ትውፊት (ወግና ልማድ)
1. ትውፊት (ወግና ልማድ) ከመጽሐፍ ቅዱስም ይልቅ በእድሜ የቀደመ ነው
2. መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉን ነገር አይጠቅስም
3. የእግዚአብሔርን መንግሥት አስመልክቶ ጌታ ያስተማራቸው ነገሮች ምን ነበሩ?
4. ትውፊት ከሐዋርያቱ ትምህርት የተወሰደ ነው
5. ሐዋርያቱ ሥርዓትን ለቤተ ክርስቲያን መሥርተዋል
6. ሐዋርያው ጳውሎስ ትምህርቶችን ከጌታ ተቀበለ
7. ሐዋርያቱ በትውፊት የተቀበሉትን በመልዕክቶቻቸው መዘገቡ
8. የትውፊት ጥቅሙ (አግለግሎቱ)
9. ተቀባይነት ያለውና የሌለው ትውፊት
10. ድንጋጌን በማውጣትና በማስተማር የቤተ ክርስቲያን ሥልጣን
11. ትውፊት ጤናማ የሚባልበት ሁኔታ
12. ሐዋርያቱ ትውፊት እንዲጠበቅ አዘዋል
ትውፊት (ወግና ልማድ)
ትውፊት ማለት ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሌላ ከሐዋርያቱና ከአባቶች ለእኛ በአደራ የደረሰን ማናቸውም ትምህርት ማለት ነው። ይህ ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተካተቱ ርዕሶችን ይይዛል፣ ነገር ግን በምንም መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያፋልስ አይደለም።
ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን በትውፊት አያምኑም ። በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ይጸናሉ። በዚህ መንገድ ቤተ ክርስቲያን ከቀደመው ትውልድ የተቀበለችውን ቅርስ ገሸሽ ያደርጋሉ።ሐዋርያትና የቤተ ክርስቲያን አባቶች የጻፉትን ፣ የቅዱሳን ጉባኤ ውሳኔዎችን፣ የቤተ ክርስቲያን ቀኖናዎችና ደምቦችን፣ የቤተ ክርስቲያን አምልኮ ሥርዓትንና የቃል ትውፊትን አያካትቱም።
ትውፊት ከመጽሐፍ ቅዱስም ይልቅ እድሜው የበለጠ ነው። ወደ አባታችን ወደ አዳም ዘመን ይዘልቃል።
ለእኛ የደረሰን ከሁሉ የቀደመው የጽሑፍ ሕግ የተጻፈው በነቢዩ ሙሴ ነበር። ሙሴ የኖረበት ዘመን ደግሞ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ14ኛውና በ15ኛው ምዕተ ዓመት ነበር። ትውፊት ግን ከዚያም የቀደመ ነበር። አንዳች ሕግ ከመጻፉ በፊት ብዙ ሺህ ዓመታት አልፈዋል። ታዲያ የጽሑፍ ሕግ ባልነበረበት በዚያን ዘመን የሰውን ሃሳብ ማን መራው? በአንድ በኩል ሕገ ልቡና (የሞራል ሕግ) ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ካንዱ ትውልድ ወደ ሌላው በአደራ የተላለፈው ትውፊት አልነበረምን?
ከተጻፈው ሕግ በፊት ስለነበረ ትውፊት አንዳንድ ማስረጃዎችን ለመግለጥ እንሞክራለን÷
(1) በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ ጻድቅ ሰው አቤል ከሰቡ በጎች መስዋዕትን አቀረበ ተብሎ ተጽፏል (ዘፍ 4:4) ።ሐዋርያው ይህንን እንዲህ ሲል ያብራራዋል፦ “አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ” (ዕብ 11÷4) ። እዚህ ላይ ጥያቄን እንጠይቃለን። ለእግዚአብሔር መስዋዕት የማቅረብን ሃሳብ አቤል እንዴት አወቀው? ያንን እምነት ከወዴት አገኘው? የተጻፈ ሕግ በእርሱ ጊዜ አልነበረም። መልሱ ያለጥርጥር ይህንን ሃሳብ የተቀበለው ከአባቱ ከአዳም በትውፊት ነበር። አዳም ደግሞ የተቀበለው ከእግዚአብሔር ከራሱ ነበር።ይህ የሆነው ስለመስዋዕትና ስለሚቃጠለው መባ ሕግ ከመጻፉ ከአሥራ አራት ምዕተ ዓመታት በፊት ነበርና።
(2) በአባቶቻችን በኖኅ ፣ በአብርሃም፣ በይስሐቅ፣ና በያዕቆብ የቀረበው ‘እሚቃጠለው መሥዋዕትም’ ይህንኑ ፈር የተከተለ ነበር ማለት እንችላለን። የመሠዋትን ሃሳብ ያወቁት በአደራ ከተሰጣቸው ትውፊት ነበር። ‘መሠውያ’ን ስለመሥራትም ይህንኑ ማለት ይቻላል። ከጥፋት ውኃ በኋላ”ኖኅም ለእግዚአብሔር መሠውያውን ሠራ” (ዘፍ 8÷20) ። አብርሃም አባታችንም በሞሬ የአድባር ዛፍ ስር መሠዊያ ሠራ (ዘፍ 12:7) ። ምንም እንኳ በዚያን ጊዜ እንዲያ እንዲያደርጉ የሚያዝ መጽሐፍ ቅዱስ ባይኖርም መሠውያን የመሥራት ሃሳብ ግን ሲተላለፍ ኖረ።
(3) ኖኅ አባታችን ከንጹሕም እንስሳ ሁሉ፣ ከንጹሐን ወፎችም ሁሉ ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕትን በመሠዊያው ላይ እንዳቀረበ እግዚአብሔርም መልካሙን መዓዛ እንዳሸተተ በቅዱስ መጽሐፋችን ተጽፏል (ዘፍ 8÷20) ። ከንጹሕ እንስሳ መስዋዕት የማቅረብን ሃሳብ ኖኅ እንዴት አገኘው? ሙሴ ስለ ንጹሕ እንስሳ በኦሪት መጻሕፍት ከማብራራቱ በፊት፤በቀጥታ ከጌታ አግኝቶት ከእርሱ በኋላ ለመጣው ትውልድ በአደራ አስተላልፎት መሆን አለበት።
(4) አባታችን አብርሃም መልከ ጼዴቅን በተገናኘበት አጋጣሚ መልከ ጼዴቅ“የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበረ” (ዘፍ 14÷18) በማለት ገልጿል። ይህ የክህነት አገልግሎት እንዴት ተቋቋመ? ማነው ለመልከ ጼዴቅ አብርሃምን እንዲባርከው ሥልጣን የሰጠው? ምን ሕግ ነው አብርሃም ለመልከጼዴቅ ካለው ሁሉ ከአሥር አንድ እንዲሰጥ ያደረገው (ዘፍ14÷20)? እንዲሁም መልከጼዴቅ ከአብርሃም የበለጠ እንደሆነ ተመልክቷል (ዕብ 7÷6፣ 7) ።
በዚያን ጊዜ ስለክህነት፣ ስለክብሩ ፣ ስለ ተግባሩና ሌሎችን ስለመባረኩ የሚያብራራ የተጻፈ ሕግ አልነበረም። በዘፍጥረት በቀደሙት ምዕራፎች ካህን ወይም ክህነት የሚል ቃል በማናቸውም አኳኋን ተጠቅሶ አይገኝም። ታዲያ ስለክህነት ያለው ዕውቀት ከትውፊት የተገኘ ካልሆነ በስተቀር ከወዴት ተገኘ?
