የነገረ መለኮት ንጽጽር
(ኦርቶዶክስ ከ ፕሮቴስታንት)
ተርጓሚ፤ ባንቱ ገብረማርያም አማረ
፳፻፲ ዓ.ም
(2017/2018)
ርእስ፤ የነገረ መለኮት ንጽጽር (ኦርቶዶክስ ከ ፕሮቴስታንት)
ጸሐፊው፤ ብፁዕ
ወቅዱስ ፖፕ ሲኖዳ ፫ኛ
በአማርኛ ተርጓሚ፤ ባንቱ ገብረማርያም አማረ
፳፻፲ ዓ.ም
መብቱ በሕግ የተጠበቀ ነው፣ ያለተርጓሚው ወይም ያለ አሳታሚው ፈቃድ አባዝቶ ማሳተምም ሆነ
ከሥራው የተወሰነውን ክፍል ማራባት በጥብቅ የተከለከለ ነው።
ሽፋን ሥዕል፣ አምቤክስና ሊቀ ባንቱ
ISBN: 978-0-692-94344-1
በEmail:
bamare98@gmail.com አስተያየት ለሚልኩልኝ ምስጋናዬ የላቀ ነው።
Comparative
Theology (Orthodox Vs Protestant)
Author:
H.H. Pope Shenouda III
Translator:
Bantu Gebremariam Amare
All rights reserved. No part of this book may be reproduced in any form without the translator or publisher
Design÷
Ambex and Like Bantu
ISBN: 978-0-692-94344-1
Printed
in United States of America
Our
Daily Bread Ministries
Any
Suggestions sent via Email bamare98@gmail.com
is appreciated
ቅዱስነታቸው ብፁዕ አቡነ ሲኖዳ
ሣልሳዊ÷ አጭር የሕይወት ታሪካቸው ጽሑፍ እንደሚያመለክተው
ቅዱስነታቸው በግብጽ አገር በ1923 ተወልደው በ2012 ከአጸደ ሥጋ ተለይተዋል። ለ40 ዓመታት ያህል 117 ኛው የእስክንድርያ
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን
ፓትረያርክና መንበረ ቅዱስ ማርቆስ ነበሩ። “ታዋቂ እና ስመጥር የሃይማኖት መሪ፣የነገረ መለኮት ሊቅ፣ተሰጥዎ የነበራቸው ሰባኪ፣ ጎበዝ ጸሐፊ፣ ተወዳጅ መንፈሳዊ አባትና የእግዚአብሔር ሰው” እንደ ነበሩም ይኽው ጽሑፍ ይመሰክራል። በአገልግሎት ዘመናቸው ለግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መታደስና ማደግ እንዲሁም ለዓለም አብያተ ክርስቲያናት “አንድ እምነት” ተግተው ሠርተዋል። http://www.copticchurch.net/topics/pope/index.html#Biograp |
የነገረ
መለኮት
ንጽጽር
(ኦርቶዶክስ
ከ ፕሮቴስታንት)
ተጻፈ
በ
ብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሲኖዳ ፫ኛ
በእንግሊዝኛ ተተረጎመ
በ
ሜሪና አማኒ ባሲሊ
በአማርኛ ተተረጎመ
በ
ባንቱ ገብረማርያም አማረ
የመጀመሪያው እትም
፳፻፲ ዓ.ም
Acknowledgements
My earnest prayer is that this project glorifies God who has kept me, sustained me and gracefully surrounded me with needed support during the years of translating. And truly, there were many that blessed me with their contribution directly and indirectly though I can’t list them all by name in this acknowledgment. I would like to thank His Grace Bishop Youssef, Bishop of the Coptic Orthodox Diocese of the Southern USA and His Grace Bishop Karas, General Bishop & Patriarchal Exarch of the Archdiocese of North America who bestowed their blessings on me for the translation of the book. I am also very grateful to Reverends Father Markos Ayoub of the Coptic Orthodox Church of St Mark, Jersey City, NJ and Father Andrew Khalil of the Coptic Orthodox Diocese of Southern United States, and Dr. Sammy Sadaka of the University of Arkansas for their respective support in making this translation comes to fruition.
