Skip to main content

ጥምቀት

 

ጥምቀት

 

 

 

(1) የጥምቀት ፍቱንነቱ

(2) ማጥመቅ የካህን ተግባር ነው

(3) የጥምቀት አስፈላጊነቱ

(4) ጥምቀት በመንከር (በመጥለቅ)

(5) የልጆች (የሕጻናት) ጥምቀትሳቦች

(6) ተቃውሞዎች

 

ጥምቀት

 

በእኛ በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንቶች መኻል ጥምቀትን በተመለከተ ያሉት ልዩነቶች

የጥምቀትን ትምህርት በአምስት ጉልህ  ፍሬ ነገሮች ሥር አጠቃሎ መነጋገር ይቻላል።


(1)    የጥምቀት  አስፈላጊነቱ  ምንድነው? ፍቱንነቶቹስ (ጠቀሜታዎቹስ) ምንድናቸው?

ኦርቶዶክስ ጥምቀት ‘ድኅነት’ን፣ ‘መንጻት’ን፣ ‘መጽደቅ’ን፣ የ‘ሕይወት መታደስ’ን እና በ’ክርስቶስ አካል አባል’ መሆን’ን መቀበያ መንገድ ነው ብላ ታምናለች። የፕሮቴስታንት ቤተ እምነቶች እንደሚሉት እነዚህን  መቀበያው “እምነት” ብቻ ነው። በእምነት ብቻ መሆኑ ትክክል ከሆነ ታዲያ የጥምቀት አስፈላጊነቱ ምኑ ላይ ነው? የክርስትና ምልክት ብቻ መሆኑ ነውን? ወይስ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴ 28:19-20) የሚለውን የጌታን ትዕዛዝ መታዘዝ ብቻ መሆኑ ነው?

(2) ማነው ማጥመቅ ያለበት?

በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጥምቀት የሚከናወነው በካህን ብቻ ነው። ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ግን የሰውን ክህነት ጨርሶ አይቀበሉም። ስለሆነም በእነርሱ ቤተ ክርስቲያን የሚያጠምቀው ካህን ወይም ቄስ ያልሆነ አገልጋይ ነው።  ይህ አገልጋይ የቤተክርስቲያኒቷ ሽማግሌ ወይም ሴት ሽማግሌ (የሴቶችን ሽምግልና የሚቀበሉ ወገኖች ከሆኑ)  ሊሆን ይችላል። ለማንኛውም እንደ ፕሮቴስታንቶች እምነት ሽማግሌዎችም ሆኑ አገልጋዮች ካህናት አይደሉም።

(3) እኛ ጥምቀትን ከምስጢረ-ቤተ ክርስቲያን መካከል አንዱ ነው ብለን ስናምን ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ግን ነው ብለው አያምኑም።

(4) እኛ በውኃ ውስጥ በመንከር (በማጥለቅ) ስናጠምቅ አብዛኛዎቹ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ግን በመርጨት ያጠምቃሉ 

(5) በወላጆቻቸው እምነት መሠረት እኛ ሕጻናትን ስናጠምቅ ፕሮቲስታንት ወንድሞቻችን ግን በሕጻናት ጥምቀት አያምኑም።ተጠማቂው ለመጠመቅ ‘አስቀድሞ እምነት ሊኖረው ያስፈልገዋልን’ ቅድመ ሁኔታ አድርገው ያስቀምጣሉና።

(6) በፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ከሚቀርቡት ሙግቶች  ጥቂቶቹ

1.  እምነት ያለጥምቀት የሚበቃ አይደለምን?

2. የተጸጸተው ሌባ እንዴት ያለጥምቀት ድኅነትን አገኘ?

3. ውኃ ልደትንና መታደስን ሊሰጥ የሚችል ጠባይ አለውን?

4. አጥማቂው ለምን ካህን ይሆናል? ጥምቀትን የሚፈጽመው ካህን ክፋ አድራጊ ቢሆንስ ምን ይሆናል? 

5. ጥምቀት በሕይወት መታደስ ከሆነ ከጥምቀት በኋላ ለምን ኃጢአትን እንሠራለን?

6. አስቀድመው ከተጠመቁና ኃጢአታቸውም ይቅር ከተባሉ ወላጆች የሚወለድ ሕጻን እንዴት አድርጎ ነው ኃጢአትን የሚወርሰው?

7. የጥምቀት ‘ውኃ’ የቃሉ ምልክት ሆኖ የቆመ ነው? ሐዋርያው በቤተ ክርስቲያንና በክርስቶስ መካከል ስላለው ግንኙነት ሲናገር “በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ” (ኤፌ 5:26) ይላልና። 

የጥምቀት ፍቱንነቱ

1) ድኅነት በጥምቀት የተሟላ ይሆናል[1] 

ይህ የሚሆነው “ያመነ የተጠመቀም ይድናል” ብሎ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረው ቃል መሠረት ነው (ማር 16÷16) ። ጌታ “ያመነ ይድናል” ብሎ አላቆመም። ነገር ግን የጥምቀትን አስፈላጊነት ከእምነት አስፈላጊነት ጎን ለጎን አስቀምጧል። 

(2) በጥምቀት በኩል ከውኃና ከመንፈስ የሆነውን ዳግመኛ ልደትን እንቀበላለን

ሀ) ይህ የሚሆነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ በነገረው ቃል መሠረት ነው። “ኢየሱስም መልሶ። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው” (ዮሐ 3÷3)። ጌታ ይህን እንዲህ ሲል አብራርቶለታል። «ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም» (ዮሐ 3÷5)።ከዚያም አከለ፦  «--- ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው።--ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ----ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው» (ዮሐ 3÷6፣8)። ጌታ እንደዚህ ከውኃና ከመንፈስ የተወለደን ሁሉ ከላይ ወይም ከመንፈስ እንደተወለደ አድርጎ ይቆጥራል።

ጌታ “አንድ ሰው በውኃና በመንፈስ ካልተጠመቀ አላለም። እርሱ ያለው “አንድ ሰው ካልተወለደ!” ነው በማለት አንዳንድ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ምንባቡን ሊያለሳልሱት መሞከራቸው እንግዳ ነገር ይመስላል። በእርግጥ ሁለቱም ሐረጎች የሚገልጡት ያንኑ አንድ ነገር ለመሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም። ምክንያቱም ከ’ውኃ መወለድ’ ማለት በውኃ መጠመቅ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምን ማለት ሊሆን ይችላል? ከቃሉ  የሚወጣው ትርጉም ካልተጠመቀ የሚል ነውና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ይህንኑ ትርጉም ሲያፀና፦ 

ለ) “እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብ ---አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤” (ቲቶ 3÷5) ብሏል።ስለቤተ ክርስቲያን ሲናገርም እንዲህ ይላል፦ “---በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት--“(ኤፌ 5÷26) ። ሐዋርያው ‘የውኃ መታጠብ’ን (በጥምቀት) ‘የመታደስ መታጠብ’ እንዲሁም ‘ኃጢአትን ማጠብ’ አድርጎ ቆጥሮታል።

(3) ጥምቀት ኃጢአትን ያጥባል

ይህም ባለፉት ሁለት ጥቅሶች መሠረትና ‘ሐናንያ’ ለሳውል “አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ” (ሐዋ 22÷16) በማለት በተናገረው ቃል መሠረት ነው።  እዚህ ላይ የጥምቀት አንዱ ውጤት ‘ከኃጢአት መታጠብ’’ እንደሆነ እናያለን። በሳውል ጉዳይ እንደነቃለን። ለአሕዛብ ሐዋርያ ሊሆን፣ ስሙን ለመሸከምና ስለስሙም ብዙ መከራ ሊቀበል  በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ የተመረጠ ዕቃ ነበር (ሐዋ 9÷15፣ 16 )። ያም ሆኖ ኃጢአቱ ይቅር የተባለው ጌታ በመንገዱ ስላጋጠመው፣ ወይም በእምነቱ ወይም ሐዋርያ በመሆኑ አልነበረም። እንደዚህም ሁሉ ሆኖ ኃጢአቱን ለማጠብ ጥምቀት የግድ አስፈልጎታል። ምናልባትም ሐዋርያው ጳውሎስ ይህ በጥምቀት ከኃጢአቱ መታጠቡ ሁል ጊዜም ትዝ እያለው ሳይሆን አልቀረም ለቆሮንቶስ ሰዎች ”ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል” (1 ቆሮ 6÷11) በማለት የጻፈላቸው። ይህን ያለበት ምክንያትም ቅዱስ ጴጥሮስ ለአይሁድ እንደተናገረው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠምቀውና የኃጢአት ይቅርታን ተቀብለው ነበርና። 

(4) በጥምቀት የኃጢአት ይቅርታ (ይቅር መባል) ይገኛል

አይሁድ ባመኑበትና ልባቸው በተነካበት በበዓለ ኅምሳ ቀን ቅዱስ ጴጥሮስንና ሌሎች ሐዋርያትን  “ወንድሞች ሆይ፥ ምን እናድርግ? አሉአቸው”። ከዚያም ቅዱስ ጴጥሮስና ሐዋርያትም እንዲህ ብለው ለአይሁድ መለሱላቸው። “ንስሐ ግቡ፣ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ” (ሐዋ 2÷37፣ 38)

እምነታቸው ብቻ የኃጢአት ይቅርታን ሊያስገኝላቸው ቢበቃ ኖሮ ታላላቆቹ ሐዋርያት አይሁድን እንዲጠመቁ ባልነገሯቸውም ነበር። በተለይም በዚያች  ታሪካዊ ቀን፣ ቤተ ክርስቲያን በተቋቋመችበት በዚያች ቀን፣ ስለድኅነት አስፈላጊ መርሖች ሁሉ በተገለጡባት በዚያች ቀን፣ ይህን ባልነገሯቸውም ነበር። 

አንድ ሰው እንዲህ በማለት ሊጠይቅ ይችላል። እንዴት ነው በጥምቀት ኃጢአት ይቅር የሚባለው? እንደሚከተለው እንመልሳለን።

(5) ጥምቀት ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መሞትና ከእርሱ ጋር መነሳት ነው

መጽሐፍ ቅዱስ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና” (ሮሜ 6÷23) እንዲልድኅነት መንገድ የተጀመረው በሞት ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ሞተ። ሐዋርያው እንዳለው ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መሞት ወይም ቢያንስ በሞቱ እርሱን መምሰል ያስፈልጋል።“……እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ……” (ፊል 3÷10)።ይህ በጥምቀት ይደረስበታል። እንዴት?

