Skip to main content

ለምን ትጮህብኛለህ ?


ምን ትጮህብኛለህ?

    አሁን ብዙም አልቆየሁም። ዳላስ በቶሎ ተመልሼአለሁ። በዛሬው የዳላስ ቆይታዬ በላፕቶፔ ላይ አንዳንድ ነገሮችን ለመሥራት ካረፍኩበት ቤት አቅራቢያ ካለ አንድ ስታርበክስ ተገኝቼአለሁ። ታዲያ ሌላ ጊዜ ስታርበክስ ስቀመጥ ልብ ያላልኩትን አንድ  ነገር በዚያ ልብ አልኩኝ። ለካ ‘ስታርበክስ’ የማይመጣ የሰው ዘር ዐይነት የለም። ይመጣል፥ቡናውን ያዛል፥ይዞ ይወጣል። ወይም እንደኔው ሊጠጣ ይቀመጣል።ሌላም ይመጣል ፣ እንዲሁ፤  አያቋርጥም። ኢትዮጵያኖቹን ጨምሮ ላቲኖዎች ፥ የሩቅ ምሥራቅ ዝርያዎች ፥ ነጮች፥ አልፎ አልፎ ጥቁሮችና የመኻከለኛው ኤስያ ሰዎች ሁሉ ይመጣሉ።

 

እዚህ ስታርበክስ ተቀምጠው ቡናቸውን ከሚጠጡት መኻል የኢትዮጵያውያንና የሩቅ ኤስያ ሰውን የሚመስል መልክ ያላቸው ይበዛሉ። በየቦታው ፈንጠርጠር ብለው በግል ላፕቶፖቻቸው የሚሠሩ፣ “ጥበበኛውን ስልካቸውን” በሚገባው ቋንቋ የሚያነጋገሩ ያታያሉ ። 

 ልማዳቸው ነው መሰለኝ የሩቅ ምሥራቅ ሰው መልክ ካላቸው  ሰብሰብ ብለው ካርታ የሚጫወቱም አሉ። ሳንቲም ሲያወጡ ስላላየሁ ቁማር አይመስለኝም። ጊዜ ማሳለፊያ ነው። የሚያልፍ ጊዜ በአሜሪካ ማግኘታቸው ያስደንቃል! አይደል?


የእኛ ሰው ግን  በጠረጴዛ ዙሪያ ተኮልኩሎ ያወጋል። በትግርኛ ወይም በኦሮምኛ የሚናገረው ተቀምጦ ሲያወራ  አልሰማሁም ። የሚያዘውን አዝዞ ይዞ  ውልቅ ነው የሚለው። ይህን የለየሁት በስልክ ከሚያወራው በሰማሁት ነው። ጠረጴዛውን ከብበው ሲያወሩ የማየውና እየሰማሁ ያለሁት  አማርኛ ተናጋሪዎቹን ነው። ወሬያቸውም  “ ቦለቲካ” ነው። 


«አይ የእኛ ነገር ይገርማል!ሁሌ ቦለቲካ! መቼ ይሆን የምንገላገለውና ሌላ ወሬ የምናወራው ? ስለ እግር ኳስ ጨዋታ እንኳን  ማውራቱ ዛሬ ቀረ።ያ እንኳ “እንኳንም የቀረ! “ የባዕድ አገር ቡድንን እንደራሳችን ቆጥረን የምንወዛገብበትና ጊዜያችንን የምናባክንበት ምክንያት አይታየኝም ነበር። ባይሆን ሩጫውን ጠበቅ አድርጎ መያዝ ነው።» የሚል ዐሰብኩና ጻፍኩት


 ስለ እግር ኳስ በጻፍኩት የሚቀየሙኝ  ብዙ ሊኖሩ እንደሚችሉ ገመትኩና ደንገጥ አልኩኝ። 


«አንድ ዘመን እኔም እንደዛው ነበርኩ። የማልረዳቸው አይደለሁም። ላሳዝናቸው አልተናገርኩም።የምንወጣው ቅድሚያ ኅላፊነት  ስላለ ያንን ስለመወጣት ለመጨዋወቱ  ቅድሚያ እንድንሰጥ መምከሬ ነው። ያልጠየቁኝን ምክር እየሰጠሁ በመሆኑ ይቅርታ ያድርጉልኝ” በማለት ራሴን ከድንጋጤዬ አረጋጋሁት።