My gratitude goes to my friend Damtew Tesfaye who read the first draft and whose feedback was encouraging and insightful in those first days of review. My special appreciation goes to Pastor Adera Mestetu of the Spring of Life Church in Memphis USA who later did thorough edits of my translation. His contribution to its completion can’t be understated. I would also like to thank Dr Sewalem Mebrate who reviewed the more challenging sections of the book in the last days of the project’s completion.
My
family was instrumental to my success. My good wife Yeshi Andenow was very
supportive of my efforts, and that level of work would not have been possible
without her. I thank my sons Ambex and his wife Emnet Aklilu, as well as Like
and Tiku for patiently assisting me in all things computer related. I also
want to thank my nephew Simeneh Betreyohannes for introducing me to helpful
translating resources. Lastly I would like to thank experienced translators
Menelik Fikreselassie and Getahun Haile for their feedback in the final stages
prior to wider circulation.
ለአማርኛው ትርጕም
መቅድም
የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ “ኦርቶዶክስ መልስ ካላት እኛም ጥያቄ አለን” የሚል ሲዲ በጌታ ወንድሜና ወዳጄ የሆነ አንድ ሰው አውሶኝ ካደመጥሁት በኋላ የመገረም ጥያቄ ጠይቄ ነበር። ጥያቄውም "ብፅዕት ማርያም እንደማታማልድና ጌታ ኢየሱስን በድንግልና ከወለደች በኋላ ሌሎች ልጆችን እንደወለደች ምን ግልጽ ያልሆነ ነገር ኖሮ ነው ይህ ሁሉ የተማረ ሰው ታማልዳለች፤ ለዘላለም ድንግል ነች እያለ በሃይማኖቱ የሚጓዘው?" የሚል ነበር። ብዙም ሳልቆይ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያን ስለ ብፅዕት ማርያም የሚያስተምሩትን በማገናዘብ ለዚህ ጥያቄ የራሴን መልስ ማግኘት አለብኝ በማለት ትምህርቶቹን እፈልግ ገባሁ። በዚህ ፍለጋዬ ወቅት ነው የኮፕቲክ ኦርቶዶክስንና የፕሮቴስታንቶችን ትምህርት የሚያነጻጽረውን በብጹዕ ወቅዱስ ፖፕ ሲኖዳ ሣልሣዊ የተጻፈውን “Comparative Theology" የተሰኘውን መጽሐፍ ያገኘሁትና ያነበብሁት።
አንብቤው እንደጨረስሁም ጠቃሚ ሆኖ የታየኝን ይህንን መጽሐፍ አብዛኛው የኢትዮጵያ ወገኔ በሚረዳው ቋንቋ እንዲገኝ የማድረግ ሸክም ተሰማኝ። በተለይም መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ መሠረት የማድረጉ አካሄድ በቸልታ እንዳላልፈው ግድ አለኝ። ስለዚህም በጋለ ስሜት ልተረጉመው ጀመርሁ