ሐዋርያው እንዲህ ይላል፦“--ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? ……ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን” (ሮሜ 6÷3፣4)። ይህንኑ አባባሉን ለማስረገጥ እንዲህ ሲል ቀጥሎበታል። “…..ከእርሱ ጋር ሞትን ……ከእርሱ ጋር ተቀበርን….. ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ተባበርን……..አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር…. ተሰቀለ……“።  ይህንኑ ማለቱን በማጽናት ሐዋርያው ለቆላስይስ ሰዎችም እንዲህ ሲል ጻፈ። “…..በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀበራችሁ …….” (ቈላ 2÷12)።

ይህ ሁሉ ግን ለምን? ሐዋርያው እንዲህ ይላል፦“ነገር ግን ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንድንኖር እናምናለን” (ሮሜ 6÷7፣8) ።

ስለዚህ ጥምቀት ለድኅነት አስፈላጊ ነው ምክንያቱም ከክርስቶስ ጋር በሞቱ መካፈል ነውና። ሞትን ወደ ሕይወት መድረሻ መንገድ አድርጎ ማመንና የኃጢአት ደሞዝ ሞት መሆኑን መመስከር ነው። ወደ ሮሜ ሰዎች በተጻፈው መልእክት ምዕራፍ 6 ውስጥ ሁለት ዋና ነገሮችን እንገነዘባለን።

(ሀ) “በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ” የሚለው ሐረግ አካል በመቃብሩ ውስጥ  ሙሉ ለሙሉ ዝቅ እንደሚል ሁሉ በውኃ  መጥለቅን ያመለክታል። 

(ለ) የጥምቀት አንዱ ውጤት የ‘አሮጌው ሰዋችን’  መሰቀል ሆኖ ይታያል።

(6)  ሌላው የጥምቀት ውጤት ‘የሕይወት አዲስነት’ ነው

ሐዋርያው እንዲህ ይላል፦“እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን” (ሮሜ6÷4) ። አዲስ ሕይወት በጥምቀት በኩል የምንቀበለው ሕይወት ነው። ስለዚህ አሮጌው ሰዋችን በጥምቀት ይታደሳል። እንዴት? 

7) በጥምቀት ክርስቶስን እንለብሰዋለን

ሐዋርያው እንዲህ ይላል፦“ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና” (ገላ 3÷27) ። ጥምቀትን ታላቅ ውጤት አጉልቶ ሊያመለክት የሚችል ከዚህ የበለጠ ብርቱ ቃል ይገኛልን? 

ክርስቶስን እንለብሰዋለን። በእኛ ላይ በጥምቀት ያጎናጸፈንን የእርሱን ጽድቅ እንለብሰዋለን። በደሙ የተቀበልነውንም ድኅነት በጥምቀት እንለብሳለን። በጥንተ አብሶ (በአዳምና ሔዋን ውድቀት ወይም መተላለፍ) የጠፋብንንም የእግዚአብሔርን መልክ እንለብሳለን (ዘፍ 12÷6) ።  

(8) በጥምቀት የቤተ ክርስቲያን አባል እንሆናለን

ጥምቀት በብሉይ ኪዳን ግርዘት መወከሉ ጥርጥር የለውም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጌታ ኢየሱስ እንዲህ እንደሚል፦ “የሥጋንም ሰውነት በመገፈፍ፥ በክርስቶስ መገረዝ፥ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ። በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ።” (ቆላ 2÷ 11፣ 12)

በግርዘት የአካላችን ክፍል ተለይቶ እንደሚቆረጥና እንደሚሞት የታወቀ ነው። ይህ በጥምቀት የሚታየውን ፈጽሞ መሞትን ያመላክታል።

 

        ግዝረት ሊጠፋ የማይችል ምልክት ነው።እንደዚሁም ሁሉ ጥምቀት ሊሰረዝ አይችልም።

        በግርዘት ደም እንደሚፈስ ሁሉ በእኛ ምትክ የፈሰሰው ደም ያስገኘውን ትሩፋት ማለትም በጥምቀት የሆነውን አዲስ ሕይወት እንቀበላለን።

        የተገረዘ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆኖ እንደሚቆጠር ሁሉ (ዘፍ 17÷7) የተጠመቀም የእግዚአብሔር አካል የሆነችው የቤተ ክርስቲያን አባል ይሆናል።

        ያልተገረዘ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ማህበረሰብ እንደማይቆጠር (ዘፍ 17÷14) እንደዚሁ ከውኃና ከመንፈስ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም (ዮሐ 3÷3 ፣ 5) ። ምክንያቱም አልተጠመቀም፣ ከክርስቶስ ጋር አልተቀበረም፤ ከእርሱም ጋር አልተነሳም።

        ግርዘት በእግዚአብሔር እንደ ታዘዘና የግድ እንደሚያስፈልግ  ሁሉ ጥምቀትም ለኃጢአት ይቅር መባልና የክርስቶስ አካል ለመሆን የግድ ያስፈልጋል።

ሰው አንድ ጊዜ ብቻ እንደሚሞትና ከዚያም እንደሚነሳ እንደዚሁ የሚገረዘውም አንድ ጊዜ ብቻ ነው።ጥምቀትም እንደዚሁ የሚከናወነው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። የሚደገም ክንዋኔ አይደለም። ምክንያቱም የተጠመቀ ከክርስቶስ ጋር ከአንድ ጊዜ በላይ መሞት አይቻለውምና።

በግርዘት፣ በጥምቀትና በኃጢአት ይቅርታ መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ሐዋርያው በመንፈሳዊ ግዝረት ንግግሩ ውስጥ ገልጾታል፣ ጥምቀትን እንዲህ በማለት ፦ በክርስቶስ የተደረገ መገረዝና  በሰው እጅ ያልተደረገ ፣ አሮጌው ኃጢአተኛ ሰውነት የተገፈፈበት ግርዘት በማለት ሐዋርያው በመንፈሳዊ ግዝረት ንግግሩ ውስጥ ገልጾታል። ሐዋርያው የሚከተለውን ሲል ጥምቀትን ማመልከቱ ነው።“የሥጋንም ሰውነት በመገፈፍ፥ በክርስቶስ መገረዝ፥ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ። ---እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ” (ቆላ 21÷1፣ 13)። ጥምቀት ክየት መጣ እዚህ ላይ???

በብሉይ ኪዳን የነበሩት የጥምቀት ምስያዎች  የሚሰጡት ይህንኑ ትርጓሜ ነው

     

        የኖኅ መርከብ የጥምቀት ምስያ ነበር። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንደሚል“ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም። ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቅት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፥ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፥ ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፥ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው” (1ኛ ጴጥ 3÷20)። በውኃ ጥምቀት ድኅነት አለ ብለን እናስረዳለን። በተመሳሳይ ሁኔታ የጥምቀት ምስያ በሆነው በኖኅ መርከብ የገቡ ሁሉ ከጥፋት ውኃ ተርፈዋል። ይህ ከላይ የተናገርነውን በማር 16÷16 ያለውን የጌታን ቃል መሠረት አድርገን በጥምቀት በኩል ድኅነት እንደሚገኝ ያብራራነውን የሚያጸና ነው።

        ግርዘት ሌላ  የጥምቀት ምስያ ነው። ይህንን አስረድተናል።

        ሌላው የብሉይ ኪዳን የጥምቀት ምስያ ‘ቀይ ባሕርን መሻገር’ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው “ወንድሞች ሆይ፥ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፤ ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ” (1ኛ ቆሮ 10÷1፣ 2)። ቀይ ባሕርን ማቋረጣቸው ለእስራኤል ልጆች ከ’ፈርዖን’  ባርነት መዳናቸው እንደነበር ይታወቃል። እዚህ ላይ ቅዱስ ጳውሎስ ከኃጢአትና ከሞት ባርነት መዳንን በጥምቀት ከመቀበላችን ጋር ያጣቅሳል። ውኃ  በሁለቱም ማለት በኖኅ መርከብና ቀይ ባሕርን በማቋረጥ ምስያዎች በግልጽ ይታያል። በቀደመው በአባቶች ዘመን ልክ በመርከቡ ምስያነት ላይ ኖኅ ‘ካህን’ን እንደመሰለ እዚህ ላይ ሙሴም ካህንን ይመስላል (ስ ይጠብቃል)።

        በብሉይ ኪዳን ሌላም የጥምቀት ምሳሌ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ላይ ይገኛል። በዚያ ጌታ በኃጢአት ከወደቀች የሰው ነፍስ ጋር ስለምትመሳሰል ስለኃጢአተኛዋ ኢየሩሳሌም እንዲህ አለ፦ “በአንቺ ዘንድ ባለፍሁና ባየሁሽ ጊዜ፥ እነሆ፥ ጊዜሽ የፍቅር ጊዜ ነበረ፤ እኔም መጐናጸፊያዬን በላይሽ ዘረጋሁ ኀፍረተ ሥጋሽንም ከደንሁ፤ ማልሁልሽም ከአንቺም ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ አንቺም ለእኔ ሆንሽ። በውኃም አጠብሁሽ ከደምሽም አጠራሁሽ በዘይትም ቀባሁሽ” (ሕዝ 16÷8፣9)። ይህ ‘ውኃና’ ይህ ‘አጠብኩሽ’ የጥምቀት ምሳሌ ነው። ዘይቱ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ የመቀባት  ምሳሌ ነው÷÷ “አንቺም ለእኔ ሆንሽ” የሚለው ሐረግ ኢየሩሳሌም (የሰው ነፍስ) የክርስቶስ አካል (የቤተ ክርስቲያን) አባል  ሆነች ማለት ነው።


ስለዚህ በአዲስ ኪዳን ትምህርት መሠረት ብቻ ሳይሆን በብሉይ ኪዳን በምሳሌነት በተመለከቱትም ጭምር በጥምቀት ድኅነትና የኃጢአት ይቅርታ አለ። እነርሱም ግርዘት፣ የኖኅ መርከብና ቀይ ባህር ናቸው።

 

በጥምቀት የምናገኘው የኃጢአት ይቅርታ “ኃጢአትን ለማስተሰረይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” በሚለው የቤተ ክርስቲያን ዶግማ በግልጽ ተመልክቷል። 

ማጥመቅ የካህን ተግባር ነው

ጥምቀት መፈጸም ያለበት ሲመተ ክህነት በተቀበለ ካህን ነው ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያጠምቁ ያዘዘው ሕዝበ ክርስቲያኑን ሁሉ ሳይሆን ቅዱሳን ሐዋርያቱን እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያሳየናል። ከዕርገቱ በፊት እንዲህ አላቸው፦ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ----ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴ 281÷9) ። ይኸው “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንልጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ። ያመነ የተጠመቀም ይድናል፣ ያላመነ ግን ይፈረድበታል” ማር 16÷15፣ 16 በሚለውም ተረጋግጧል።  

የማጥመቁን ሥራ  ያከናወኑት ሐዋርያቱ እንደነበሩ በቀደሞዋ ቤተ ክርስቲያን ወንጌል እንዴት እንደተሰራጨ ከሚያስነብበን ከ“ሐዋርያት ሥራ” መጽሐፍ ግልጽ ሆኖ ይታያል። ከዚያም የማጥመቁን ሥራ ደቀ መዛሙርት ለነበሩቱ ለኤጲስ ቆጶሳቱ፣ እነርሱ ደግሞ በተራቸው ለቀሳውስቱ አስተላለፉ።

በነዚህ ምክንያቶች በካህን ያልተፈጸመ ጥምቀትን አንቀበልም። ካህኑም ቀኖናዊ ካህን ማለትም ‘ሐዋርያዊ’ና ‘ቀኖናዊ’ በሆነ ኤጲስ ቆጶስ እጅ በመጫን የቀሰሰ ሊሆን ይገበዋል። ከቤተ ክርስቲያን ያልተባረረ ወይም ያልተወገዘ ነገር ግን ምስጢራትን ለማደል ሥልጣነ ክህነት የተቀበለ መሆን አለበት።

“ለምንድነው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከፕሮቴስታንት ወገን ወደ ኦርቶዶክስ እምነት የተለወጡትን ደግማ የምታጠምቀው?” እየተባለ በተደጋጋሚ ለሚቀርብልን ጥያቄ ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች  መልሶቻችን ናቸው። 