(5) አብርሃም መልከጼዴቅን ማግኘቱ በተገለጠበት በዚሁ ክፍል “አብራምም ከሁሉ አሥራትን ሰጠው” (ዘፍ14÷20) የሚለውን እንሰማለን። ከአሥር አንድ እጅ የመስጠት ሕግ በጽሑፍ ገና አልተሰጠም ነበር። በትውፊት ካልሆነ በስተቀር በአባታችን በአብርሃም ጊዜ ከአሥር አንድ እጅ ለካህን የሚሰጥ መሆኑ በምን ታወቀ?
ይህን ስለ አባታችን ያዕቆብም ማለት ይቻላል። እግዚአብሔርን “ከሰጠኸኝም ሁሉ ለአንተ ከአሥር እጅ አንዱን እሰጥሃለሁ” (ዘፍ 28÷22) ያለው አሥራት የመስጠትን ሃሳብ እንዴት አውቆ ነው? ምንም ጥርጥር የለውም ከአሥር አንድ እጅን የመስጠት አሳብ ያገኘው ከአሥር አንድ እጅን ለመልከ ጼዴቅ ከሰጠው ከአያቱ ከአብርሃም ትውፊት ነበር። አብርሃምም ራሱ በጽሑፍ ከተሰጠ ሕግ አልተቀበለውም። በጽሑፍ ሳይሰጥ አስቀድሞ የሰው ልጆች ሁሉ አስተማሪያቸው ትውፊት እንደነበር ግልጽ ነው። ከዚያም ወዲያ ቢሆን ይኸው የቀረ አልነበረም።
(6) ያዕቆብም ከወንድሙ ከዔሳው በሸሸ ጊዜ ከምድር ወደ ሰማይ በተዘረጋ መሰላል ላይ የእግዚአብሔር መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ አየ።እግዚአብሔርም አናገረው፣ ቃልንም ሰጠው ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል ያዕቆብ እንዲህ አለ፦ “በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ነው ---- ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህም የሰማይ ደጅ ነው” (ዘፍ 28÷16፣ 17) ማለቱን መጸሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ያንን ሥፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው፣ ትርጓሜውም የእግዚአብሔር ቤት ማለት ነው። ያዕቆብም ድንጋዩን ወስዶ ተንተራሰው፣ ሓውልት አድርጎ አቆመውም ፤ በላዩም ዘይትን አፈሰሰበት (ዘፍ 28÷12) ።
አባታችን ያዕቆብ ‘የእግዚአብሔር ቤት’ የሚለውን ሐረግ እንዴት አወቀው? በላያቸው ላይ ዘይትን በማፍሰስ የእግዚአብሔርን ቤቶች የመቀደስ ሕግ በጽሑፍ ከመሰጠቱ በፊት የመቀደስን ሃሳብ እንዴት አወቀ? በትውፊት ነው ከማለት በስተቀር ሌላ መግለጫ መስጠት አይቻልም።
(7)ሕግን በጽሑፍ በሰጠም ጊዜ ቢሆን እግዚአብሔር ትውፊትን እንዲቀጥል ፈቅዷል። ለምሳሌ ያህል ትእዛዛቱን ለልጆቻቸው እንዲያሳስቡና አደራ እንዲሉ በተለያዩ አጋጣሚዎች አባቶችን ማዘዙን መጥቀስ ይቻላል። ማሕፀንን የከፈተ በኵር ወንድን ሁሉ ለእግዚአብሔር ስለ መሰዋት ለልጆቻቸው እንዲያሳውቁ ጌታ (ዘፀ 13:14-16) ማዘዙንም መጨመር ይቻላል ። እግዚአብሔርም ደግሞ ለሕዝቡ እንዲህ አለ፦ “---ዓይኖችህ ያዩትን ነገር እንዳትረሳ፥ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ ከልብህ እንዳይወድቅ ተጠንቀቅ፥ ነፍስህንም በትጋት ጠብቅ፤ ለልጆችህም ለልጅ ልጆችህም አስታውቀው።” (ዘዳ 4÷9)
(8) በክርስትናም እንኳ አንዳንዶቹ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች በብሉይ ኪዳን ዘመን ስለነበረው ሁኔታ በትውፊት ከተቀበሉት ጽፈዋል። ለምሳሌ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ነቢዩን ሙሴን የተቃወሙትን ሁለት ጠንቋዮች በመጥቀስ÷“ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥--- እንዲሁ እነዚህ ደግሞ እውነትን ይቃወማሉ” (2 ጢሞ 3÷8) ብሏል። የእነዚህ አስማተኞች ስሞች በሙሴ መጻሕፍትም ሆነ በተቀረው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ቢፈለጉ አይገኙም። ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህን ስሞች ያወቀው ከአባቶች ትውፊት መሆን አለበት።
(9) በትውፊት አደራ የማለቱ ነገር ባይበዛም እንደ ብሉይ ኪዳን ሁሉ በአዲስ ኪዳንም ተደጋግሞ ታይቷል። የአዲስ ኪዳን ወንጌሎችም ሆኑ መልእክቶች በጽሑፍ ከመገኘታቸው በፊት በርካታ ዓመታት አልፈዋል። ለሃያ ዓመታት ያህል መላውን እምነት፣ የክርስቶስን ታሪክ፣ ትምህርቱንና መቤዠቱን ሰዎች የተቀበሉት በትውፊት ነበር።
