ለ ምን ትጮህብኛለህ? አሁን ብዙም አልቆየሁም። ዳላስ በቶሎ ተመልሼአለሁ። በዛሬው የዳላስ ቆይታዬ በላፕቶፔ ላይ አንዳንድ ነገሮችን ለመሥራት ካረፍኩበት ቤት አቅራቢያ ካለ አንድ ስታርበክስ ተገኝቼአለሁ። ታዲያ ሌላ ጊዜ ስታርበክስ ስቀመጥ ልብ ያላልኩትን አንድ ነ ገር በዚያ ልብ አልኩኝ። ለካ ‘ስታርበክስ’ የማይመጣ የሰው ዘር ዐይነት የለም። ይመጣል፥ቡናውን ያዛል፥ይዞ ይወጣል። ወይም እንደኔው ሊጠጣ ይቀመጣል።ሌላም ይመጣል ፣ እንዲሁ፤ አያቋርጥም። ኢትዮጵያኖቹን ጨምሮ ላቲኖዎች ፥ የሩቅ ምሥራቅ ዝርያዎች ፥ ነጮች፥ አልፎ አልፎ ጥቁሮችና የመኻከለኛው ኤስያ ሰዎች ሁሉ ይመጣሉ። እዚህ ስታርበክስ ተቀምጠው ቡናቸውን ከሚጠጡት መኻል የኢትዮጵያውያንና የሩቅ ኤስያ ሰውን የሚመስል መልክ ያላቸው ይበዛሉ። በየቦታው ፈንጠርጠር ብለው በግል ላፕቶፖቻቸው የሚሠሩ፣ “ጥበበኛውን ስልካቸውን” በሚገባው ቋንቋ የሚያነጋገሩ ያታያሉ ። ልማዳቸው ነው መሰለኝ የሩቅ ምሥራቅ ሰው መልክ ካላቸው ሰብሰብ ብለው ካርታ የሚጫወቱም አሉ። ሳንቲም ሲያወጡ ስላላየሁ ቁማር አይመስለኝም። ጊዜ ማሳለፊያ ነው። የሚያልፍ ጊዜ በአሜሪካ ማግኘታቸው ያስደንቃል! አይደል? የእኛ ሰው ግን በጠረጴዛ ዙሪያ ተኮልኩሎ ያወጋል። በትግርኛ ወይም በኦሮምኛ የሚናገረው ተቀምጦ ሲያወራ አልሰማሁም ። የሚያዘውን አዝዞ ይዞ ውልቅ ነው የሚለው። ይህን የለየሁት በስልክ ከሚያወራው በሰማሁት ነው። ጠረጴዛውን ከብበው ሲያወሩ የማየውና እየሰማሁ ያለሁት አማርኛ ተናጋሪዎቹን ነው። ወሬያቸውም “ ቦለቲካ” ነው። «አይ የእኛ ነገር ይገርማል!ሁሌ ቦለቲካ! መቼ ይሆን የምንገላገ...