በ’ፕሮቴስታንት ጥምቀታቸው ያልተቀበሏቸውን መንፈሳዊ ሐብቶች ሁሉ  እናጎናጽፋቸዋለን እንላለንም።ብዙ ጊዜም ጥያቄዎችን እንጠይቃቸዋለን፦ “በጥምቀታችሁ ድኅነትን አግኝታችኋልን? ጽድቅን፣ የሕይወት አዲስነትንና የኃጢአት ይቅርታን ተቀብላችኋልን? በጥምቀት ክርስቶስን ለብሳችሁታልን? አዲስ ሆናችሁ ተወልዳችኋልን?  በተለይ ከዚህ ቀደም ጥምቀት እነዚያን ሁሉ ጸጋ የያዘ እንደሆነ አልቆጠራችሁምና”

ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን የሰውን ክህነትም የቅዱሳት ምስጢራትን ትምህርት ቢሞግቱም የኦርቶዶክስ ያልሆነ ጥምቀትን ደግመን እናጠምቃለን። በቀኖናዊ ካህን አልተጠመቀምና።

ምንም እንኳ በቅድስት ሥላሴ ስም የተፈጸመ ቢሆንም ከፕሮቴስታንት የተመለሱትን ስናጠምቅ ይህንን ዳግመኛ ጥምቀት አድርገን አናስበውም። ምክንያቱም የእነርሱ ጥምቀት ሦስት ትልልቅ ጉዳዩችን አጓድሏልና።

(1ኛ) በካህን አልተፈጸመም

(2ኛ) እንደ ቅዱስ ምስጢር ተደርጎ አልተቆጠረም

(3ኛ)ምንም ዓይነት  መንፈሳዊ ፍቱንነት አዝሏል ተብሎ አልታሰበም

ቤተ ክርስቲያን ከተቋቋመችበት ጊዜ ጀምሮ የጥምቀት አስፈላጊነት

ክርስትና ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ጥምቀት ሃይማኖቱን (እምነቱን)  ከመቀበል የማይነጠል (የማይገነጠል) አካል ሆኖ ኖሯል።በተለይ በክርስቶስ በራሱ የታዘዘ የማያከራክር ትዕዛዝ  ነውና።

የእርሱ ቅዱስና ታላቅ የሆነው ትዕዛዙ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው----ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴ 281÷9-20) የሚል ነው። ደግሞም “ያመነ የተጠመቀም ይድናል” (ማርቆስ 16÷16) ብሎ አዟል። ጥምቀት ምልክት ብቻ ቢሆን ኖሮ ጌታ የዚያን ያህል የቀዳሚነት (የአስፈላጊነት) ሥፍራ ባልሰጠውም ነበር።

አተገባበሩን በተመለከተ አይሁድ በጴንጤ ቆስጤ ቀን ባመኑ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ወዲያውኑ እንዲጠመቁ ጥሪ አደረገላቸው። እንዲህም አላቸው፦ “ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤-” (ሐዋ2÷38)።  በዚያን ቀን 3000 አማኞች ተጠምቀዋል። ያለጥርጥር ያንን ያህል ሕዝብ ማጥመቅ ከባድ፣ አስቸጋሪና ረዥም ጊዜ የወሰደም ተግባር ነበር።ጥምቀት ለድኅነት  እጅግ አስፈላጊ ካልነበረ  በሺህ የተቆጠሩትን እነዚያን ሁሉ ሰዎች የማጥመቅ ጣጣ ለማስቀረት ሐዋርያቱ በተውት ነበር። ለሐዋርያቱ እንዲህ ቢሉ ይቀልላቸው ነበር፦ “አሁን እንግዲህ ስላመናችሁ ድኅነትን ተቀብላችኋል። ሂዱ፣ የጌታ በረከት ከእናንተ ጋር ይሁን”

እንዳመነ ወዲያው እንዲጠመቅ ራሱ በጠየቀው በኢትዮጵያዊው ጃንደረባም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው የምናገኘው ። ወዲያው ፊሊጶስ እንዳጠመቀው ደስ እያለው መንገዱን ቀጠለ (ሐዋ 8÷36-39) ።

የጠርሴሱ ሳውልም ካመነ በኋላ ከኃጢአቱ ለመታጠብ እንዲጠመቅ ተነገረው (ሐዋ 22÷16) ። ቀይ የሐር ነጋዴዋ ልድያ ከነቤተ ሰዎቿ እንዳመኑ ወዲያውኑ ነበር የተጠመቁት። “እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው?” (ሐዋ 10÷44፣ 47) ካለ በኋላ ቆርኔሌዎስም እንዳመነ ነበር ቃሉን ከሰሙት ከሌሎች ሁሉ ጋር ሐዋርያው ጴጥሮስ ያጠመቃቸው።  

ድኅነት በማመን ብቻ የሚገኝ ቢሆን ኖሮ እነዚያ ያመኑት ሁሉ ለምን  መጠመቅ አስፈለጋቸው? 

ጥምቀትን በመንከር (በማጥለቅ) እንፈጽማለን

(1) በመጥምቁ ዮሐንስ ጊዜ እንኳ ጥምቀት በመነከር እንጂ በመርጨት እንዳልነበረ ከመጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ሆኖ ይታያል።ጌታ ኢየሱስ ራሱ የተጠመቀው በመጥለቅ ነበር። ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ “ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ” (ማቴ3÷16) ፤ (ማር 1÷10) የሚለው። ይህንኑ ለማጽናት ቤተክርስቲያናችን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀበትን ቀን “የጥምቀት” ቀን ብላ ትጠራዋለች።

(2) ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ባጠመቀበት ጊዜም “ወዲያው ከውኃ ወጣ” ለሚለው አባባል ተመሳሳይ ትርጉምን ነው የተጠቀመው። ቅዱስ ወንጌል እንዲህ ይላል፦ “ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም። ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፥ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና” (ሐዋ 83÷8፣ 39) ። ይህ የሚያረጋግጠው ጥምቀት በመጥለቅ እንደነበር ነው። መርጨት ቢሆን ኖሮ ሁለቱም ወደ ውኃው መውረድ ሳያስፈልጋቸው ፊልጶስ ከሠረገላው ሳይወርድ በጃንደረባው ላይ መርጨት በበቃ ነበር። 

(3) ‘ባፕቲዝማ’ የሚለው ቃል ማቅለም ማለት ነው። ማቅለም ደግሞ ያለመንከር አይሆንም። 

(4) ጥምቀት ከክርስቶስ ጋር የመቀበርና ከእርሱ ጋር ሞትን የመቅመስ ድርጊት ነው። ሐዋርያውም “ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን” (ሮሜ 6÷4)  በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ” (ቆላ 2÷12) እንደሚለው ማለት ነው። የመቀበር ፤ ድርጊትን ያለ መነከር መፈጸም አይቻልም። ‘መውጣት’ ከሚለው ቃል የሚገኘው ሃሳብ የሚያመለክተው መጀመሪያ ከክርስቶስ ጋር ሞቶና ተቀብሮ ከእርሱ ጋር መነሳትን ነው።መርጨት ግን ሞቶ የመነሳትን ድርጊት አያሳይም።

(5) ጥምቀት ዳግም መወለድ ነው። መወለድ ማለት አንድ አካል ከሌላ አካል መውጣት ነው። ይህ የሚታየው በጥምቀት ጊዜ የተጠማቂው አካል ከውሃ ሲወጣ ነው። መርጨት የመወለድን ሁኔታ በጭራሽ አያሳይም።

(6) ለቅዱስ ጳውሎስ እንደተባለው ጥምቀት ከኃጢአት መታጠብ ነው (ሐዋ 221÷6) ። ቅዱስ ጳውሎስ ለቲቶ በጻፈው መልእክት እንዲህ አለ፦ “እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ” (ቲቶ 3÷5) ።መታጠብ ድርጊት በውኃ ውስጥ ጠልቆ መግባትን ይጠይቃል ፤ ይህ የሚገለጸው (የሚታየው) በመነከር እንጂ በመርጨት አይደለም። 

(7) የጥንት ቤተ ክርስቲያን ሕንጻዎችን ያየን እንደሆነ ሁሉ የማጥመቂያ ገንዳዎች እንደነበሯቸው እንገነዘባለን።ይህ ማጥመቅ ይደረግ የነበረው በመነከር እንጂ በመርጨት እንዳልነበረ ማረጋገጫ ነው። ምክንያቱም የመርጨት ድርጊት የጠለቀ ገንዳ አያስፈልገውም። 

የሕጻናት ጥምቀት

ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ከጥምቀት በፊት እምነት ሊኖር ያስፈልጋል በሚለው ትምህርታቸው ላይ ብርቱ አቋም ስላላቸው ሕጻናትን አያጠምቁም። ይህንንም የሚሉት ጌታ “ያመነ የተጠመቀም ይድናል” (ማር 16÷16) በሚለው ቃሉ መሠረትና ሕጻናት በጥምቀት የሚሆነውን መገንዘብ አለመቻላቸው ሐቅ በመሆኑ ነው። ስለዚህ “ሰው እንዴት ሳያምን በፊት ወይም ሳይገነዘብ በፊት ሊጠመቅ ይችላል?” ነው የሚሉት።

እኛ ግን በሚከተሉት ምክንያቶች  የሕጻናት ጥምቀትን አጠንክረን እንይዛለን።

(1) ስለሕጻናት የዘላለም ሕይወት ይገደናል። ምክንያቱም ጌታ “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” (ዮሐ 3÷5) ይላልና። ጌታ ከላይ በተጠቀሰው ቃሉ ሕጻናትን እስካላገለለ ድረስ እንዴት አድርገን ነው እኛ ሕጻናትን እንዳይጠመቁ በመከልከል ለእግዚአብሔር ፍርድ የምናጋልጣቸው? 