(10) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ራሱ የጻፈውን ወንጌል ወይም በጽሑፍ የተቀመጠ ወንጌልን አላኖረልንም። ያም ቢሆን ከእርሱ በኋላ ላሰራጩት ሰዎች ቃሉን “መንፈስም ሕይወትም” (ዮሐ 6÷63) አድርጎ በማኖር ይሰብክም ያስተምርም ነበር። ጌታ ትምህርቱንና ስብከቱን በጀመረ ጊዜ ለሕዝቡ እንዲህ አለ፦ “ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ” (ማር 11÷5)። በጽሑፍ የቀረበ ወንጌል (የምሥራች ቃል) ሳይሆን፣ ነገር ግን በአንደበት የተገለጸ የምሥራች ቃል ወይም በአደራ የተላለፈ መለኮታዊ ትምህርት ይሰበክ ነበር። ጌታ ለደቀመዛሙርቱ “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” (ማር16÷15) በማለት ስለሰጠው ቃልም (ትዕዛዝም) ሊባል የሚቻለው ይኸው ነው። ይህ ትዕዛዝ በጽሑፍ የተሰጠ አልነበረም።
11) እዚህ ላይ አንድ አስፈላጊ ሐቅ መጥቀስ እፈልጋለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉን ነገር አይጠቅስም።
(ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ጌታ ኢየሱስ ያደረገውን ወይም የተናገረውን ሁሉ አይጠቅስም። የተደረገው እንደዚህ ነው። ወንጌላውያኑ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ካስተማረው (ከተናገረው)ና ካደረገው ሁሉ መረጡ። በሆነ ጊዜ ላይ የተወሰነውን በጽሑፍ ለሕዝቡ በማኖር የተቀረውን ተዉት። የተደረገው ይህ ለመሆኑ በመጨረሻ በተጻፈው ወንጌል ግልጽ ሆኖ ተመልክቷል። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ብሏል፦ “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል” (ዮሐ 21÷25)። እንዲሁም “ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤ ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል” (ዮሐ 20÷30፣31) ብሏል ።
ክርስቶስ ያደረጋቸው ተአምራዊ ምልክቶች በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፉት እነዚያ ብቻ ናቸው ብላችሁ አታስቡ። በሺህ የሚቆጠሩ ታምራት ያልተጻፉ ነበሩ። ይህን ለማረጋገጥ ወንጌላዊ ሉቃስ “ፀሐይም በገባ ጊዜ በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙ በሽተኞችን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡአቸው፤ እርሱም በእያንዳቸው ላይ እጁን ጭኖ ፈወሳቸው።” (ሉቃ 4÷ 40) በማለት የጻፈው በቂ ማስረጃ ነው።
የታመሙት ምን ያህል ነበሩ? እጅግ ብዙ ነበሩ። የፈውስ ታምራቱ ሁሉ አልተመዘገቡም። አስተማሪያችን ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስም “ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር።” (ማቴ 423) ብሏል።
ደዌና ሕማም ሁሉ የሚለው ዝርዝራቸው ምን ያህል ነበር? አልተመዘገቡም። ጌታ በምኩራብ ያስተማረውና የሰበከውስ? እነርሱም ቢሆኑ ሁሉም አልተመዘገቡም። አስተማሪያችን ወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስ ሲጽፍ ጌታ ኢየሱስ ወደ ቅፍርናሆም በሄደ ጊዜ ወደ ምኩራብ ገባና አስተማረ፣ “እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበር እንጂ እንደ ጻፎች አይደለምና በትምህርቱ ተገረሙ” (ማር 1÷21፣22) ይላል። ያስደነቃቸው ትምህርት ምን ነበር? አልተመዘገበም።
በአምስት ዳቦና ሁለት ዓሣዎች ተአምር ባደረገበት ዕለት ጌታ ኢየሱስ ያስተምር የነበረው ከጠዋት እስከ አመሻሹ ነበር። ያስተማራቸው ምን ነበር? በወንጌላት አንዳች አልተመዘገበም። ጌታ በሐይቁ፣ በባህሩ ዳርቻ፣ በጀልባውና በየመንገዱ ላይ ያስተማረው ምን ነበር? ወንጌላቱ በጻፉት በዝርዝር የተመለከተ ነገር የለምና አናውቀውም።
(ለ) ከጌታ ትንሳኤም በኋላ ተመሳሳይ ሁኔታ እናገኛለን። ጌታ በኤማኦስ መንገድ ላይ ያገኛቸውን ሁለት ሰዎች “ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው” (ሉቃ 24÷27) ። እነዚህ ሁሉና ሌሎችም ትምህርቶቹ በወንጌላውያኑ አልተመዘገቡም።ነገር ግን ያለ ጥርጥር እነዚህ ሁሉ ወይም ከእነዚህ ገሚሶቹ በትውፊት ደርሰውናል።
(ሐ) ከትንሣኤው በኋላ ለ40 ቀናት ጌታ ከደቀመዛሙርቱ ጋር ኖሮ ከእግዚአብሔር መንግሥት ጋር ስለተገናኙ ጉዳዮች የነገራቸውስ ምን ነበር? (ሐዋ 1÷3)
የእግዚአብሔርን መንግሥት አስመልክቶ ጌታ ያስተማራቸው ነገሮች ምን ነበሩ?