በመተርጎም ላይ እንዳለሁ ግን ከወንጌላውያን ወገን የምቆጠር
ባፕቲስት ሆኜ ሳለ ጊዜዬን ለምን የኦርቶዶክስ ቤተ
ክርስቲያን
በምታስተምረው
ላይ አጠፋለሁ? እግዚአብሔር የሰጠኝን ጊዜ የወንጌላውያን ቤተ እምነቶች በሚያስተምሩት ላይ
ባውለው አይሻልም ወይ?” የሚል
የኅሊና
ሙግት ገጥሞኝ ተቸገርሁ። ለመተርጎም የከበዱኝ ክፍሎች ሲገጥሙኝና መተርጎሙ ጊዜ እየወሰደብኝ ሲሄድ ጨርሶውኑ እመተው ደረጃም ደርሼ
ነበር። ይሁን
እንጂ
“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶና የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ክርስቲያኖች ውይይት በሚያደርጉበት ጊዜ ያገለግላቸዋልና መበርታቱ ይሻላል” የሚል ሃሳብ
ስላመዘነብኝ ተበራትቼ ወደ
ፍጻሜ አምጥቼዋለሁ። ለንባብም አብቅቼዋለሁ። ክብሩ ሁሉ ይህን ሃሳብ በውስጤ በማሳደር ሥራውን
ለፍጻሜ እንዳደርሰው ለረዳኝ ለእግዚአብሔር አምላክ ይሁን።
ቅዱስነታቸው በኮፕቲክ ኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንቶች
መሐል ያሉትን የእምነት
ልዩነቶች ሲያስረዱ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገው ከመሆኑም
በላይ በተብራራና በቅጡ በተደራጀ መልኩ ነው።ፕሮቴስታንቶችንም “በፍቅር
ድባብ” ለሆነ ውይይት
ጋብዘዋል። እንደ እኔ አስተያየት ከሆነ አማርኛ አንብበው የሚረዱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችም ሆኑ የወንጌላውያን ክርስቲያኖች “የነገረ መለኮት ንጽጽር” ትርጕምን ቢያነቡት
ጠቃሚ ትምህርት ያገኙበታል እላለሁ። አንብበው በመጽሐፉ መነሻነት ለመወያየት የሚፈልጉም በብጹዕነታቸው መንገድ ፤ ማለትም በ”ፍቅር ድባብ”’ እንዲወያዩ በትህትና ሃሳቤን አካፍላለሁ።
ትርጕሙ ቀጥተኛ ትርጉም ሲሆን አማርኛውን የተስማማና የተዋደደ ለማድረግ ሞክሬአለሁ። የቤተ ክርስቲያኗን ዶግማና ቀኖና ላለማዛባትም የተቻለውን ሁሉ ጥንቃቄ አድርጌአለሁ። የተዛባ ሃሳብ ከኅትመት በኋላ ቢገኝ በሚቀጥለው እትም አስተካክላለሁ።
የመጽሐፍ
ቅዱስ ጥቅሶች የተወሰዱት በኢየሩሳሌም ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ከተዘጋጀው “የ1954 ትርጉሙ ኤሌክትሮኒክስ መጽሐፍ ቅዱስ” ነው። The Haile Selassie Amharic Bible - Bible.org በሚል ማስፈንጠሪያ ይገኛል።
ባንቱ ገብረማርያም አማረ
ስተትጋርት፣ አርካንሳ ፳፻፲ ዓ.ም
ማውጫ
▪
መቅድም 2
▪
መግቢያ 4
ክፍል 1
▪
ጥምቀት 10
▪
ትውፊት
(ወግና ልማድ) 35
▪
ምልጃ 48
▪
ጾም 62
ክፍል 2
▪
የድንግል
ማርያም ክብርና ስለ ዘላለማዊ ድንግልናዋ 71
▪
የመንፈስ
ቅዱስ ስጦታዎችና በልሳን የመናገር ስጦታ 91
▪
ሥርዓቶች 101
▪
ንስሐ 125
የጥንቱ የክርስቲያን አንድነት እንዲመለስ ለማድረግ የዓለም አቀፍ አብያተ ክርስቲያን ሥራዎችና