(2) በጥምቀት በኩል ትንንሽ ልጆች የቤተ ክርስቲያንን ሕይወት የመለማመድና መለኮታዊ ምስጢራትን ከፍቱንነታቸው ሁሉ (ከሚያስገኙት ጸጋዎቻቸው ሁሉ) ጋር የመቀበል ዕድል ይሰጣቸዋል።በቤተ ክርስቲያን ያሉትን የጸጋ መቀበያዎችን ሁሉ በሕይወታቸው ከሚያስከትሉት ውጤቶቻቸው ጋር ያገኟቸዋል። በዚህ ዓይነት መንገድ ሕጻናቱን በእምነት ላለው ሕይወት በተግባር እናዘጋጃቸዋለን። ከቤተ ክርስቲያን ባናካትታቸው ግን እምነትንና የጸጋ መቀበያዎቹን ሁሉ እናስቀርባቸዋለን።

(3 “ያመነ የተጠመቀም ይድናል” የሚለው የጌታ ቃል የእምነትን ትርጉም መገንዘብ ለሚችሉ አዋቂዎች የተባለ ነው። ለዚህም ነው በማርቆስ 16:16 በተጻፈው የጌታ ቃል መሠረት ካላመኑ በስተቀር አዋቂዎችን የማናጠምቀው። ሕጻናትን በተመለከተ ግን  የምንጠቅሰው ማቴዎስ 19÷14 “ሕፃናትን ተዉአቸው፥ ወደ እኔም ይመጡ ዘንድ አትከልክሉአቸው፤ መንግሥተ ሰማያት እንደነዚህ ላሉ ናትና” የሚለው የጌታ ቃል ነው።


(4) ከእምነት አንጻር ሲታይ ሕጻናት ሁሉን ነገር በሚያምኑበትና በሚቀበሉበት ዕድሜ ላይ ናቸው። እምነትን እምቢ አይሉም፤ አይገፈትሩትም። እንደ አዋቂዎች ወደ መጠራጠር ፣ መመራመር፣ መጠየቅና ማብላላት ላይ ገና አልደረሱም። እነርሱን ከመንግስተ ሰማያት ሊከለክላቸው የሚችል ምንም ነገር የለም። እነርሱን ማጥመቅ ”ነጻ ድኅነት” ከሚለው መርሕ ጋር ይስማማል። ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ደግሞ “ነጻ ድኅነት” የሚያምኑበትና አበክረው የሚያሰራጩት ትምህርት ነው።

(5) አስቀድሞ እምነት (ተረድቶ ማመን) መኖር አለበት የሚለውን እጅግ አጥብቀን የምንይዝ ከሆነ በአዕምሮ ዕውቀት ያልሰሉ  በመሆናቸው ምክንያት ስለ እምነት ያለውን መረጃና ጥልቀቱን ለመገንዘብ የሚሳናቸውን በርካታ አዋቂዎች ሳይቀር ከጥምቀት ልንከለክል ነው ማለት ነው። ለምሳሌ አራሾችን፣ የቀን ሙያተኞችን፣ ጨርሶ ያልተማሩን ፣ በብቃት ያልተማሩንና ጥልቅ ነገረ መለኮትን ለመረዳት ውስን ችሎታ ብቻ ያላቸውን ሌሎችንም ሁሉ ላናጠምቅ ነው ማለት ነው። መጠየቅ ቢፈቀድልን የእነዚህ ሰዎች እምነት ስፋቱና ጥልቀቱ የቱን ያህል ነው? ሕጻናትን እንከልክል እንደምንል እነዚህንም እንዳይጠመቁ እንከልክልን?           

(6) አንዳንዶች “ሕጻኑ ሲያድግ እምነትን እምቢ ቢል ምን ይሆናል?” ብለው ይጠይቃሉ 

በዚያን ጊዜ እምነትን የካደ ሆኖ ይቆጠራል። ማንም ሰው ቢሆን በጥምቀት የተቀበለውን ጸጋ በገዛ ፈቃዱ እምቢ ሊል ይችላል። በእኛ በኩል ልናደርግ የሚገባውን አድርገንለታል። ከዚያ በኋላ ጉዳዩ ለእርሱ የሚተው ይሆናል። እንዲህ ያለውም ሰው በመንፈስ ከጀመረ በኋላ በሥጋ ፍጹም ለመሆን የሚሞክርን ሰው ይመስላል ማለት ነው (ገላ3÷3) ።

ምናልባትም በሕጻንነታቸው ተጠምቀውና የጸጋ መቀበያዎችን እየቀመሱ በቤተክርቲያን ያደጉ ሳይጠመቁ እንዲያድጉ ከተተዉት ይልቅ  የተዛባውን መንገድ ባለመከተል የተሻሉ ይሆናሉ።

(7) የሕጻናትን ጥምቀት የሚክዱ በማርቆስ 161÷6 ጥምቀት ለድኅነት ያስፈልጋል የሚለውን ቃል በእርግጠኛው መካዳቸው ነው። ጥምቀትን ለድኅነት የሚያስፈልግ መሆኑን አምነውማ ከሆነ ትናንሽ ልጆችን እንዳይጠመቁ ማድርጋቸው ድኅነትን ከለከሏቸው ማለት ነው።ይህ ደግሞ አደገኛ ነገር ማድረግ ነው።

ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን እምነት ለድኅነት መሟላት ያለበት ቅድመ ሁኔታ ነው ስለሚሉና ሕጻናት ደግሞ እምነት የላቸውም ስለሚሉ በእነርሱ ሃሳብ ታዲያ ያላመኑም ያልተጠመቁም ልጆች ዕጣ ፈንታቸው ምን ሊሆን ነው? ያለ እምነትና  ያለጥምቀት ይድናሉን? ጥያቄው ሳይመለስ ሊቆይ ነው።

(8) እኛ ሕጻናትን እናጠምቃለን። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ይህንኑ ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስ መላ ቤተሰብን ወይም አንድ ሰው ከነመላ ቤተሰቡ መጠመቁን ይጠቅሳል። በነዚያ ቤተሰቦች ውስጥ ደግሞ ልጆች መኖራቸው ምንም አያጠራጥርም። የሚከተሉት ከበርካታዎቹ መካከል ጥቂቶቹ ምሳሌዎች ናቸው።

(ሀ) በፊልጵስዩስ የእስረኞች ጠባቂውን ጥምቀት

ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ሲላስ እንዲህ አሉት፦ “በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ” (ሐዋ 16÷31)። ይህ ማለት የእስረኛው እምነት ወደ ድኅነት የሚመራ የመጀመሪያው እርምጃ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ነው ከዚያ በኋላ እንደሚከተለው የተባለው ፤ “ለእርሱና በቤቱም ላሉት ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ተናገሩአቸው።በሌሊትም በዚያች ሰዓት ወስዶ ቍስላቸውን አጠበላቸው፥ ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ” (ሐዋ 16÷32፣ 33) ።  ይህ ማለት በእርግጥ ከልጆቹም ጋር ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በፊልጵስዩስ ከነበረው እስረኛ ጠባቂ ቤተሰብ መካከል ልጆችን አላገለላቸውም። “እርሱ ከቤተሰቡ ሁሉ ጋር” በማለቱ በእርግጥ ሕጻናትን ጨምሯቸዋል።

(ለ) ስለ ቀይ ሐር ነጋዴዋ ስለልድያ ጥምቀት

“እርስዋም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ከተጠመቀች በኋላ” (ሐዋ 16÷15) ተብሎ ተጽፏል።

(ሐ) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የእስጢፋኖስንም ቤተ ሰዎች ደግሞ አጥምቄአለሁ፤ ጨምሬ ሌላ አጥምቄ እንደ ሆነ አላውቅም” (1 ቆሮ 1÷16) ይላል ።ነዚህ ሁሉ ቤተሰዎች ልጅ ያልነበሯቸው ሊሆኑ ይችላሉን?

(መ) መጽሐፍ ቅዱስ በበዓለ ሃምሳ ቀን ከተጠመቁት መኻከል ልጆች እንዳልነበሩባቸው አይጠቅስም።

(9) የሕጻናት ጥምቀት ደግሞ ጥንት እንደተጀመረ በታሪክ ይታወቃል። ጥንቱንም የተለመደ እንደነበረ የሚያሳይን አንድ ታሪክ እዚህ ላይ እናነሳለንን። ቅዱስ አውገስጢኖስና ቅዱስ ‘የሮም’ (ጀሮም) ስለ ነፍስ መነሻ ተጠያይቀው ነበረ። መጠያየቁም “ነፍስ ተወለደች ወይስ ተፈጠረች?”  የሚል  ነበር። ቅዱስ አውገስጢኖስ “ከሰው ጋር አብራ ተወልዳለች” ሲል ቅዱስ የሮም ደግሞ “ተፈጥራለች” ብሏል።“ከተፈጠረችማ የአዳምን ኃጢአት አልወረሰችም ማለት ነዋ፤ እንዲያ ከሆነማ ታዲያ ሕጻናትን ማጥመቅ ለምን አስፈለገ?” ብሎ አውገስጢኖስ ጠየቀ። ቅዱስ የሮም ለዚህ ጥያቄ መልስ ሊሰጥ አልቻለም።

(10) ልጆች እንዳይጠመቁ የሚከለክል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድም ጥቅስ የለም።      

(11) እምነትን በተመለከተ ልጆችን የምናጠምቀው በወላጆቻቸው እምነት ነው። በወላጆች ምክንያት ለልጆች ስለሚደርስ ነገር ብዙ ምሳሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን።

(ሀ) የብሉይ ኪዳን ግርዘት ቀደም ብለን እንዳስረዳነው የጥምቀት ምሳሌ ነው። ከዘፍጥረት እንደምናነበው በእግዚአብሔርና በአብርሃም መካከል በነበረው ቃል ኪዳን መሠረት የተገረዙ ሁሉ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ይቆጠሩ ነበር (ዘፍ 171÷1) ።እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ግርዘት የሚደረገው አንድ ሕጻን በተወለደ በስምንተኛ ቀን እንደነበር ይታወቃል (ዘፍ 17÷12) ። የስምንት ቀን ሕጻን በእግዚአብሔርና በአብርሃም መካከል ስላለው ቃል-ኪዳን ምን ዓይነት ዕውቀት ኖሮት ይሆን? የቱንስ ያህል ስለእግዚአብሔር ሕዝብ አባልነት ያውቅ ኖሯል? እንደዚህ ዓይነት ነገር እንደማያውቅ ምንም አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ የሚገረዘው ወላጆቹ ስለ ቃል ኪዳኑ ከነበራቸው እምነት የተነሳ ነበር። በዚህ ቃል ኪዳን መሠረት የእግዚአብሔር ሕዝብ አባል ይሆን ነበር። አዎ! እግዚአብሔር ለአባታችን ለአብርሃም የቸረውን ተስፋ ሁሉ ለመውረስ ባለመብት ይሆን ነበር። ሕጻኑ እነዚህን ሁሉ ያገኝ የነበረው  በወላጆቹ እምነት ነበር።

(ለ) የቀይ ባህርን መሻገራቸው (ማቋረጣቸው) የጥምቀት ምሳሌ ነው ወይም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች እንደገለጠው ራሱን  ‘ጥምቀት’ን ነው(1 ቆሮ 10÷2 )። ከሞት፣ ከሰይጣንና ከኃጢአት ባርነት መዳንን ያመለክታል። እግዚአብሔር ለነቢዩ ሙሴ የገባውን ቃል የሚያውቁቱ አዋቂዎች  ቀይ ባህርን አቋረጡ። እነርሱ የፈርዖን ባሪያዎች እንደነበሩ አውቀዋል።  በጸናች የእግዚአብሔር እጅ  ከባርነት ድኅነት የማግኘት ትርጉሙን እነርሱ ተገንዝበዋል። ቀይ ባህርን በተሻገሩ ጊዜ (ጥምቀት) እነርሱ ድነዋል።  በእናቶቻቸውና በአባቶቻቸው ታዝለው ቀይ ባህርን የተሻገሩቱ ትንንሽ ልጆች ስለዚህ  ጉዳይ ምን ሃሳብ ያስቡ ነበር? በእርግጥ ከባርነት ነጻ መውጣትን ተቀብለዋል። ከራሳቸው እምነት የተነሳ ሳይሆን ከወላጆቻቸው እምነት  የተነሳ ተጠምቀዋል። በራሳቸው እምነት እንዳይባል እነዚያ ልጆች ስለሆነው ነገር ሁሉ የሚያውቁት አልነበረም።