ከትንሳኤው በኋላ ከሐዋርያቱ ጋር በርካታ ስብሰባዎችን ያስደረጉ በመሆናቸው ቃሎቹ ያለጥርጥር እጅጉን አስፈላጊ ነበሩ። ይህን ያህል አስፈላጊ የነበሩ ይሁኑ እንጂ እነዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግበው የምናገኛቸው አይደሉም። ምናልባትም የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን የሚመለከቱ ሳይሆኑ አይቀሩም። ትዕዛዞቹ ምን እንደነበሩ ሳይገለጡ “ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው” (ማቴ 28÷20) ብሎ የሰጣቸውን አደራ ለመረዳትና ይህንኑ ለማስተማር የሚያስፈልጓቸው ጉዳዮች ሳይሆኑ አይቀሩም።
የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶችና ትዕዛዞች ጠፍተዋል ወይስ ለእኛ ደርሰዋል? እጅግ ጠቃሚ ናቸውና ጠፍተዋል ብሎ ማመን የማይመስል ነገር ነው። ታዲያ ወደ እኛ እንዴት ደረሱ? ሐዋርያው ጳውሎስ ከአስራ አንዱ ሐዋርያት ጋር አልነበረም።ከትንሳኤው በኋላ ጌታ ከአሥራ አንዱ ጋር ያደረገውን ስብሰባ አልተካፈለም። እርሱ ሲቀር ከትንሳኤው በኋላ 40 ቀን ከጌታ ጋር ያሳለፉት አሥራ አንዱ ሐዋርያት የጻፉት በጣም ጥቂቱን ነው። የጻፉትም ደግሞ ሁሉን የክርስትና ትምህርቶች አያካትቱም። ለዚህ አንድ ማብራሪያ ብቻ ነው ያለው። ያም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ ያስተማረው በትውፊት ለእኛ ደርሷል ነው ። ያም ሊሆን የቻለው ሐዋርያቱ በአደራ ስላስተላለፉት ነው ።
ጌታ “እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው” (ዮሐ 6÷63) እንዳለው እነዚህን የጌታን ትምህርቶች ቤተ ክርስቲያን በሕይወቷ ገልጣለች። ሐዋርያቱ የቃሎቹን መንፈስ ስለተረዱ በሕይወት ጻፏቸው። እነዚህ ቃላት በቤተ ክርስቲያን ሕይወት (እያደረገች በኖረችው) በኩል ደርሰውናል።
ስለዚህ ትውፊትን የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ነው ወይም ሕያው ቤተ ክርስቲያንን ነው ማለት እንችላለን። ሐዋርያቱ ከጌታ ከተማሩትና ከተቀበሉት ሁሉ ጋር በማድረግ ይህን ሕይወት ለቅዱሳን አደራ ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ በወንጌሎች ወይም በመልእክቶች አልጻፉትም። በቤተ ክርስቲያን ሕይወት የሚታዩ ሕያው ልምምዶችና ትምህርትቶች (አስተምህሮዎች) አድርገው ትተውታል። ከነዚያ ትምህርቶች መካከል የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ፣ ወግና ምስጢራት ይገኙባቸዋል።
ጌታ ሦስት ዓመት ሙሉ የሰበከው የተራራውን ስብከት ብቻ ይመስላችኋልን (ማቴ 5-7)? ይህ ብቻ ነበር ቢባል የማይታመን ነው። የጌታ ትምህርት አልጠፋም። ደቀ መዛሙርቱ በልባቸው፣ በጆሮአቸው፣ በአእምሮአቸው አኑረውታል። ጌታ ያስተማረውን በመልካም ልባቸው ከነበረው መዝገብ ፣ከተባረከው ትውስታቸው በማውጣት ለቤተ ክርስቲያን አስተላለፉ። ያስተላለፉትም ‘ ትውፊት’ ወይም የ’ሐዋርያት አደራ’ በሚል ርዕስ ነው። ጌታ በተናገረው እውነተኛ ተስፋ መሠረት መንፈስ ቅዱስ ሁሉን አስተማራቸው፤ ጌታ የተናገረውን ሁሉንም አስታወሳቸው (ዮሐ 142÷6) ።
ትውፊት የተወሰደው ከሐዋርያቱ ትምህርት ነው
ብዙዎቹ ሐዋርያት መልዕክቶችን አልጻፉም።ታዲያ ያስተማሩት የታለ? በእነርሱ በኩል የነበረው መለኮታዊ እስትንፋስ ሥራ የት አለ? በነቢያቱ በኩል የሚናገረው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ የት አለ? አንዳንዶቹ ሐዋርያት ያስተማሩት በመልእክቶች የጻፉትን ብቻ ነበር ማለት አይቻልም። ሐዋርያው ያዕቆብ ያስተማረው በአንድ መልእክት ብቻ የተወሰነ ነበር ለማለት አዳጋች ነው ። ወይስ ሐዋርያው ይሁዳ ያስተማረው አንድ ምዕራፍ ብቻ ነበረ ሊባል ይችላልን? ከትምህርታቸው አንድም ቃል ያልተቀበልነው የተቀሩት የአሥራ አንዱ ሐዋርያት ትምህርትስ ምን ነበር? ምን ሰበኩ? ለቤተ ክርስቲያን ምን ተውሏት? ምናልባት ሁሉም ወይም በከፊል በትውፊት ደርሰውናል ማለት ይቻላል።
ሐዋርያት በየምኩራቡ ገብተው ያስተምሩና ተቃዋሚዎችንም ይከራከሩ ነበር። ይሁን እንጂ ከዚህ አንድ እንኳ አልተጻፈም። በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ና በሰማርያ ያሉ ሁሉ እስኪያምኑ ድረስ ሰብከዋል፣ ይሁን እንጂ ካስተማሩት በጽሑፍ የደረሰን ጥቂቱ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለሁለት ዓመታት በቆየበት ቤት ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በድፍረት ያለመከልከል አስተምሯል (ሐዋ 28÷ 30፣ 31) ። ከዚያ ውስጥ በጽሑፍ የቀረልን አንዳችም የለም። ታዲያ ያስተማረው ሁሉ የት ደረሰ?