ወደ ጀመርሁት የቦለቲካ  ወግ ተመለስኩኝ፦ታዲያ  ቦለቲካው የከረረ ይመስላል።ዛሬ ሦስት ነገሮች ተገጣጥመውበታል- የሱዳኑ የእርስ በእርስ ጦርነት- የፋኖና የአማራ ልዩ ኃይል መሳደድ- የቪክቶሪያ በተባለው የሰላም ስምምነት ሳቢያ  መሞጋገሱ -የዚህን ሰሞን ሁነቶች ናቸው። የኢትዮጵያውያኑ ወጋቸው በነዚህ ዙሪያ ነበር።የሱዳኑን የእርስ በእርስ ጦርነት፣ የፋኖውና የአማራ ልዩ ኃይልን በተመለከተ ያነሱት በየማህበራዊ ሚዲያ ከሰማሁት የተለየ አልነበረም።


የሱዳኑን ጦርነት ማን ያሸንፋል? የትኞቹ አገሮች ተሳትፈውበታል? ኢትዮጵያዊኖቹ እንዴት ይሆኑ? ማን ቢያሸንፍ ለማን ይበጃል የሚሉ ናቸው? እንደ ወገኖቻቸው አይተዋቸው ነው መሰለኝ ስለ ሱዳኖቹ በደረሰባቸው መከራ ከንፈር መጠዋል። ከዚህ ያለፈ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ የተረዱ ይመስላል።


ስለ ፋኖና  የአማራ ልዩ ኃይልም ያልሰማሁትን  አዲስ ነገር ያላወሩ ቢሆንም ስሜታቸው ግን የጋለ መሆኑ አስደንቆኛል። ሲያወሩ የፊታቸው ገጽታ ተኮሳትሮ ነው።


አንደኛው ፋኖዎቹ  የት እንደታሠሩ እየጠቀሰ ተናገረ፦

 «እስር ቤቶችን ሰብሮ ፋኖዎችን ማስለቀቅ ያስፈልጋል» አለ እጁን ጨብጦ አየሩን  በቡጢ እያቀመሰ።


ምሳሌ እያቀረበ፦ «ቢፈቱም መገደላቸው አይቀርም።  ለማንኛውም ልዩ ኅይሉም ያልተያዙት ፋኖዎችም  ትጥቅ መፍታት የለባቸውም» ሁለተኛው ቀጠለ፣ አመልካች ጣቱን በመቀሰር እያወዛወዘ


«የአማራ ህልውናው ሳይረጋገጥና ሕጋዊ ጥያቄዎቹ ሳይመለሱ ትጥቅ ማስቀመጥ ራስን መግደል ነው። አብዝቶ መሰልጠንና መታጠቅ እንጂ የምን ትጥቅ መፍታት ነው?» ሦስተኛው ድምጹን ከፍ አድርጎ አስረገጠ (የመናገር ተራ እንዳይወሰድበት የቸኮለ ይመስላል)


አራተኛው ሰው ቀጠል አደረገ ፦«የኦሮምያ ልዩ ኃይል ሳይፈታ እንዳውም በትጥቅም በስልጠናም እየደረጀ ማን ሞኝ አለ የሚፈታ!» (ከንፈሩን በመንከስ)

‹‹ፋኖና የዐማራ ልዩ ኃይሉ ለመላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሑረሰቦችም ዋስትና ናቸው» የመጀመሪያው ሰው ሁለተኛ የመናገር ዕድሉን ወሰዶ ተናገረ- በተስፋና በኩራት የተሞላ ይመስላል።ፊቱ በፈገግታ ፈካ።


« ደግሞ  “ልዩ ኃይሉ” ወደ ክልል፣ ወደ ፌደራል ፖሊስ ፣ወይም ወደ  መከላከያ መግባት አለበት" ይባልልኛል እኮ። ያንን እሺ ብሎ መቀበልማ  የኦሮሚያ ብልጽግና አሽከር ሁን ማለት ነው። እንዴት ይደረጋል?» አለ ዝም ብሎ ቆይቶ የነበረው አምስተኛው ሰው፣ መሬቱን በጫማው እየደቃ።ሌሎችም ሰዎች በአካባቢው መኖራቸውን የዘነጋ ይመስላል። ረበሸ


«አማራ ቀድሞ ያደርግ እንደነበረው መንግሥትን ማመን፣ ይጠብቀኛል፤ ፍትሕን ያሰፍነኛል ብሎ መጠበቅን  ትቶ ራሱን በራሱ የሚረዳበት ዘዴ ይቀይስ ፣ አይታለል» ሲል አስጠነቀቀ ጀርባውን ሰጥቶኝ የነበረው ስድስተኛው ሰው።