(ሐ)ሌላውና ጠንካራው ምሳሌ የበኩር ወንድ ልጅን ሁሉ ከገደለው መልአክ በፋሲካው በግ ደም የታናናሽ ብላቴናዎች መትረፍ (መዳን) ነው። የበኩር ወንድ ልጅ ሁሉ በመልአኩ ሲገደል ደሙ ምልክት ሆኖላቸው የነበሩቱ ተረፉ። ምንም ጉድለት የሌለባቸውን የአንድ ዓመት ወንድ ፍየልን ወይም በግን እንዲያርድና ደሙን በየጉበኑና በየመቃኑበ ላይ እንዲያደርገው ጌታችን ሙሴን አዘዘው። እናም “ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልበፋለሁ” (ዘጸ 121÷3) አለው።

የፋሲካው በግ ደም ድኅነትን ያገኘንበት የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ደም ምሳሌ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው “ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና” (1 ቆሮ 5÷7) ።

ታዲያ አሁን ጥያቄው በፋሲካው በግ ደም የዳኑት የትናንሾቹ ልጆች እምነት ምን ነበረ? በእግዚአብሔርና በሙሴ መካከል ስለነበረው ቃል ኪዳን ወይም  ስለፋሲካና በፋሲካ በግ ደም ስለ መዳን ምን ያውቁ ነበረ? ያለ ጥርጥር የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ነገር ግን በወላጆቻቸው እምነት ዳኑ። አዎ!  በደሙ፣ ደሙ በሚሠራው ሥራና የፋሲካው በግ ከሞት ለመዳን በነበረው ጠቀሜታ ባመኑ ወላጆቻቸው ዳኑ። 

በግርዘት፣ በፋሲካው በግ ደምና ቀይ ባሕርን በመሻገር የዳኑት እነዚህ ትናንሽ ልጆች የነዚህን ሁሉ ትርጉም ካደጉ በኋላ አወቁ። ይሁን እንጂ እግዚአብሔርን በተስፋውና ከሰው ጋር በገባው ቃል ኪዳን  ባመኑት ወላጆቻቸው  እምነት የተነሳ ድኅነትን  ገና በልጅነታቸው በነጻ ተቀበሉ። ልጆቹ ባደጉ ጊዜ ወደዚሁ እምነት በተግባር ገብተዋል። 

ተቃውሞዎችና ምላሾቻቸው

ጥያቄ 1፡ ጥምቀት የሕይወት መታደስ ከሆነ ከተጠመቅን በኋላ ለምን ኃጢአት እናደርጋለን?

በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሠረት ጥምቀት የሕይወት መታደስ ነው (ሮሜ 6÷4) ። ነገር ግን ፍጹምነትን አያቀዳጀንም (አያጎናጽፈንም)። አዲስ ልደትን፣ አዲስ ሕይወትንና አዲስ ጸጋን በጥምቀት እንቀበላለን። አዲስ ተፈጥሮንም እንወስዳለን። ሐዋርያው እንዳለ፦“እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ” (ቲቶ 3÷5) ። ይህ ተፈጥሮ መንፈሳዊ ሕይወትን ለመኖር አቅምና ችሎታ አለው። ይሁን እንጂ በሥጋ እስካለን ድረስ የማንሳሳትና ፍጹም አይደለንም። በዚህ ዓለም እንፈተናለን።ክፉን ወይም ደጉን ለማድረግ ነጻነታችንን እንደያዝን ነን። በጥምቀት የተቀበልነው የመታደስ ጸጋ፣ የእኛ የሆነውንና እግዚአብሔርን መስለን የተፈጠርንበትን የነጻነት ጸጋችንን (ነጻ ፈቃዳችንን) አይገፈውም። ለዚህ ነው ጻድቅ ሰው በቀን ሰባት ጊዜ ወድቆ እንደገናም የሚነሳው። ነገር ግን በሚመጣው ሕይወት ፍጹምነትንና የጽድቅ አክሊልን እንቀበላለን። አስተማሪያችን ሐዋርያው ጳውሎስ ሰዓቱ በደረሰ ጊዜ በደስታ ተሞልቶ (በተፍለቀለቀ ስሜት) “ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል” (2 ጢሞ 4÷8) አለ።

ጥያቄ 2፡ አጥማቂው ካህን ክፉ አድራጊ ቢሆንስ ጥምቀቱ ፍቱንነቱን ይዞ ይኖራል?

በጥምቀት የምንቀበለው ጸጋ ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከካህኑ አይደለም። ካህኑ የቸሩ የእግዚአብሔር አገልጋይ ብቻ ነው። ጸጋዎቹ ሁሉ በእግዚአብሔር እውነተኛ ተስፋ የተመሠረቱ እንጂ በካህኑ ጠባይ/ አካሄድ ላይ አይደለም።

ካህኑ ደስታ የተሞላ ደብዳቤን እንደሚያደርስላችሁ መልዕክተኛ (ፖስተኛ)  የሚታይ ነው፤ መልከ ቀና ሆነ ወይም መልከ ጥፉ መሆኑ ደብዳቤው የሚያደርሰውን ደስታ አይቀይረውም።

ካህኑን ፍሬን እንዲያፈራ አትክልትን በጓሮ ከሚተክል አትክልተኛ ጋር ማስያተያየት ይቻላል። ኃጢአተኛ ሆነ መልካም ሰው ልዩነት አያመጣም። ወሳኙ ነገር ዘሮቹና በውስጣቸው ያለው ሕይወታቸው ነው እንጂ ዘሩን የዘራው  የአትክልተኛው እጅ አይደለም።

ውኃን በወርቅ ወይም በመዳብ ዕቃ ትጠጡት ይሆናል። በየትኛውም መጠጫ ብትጠጡት ውኃው ግን ያው ውኃ  ነው።

ስለጥምቀትና ስለ ፍቱንነቱ ስንወያይ ዶግማውን (ትምህርቱን) ከአጥማቂው ጋር ሳናያይዝ ነው።  ስለ አጥማቂው ካለ የግል ስሜት ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን አንነካም። ይህን ማድረግ በሌሎች ላይ ወደ መፍረድና  እንደ ወንጌሉ እውነተኛ ቃል ጌታ በጥምቀት በሰዎች ላይ ያትረፈረፈውን ጸጋ ወደ መጣል ያመራል።

ጥያቄ 3፡ የተጸጸተው ሌባ ያለጥምቀት እንዴት ነበር የዳነው? 

ይህን ጥያቄ ስንመልስ ያ ሌባ ምርጥ የሆነውን ጥምቀት ተቀብሏልና እኛም ሁላችን የእርሱን ምሳሌ ተከትለን ተጠምቀን ቢሆን የምንመኘው ነበር በማለት ነው። ጥምቀት ምንድነው? አስተማሪያችን ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ከክርስቶስ ጋር መሞት አይደለምን (ሮሜ 6)? የተጸጸተው ሌባ በእርግጥ ከክርስቶስ ጋር ሞቷል። ሞቱ ጥምቀት ሆኗል። በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው፣ በውኃ ጥምቀት የሚገኘውን ጸጋ ከመቀበላቸው በፊት፣ በመከራ ለተገደሉ ለሰማዕታቱ መለያ የሆነው በ‘ደም መጠመቅ’ም ተመሳሳይ ነው። ሞታቸው ጥምቀት ይሆናል፣ ምክንያቱም ልክ እንደ ሌባው ከክርስቶስ ጋር ሞተዋልና(‘ድኅነት’ በሚለው መጽሐፋችን  ስለዚህ አብራርተናል)።

ጥያቄ 4፡ ጥምቀት አስፈላጊ ከሆነ፣ በፈልጵስዩስ ከተማ  ሐዋርያቱ  ጳውሎስና ሲላስ   ለእስረኛ ጠባቂው ለምን  በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ” አሉት፤ ለምን “እመን ተጠመቅም” አላሉትም? ይህ ለድኅነት እምነት ብቻ በቂ መሆኑን ማረጋገጫ አይደለምን?

ለዚህ መልሱ ሁለቱ ሐዋርያት የተናገሩት ገና ላላመነ ሰው ስለነበር ነው። ምንም ቢያደርግ ያለ እምነት ሊድን አይችልም። ስለዚህ ይድን ዘንድ መጀመሪያ እንዲያምን መምራት ነበረባቸው። እምነትን ተቀብሎ ቢሆን ኖሮ ከዚያ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ደግሞ ያስረዱት ነበር። ለዚህ ነው ይህን ቃል ከተናገሩ በኋላ የሚከተሉት ሁለት ነገሮች የሆኑት።

ሀ) ለእርሱና በቤቱም ላሉት ሁሉ የጌታን ቃል ተናገሩአቸው”(ሐዋ 16÷32)

ለ) ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ” (ሐዋ 16÷33)

ስለዚህ በፊታችን አንድ ጥቅስን አኑረን ከተመሳሳይ ጉዳይ ጋር የተያያዙትን ሌሎች ጥቅሶች መዘንጋት የለብንም። ስለ ፊልጵስዩሱ እስረኛ ጠባቂ እምነት  ስናወራ አብረን ስለ እስረኛ ጠባቂው ጥምቀትም ማውራት ይኖርብናል። “እመን----- ትድናለህ” ከሚሉት ከሁለቱ የሐዋርያቱ ቃላት ጋር በፊት ለፊታችን “ያመነ የተጠመቀም ይድናል” (ማር 16÷16) የሚለውን የጌታን የራሱን ቃላት መናገር አለብን።ያም ብቻ አይደለም ድኅነት በጥምቀት በኩል ከመሆኑ ጋር የተያያዙትን 1ጴጥ 3÷21ና ቲቶ 3÷5  የመሳሰሉትን ጥቅሶች ሁሉ ማንሳት ይገባል።

ጥያቄ 5፡ ጥምቀት ይህን ያህል ጠቃሚ ከሆነ ነቢያት በብሉይ ኪዳን ተጠምቀው ኖሯልን?

በነቢያቱ ጊዜ ጥምቀትን የሚያዘው ትዕዛዝ ኖሮ  ቢሆን ይጠመቁ ነበር።   ነገር ግን ጥምቀት የታዘዘው በክርስትና ነው ። ለምን?  ቢባል ጥምቀት ማለት ከክርስቶስ ጋር መሞት ነውና ፤ ክርስቶስም በብሉይ ኪዳን ጊዜ አልሞተምና። በብሉይ ኪዳን  ጊዜ ነቢያት በጊዜያቸው  ሊያደርጉ የሚችሉትን አድርገዋል፤ ማለትም የጥምቀት ምልክት የሆኑትን ግርዘትንና ቀይ ባህርን አቋርጦ መሻገርን ፈጽመዋል። የክርስቶስም ደም ምሳሌ የሆነውን ፋሲካን አድርገዋል። በጊዜያቸው ያልተሰጠውን ትዕዛዝ እንዲታዘዙ አንጠብቅባቸውም። ጥምቀት የእነርሱን ዘመን ተከትሎ በኋላ የመጣ ነው።

ጥያቄ 6 ድኅነት በውኃ በኩል ሳይሆን በቃሉ በኩል ነውን?

ሐዋርያው ስለቤተ ክርስቲያን “በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት----”(ኤፌ 5÷26) ያለው ‘መንጻት’ በቃሉ በኩል ማለትም ድኅነት በ’ቃሉ’ በኩል ማለት ነውን? ቃሉ ለድኅነት ማስፈለጉን የሚያመለክቱት የሚከተሉትን የመሳሰሉት ሌሎች ጥቅሶችስ? “--ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ--” (1 ጴጥ 1÷23)ና “ለፍጥረቱ የበኵራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን” (ያዕ 1÷18) የሚሉትስ? በ“ጥምቀት ዳግም ተወልደናል”፣ ወይም “በጥምቀት አዳነን” የማይሉት እነዚህ ሁሉስ? 