ያለጥርጥር ሐዋርያቱ ለቤተ ክርስቲያን ሥርዓትን ደንግገዋል፤ እነርሱ ምንድናቸው?
የጌታ ሐዋርያት ያንን ሁሉ ትምህርት ከጌታ ከተቀበሉ በኋላ ቤተከርስቲያንን ጉዳዮቿን የምትመራበትን አንዳች ደምብና ሥርዓት ሳያበጁላት ተዉአት ማለት የሚመስል ጉዳይ አይደለም። እነዚህን በመልእክቶቻቸው አልጻፏቸውም። ለዚህ ምክንያታቸው እንደዚህ ዓይነቶቹ ለሕዝበ ምዕመናኑ ይፋ ባለመሆናቸው ወይም በትውፊት በኩል ለሁሉ ሊታወቅ በመቻሉ ሊሆን ይችላል። ያለጥርጥር እነዚያ ሥርዓቶች በቤተ ክርስቲያን ትውፊት ወይም አንዱ ለሚቀጥለው በአደራ በማስተላለፍ ለእኛ ደርሰዋል።
ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በሁለተኛ መልዕክቱ መደምደሚያ “እንድጽፍላችሁ የምፈልገው ብዙ ነገር ሳለኝ በወረቀትና በቀለም ልጽፈው አልወድም፥ ዳሩ ግን ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ወደ እናንተ ልመጣ አፍ ለአፍም ልናገራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ” (2ኛ ዮሐ 12) ይላል።
እነዚህኑ ቃላት በ3ኛ ዮሐ 13ና 14 ላይ ደግሟቸዋል። ይህ ‘አፍ ለአፍ ልናገራችሁ’ ማለት ምን ማለት ነው? ለምንድነው በጽሑፍ ያልተቀመጠው? እንዴት ነው የደረሰን?
ከላይ ከሁለቱ መልእክቶች ከተገኙት ጥቅሶች ሐዋርያዊ አባቶቻችን አንዳንድ ጊዜ ከመጻፍ ይልቅ የሚመቻቸው ሆኖ ሲያገኙት በቃል መናገርን ይመርጡ እንደነበር መረዳት እንችላለን። ይህ በቃል ያስተማሩት ካንዱ ትውልድ ወደ ሚቀጥለው በአደራ እየተላለፈ እኛ ዘንድ ደርሷል።
ሐዋርያቱ ምናልባት ስለ እምነት ዋና ስለሆኑት መርሆዎች በመልእክቶቻቸው የተቻለውን ያህል ትኩረት ሰጥተውት ቢጽፉም፤ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓትንና የአምልኮ ልማድን ዝርዝር ጉዳዮች ግን ለቤተ ክርስቲያን እንዲተገበሩ አደራጅተው ትተውታል። ሰዎች እነዚህን የሚማሩት ከተጻፈ መጽሐፍ ሳይሆን የምስጢራትን ሕይወት ከመተግበር (ከመካፈል) ነው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ“የቀረውንም ነገር በመጣሁ ጊዜ እደነግጋለሁ” በማለት ለቆሮንቶስ ሰዎች ጽፎላቸዋል (1 ቆሮ 11÷34) ። እነዚህ የሐዋርያው ድንጋጌዎች ምን ነበሩ? በትውፊት ተቀብለናቸዋልን? ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀመዝሙሩ ለቲቶ (የቀርጤስ ኤጰስ ቆጶስ) “ስለዚህ ምክንያት የቀረውን እንድታደራጅ በየከተማውም፥ እኔ አንተን እንዳዘዝሁ፥ ሽማግሌዎችን እንድትሾም በቀርጤስ ተውሁህ”(ቲቶ 1÷5) ይላል። ነገር ግን ካህናትን እንዴት እንደሚሰይም፣ ምን እንደሚጸለይ ፣ ሥርዓቱንና ለዚህ የሚያስፈልገውን ሁኔታ ሁሉ በጽሑፍ አልገለጸለትም። ይህንን ቅዱስ ቲቶ በቃል ከተነገረው በቀር ሌላ በምን መንገድ አውቆት ሊሆን ይችላል? ለዚህ ነው ሐዋርያው “እንዳዘዝሁህ” ያለው። ዝርዝር ትዕዛዙ በደብዳቤው ላይ አልተመዘገበም፤ ነገር ግን ቲቶ በቃል በ“ፊት ለፊት ንግግር” ትምህርቶቹን አገኛቸው (ተማራቸው)። ለእኛም ደግሞ በትውፊት ደረሱ።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀመዝሙሩ ለጢሞቲዎስ (የኤፌሶን ኤጲስ ቆጶስ) በተመሳሳይ ሲናገረው “ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ” (2 ጢሞ 2÷2) ብሎታል። እዚህ ላይ ሐዋርያው ‘የሰማኸውን’ አለው እንጂ ‘የተጻፈልህን’ አላለውም። ደቀመዝሙሩ ከእርሱ የሰማው ምን እንደነበር አልጻፈልንም። ይሁን እንጂ ትምህርቱ ከቅዱስ ጳውሎስ ለቅዱስ ጢሞቲዎስ ያለጥርጥር በአደራ ደርሶታል። ከዚያ በኋላ ደግሞ በፈንታው ለታመኑና እምነት ለሚጣልባቸው ለሌሎች ሰዎች እንደዚሁ አስተላለፏል። በዚህ መልክ እኛጋ እስከሚደርስ ድረስ ቀጠለ።
ሁሉን ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ለማረጋገጥ የሙጥኝ የሚሉ ሁሉ ሐዋርያው ‘አፍ ለአፍም መናገር’ (2 ዮሐ 12) ያለውን፣ ሐዋርያቱ ስለአብያተ ክርስቲያናት የሰጡትን መመሪያዎች ነገር ግን ያልተመዘገቡትን (1 ቆሮ 11÷ 34) ፣ ተማሪዎቻቸውን ያዘዟቸውን (ቲቶ 1÷5)ና ሐዋርያዊ ትምህርቶች በመልዕክቶች ወይም በወንጌል በሚገኝ ጥቅስ ሳይሆን፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሕይወትና ልምምድ የተለወጡ መሆናቸውን ቸል ይሉታል።
ይህን ነጥባችንን ለማሳየት ’እሁድ’ን የጌታ ቀን አድርጎ መቀደስን እናነሳለን
መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ የሚያምኑና ትውፊትን የሚቃወሙ ክርስቲያኖች ሁሉ በቅዳሜ ፈንታ እሁድን እንደ ጌታ ቀን ያከብራሉ። “የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ” (ዘጸ 20÷8) ፣ “እግዚአብሔር አምላክህ እንዳዘዘህ የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ ጠብቅ” (ዘዳ 5÷12) የሚሉትን ጥቅሶች ቃል በቃል አይወስዷቸውም። እነዚህ ታዲያ ቅዳሜን በማክበር ፈንታ እሁድን ማክበርን ከየት አመጡት? ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው ወይስ ከትውፊት ነው? ያለጥርጥር ከትውፊት ነው። ምክንያቱም “እሁድን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ’ ወይም ‘እሁድን ቀን ትቀድሰው ዘንድ ጠብቅ ፤ በዚያ ቀን ምንም ሥራ አትሥሩ” የሚል አንድም ጥቅስ በመጽሐፍ ቅዱስ አይገኝም።
እሁድን ማክበር የቤተ ክርስቲያን ልማድ ሆኗል። ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ወስደው ሐዋርያቱ ያከብሩት ነበር ። በወንጌል ውስጥ በግልጽ አልተጠቀሰም። ነገር ግን በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ‘በተዘዋዋሪ መንገድ’ ይህንኑ መለኮታዊ አደራ የሚያመለክት ነገር ተመዝግቧል። ስለዚህ ጉዳዩ ምንም የተጻፈ ትዕዛዝ ሳያስፈልገው በቤተ ክርስቲያን የታመነ ልምምድ ሆኖ ቅዳሜን ማክበር ተቀይሯል÷÷ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በአንድ ድምጽ እሁድን ማክበራቸው ትውፊትን ስለመቀበላቸው ማስረጃ ነው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጻፈው መልዕክቱ ትምህርትን ከጌታ እንደተቀበለ የጠቀሰበት ሥፍራ አለ
የቅዱስ ቁርባንን ምስጢር በተመለከተ ሐዋርያው “ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና፤ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠበት በዚያች ሌሊት እንጀራን አንስቶ” (1 ቆሮ 11÷23) ይላል። በዚህ ሥፍራ ሐዋርያው ከጌታ በአደራ የተቀበለውንና በቆሮንቶስ ያለችውን ቤተ ክርስቲያንን ያዘዘውን ይናገራል።የተቀበለውን ይኸንኑ እንዲያደርጉ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያንን አዟልም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዴትና መቼ ይህን ከጌታ እንደተቀበለው አይነግረንም። ይህ ስለቤተ ክርስቲያን ዶግማዎችና እነርሱም በአደራ ለቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደደረሷት ሃሳብን ይፈነጥቅልናል።
የቅዱስ ቁርባን ምስጢርን ሐዋርያቱ ከጌታ እንዴት እንደተቀበሉ ከወንጌላት ማወቅ እንችላለን። ሐዋርያቱ ግን ለቤተ ክርስቲያን እንዴት በአደራ እንደሰጡ አልነገሩንም። ይህንን መጻፍ አላስፈለገም። ቁም ነገሩ ግን ቤተ ክርስቲያን ይህንኑ ምስጢር መኖሯና መተግበሯ ነው። ይሁን እንጂ ቅዱስ ጳውሎስ አደራውን መቀበሉን ጠቅሷል።
ሐዋርያቱ በትውፊት የተቀበሏቸውን ነገሮች በመልእክቶቻቸው ጽፈዋ
(ሀ) ቀደም ሲል አንዳንዶቹን ገልጸናል፤ አሁን ደግሞ ሐዋርያው ይሁዳ በመልእክቱ በመላእክት አለቃ በሚካኤልና በሰይጣን መካከል ስለሙሴ ሥጋ የነበረውን ክርክር እናክላለን። እንዲህ አለ÷-“የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር፦ ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም” (ይሁዳ 9) ። ከዚህ አንዱም በብሉይ ኪዳን አልተጠቀሰም። ይሁዳ ይህን ያወቀው ምናልባት ከትውፊት ይሆናል።
(ለ) ሐዋርያው ጳውሎስ ሕዝቡ ሕጉን ሲቀበሉ ያደረባቸውን ፍርሃት ሲገልጥ እንዲህ ብሏል፦ “ሙሴም። እጅግ እፈራለሁ እንቀጠቀጥማለሁ እስኪል ድረስ የሚታየው እጅግ የሚያስፈራ ነበር” (ዕብ 12÷21) ። ይህ ሐረግ ከሙሴ ጋር ተያይዞ በኦሪት ዘጸአትም ሆነ በዘዳግም መጽሐፍ አልተጻፈም። ስለዚህ ሐዋርያው ይህን ምናልባት ከትውፊት አውቆት ይሆናል።
ሐ) በዮሐንስ ራዕይ ላይ በለዓም ትምህርትን ስለ ማዛባቱ የተጻፈውንም እንጨምራለን፣ ዝርዝሩ በዘኁልቁ አልተጠቀሰም (ዘኁ 24÷25) ። በራዕይ መጽሐፍ “ዳሩ ግን ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉና እንዲሴስኑ በእስራኤል ልጆች ፊት ማሰናከያን ሊያኖርባቸው ባላቅን ያስተማረ የበልዓምን ትምህርት የሚጠብቁ በዚያ ከአንተ ጋር ስላሉ፥ የምነቅፍብህ ጥቂት ነገር አለኝ” (ራዕ 2÷14) የሚል ተጽፏል። በዘኁልቁ ላይ ሕዝቡ ያንን እንዳደረጉ ተጠቅሷል፤ ነገር ግን የ‘በለዓም’ ትምህርት መሆኑ አልተጠቀሰም። የዮሐንስ ራዕይን የጻፈው ባለ ራዕዩ ቅዱስ ዮሐንስ ምናልባት ይህን ያወቀው በትውፊት ሳይሆን አይቀርም።