ይሁን እንጂ የክርስቲያን አንድነት ከዚህ ዐይነቱ ግንኙነት በላቀ እርከን ላይ መገኘት አለበት። እኛ እንደምናስበው ከሆነ የክርስቲያን አንድነት በ”አንድ ሃይማኖት (እምነት)” መሠረት ላይ መገንባት ይገበዋል። በአብያተ ክርስቲያን መኻከል ነገረ መለኮታዊ ውይይት የተጀመረውም እዚህ መሠረት ላይ ለመድረስ ነው።
ይህ በእጃችሁ የገባው መጽሐፍ በፕሮቴስታትንት ወንድሞቻችንና በእኛ መኻከል ለሚኖር ለዚሁ የነገረ መለኮት ውይይት እንዲያገለግል የቀረበ አንድ ሥራ ነው።
እንደሚታወቀው ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን በብዙ ቤተ እምነቶች ሥር ይገኛሉ። በቤተ እምነቶቹ መኻከል በከፊልም ቢሆን ልዩነት አለ።ይሁን እንጂ በጥቅሉ ሲታዩ በአንድ አውታር የተዋቀሩ ናቸው። ከእነርሱ ጋር በሚጋሩት ነጥቦች ላይ በፍቅር ድባብ ሆነን ለመወያየት እንሞክራለን።
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ብዙዎቹ ርዕሶች ሌሎቹን የፕሮቴስታንት ወገኖች የሚመለከቱ በመሆናቸው ‘አንግሊካን’’ ወንድሞቻችንን አናካትትም።
ውይይታችንን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብቻ ለመመሥረት ተጠንቅቀናል፤ አንድም የቤተ ክርስቲያን አባቶችንም ሆነ የትውፊት አባባሎችን አልጠቀስንም።
በፕሮቴስታንታዊና በኦርቶዶክሳዊ መካከል ያሉ የልዩነት ዐሳቦችን ስናስረዳ በፍጹሙ ግልጽነት እንናገራለን፤ እንተነትናለንም። መጽሐፍ ቅዱስ በነዚሁ ትምህርቶች ላይ ያለውን ሃሳብም እንመለከታለን።
ይህ መጽሐፍ የውይይታችን የመጀመሪያው ቅጽ ነው። ቀሪዎችን የልዩነት ነጥቦች የሚሸፍኑ ሌሎች ቅጾች ይከተላሉ። ይህንም የምናደርገው ምሁራዊ ግንዛቤ ያስጨብጠናል፤ ቀጥተኛዋ እምነት ላይም ያደርሰናል በሚል ጉጉት ነው::
ለሚደርሱን ለማናቸውም አስተያየቶች መልስ ለመስጠት ዝግጁ ነን።
በመጨረሻም ውይይታችንን በፍቅር ድባብ ሆነን ማከናወን እንድንችል ጌታ እንዲረዳን እንጸልያለን፤ በበኩላችን እንዲሁ እንዲሆን እንጠነቀቅበታለን።
ኦገስት 1988 ፖፕ
ሲኖዳ ሣልሳዊ
አንዲት ሃይማኖትና ጤናማ
አስተምህሮ
ነገረ መለኮት ማለት ስሙ የተባረከ ይሁንና ስለ እግዚአብሔር የሆነ ሰፊና ጥልቅ ንግግር ነው። ይህን ንግግር ማድረግ የሚችሉትም እግዚአብሔርን ያወቁቱና የእነርሱ ደቀመዛሙርት የሆኑቱ ብቻ ናቸው።
ነገረ መለኮት የአገላለጽና የአተረጓጎም ትክክለኝነትን እንዲሁም በክርስቲያን ሁሉ ተአማኒ የሆኑ ምንጮችን ማወቅ ይጠይቃል። እኛ የጥንቱን የምትይዝና የቆየውን ወግ የምትጠብቅ ቤተ ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን ለቅዱሳን አንድ ጊዜ የተሰጠንን ሐዋርያዊ ሃይማኖት እንይዛለን (ይሁዳ 1-3) ። በሃይማኖታችን ላይ አዲስ ሃሳብን አንጨምርም። አባቶቻችን በድንበርነት ካቆሙት ጥንታዊ ምልክትም ንቅንቅ አንልም (ምሳ 22÷28) ።
የቤተ ክርስቲያን “እምነት አንድ ሃይማኖት ነው። እርሱም ቤተ ክርስቲያን ዕለት ዕለት የምታስታውሰን ነው።ይኸንንም የምታደርገው በነግሕ (ንጋት)[1] በምታደርሰው ጸሎቷ የጳውሎስ መልእክት የሆነውን ኤፌሶን 4÷5ን በንባብ በማሰማት ነው። የእያንዳንዱ ምዕመን እምነት ይኸው ‘አንድ ሃይማኖት’ ሲሆን ይህንን ያላመነን ሰው ከሚያምኑት ከሌሎቹ ጋር እንዳይደባለቅ ቤተ ክርስቲያን ታገለውም ትለየውም ነበር። ለዚህም ምክንያቷ የምዕመናንን እምነት እንዳይበክል ነው። ስለማግለልና ስለመለየት አስተማሪያችን ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ይላል፦ “ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤ ሰላም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና“ (2ኛ ዮሐ 10-11 ) ።