የመጀመሪያው ሰው ስለተፈናቀሉት ብዛት፥ ቤታቸው ስለፈረሰባቸው፥ የሁኔታቸውን አሳዛኝነት ተረከና እንደማልቀስ ቃጣው። ትንሽ ቀደም ቀደም ይላል። ስሜቱ የሚነካ ዐይነት ሰው ሳይሆን አይቀርም።ልበ ደንዳና አይመስልም።


ሁሉም «በማዕከላዊ መንግሥት የሚታዘዝ እንድ ወታደራዊ ሠራዊት ብቻ ነው  አንድ አገር ሊኖረው የሚገባውና ስለዚህ ልዩ ኃይል የሚባል መኖር የለበትም» የሚለውን ክርክር ሳይሰሙ አልቀረም። በይፋ የተደመጠ ነውና። ይሁን እንጂ ዐማራው ጥበቃ የሚያደርግለት፥ ከለላ የሚሰጠው መንግሥት እስከሌለው ድረስ፣ ችግሩን ለማቅለል ራሱን በወታደራዊ አቅም ጭምር ማደራጀት አለበት ብለው የተስማሙ ይመስላል። “ወታደራዊ ኅይል መንግሥት ብቻ ይኑረው” የሚለው ሚዛን የደፋላቸው ሙግት አይመስልም።በጭውውታቸው መኻል እንዳውም አላነሱትም።


ሁሉም ሲናገሩ ዐማራው በአጠገባቸው ሆኖ የሚሰማቸው ሳይመስላቸው አልቀረም። ምኞታቸው እነርሱ ስለተወያዩ  ሊሳካ የሚችል መሆኑን ይገምቱ እንደሆን እንጃ።  

<<ብቻ እዚያው  ሜዳው ላይ ያለው ፋኖና  ዐማራው ተደጋግፎና ተባብሮ እነርሱ የሚሉትን ካደረገ ያኔ የተመኙት ይደርስ ይሆናል። አለበለዚያም ጨዋታቸው እንዳው ቡና ማጣጪያ ወሬ ነው» አልኩኝ ባለሁበት ተቀምጬ


ሌላ የገረመኝ ግን  ይኼን ሁሉ ሲያወሩ መሬት ላይ እየተደረገ ያለ ነገር ካለና ስለዚያ የሚያውቁ ከሆነ አንዳችም ነገር አለመተንፈሳቸው ነው። ከፋኖዎቹ ጋር ግንኙነት ኖሯቸው ስለዚያ አለመተንፈሳቸው ከሆነ የሚያስደንቃቸው  ነው። “ሚስጢር እኮ  የስታርበክስ  ቡናን መፍጨት አይደለም"።


ደግሞም በሆዴ አማኋቸው፡-  በእነርሱ በኩል ሊያደርጉ ስለሚችሉትና ስለሚገባው ነገርም ትንፍሽ አላሉም።ጉዳዩ እውነት  እንደዚህ የሚያንገብግባቸው ከሆነ መፍትሔውን ስለምን ከሌሎች ብቻ ይጠብቃሉ? ራሳቸው ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ስለምን አይወያዩም? ለወሬ ምን ፍሬ አለው?» አልኩና 

«እንዳውም ተነስቼ ይቺን ጥያቄ ጣል ላድርግላቸው ይሆን?» ተንቀሳቀስኩ። ግና እንዴት ይሆናል? አላውቃቸው አያውቁኝ!


ከንግግራቸው መኻል ሦስተኛው ሰው ስለሽምግልና የተናገረው ግን ተመችቶኛል። <<ሽምግልናን አምኖ መታረቅ አደጋ አለው >>አለ ።የአገር ሽማግሌዎች እንዲያግባቡ ከመንግሥት በኩል ወደ ፋኖዎቹ ሊላኩ ነው መባልን ሰምቶ መሆን አለበት።ይኼኛው ንግግር ዐሰብ እንዳደርግና ድምዳሜ ላይ እንድደርስ አነቃኝ።


   «በአንደኛው ወገን ላይ ብቻ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችል ወይም የሚፈልግ ሽማግሌ ተጽዕኖ ሊያሳድርበት ለማይችለው ወይም ላልፈለገው ወገን መልዕክተኛ እንጂ አስታራቂ አይሆንም። እንደ መልዕክት የሚታየው የዚህ ዐይነት ሽምግልና በጥንቃቄ ሊመረመር ይገበዋል። መልዕክቱ በጎ ምክር

ወይም ክፋ ምክር ወይም በጎ መስሎ ክፋ ምክር ሊሆን ይችላል።>> አልኩኝ። አዎን ያን ዕለት በዋለው የኅሊና ችሎቴ ይኸንን ብይን ሰጠሁኝ።