መ) የዚህኑ የ’በለዓም’ን ጉዳይ ሐዋርያው ጴጥሮስም÷ “ቅንን መንገድ ትተው ተሳሳቱ፤ የባሶርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከተሉ፤ እርሱ የዓመፃን ደመወዝ ወደደ፥” (2 ጴጥ 2:15) በማለት ጠቅሶታል ። ሐዋርያው ይሁዳም “ወዮላቸው፥ በቃየል መንገድ ሄደዋልና ስለ ደመወዝም ለበለዓም ስሕተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል በቆሬም መቃወም ጠፍተዋል” (ይሁዳ 11) በማለት ጠቅሷል ።
(ሠ) እንደዚሁም ቅዱስ ይሁዳ ስለ ሄኖክ ትንቢት ሲናገር በብሉይ ኪዳን ያልተጻፈውን እንዲህ አለ፦ “ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክ። እነሆ፥ ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ፥ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዓመፀኞችም ኃጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ሁሉ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል ብሎ ለእነዚህ ደግሞ ትንቢት ተናገረ” (ይሁዳ 14፣15) ተብሏል ። የዚህ ትንቢት ምንጩ ትውፊት መሆን አለበት።
(ረ) የግርዘት ትዕዛዝ ለአባታችን ለአብርሃም ከእግዚአብሔር እንደተሰጠና የተጻፈ ትዕዛዝ ከመኖሩ በፊት ለሕዝቡ በአደራነት እንደታዘዘ እንገነዘባለን (ዘፍ 17) ።
የትውፊት ጥቅሙ
(1) መጽሐፍ ቅዱስ’ን ራሱን ልናውቅ የቻልነው በትውፊት በኩል ነው።መለኮታዊ መጽሐፎቹ እኛ ዘንድ የደረሱት በትውፊት በአደራ እየተላለፉ ነው። በትውፊት ባይሆን ኖሮ ልናውቃቸው ወይም ከሌሎቹ ልንለያቸው ባልቻልንም ነበር። የተቀደሰው የአባቶች ጉባኤ ነው የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ዝርዝር ለይቶ ያሳወቀን።
(2) በትውፊት ነው የቤተ ክርስቲያን ቅርስ፣ ሥርዓትና የአምልኮ ወግ የደረሰን።
(3) ትውፊት ነው ጤናማውን ትምህርት ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ያስተላለፈልን። መጽሐፍ ቅዱስን እያንዳንዱ ሰው እንደ ዕውቀቱ እንዲተረጉም ተትቶ ቢሆን ኖሮ በ‘አንዱ ሃይማኖት’ ብዙ ቡድኖችና የተለያዩ ክፍልፋይ ቤተ እምነቶች በተፈጠሩ ነበር። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሲሆን፣ የአተረጓጎሙ ጉዳይ ግን ሌላ ነውና።
(4) ትውፊት አንዳንድ እምነቶችንና ትምህርቶችን አቆይቶልናል። ለምሳሌ፦
❖ እሁድን ማክብርን
❖ መስቀል ማማተብን
❖ የአንድ ለአንድ ጋብቻን
❖ በሞት ለተለዩቱ መጸለይን
❖ በያንዳንዳቸው የክህነት ማዕረጎች የሚከወኑትን ሥራዎች ቅደም ተከተል ያቆየልን ትውፊት ነው።
ተቀባይነት ያለውና ተቀባይነት የሌለው ትውፊት
‘ትውፊት’ን የሚጥሉቱ ተቃውሟቸውን የሚገነቡባቸው ሰበቦች ጌታ ትውፊትን የጣለባቸው ሁለት ጥቅሶች ናቸው። እነርሱም፦“እናንተስ ስለ ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ምን ትተላለፋላችሁ?” (ማቴ 15÷3) በማለት ጻፎችንና ፈሪሳውያንን የወቀሰበት እንዲሁም አንዳንድ የተሳሳተ ወጋቸውን ያወገዘበት (ማቴ 15÷4-6) ናቸው።
ሐዋርያው ለቆላስይስ ሰዎች “እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ” (ቆላ 2÷8) ያለውንም ሰበብ አድርገው ይጠቀማሉ።
ስለ ትውፊት ስንወያይ ግን በሰው ስለተመሠረተ ስለከንቱ ወግ ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትና ከመንፈሱ ጋር ስላልተጣጣሙት እንዲሁም ጌታ መሻራቸውን ስለገለጻቸው ማለታችን አይደለም። ከሚከተሉት ጋር የሚስማሙትን ጤናማ ትውፊት ማለታችን ነው።
(1) በትውፊት ተላልፎ እኛ ዘንድ ስለደረሰው የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት
(2) የሐዋርያት ትውፊት ማለትም ከትውልድ ወደ ትውልድ በአደራ የተላለፈው የሐዋርያቱ ትምህርት
(3) የቤተ ክርስቲያን ትውፊት፤ ያም ማለት ከቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ አስተማሪዎችና የእምነት አርበኞች የተረከብነውን እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጉባኤ ቀኖናና ወግ እንዲሆን የተደነገገውን ማለታችን ነው።
ይህ ታዲያ ወደ ሚቀጥለው ነጥብ ይወስደናል።
የቤተ ክርስቲያን ሥልጣን ለማስተማርና ሕግን ለመደንገግ