ታዲያ ለድኅነት የውኃ አስፈላጊነት ምኑ ላይ ነው ? ጌታ “ያመነ የተጠመቀም ይድናል” (ማር 16÷16) ስላለ ድኅነት የሚገኘው በዚሁ መንገድ ነው። ነገር ግን ‘ያመነ’‘ የሚለውን ሐረግ ትምህርትና ስብከት ሊቀድመው ያስገፈልገዋል።ምክንያቱም ሐዋርያው ይላል፦ “--- ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?” (ሮሜ 10÷14)።  የ‘ቃሉ’  አስፈላጊነት ከዚህ ይመነጫል።

ውጤቱ እምነት የሆነው ‘ቃል’ መጀመሪያ ይደርሳል።ከእምነት በኋላ ደግሞ ውጤቱ ድኅነትና የሕይወት መታደስ የሆነው ጥምቀት ይፈጸማል።ምንም እንኳ ድኅነትና የሕይወት መታደስን መቀበል በጥምቀት ቢሆንም አስቀድሞ ቃል መድረስ አለበት። ምክንያቱም ቃሉ ወደ እምነት ይመራናል፤ እምነትም ወደ ጥምቀት ይመራናል። ለዚህ ነው ሐዋርያው እንዲህ ያለ፦ “በእውነት ቃል አስቦ ወለደን” እንዲሁም “ዳግመኛ የተወለዳችሁት---- በእግዚአብሔር ቃል----”  ወደነዚህ ሁሉ ያደረሰው መነሻው ቃሉ መሆኑን በማሰብ ነው  ይህን መናገሩ።

ስለቤተ ክርስቲያን “በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት…“(ኤፌ 5÷26) የሚለው የሐዋርያው ቃል መንጻት በቃሉ በኩል በጥምቀት (በውኃ መታጠብ) ይፈጸማል፤ ያም ማለት በስብከትና በቃሉ አገልግሎት በኩል እምነት ይሆንና ከዚያም ጥምቀት ይመጣል ማለት ነው።

እዚህ ላይ ልብ እንላለን፤ ሐዋርያው “በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንጂ” “በውኃ መታጠብ ያም በቃሉ ነው” አይልም። በውኃ መታጠብ ማለት ቃሉ (በቃሉ መታጠብ) ቢሆን ኖሮ ድግግሞሽ ባላስፈለገውም ነበር። ነገር ግን  “በውኃ መታጠብ ከቃሉ ጋር” ማለት የቃሉ ውጤት የሚያስከትለው በውኃ መታጠብ ማለት ነው። ሰዎች ያለ ቃሉና ያለቃሉ ሥራ በውኃ ወደ መታጠብ ማለትም ወደ ጥምቀት ባልደረሱም ነበር።

“ዳግመኛ የተወለዳችሁት---- በእግዚአብሔር ቃል” (1 ጴጥ 1:23)   “በእውነት ቃል አስቦ ወለደን።” (ያዕ 1:18) በሚሉት ጥቅሶች ውስጥ ‘እምነት’ አለመጠቀሱን ልብ እንላለን። ቃሉ ያለ እምነት ለአዲስ ልደት በቂ ነውን? ይህ በጭራሽ ሊሆን አይችልም። በዚህ ጥቅስ ውስጥ ‘እምነት’ የሚለው ቃል ባይጠቀስም ውስጠ ታዋቂነቱ ግልጽ ነው።

ምን ለማለት እንደተፈለገ እየታወቀ ሁል ጊዜ ቃልን መደጋገም አያሻም። በእያንዳንዱ አጋጣሚ ሁሉ ቃሉ-እምነት-ጥምቀት-ዳግም ልደት የሚሉትን ቃላት መደጋገም አያስፈልገንም።

ስብከት የራሱ ተፈላጊነት አለው፤ የቃሉን አገልግሎት አስፈላጊነት ማንም አይክድም። ይሁን እንጂ ሰዎች «በእውነት ቃል ወለደን» በሚለው ቢያምኑም ባያምኑም ዳግም ይወለዳሉ ማለት አይደለም። ይኸው አባባል ለጥምቀትም ይሠራል።

«በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ» የሚለው ቃል ሁለት ነገሮችን በውስጠ ታዋቂነት ይገልጻል። ቃሉንና ጥምቀትን ፤ እምነት የሚለው በዚህም አልተገለጠም። በውስጠ ታዋቂነት የተባለ ነውና።

ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ሁል ጊዜ በእምነት ላይ ያተኩራሉ። እምነት የሚለው ቃል (ኤፌሶን 5÷26)፤(ያዕቆብ 1÷18) እና (1 ጴጥ 1÷23) ውስጥ ባለመኖሩ እምነት አይጠቅምም ወይም አያስፈልግም ማለት ነውን? ፈጽሞ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ የአንድ ቃል አለመኖር ቃሉን የማያስፈልግ አያደርገውም ለማለት ነው። ነገር ግን ያ ትርጉም በውስጠ ታዋቂነት የተገለጠ ነው። ይህ ሃሳብ ‘ጥምቀት’ ለሚለውም ቃል ያገለግላል።  

ጥያቄ 7÷ በድኅነትና በዳግም ልደት ውስጥ ውኃ ምን ሥፍራ አለው።

(ሀ) ምንም እንኳ “ዳግመኛ የተወለዳችሁት---- በእግዚአብሔር ቃል---- እንጂ” ና “በእውነት ቃል --- ወለደን”(ያዕ 1÷18) በሚሉት ጥቅሶች ውስጥ ‘ውኃ’ የሚለው ቃል ባይጠቀስም “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” (ዮሐ 3÷5) በሚለው በጌታ ቃል ውስጥ ግን ‘ውኃ  በግልጽ ተጠቅሷል። ከዚህ ጥቅስ ዳግም ልደት ከውኃ እንደሆነ ግልጽ ነው።  ውኃ’ የሚለው በእውነተኛው ውኃ ማለት እንጂ ምሳሌያዊ አይደለም። 

ለ) ቆርኔሌዎስና አሕዛብ ተከታዮቹ እምነትን በተቀበሉና ቤተ ክርስቲያንን በተቀላቀሉ ጊዜ ይህ መሆኑ ግልጽ ሆኖ የሚታይ ነው። እዚህ ሥፍራ ጻድቅ ሰዎች በእግዚአብሔር ወደ እምነቱ ተጠሩ፤ መልአክ ለቆርኔሌዎስ ታየው፤ ጴጥሮስ ደግሞ የመለኮት ትዕዛዝ የሆነውን ራዕይ አየ። ከዚያ ቅዱስ ጴጥሮስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰበከላቸው።የእግዚአብሔር መንፈስም ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ ወረደና (ሐዋ 11÷1) በልሳን ተናገሩ ። 

ለዳግም ልደታቸው ያ ብቻ ይበቃ ነበርን? ቅዱስ ጴጥሮስ “ይህ የሁላችሁ ዳግም ልደት ብሩክ ነው” ሊላቸው ይችል ነበርን? ነገሩ እንደዚህ እንዳልነበረ ቅዱስ ጴጥሮስ  የመንፈስ ቅዱስን መውረድ ከተመለከተ በኋላ፦ “እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው?” አለ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው” (ሐዋ 10÷47፣48) ባለው ግልጽ ሆኗል።

የሐዋርያት ሥራ  ጸሐፊ ወዲያውኑ እንዲህ ያለ ቃል ተናገረ። “አሕዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰሙ” (ሐዋ 11÷1) ።  በዚህ ሥፍራ ላይ የጥምቀት አስፈላጊነት ከቃሉ አስፈላጊነት ጋር አብሮ ነው የሄደው። በኤፌ 5÷26 ያለው ‘ውኃ’ የሚለው አንዳንዶች እንደሚተረጉሙት ‘ቃል’ ማለት አይደለም።

ሐ) ሌላ ግልጽ ምሳሌ የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ጥምቀት ነው። ባመነ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም፦ እነሆ ውኃ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው? አለው።ፊልጶስም፦ በፍጹም ልብህ ብታምን፥ ተፈቅዶአል አለው። መልሶም፦ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ አለ። ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም” (ሐዋ 8÷36-38) ።

ልክ የቆርኔሌዎስና የተከታዮቹ እንደነበረው ይህም ጥምቀት በውኃ ነበር። የውኃ ጥምቀት ከቃሉ ስብከት በኋላ ወዲያውኑ ያስፈልግ ነበር። በዚህ ሥፍራ ውኃ ማለት ቃል ማለት አይደለም። ጃንደረባው ከቃሉ ተወልዶና በቃሉ ታጥቦ ቢሆን ኖሮ ውኃ ለምን ያስፈልግ ኖሯል?

ይህን በተመለከተ ስለ አንድ ዋና  ርዕሰ ጉዳይ ልናገር  እወዳለሁ።

ያም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ውኃ ስላለው አስፈላጊነትና ተምሳሌቶቹ  ነው

በምስጢረ ጥምቀት ለመታጠብና ለመታደስ ለምን ውኃ እንደተመረጠ ለመረዳት ገና ከመጀመሪያው፣ ከፍጥረት ታሪክ አንስቶ በውኃና በሕይወት መካከል ግንኙነት እንደነበረ ማስታወስ ይገባናል።

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል÷“የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።” (ዘፍ 1÷2) እግዚአብሔርም አለ፦ “ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ፥ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ ጠፈር በታች ይብረሩ” (ዘፍ 1÷20) ። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሕይወት ከውኃ ወጣ። እንግዲህ በውኃ፣ በሕይወትና በእግዚአብሔር መንፈስ መካከል ያለውን ግንኙነት ማየት አይሳነንም።

ሕዝቡን በገሰጸበት ጊዜ እግዚአብሔር ራሱን ከውኃ ጋር ሲያመሳስል በብሉይ ኪዳን ደግሞ እናነባለን። “ሕዝቤ ሁለቱን ክፉ ነገሮች አድርገዋልና፤ እኔን የሕያውን ውኃ ምንጭ ትተውኛል፥የተቀደዱትንም ጉድጓዶች፥ ውኃውን ይይዙ ዘንድ የማይችሉትን ጉድጓዶች፥ ለራሳቸው ቆፍረዋል።” (ኤር 21÷3) ይኸው መዛመድ በጌታ ኢየሱስ ቃልም ተጠቅሷል። “በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ። ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና” (ዮሐ 7÷38፣ 39) ።

እነዚህ ቃላት ከዚያች ከሰማርያዊቱ ሴት ጋር ስለ ሕያው ውኃ በነበረው ጭውውት ጌታ እርሱ የሕይወትን ውኃ የሚሰጥ እንደሆነ በተናገረ ጊዜ ስለ ራሱ ከተናገራቸው ቃላት ጋር ይመሳሰላሉ። እንዲህ አለ÷ “እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት” (ዮሐ 4÷10-14) ።

ስለዚህ ውኃ የሕይወት አንዳንድ ጊዜም የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው። በመዝሙረ ዳዊት አንድ በክፉዎች መንገድ ስለማይሄድ ሰው በመለኮታዊ እስትንፋስ የተነገረው ቃል እንዴት ያማረ ነው። “እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” (መዝ1÷3) ይላል ። ሬውም የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው።