እነዚያ ኢትዮጵያኖች አሁን ወደ የጉዳያቸው መሄጃቸው ደረሰ መሰለኝ ብድግ ብድግ አሉ።


ያን ጊዜ «ራሳቸው ለመፍትሔው ስለሚያዋጡት ነገር ባይነጋገሩም ስለጉዳዩ እያነሱ መነጋገራቸው እኮ የተሻለ ነው » አልኩ፦ መነጋገራቸውን በበጎ ጎኑ አያየሁላቸው። «ዛሬ እንዲህ ተግባብተው ካወሩ ነገ ተማምነው ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ መፍትሔ የሚያበረክት  ማኅበር አቁመው ሊሠሩ ይችላሉ። ደግሞስ በግላቸው እያደረጉ ያሉት ነገር እንዳለ እኔ የት አውቄ? ይልቁንም ስንቶቹ የኢትዮጵያ ልጆች አሉ በየቦታው አፈናንና በደልን እየሰሙና እያዩ ስሜታቸውን የማይገልጹ--- ድምጻቸውን አጥፍተው “ቀን እስኪያልፍ የአባትህ  ባሪያ ይግዛህ” ብለው ተሸሽገው ያሉ?”--- ሁሉ ነገር መልካም እንደሆነ ነገር አሸሸ ገዳሜ የሚሉትስ- ቁማር ቤት የሚውል ወጣት?- ሞራል የሚያላሽቁ ነገሮችን ሲያይና ሲያወራ የሚያድር - ችግር እስከመኖሩም እንኳ ለማሰብ የማይፈልግስ? ------ በራሴና በቤተሰቤ ላይ ካልመጣ እኔ ምን አግዶኝ የሚል ሞልቶ አይደል? ----አሸናፊው ይግዛኝ ብሎ ለመገዛት ተስፋ ቆርጦ የተቀመጠስ? ኧረ እናንተዬ የባሰም አለ፤ ለአፋኞቹና ለበዳዮቹ የሚሠራና የሚሟገትም ሞልቷል!» (ትንሽ ህሊናዊ አሰሳ አደረግሁ።)


"ሆ ሆ የቀበጡ ዕለት ሞት አይገኝም አሉ" አልኩ በመቀጠል። ደግሞ ሲያቀብጠኝ እንዲህ ዐይነት አቃቂር ላውጣ!ማህበርዊ አንቂዎች ሲቀባበሉኝ ታየኝ። ሕዝቡ ያለበትን ሁኔታ የት አውቆ ነው የሚለፋደደው? --እርሱ ዲያስቦራ ምን አለበት የስታበክ ቡናውን እያጣጣመ የማክዶናልድ ሐምበርገሩን እየቀረደደ ይቀባጥር እንጂ - ሌላው ስለሚያደርገው ነገር ምን ያገበዋል አርፎ ሥራውን እየሠራ አይቀመጥም---- ምን ዐይነቱ ቂላቂል ነው፣ ሁሉ እንደ እርሱ እንዲያስብ ይፈልጋል? --- ዘረኛ--- በሕዝብ ምርጫ ያሸነፈ መንግሥትን ማውረድ የሚቻለው በሕዝብ ምርጫ ብቻ ነው። እኛኮ እንደርሱ ዐይነቱ እየተንጫጫ አገሪቱን ወደ ፊት እያስፈነጠርን ነው። ይህ እንዴት አይገባውም ?ደነዝ ! ደደብ!፣ አህያ ምን ይላል? ጭቃ፣ መሃይም ደንቆሮ እከክ። በታሪካዊ ጠላቶቻችን የተገዛ! ። አዎ እንዲህ እያሉ ሲቀባበሉብኝ ታየኝ። የሚገርመው አድማጩ የበለጠ የመሳደብ ችሎታ ያለውን እንዳሸናፊ ይቆጥራል ልበል? ተሳዳቢን ደጋግሞ ማዳመጡ ያስደንቃል። ሱስ ይሆንበታል ልበል?

እድለኛ ሆኜ ልክ ነህ የሚለኝ አገኝ ይሆን?