የ’አንዲት ሃይማኖት’ መሠረታዊ ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ሌሎች ምንጮችም አሉ። እነርሱም ቅዱሳን የተናገሯቸው ቃሎች፣ በቅዱስ ጉባኤ ትክክለኛነታቸው የተረገጋጡት የእምነት መግለጫዎች ፣ በቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት በተለይም በሥርዓት መጻሕፍቱ የተመዘገቡት ሲሆኑ ሁሉም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚስማሙ ናቸው። በጥቅሉ የ“ቤተ ክርስቲያን ትውፊት” ተብለው ይጠራሉ።
ትውፊቱ ትክክለኛነቱን የምናረጋግጥበትን ተፈላጊውን ሁኔታ ያሟላል፤ ማለትም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማል። መምህራችን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን” (ገላ 1÷8) ይላል። ያም ብቻ አይደለም፦ “አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን” (ገላ 1÷9) ይላልም ።
ለዚህ ነበር በሐዋርያት አባቶቻችን
ዘመንና ከዚያም በኋላ በቀደመው ዘመኗ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትን እንዳይበረዝ በመከላከል ሲበዛ የተጠነቀቀችው፣
በመጠንቀቋም ሃይማኖትን የጠበቀችው ። በዚህም ምክንያት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ፣ ለ’ቀርጤስ’ ኤጲስ ቆጶስ[2]“ ለቅዱስ ቲቶ ፡-"አንተ ግን ሕይወት ለሚገኝበት ትምህርት የሚገባውን ተናገር” (ቲቶ
2÷1) ይለዋል። ይህ ጤናማ ትምህርት ለመጀመሪያዎቹ ኤጲስ ቆጶሳት
አባቶቻችን ከሐዋርያቱ በቀጥታ ታዘዘ። ኤጲስ ቆጶሳቱ ደግሞ ለሚለጥቀው ትውልድ በታማኝነት ትዕዛዙን አስተላለፉ። በዚህ መንገድ ይህ
ጤናማ ትምህርት ካንዱ ትውልድ ወደ ሚቀጥለው ተላለፈ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙሩ ለነበረው ለኤጶስ ቆጶስ ጢሞቲዎስ እንዲህ
ይለዋል፦ “ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ
ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ” (2 ጢሞ 2÷2)።
ይህም ብቻ አይደለም፦ “በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር አድርገህ፥ ከእኔ የሰማኸውን ጤናማ ቃል ምሳሌ ያዝ “ (2
ጢሞ 1÷13 ) ይለዋልም።
ማስተማር የካህን ተግባር ነው
ማስተማር የሐዋርያቱና ከዚያም ደቀ መዝሙሮቻቸው የነበሩቱ የኤጲስ ቆጶሳት ፣ የካህናትና የዲያቆናት ተግባር ነበር። የምዕመናን ሥራ ሆኖ አያውቅም። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴ 28÷19-20)ና “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” (ማር 16÷15) ባለበት ጊዜ የማስተማሩን አደራ ለሐዋርያቱ ሰጣቸው። ጌታ ይህንን ለሌሎች አላለም።