በውኃ ፣ በሕይወትና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ያለው ግንኙነት ከዘፍ 1÷2 ጀምሮ እስከ ዮሐንስ ራዕይ ይዘልቃል። “ለተጠማ ከሕይወት ውኃ ምንጭ እንዲያው እኔ እሰጣለሁ”(ራዕ 21÷6)። “በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውኃ ወንዝ አሳየኝ” (ራዕ 2÷21) ። “የተጠማም ይምጣ፥ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ” (ራዕ 22÷17)  

ቀይ ባሕርን በማቋረጥ ጊዜ ውኃው ሕይወትንና ሞትን በአንድ ላይ ወክሏል።  በ’ባርነት’ ለሚኖር ሰው  የ’ሞት’፣ ከውኃው ለወጣው ‘ነጻ’ ሰው ደግሞ የሕይወት ምሳሌ ነበረ።

የጸሎተ ሐሙስ ውኃው የመንጻት ምሳሌ (ምልክት) ነው። ስለዚህ ነው የሐዋርያቱን እግር ካጠበ በኋላ ጌታ “እናንተም ንጹሐን ናችሁ” (ዮሐ 13÷10) ያላቸው። መዝሙረኛው ደግሞ “እጆቼን በንጽሕና አጥባለሁ” (መዝ 26÷6) አለ። ይህ መንጻት በቃሉ የአዲስ ልደት መታጠብ ነው፤ (ማለትም) በአዲስ ልደት መታጠብ በኩል የምንቀበለውና በጥምቀት የተገኘ መንጻት ነው። “ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን” (ዕብ 10÷22) በሚሉት የሐዋርያው ቃሎች እንደተጠቀሰው ይኸው መንጻት በጥምቀት የተገኘው ነው።  

ውኃና ደም 

በመስቀሉ ላይ እንዳለ ከወታደሮቹ አንዱ የ’ጌታ ኢየሱስ’ ጎኑን በጦር ሲወጋው፣ “ወዲያውም ደምና ውኃ ወጣ” (ዮሐ 19÷34) ። በዚህ ያለው መለኮታዊ ጥበብ ምንድነው?

የመቤዠትን ትርጉም ሊሰጠን ከጎኑ ደም ወጣ። ነገር ግን ይህንን  መቤዠት የምንቀበለው እንዴት ነው?

በጥምቀት ውኃ በኩል እንቀበለዋለን። ስለዚህ ከጎኑ የሁለቱ ማለትም የውኃና ደም መውጣቱ የመቤዠታችንን መንገድ አሳይቶናል። ከእያንዳንዱ ኃጢአት የሚያነጻንን የክርስቶስን ደም በውኃው በኩል እንቀበላለን። በቅዱስ ቁርባን ውኃን ከደም ጋር መቀየጣችን[2]ንዴት መልካም ነገር ነው!

የደሙንና የውኃውን መውጣት በዓይኑ ያየው ተወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስ ይህንኑ እንዲህ በማለት ግልጽ ያደርገዋል።“የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና፤ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ” (1ኛ ዮሐ 5÷8)። ይህ ጥቅስ የምንቀበለውን መቤዠት ያስረዳል።                                    

መቤዠት በደሙ (በክርስቶስ ደም) ተሰጠን። የደሙን ትሩፋት (ደሙ ያስገኘውን በረከት) ከውኃና ከመንፈስ በመወለድ እንቀበላለን። ስለዚህ እነዚህ ሦስቱ ማለትም  ደም፣ ውኃ፣ መንፈስ በጥምቀት አንድ ላይ ይሆናሉ።

ጥያቄ 8፡ ውኃ እነዚህ ሁሉ ውጤታማ ሥራዎች አሉትን?

(ሀ) ይህ ጥያቄ የሶርያዊውን ‘ንዕማን’ ቁጣ ያስታውሰኛል። ሶርያዊው ንዕማን በዮርዳኖስ ወንዝ ገብቶ እንዲታጠብ ኤልሳዕ በነገረው ጊዜ ተቆጣ። ነገሩ በውኃ ውስጥ ገብቶ የመታጠብ ያህል ቀላል መሆኑን ማመን አልቻለም፣ በተለይም ከእስራኤል ይልቅ በደማስቆስ የተሻሉ ወንዞች እያሉ (2ኛ ነገ 5÷10-12) ። ነገር ግን በታዘዘና በታጠበ ጊዜ በእምነቱ ነጻ። 

ነቢዩ ‘ንዕማን’ን በዮርዳኖስ ወንዝ እንዲታጠብ አዘዘው። ዮርዳኖስ ወንዝ መጥምቁ ዮሐንስ በኋላ ዘመን ላይ ያጠመቀበት ወንዝ ነው (ማቴ 3÷6) ። “ውኃ ይህን ያህል ፍቱንነት አለውን” ብለን በመጠየቅ እኛም እንደ ‘ንዕማን’ እንሁንን?   እግዚአብሔር እርሱ ራሱ በፈቀደው መንገድ ጸጋን ይሰጣል። ጸጋው በዮርዳኖስ ወንዝ ባለው ውኃ በራሱ ሳይሆን ነገር ግን እግዚአብሔር በሰጠው የማንጻት ኃይል ነው።  በኋላ ላይ እንደምናብራራው ስለጥምቀት  የተባለውም ይኸው ነው።

(ለ) ጌታችን ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ሲፈውሰው፤ ጭቃ ባይኑ ላይ አደረገና “ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ አለው፤ ትርጓሜው የተላከ ነው። ስለዚህ ሄዶ ታጠበ እያየም ተመለሰ” (ዮሐ 9÷6፣ 7) ። በእምነቱ ብቻ ዓይኑ ሊበራ በቻለ። ይሁን እንጂ በውኃ በኩል እግዚአብሔር አብርሆትን ሊሰጠው (ሊገልጽለት) ፈለገ (ጥምቀት መንፈሳዊ አብርሆት ነው) ። የእግዚአብሔር ፈቃዱ እንደወደደው ይፈጸም። እግዚአብሔር ይፈጽመው ዘንድ ዕቅድን እኛ አንነድፍለትም። ስሙ ይባረክ።

(ሐ) በተጨማሪም ለዚህ ጥያቄ መልስ ስንሰጥ እንዲህ  እንላለን። የመጠመቂያው ውኃ ተራ ውኃ ብቻ አይደለም። የተጠመቀውም የሚወለደው ከውኃ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ከውኃና ከመንፈስ ነው። መንፈስ ቅዱስ የመጠመቂያውን ውኃ  በመቀደስ የጠለቀበት ሁሉ ከውኃና ከመንፈስ እንዲወለድ የሚያደርግ ልዩ ተፈጥሮን ይሰጠዋል። የሚጠመቀው ሰው በእንደዚህ ዓይነት የሚበዠውን የክርስቶስ ደም ትሩፋት (ዋጋ) ይቀበላል። በውኃ ውስጥ ሲጠልቅ ከክርስቶስ ጋር ይቀበራል፤ በትንሣኤውም ኅብረት የመካፈል ትሩፋት ያገኝ ዘንድ በሞቱ ኅብረት  ይካፈላል። ለዚህ ነው የመጠመቂያውን ውኃ ለመቀደስ፣ የመንፈስ ቅዱስ ቅባት፣  ‘ቅባ ቅዱስ’ የምናፈስበት።እንደዚህ ውኃው በመንፈስ ቅዱስ ይቀደሳል። ከዚህ ውኃ የተወለደ ሁሉ በውኃና በመንፈስ ተወልዷል።

የመጠመቂያውን ውኃ ለመቀደስ ካህኑ ውኃውን የሚቀድሰውንና መንፈስ ቅዱስን የሚለምንበትን ‘ሊጦን’[3] የሚያሰማው ለዚህ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስም  የተወሰነ ክፍል ያነባል። የሚያነጻንም የመጠመቂያው ውኃ   በዚህ መንገድ በቃሉም ይቀደሳል።

ጥያቄ 9፡ ጥምቀት ከክርስቶስ ጋር መነሳት ነው ፤ ከክርስቶስ ጋር መሞት አይደለም ብንል አይሻልም? ምክንያቱም ሞት ጎጂ እንጂ የሚጠቅም አይደለምና፤ መነሳት ግን የሚጠቅም ነውና

ሐዋርያው ወደ ሮሜ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ እንዳስረዳው ጥምቀት ከክርስቶስ ጋር መሞትና ከእርሱ ጋር መነሳት ነው። “ እንዲህም ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን” (ሮሜ 6÷5) ። “--- ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንድንኖር እናምናለን” (ሮሜ 6÷8) ይላል።  እዚህ ላይ ሞት ጥቅም የለውም፤ ትንሣኤ ግን ይጠቅማል በማለት ማንም በራሱ ሃሳብ አይደገፍ። ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረውንም ትምህርት አይሳት። ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ይላል÷-“ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን” (ሮሜ 6÷3፣ 4) ። ሐዋርያው ለቆላስይስ ሰዎች በጻፈው ይኸንኑ ይደግመዋል። “-----በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ” (ቆላ 2÷2)። ከነዚህ ጥቅሶች ጥምቀት ሞትም ትንሳኤም መሆኑን እናያለን። በእውነትም ከክርስቶስ ጋር መሞትን የሚጠየፉ የትንሳኤውን በረከት ሊቀበሉ አይችሉም።

እዚህ ላይ እንጠይቃለን። ለምንድነው በጥምቀት ሞት ያለው? አስፈላጊነቱስ ምንድነው?

(ሀ)  ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት ለማድረግ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ትንሳኤው ኃይል ብቻ እገባለሁ አላለም። ነገር ግን እንዲህ አለ፦ “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ” (ገላ 2÷20)። “እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ” (ፊል 3÷10፣11)። ከክርስቶስ ጋር መሞት የሚለው ሐረግ ተደጋግሞ በሮሜ መልእክት ምዕራፍ 6 ተጠቅሷል።

(ለ) አዲሱን ተፈጥሮ ይቀበል ዘንድ የሰው የተበላሸው አሮጌው ማንነት (እኛነት) በጥምቀት መሞት አለበት። ሐዋርያው በቃሉ የሚያስረዳው ይህንኑ ‘አሮጌውን ሰው በጥምቀት መስቀል’ን ነው። በሮሜ መልእክቱ  በዚሁ ምዕራፍ እንዲህ ይላል፦“ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና።ነገር ግን ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንድንኖር እናምናለን” (ሮሜ 6÷6፣ 7)። የሞት ጥቅሙ ይኸው ነው። አንዳንዶች እንደሚያስቡት ሞት ጎጂ አይደለም። እንደ እግዚአብሔር አምሳል በሆነው በአዲስ ተፈጥሮ እንድንነሣ ለእኛና ለአሮጌው ማንነታችን የሚሻለው መሞት ነው። የተበላሸው ተፈጥሮአችን ከክርስቶስ ጋር የመነሳት አቅም የለውም። በሕይወት ለመኖር አሮጌው ሰዋችን ይሞት ዘንድ ያስፈልጋል። 

(ሐ) ከሞቱ ጋር መተባበራችን በውስጠ ታዋቂነት በሞት ቅጣት ሥር የነበርን መሆኑን መመስከራችንን ይናገራል፤“በበደላችን ሙታን ነበርን”። ክርስቶስ ስለ እኛ ሞተ፤ ተቀበረም። ለዚህ ነው በሞቱ የምንጠመቀው። የኃጢአታችን ደሞዝ ሞት እስከሆነ ድረስ ከእርሱ ጋር በጥምቀት እንቀበራለን። በዚህ መንገድ ከክርስቶስ ጋር ከሙታን በመነሳት ያለውን በረከት እንቀበላለን።

(መ) ትንሳኤ ማለት ከሙታን መነሳት እንደሆነ በጣም ግልጽ ነው። ማንም በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር ለመነሳት አስቀድሞ ከእርሱ ጋር መሞት አለበት። ካልሞተ ታዲያ እንዴት ይነሳል?

