቅዱስ እንዳስተማረው መናገሩ መከልከል የለበትም የሚል እምነት አለኝ።ቁጥጥር አያሻውም ባይ ነኝ። የሚነገረውን መቀበል አለመቀበል
የተከታታዩ ጉዳይ ነው።
ጎበዝ
ምን ትላላችሁ? ካውንስሉ “ትሻልን ትቼ ትብስን አመጣሁ” ሊሆንብን ይሆን እንዴ? ምን ይመስላችኋል? ደግነቱ ቀልድ መሆኑ ነው መሰለኝ
(bluffing እንደሚባለው) ፣ ቦርዱ የዜናውን ልጥፍ ከፌስ ቡክ አንስቶታል አሉ።
በትዕግሥት ስለተከታተላሁኝ አመሰግናለሁ።
ሁሉ ቀን መልካም ቀን ይሁንላችሁ!
ባንቱ ገብረማርያም።
12/18/2025
Comments
Post a Comment