ሐዋርያቱ መስበክን፣ ማስተማርን፣ ቃሉን ማገልገልንና ሃይማኖትን ለሌሎች በአደራ ማስተላለፍን የራሳቸው ዋና ሥራ አድርገው ወስደውታል። ሰባቱን ዲያቆናት በሾሙ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ “እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን” (ሐዋ 6÷4) አለ። ስለ ጌታም እንዲህ አለ፦ “ለሕዝብም እንድንሰብክ-- አዘዘን” (ሐዋ 10÷42) ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ስለወንጌል “-----እኔ ሰባኪና ሐዋርያ አሕዛብንም አስተማሪ እንድሆን በተሾምሁበት----” (2 ጢሞ 1÷11) ይላል ። ይኸው ሐዋርያ የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከና ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ እያስተማረ ኖረ (የሐዋ 28÷31)።
ቅዱስ ጳውሎስ የማስተማርንና የመስበክን ሥራ ደቀመዛሙርቱ ለነበሩት ለኤጲስ ቆጶሳቱ በአደራ ሰጣቸው። ለደቀ መዝሙሩ ለቅዱስ ጢሞቴዎስ “ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም” (2 ጢሞ 4÷2) አለው። እንዲሁም ለደቀ መዝሙሩ ለኤጲስ ቆጶስ ቲቶ ፡-“ይህን በሙሉ ሥልጣን ተናገርና ምከር ገሥጽም፤ ማንም አይናቅህ” (ቲቶ 21÷5) አለው።
የማስተማር ሥራ አደራ የተሰጠው መጀመሪያ ለኤጲስ ቆጶሳቱ፣ በኋላም ለቀሳውስቱና ባጠቃላይ ለካህን ነው። በተገቢው ሥፍራ በዝርዝር እንደምናየው ስለዚህ ነበር ሕግ ከካህን አንደበት ለመስማት ይፈለግ የነበረው።
እንደሚታወሰው የኤጲስ ቆጶሳት ቅዱስ ጉባኤ ተሰይሞ ነበር። ጉባኤውም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ‘ሕግን’ና ‘ቀኖናን የመደንገግ ሥልጣን ነበረው። ይህም ብቻ አልነበረም። ስለሃይማኖት ጉዳይ የብዙዎቹ ኤጲስ ቆጶሳት መልስ ቅዱስ ቀኖና ሆኖ ይቆጠርና ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ትቀበለውም ነበር። ለዚህ ጉልህ ማስረጃ 22 ኛው የቊስጥንጥንያ ሊቀ ኤጲስ ቆጶሳት የነበሩት ጢሞቴዎስ እለስክንድሮስ በ381 በተደረገው ሁሉ አቀፍ የቤተ ክርስቲያን (ኢኩሜኒካል) ጉባኤ በተገኙበት ጊዜ የሆነው ነው። እርሳቸው የሰጧቸው መልሶች ሁሉ የቤተ ክርስቲያን ቀኖና ሆነዋል። (“ኒቅያና ከኒቅያ በኋላ ስለነበሩት አባቶች” ተከታታይ ቅጾች ቅጽ 14 ይመልከቱ)።
ምዕመናን የሆኑ እንደሆነ ግን ሁል ጊዜም የሚይዙት የተማሪነትን ሥፍራ ነበር። ካህናቱ አስተማሪዎች የሚሆኑት ከቤተ ክርስቲያን መስበኪያ ሰገነት በመስበካቸው ብቻ ሳይሆን በኑዛዜና በመሳሰለውም መንፈሳዊ አማካሪዎች በመሆናቸው ጭምር ነበር።