ጥያቄ 10፡ከተጠመቁና ከአዳም ኃጢአት ከዳኑ ወላጆች የተወለደ ሰው ለምን እርሱም መጠመቅ ይኖርበታል?

እነርሱ በተጠመቁ እኛ ለመዳን እንዳንችል የሞት ቅጣትን የወረስነው ከወላጆቻችን አይደለም።ነገር ግን የመጀሪያው የሰው ዘር ከሆኑት ከአዳምና ከሔዋን በቀጥታ ነው የወረስነው። በአዳም ወገብ (አብራክ) ነበርን። የአዳም ተፈጥሮው ኃጢአትን ባደረገ ጊዜና እንዲሞት በተፈረደበት ጊዜ  ከአብራኩ የወጡ ሁሉ ሟቾች ሆኑ። ከአዳም አብራክ ስንከፈል በሞት ቅጣት ሥር ሆነን ነው የተከፈልነው። ስለዚህ የሞት ፍርዱ (ብያኔው) በአዳም ላይ እንዲሁም   በሁሉም  ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ተላለፈ፣ በቃየል፣ በአቤልና በሴት ብቻ አይደለም። ይህን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ” (ሮሜ 5÷12) ይላል። “ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና” (1ቆሮ 15÷22)።  ስለዚህ የአዳም ልጅ በመሆን ሞት በሰው ልጅ ሁሉ ላይ የተላለፈ ፍርድ ነበር። ማንም የተወለደ ሰው ሁሉ የሞት ፍርድ ተፈርዶበታል፣ ምክንያቱም አዳም በተፈረደበት ጊዜ በአዳም አብራክ (ወገብ) ነበረና።

ወላጆች የተቀበሉት ሆነም አልሆነም ከሞት ድኅነት ጉዳይ በነፍስ ወከፍ የሚቀበሉት ነው።ይህ ድኅነት ንስሐ መግባትን፣ በጥምቀትና በክርስቶስ ደም ማመንን እንዲሁም በሁሉም ጸጋ መቀበያዎች ማመንን ይጠይቃል። ያለኃጢአት የሆኑ ወላጆች የሉም። መዝሙረኛው እንዳለ “እነሆ፥ በዓመፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ።” (መዝ 51÷5) ።

ከጥፋት (ከመበላሸት) ባርነት ነጻ እስካልተደረግን ድረስ በኃጢአት የተወለድን ነን (ሮሜ 8÷21) ። መቼ ነው ከዚህ መበላሸት ነጻ የምንሆነው? ሐዋርያው ስለ አካላችን እንዲህ ይላል፦ “የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው። በመበስበስ ይዘራል፥ባለመበስበስ ይነሣል…. ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና” (1 ቆሮ 15÷42፣ 53) ። ይህ መቼ ይሆናል? የመለከቱ ድምጽ ሲሰማና ሙታን ሁሉ ሲነሱ።



[1] Completed’ የሚለው ቃል ‘ፍጻሜ ያገኛል’  ‘ይጠናቀቃል’ ‘ይደመደማል’ ማለት ሊሆን ቢችልም መዳናችን በጥምቀት ‘የተሟላ ይሆናል’ የሚለውን የዲያቆን አሐዱ አስረስ አባባል ተጠቅሜአለሁ። የመናፍቃን ማንነትና መልሶቻቸው÷ በዲያቆን አሐዱ አስረስ ገጽ 39 ይመልከቱ

[2]http://www.copticchurch.net/topics/liturgy/liturgy_of_st_basil.pdf

 ገጽ 18 Wine በሚለው ሥር የተገኘ፦

የቅዱስ ቁርባኑ ወይን የሚዘጋጀው ፍሬው ንጹህ፣ ቀለሙም ቀይ ከሆነና ሽታውን ካልቀየረ የወይን ፍሬ ተጨምቆ ነው። በመስቀል ላይ ከርስቶስ በጦር የተወጋ ጊዜ ደምና ውኃ ድብልቅ ከጎኑ እንደ ወጣው እንዲሆን ወይኑ ከውኃ ጋር ይደባለቃል።

http://www.ethiopianorthodox.org/english/calendar.html

በዲዮስቆሮስ፣ በኢጲፋንዮስ ፣ ዮሐንስ አፈወርቅ ባስልዮስ የቁርባን ምሥጋና ውስጥ ከአንድ ሦስተኛ ከማይበልጥ ውኃና ወይን ስለመቀላቀል ተገልጿል። “14ቱ ቅዳሴያት በግዕዝና አማርኛ”

[3]ሊጦን በቤተክርስቲያን ቄሶች በየዕለቱ ተራ አስገብተው የሚያዜሙትና የሚደግሙት የምስጋና ጸሎት ነው። ILS

 

Comments

Popular posts from this blog

Comparative Theology የነገረ መለኮት ንጽጽር (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት)/ በብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሲኖዳ ሳልሳዊ

 የነገረ መለኮት ንጽጽር  (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት): የወደደ  ሁሉ በነጻ እንዲጠቀምበት ተፖስቷል። ይሁን እንጂ መብቱ በሕግ የተጠበቀ ስለሆነ በየትኛውም መልኩ ለንግድ እንዲውል አልተፈቀድም። ልዩ ልዩ መግቢያ የሚለውን መጀመሪያ ካነበቡ በኋላ የተቀረውን በተመረጠው ቅደም ተከተል ማንበብ ይቻላል። ልዩ ልዩ መግቢያ   ጥምቀት   ትውፊት (ወግና ልማድ)   መካከለኝነት   ጾም የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ መንፈሳዊ ስጦታዎችና በልሳኖች የመናገር ስጦታ   ሥርዐት ንስሐ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ (1)  ድንግል ማርያምን ስለማክበር (2) ለጥያቄዎች መልስ (ሀ) ድንግሊትን ‘የወይን ግንድ (ተክል)’ና የ ‘ሕይወት በር’ የሚል ማዕረግ  ለምን እንሰጣታለን? (ለ) ወደ ድንግል ማርያም መጸለይ ትክክል ነው ወይ? (3) የድንግል ማርያም ድንግልና ዘላለማዊነት (4) ለተቃራኒ አስተያየቶች መልስ (ሀ) “የመጀመሪያ ልጇን” የሚለው ሐረግ (ለ) “ሚስትህ” የሚለው ሐረግ (ሐ) “አብረው ከመሆናቸው በፊት ጸንሳ ተገኘች” (መ) “የመጀመሪያ ልጇን እስክትወልድ አላወቃትም” (ሠ)  “ወንድሞቹ” የሚለው ሐረግ   የቅድስት ድንግል ማርያም  ክብሯ (1) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ድንግል እመቤታችንን አያከብሩም፤ ደግሞም እንድታማልድላቸውም (እንድትማልድላቸውም)  አይጠይቋትም።ከእነርሱ ወገኖች አንዳንዶቹ እንዲያውም ጫጩቱ ከተፈለፈለ በኋላ ዋጋ ከሌለው የዶሮ እንቁላል ቅርፊት ጋር እስከሚያመሳስሏት ይደርሳሉ።ይህ የተጋነነ ማቃለል የመጣው ምናልባት ሮሜዋውያን ካቶሊኮች የተጋነነ ማክበር ስለሚያከብሯት ለዛ ተቃርኖ ከማሳየት አዝማሚያ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን አንዱንም የእርሷን በዓል አያከብሩም።  (2) አንዳንዶቹ የፕሮቴስታንት ወገኖች ድንግል ማርያምን “እህታችን” ይሏታል። (3) በተጨማሪ አንዳንዶቹ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ጌታ ኢየሱስን በድንግልና ከወለደች በኋላ ከዮሴፍ ጋር ጋብቻዋን ፈጽማለች፤ የ‘ኢየሱስ ወንድሞች’  ወይም የ’ጌታ ወንድሞች’ ተብለው የተጠሩ ልጆችን ወልዳለች ይላሉ።  (4) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ቤተክርስቲያናችን ለድንግል እመቤታችን የሰጠቻቸውን አንዳንድ የማዕረግ ስሞችም ይቃወማሉ።  (5) ድንግልን ያለማክበራቸው አንዱ...

ስለ "አስታዋሽ ጾምና በዐሉ" ጥያቄና መልስ

 ስለ "አስታዋሽ ጾምና በዐሉ" ጥያቄና መልስ  ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ፦ ሕልውናችንን-ነጻነትችንን የማረጋገጥና የማስቀጠል አንድነታችንን የመጠበቅና የማጠንከር  በእሴቶቻችን የመደሰት፣ እነርሱን የመንከባከብና የማስተዋወቅ  በረከታችንን የማብዛትና የማካፈል  ኃላፊነቶቻችንን በማኅበር ፣ በማስተዋልና በትጋት እንድንወጣ “ጾሙና በዐሉ" አስታዋሽ ባሕላዊ ምልክታችን ይሁንልን   ጥያቄ 1 ፡ አድማጭ ተመልካቾቻችን እንኳን ደህና መጣችሁ።የከበረ ሰላምታችን ይድረሳችሁ። ዛሬ የምንወያየው ከአቶ ባንቱ ገብረማርያም ጋር ይሆናል። አቶ ባንቱ በሙያው ፋርማሲት ነው። እንደነገረኝ በእምነቱ ደግሞ ባፕቲስት ነው።ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ባሕላዊ ምልክት የሚሆን “ጾምና በዐልን” በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል። የምንወያየውም ስለዚሁ "ጾሙና በዐሉ" ምልክትነት ይሆናል።  አቶ ባንቱ ለመወያየት  ወደ እኛ በመምጣትህ አመሰግንሃለሁ። እንኳን ደህና መጣህ። አንተ እያልኩ ልቀጥል ወይስ አንቱ? መልስ 1፡ ዎገኔ፡   እንኳን ደህና ቆየኸኝ። ለአድማጭ ተመልካቾቻችሁም ሰላምታዬ ይድረስልኝ። አንተ በለኝ። የሚያውቀኝ ሁሉ አንተ ነው የሚለኝ።  ጥያቄ 2 ፡ እሺ  አንተ እያልኩ እቀጥላለሁ። አቶ ባንቱ፣ ምናልባትም ብዙ ሰው ስለማያውቅህ  እስቲ ስለራስህ በአጭሩ ንገረን። ወዲያውም መክፈቻ ይሆነናል መልስ 2 ዎገኔ ፦ አስቀድሜ ይኸን ዕድል ስለሰጠኸኝ ላመሰግንህ እወዳለሁ። አድማጭ ተመልካቾችህንም ጊዜ ወስደው  ውይይቱን  ስለሚከታተሉ ላመሰግናቸው እወዳለሁ።አዎን፣ ባንቱ ገብረማርያም እባላለሁ።እንደነገሩኝ የተወለድኩት ሽርካ በዛሬ አጠራሩ በአርሲ ዞን ነው።ነፍስ ያወቅሁትና ትምህርት ...