ይህ ሥልጣን የተሰጠው በጌታ በራሱ ለአባቶቻችን ለሐዋርያቱ ነበር። እንዲህ በማለት:-“እውነት እላችኋለሁ፥ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል” (ማቴ 18÷18)። ቤተ ክርስቲያን ይህን ሥራዋን የጀመረችው የመጀመሪያውን የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ በ45 ዓ.ም ባደረገችበት ጊዜ ነበር። ጉባኤው አሕዛብ እምነትን ስለመቀበላቸው ተወያየበት፣ ሐዋርያቱም ለአህዛቡ እንዳይከብድባቸው “ለጣዖት ከተሠዋ፥ ከደምም፥ ከታነቀም፥ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና፤ ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ” (ሐዋ 15÷ 28፣ 29) በማለት ወሰኑ።
ስለዚህ ጌታ ለካህናት ለማስተማር፣ ደምብንና ቀኖናን ለማውጣት በሰጣቸው በዚሁ ሥልጣን መሠረት በየሰበካውና በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያን ደረጃ ተከታታይ ቅዱስ ጉባኤዎች ተደርገዋል።እነዚህ ጉባኤዎች ትምህርቶችን፣ ውሳኔዎችንና ሥርዓቶችን ለቤተ ክርስቲያን አኖሩልን። እነዚህም ከቤተ ክርስቲያን ትውፊት ተካተቱ።
ትውፊት ጤናማ የሚባልበት ሁኔታ
(1) ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የሚጋጭ መሆን የለበትም (ገላ 1:8)
(2) ሌሎቹን የቤተ ክርስቲያን ትውፊቶችን መቃረን የለበትም
(3) አብያተ ክርስቲያን ሊቀበሉት ያስፈልጋል
ሁሉም ትውልድ በቀደሙት ትውልዶች ያልነበሩ አዳዲስ ነገሮች እንደሚገጥመው የታወቀ ነው።ሰዎች በሃሳባቸው ግራ እንዳይጋቡ ወይም ስህተቱን ከትክክለኛው ለመለየት እንዳይደናገራቸው፤ ስለእንደነዚህ ዓይነት ጉዳዮች ያለው ሃይማኖታዊ ዕይታ እንዲታወቅ ይፈለጋል። ምክንያቱም ሰው ሁሉ የሃይማኖት ሕግጋትን ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈውን ያውቃል ማለት አይደለምና። ኤልያስ አረገ
ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን በትምህርቷ በኩልና ሕግን በማውጣት ሥልጣኗ በመጠቀም በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ የሃይማኖትን ሃሳብ ታቀርባለች። መጽሐፍ ቅዱስ ሕግን ከካህኑ አፍ ይፈለግ (ሚልክ 2፣ 7) ይላልና ትውልድ ትውልድን ሲተካ እነዚህ የቤተ ክርቲያን ትውፊት ሆነው ለትውልዶች ሁሉ ይደርሳሉ።
ሐዋርያቱ ትውፊት እንዲጠበቅ አዘዋል
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እንግዲያስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጸንታችሁ ቁሙ፥ በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ወግ ያዙ።” (2ኛ ተሰ 2÷15) ደግሞም “ወንድሞች ሆይ፥ ከእኛ እንደ ተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለ ሥርዓት ከሚሄድ ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን።” (2ተሰ3÷6) ብሏል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎችም “ወንድሞች ሆይ፥ በሁሉ ስለምታስቡኝና አሳልፌ እንደ ሰጠኋችሁ ወግን ፈጽማችሁ ስለ ያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ።” (1 ቆሮ 11÷2) በማለት ጽፏል።
ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን መጽሐፍ ቅዱስን ሲተርጉሙ ስለ ‘ወግ’ የሚያረጋግጠውን (በቤሩት የአረብኛው ትርጉም ነው) “ወግ” የሚለውን ቃል “ትምህርት” ብለው ተርጉመውታል ብለን ስንናገር እያዘንን ነው። በዚህ ትርጉማቸው ስለ ወግ የሚያረጋግጠውን ጥቅስ (ክፍል) ሽረውታል። ‘ወግ’ ብለው የሚተረጉሙት የሚያስከፋ ሆኖ የተገኘውን ብቻ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ወግ ደግሞ ቀድሞውንም ቢሆን በቤተ ክርስቲያን ተቀባይነት አልነበረውም።
እኛ ያላደረግነው ሁሉ ልክ አይደለም ካላልን በስተቀር
ምንም እንኳ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ‘ትውፊትን ቢክዱም እነርሱ ራሳቸው የራሳቸውን ‘ትውፊት’ አቁመዋል። በአንድ በኩል ሥርዓትን ሲክዱ በሌላ በኩል ደግሞ የራሳቸውን ሥርዓት እያቆሙ ነው። የሚደገሙ ጸሎቶችን ቢቃወሙም የሚያሰሙት የራሳቸው ጸሎት፣ ሹመትን በሚሰጡበት፣ በጋብቻ ፣ በጥምቀት፣ በቀብር ጊዜ የሚያነቡት ቋሚ ንባብ አላቸው። የራሳቸውን ትውፊት ይጠብቃሉ፤ ከእነርሱ ጋር የማይስማማውን የሌሎችን ግን ይክዳሉ። ትውፊት የከበረ ቅርስ ነው። እናም ይህን ያጣች ማንኛዋም ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ውድቀት ይሆንባታል።ነገሮችን በየመረጡት መንገድ የሚተርጉሙትንና የሚያስተምሩትን የምትከላከልበት ታሪክና ደምብ የሌላት ቤተ ክርስቲያን ትሆናለች።
Comments
Post a Comment