በምክር ቤቶቿና በኤጲስ ቆጶሳቱ እየተወከለች እምነትንና አስተምህሮን መወሰንና መደንገግ የቤተ ክርስቲያን ተግባር ነው። ይኸው ለምዕመናኑ በካህናቱ ይተረጎማል። እምነትንና አስተምህሮን በተመለከተ ሰባኪዎች (አስተማሪዎች) የራሳቸውን አስተያየት እንዲያስተምሩ ሥልጣን የላቸውም፣ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ተመዝግቦ ያለውን አደራ እንደተሰጣቸው ያስተምራሉ። ማንም የየራሱን ሃሳብ እንዲያስፋፋ ነጻነት ከተሰጠው የተለዩ ዶግማዎች ይኖራሉና። እነዚህን ደግሞ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ናቸው ልንላቸው አንችልም።
ሰው የፈለገውን የማመን ነጻነት አለው። ይሁን እንጂ እንደ ራሱ ሃሳብ የሆነን ነገር ለማስተማር ነጻነት የለውም፣ ምክንያቱም የመናፍቅ ትምህርት ከተለያዩ የትምህርት ሥፍራዎች ተነስተዋልና።
‘ሉተር’ እንደ ራሱ ሃሳብ ማስተማር የጀመረ ጊዜና ‘ካልቪን’፣ ‘ዚዊንጊሊ’ና ሌሎችም በተከተሉት ጊዜ የከፋ አዲስ መለያየት በቤተ ክርስቲያን ሆነ። ጊዜ እየገፋ ሲሄድ እርስ በእርሳቸው የሚፋለሱ ሌሎች ዶግማዎች (ትምህርቶች) ተፈጠሩ። ቤተ ክርስቲያን ታውቀው የነበረው “አንድ ሃይማኖት” መደብዘዝ ጀመረ።
ማንም በእምነቱ ነጻ ነው። ይሁን እንጂ ከዚህ ነጻነቱ የተነሳ ለቤተ ክርስቲያን አንድ እምነቷ ባዕድ ወደ ሆነ መናፍቅ ትምህርት ወይም መናፍቅ ባይሆን እንኳ ከጥንቱ ወዳፈነገጠ ትምህርት ፈቀቅ ወይም ዞር ሊል ይችላል። እምነትን ለመጠበቅ ሁል ጊዜም የነቃችው ቤተ ክርስቲያን ይህን ፈቀቅ ማለት አትፈቅድም፣ የማስተማርንም ሥልጣን ለሁሉ አትሰጥም። ነገር ግን ለቅዱሳን አደራ በተሰጠው ሃይማኖት መሠረት የሚያስተምሩትን ትመረምራለች። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ 1÷9 የተናገረውን ቃል ቋሚ መመዘኛ አድርጋ በማኖር ትሠራለች።
ማንም በእምነት ወይም በአስተምሮ ስህተት ውስጥ የሚገባው አንዳንድ ጊዜ ከተለያዩ ዶግማዎች ጋር በመደባለቅ (በመነካካት)፣ ወይም በዶግማዎቹና ዶግማዎቹን በሚያስተምሩ አስተማሪዎች ተጽዕኖ ሥር በመውደቅ፣ ወይም የእነዚህ አስተማሪዎች ወይም የጽሑፎቻቸው ተከታይ በመሆን ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በግል አመለካከት ላይ ግትር በመሆን ለውጥን አልቀበልም ወይም ለቤተ ክርስቲያን አልታዘዝም በማለት ነው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ እጅግ ምናልባትም አልቀበልም ከሚለው ሰው በስተጀርባ ያለው የልብ ደንዳናነት ይሆናል። ይህ የልብ ሁኔታ የራሱን ሃሳብ ብቻ ትክክል፣ ሃሳቡን የሚቃወመውን የሌላውን ሰው ግን ስህተት አድርጎ ያሳየዋል። ሌላ ሰው የማይረዳውን እርሱ ብቻ የሚያስተውል እንደሆነ አድርጎም ይስልለታል።
ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ሁሉ ትምህርቷ እንዳይጣመም ( እንዳይዛነፍ) ስትጠነቀቅ ኖራለች። ይህን ለመረዳት ‘አርዮስ’ን በመሰለ በአንድ የቀድሞ ቄስ በተሰጠ አንድ የተሳሳተ ትምህርት ብቻ ሁለት ኤጲስ ቆጶሳት ማለትም ተፍጻሜተ ሰማዕታት ሊቀ ኤጲስ ቆጶሱ (ፓትረያርኩ) ‘ጴጥሮስ’ና ሊቀ ኤጲስ ቆጶስ ‘እለእስክንድሮስ’ ጣልቃ መግባታቸውን መመልከት ይበቃል። በእስክንድርያ በተጠራ የምክር ጉባኤ ላይ አንድ መቶ ያህል ኤጲስ ቆጶሳት ከእስክንድርያና ከሊብያ በመገኘት መከሩ። በኋላም 318 ኤጲስ ቆጶሳት ከዓለሙ ሁሉ በመምጣት የመከሩበት ሌላ ጉባኤ በ 325 ዓ.ም በ’ኒቅያ’ ተደረገ። ይህ ሁሉ የሆነው አንድ ቄስ ባስተማረው ስህተት ብቻ ነበር። የትምህርቱ መስፋፋት አደጋ ነበረውና፣ “የእምነት ነጻነት አለና ጉዳዩን ተውት” ያለ ማንም አልነበረም።
የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን መከፈል የሆነው በ5ኛው ምዕተ ዓመት አጋማሽ ማለትም በ451 ዓ.ም ነበር። ይህም በክርስቶስ ባሕርይ (ነገረ ሥጋዌ) ላይ በነበረው የተለያዩ ትምህርቶች የተነሳ ነበር። ሌላው መከፈል የሆነው በ11ኛው ምዕተ ዓመት ነበር። ይህም በካቶሊክና በቤዛንታይን ኦርቶዶክስ መካከል መንፈስ ቅዱስ ከማን ሠረጸ በሚለው ዶግማ (ትምህርት) ልዩነት የተነሳ ነበር። 3ኛውና ትልቁ መከፈል የደረሰባት በ15ኛው ምዕተ ዓመት የፕሮቴስታንታንት እምነት መሥራች በሆነው በሉተር ነበር። ከዚያም በኋላ የተለያዩ አስተምህሮዎች በፕሮቴስታንት እምነት ውስጥ መንጭተዋል።
ስለዚህ በተለያዩ ክርስቲያን ክፍፍሎች ውስጥ ያለውን ትምህርት ለማነጻጸር (ለማስተያየት) ፣ ልዩነቶቹን ለማጥናት፣ ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር ለማይስማማው ለማንኛውም ትምህርት መልስ ለመስጠት ይህን “የነገረ መለኮት ንጽጽር”ን ማቅረብ አስፈለገ።
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በኦርቶዶክሳዊነትና በፕሮቴስታንትነት መካከል ስላለው አንኳር የእምነት ልዩነት
ለማብራራትና በመጽሐፍ ቅዱስ ብርሃንነት ለመወያየት እንሞክራለን። እምነታችንን እግዚአብሔር አንድ እንዲያደርገውም እንጸልያለን።
የክርስቲያኖችን አንድነት በተመለከተ የምናደርገው ዋናው ጥሪ ከ’እምነት
አንድነት’ ላነሰ ጉዳይ አይደለምና።
[1]ከhttp://www.agpeya.org/ የተወሰደ፡ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሰባት ቀኖናዊ የጸሎት ሰዓቶች አሏት። ይህም “ስለ ጽድቅህ ፍርድ ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለሁ” (መዝ 119÷164) የሚለውን የተከተለ ነው። እነርሱም የነግሕ (የንጋት) ፣ የሦስተኛ ሰዓት ፣ የእኩለ ቀን ፣ የዘጠነኛ ሰዓት ፣ የአሥራ አንደኛ ሰዓት (የማታ) ፣ የአሥራ ሁለተኛ ሰዓት (የመኝታ)ና የእኩለ ሌሊት (የሌሊት) ናቸው። ከእኩለ ሌሊት በኋላ እስኪነጋ ያሉት ሰዓቶች ሦስት እኩል ሰዓቶች ላይ ይመደቡና የመጀመሪያው ፣ ሁለተኛው እና ሦስተኛው ክፍል?? በመባል ይታወቃሉ። በያንዳንዱ የጸሎት ሰዓት ከሚነበቡት መሐል ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተለያዩ ጉዳዮች ይገኙበታል። ለምሳሌ፦ በሦስተኛው የጸሎት ሰዓት ከሚነበቡት መሐል ክርስቶስ በጲላጦስ ፊት ስለ መፈተኑ ይገኝበታል።
[2]
አባ ዮሐንስ ቢሰማኝ ይግዛው ጳጳስና ኤጲስ ቆጶስ በሚሉት ስያሜዎች መሐል
ያለውን የስም ድንግርግር ባብራሩበት ምዕራፍ ውስጥ የእንግሊዝኛው ‘ቢሾፕ’ ትርጉም ‘ኤጲስ ቆጶስ’ እንደሆነና ከዐረብኛውም ጋር
የሚስማማው ይኸው እንደሆነ አስረድተዋል። እኔም እርሳቸውን ተከትዬ ‘ቢሾፕ’ የሚለውን ቃል ‘ኤጲስ ቆጶስ’ ብዬ ተርጉሜዋለሁ። ኑ!እንማማር
1ኛ እትም መስከረም 2007/2014 ገጽ 255
Comments
Post a Comment