ለነገሩ ይኼ ሁሉ ስድብ የአማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ሰቆቃ እንዳይሰማ ለመጥለፍ የሚለቀቅ ሞገድ መሆኑ ነው።


ግን እኮ ይዋል ይደር እንጂ የመከራው ዶፍ የማይዘንብበት እንደማይኖር ይገነዘባልና ሁሉም በየቤቱ ዝናቡ እንዳያበሰብሰው ጃንጥላ ይዘረጋል፣ ጎርፉም እንዳይወስደው ቦይ ይቆፍራል በሚል ተስፋ ራሴን መታ መታ አድርጌ ለማጽናናት ሞከርሁ።


ታዲያ እነዚያ የኢትዮጵያ ልጆች በ“ሰላሙ ስምምነት የተነሳ ስለታየው መሞጋገስ" ጉዳይ ከመሳቅ ያለፈ ሳይነጋገሩ ነው ወደ የጉዳያቸው የሄዱት። ስለ መሞጋገሱ ሳይወያዩበት በመበተናቸው ትንሽ ታዝቤአቸዋለሁ።ቢነጋገሩ ኖሮ የሚወዛገበውን ዐሳቤን ያጠሩልኝ ነበር።


«የመንግሥትና የትግራይ መከላከያ ኃይሎች ሕዝብን ለጦርነት ገፋፍተው፣ ለእልቂት ማግደው፣ በግራና በቀኝ-በፊትና በኋላ ፣እስላም ክርስቲያን ሳይለዩ፣ ሴት-እርጉዝ-ልጅ-አዋቂ ሳይለዩ ሕዝብን ጨርሰው ፤ አስጨርሰው ፥ አካለ ስንኩል አድርገው በርካታ ሴቶችን ደፍረው አስደፍረው፣ የጋራ ሀብታችንን አውድመው ፣ ወደ ኋላ በብዙ ዓመት ወስደውን፣ ማህበራዊና ግብረገባዊ  ምስቅልቅልና ቀውስ አስከትለው ፍትሕ ሳይገኝ ሲቀር ራስ ያሳምማል። ደግሞ ዐይናቸውን በጨው ታጥበው ተመልሰው እነርሱ የሰላም ሰው ሆነው ትያተር ሲሠሩ ማየት ራስ ምታቱን  “በፓናዶል” ወደማይሻል ደረጃ ያባብሰዋል። ለብሔር ብሔረሰቦች ምን ዐይነት ምሳሌ ነው ያስቀመጡላቸው? እነርሱ በሄዱበት የአመጽ ሥራ ይሂዱን? »  በአንድ በኩል ይኸንን አሰብኩ።


በሌላ በኩል ግን «በእሳት የተቃጠለ በእሳት አይጫወትም እንዲሉ እነዚህ ሰዎች እሳቱ ለብልቧቸዋልና ለወደፊት ጦርነትን ኣያስቧትም ። መልካም ነው፣ ያለፈውን እንተወው። ዋናው የወደፊቱ ነው ። ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራም » በማለት ተረጋጋሁ። ይሁን እንጂ ያለፈ ታሪካችን ያንን እንደማያስተምረን አስታወስኩና «በአፌ  ውኃ ይሙላበት፣ እንዳፌ ያድርግልኝ» ብዬ በጎ ከመመኘት ያለፈ እንደማይሆን ትንሽ ቆይቶ ታየኝ። ለማንኛውም እነዚያ ኢትዮጵያኖች ስለዚህ ሲነጋገሩ ሰምቼ ቢሆን በእዚህ መንታ መንገድ ላይ የቆመ ዐሳቤን ባስተካከልኩ ነበር አልኩኝ።


ታዲያ እንዲህ ጆሮዬን ጣል አድረጌ፣ ክብ ሠርተው ቦለቲካ የሚያወጉትን ኢትዮጵያኖች እያዳመጥኳቸው ፥ አልፎ አልፎ ፌስ ቡክን አይ ነበርና  በዚህ መኻል በነቀምቴ ምስጢራዊ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናግረውታል የተባለውን ከፌስ ቡክ አነበብኩ።በአጭሩ ዐሳቡ «ዐማራውን ለዘለዐለም አንበርክከን እንገዘዋለን»ነው የሚለው። ከልባቸው ይሁን ወይም የአካባቢውን ሕዝብ ድጋፍ  ያስገኝልኛል ብለው የተናገሩት ይሁን እኔ አላውቅም። የአካባቢው ሕዝብ በዚህ ንግግራቸው ይደግፋቸዋል ብዬ ግን አላምንም።እንዴት አድርጎ? [በሕይወት ያሉትና ለሁሉ ተቆርቋሪ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አልጋ ወራሽኮ ግማሽ ጎናቸው የወለጋ ኦሮሞ ነው ይባላል]። ያንን ስለተናገሩ የአካባቢው ሕዝብ ዶ/ር አብይን ይደግፋችው አይመስለኝም።የሁሉ ጎሳዎች ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆነው እንደዚያ ማሰባቸው ግን ‘ሼም’ ነው» በማለት በንግግሩ አለመደሰቴን ተነፈስኩ።


«አግባብ እንዳልሆነ የተሰማኝ መሆኑን ለመናገር እንጂ “ዐማራን የምትለዋ ጨዋታ “የተበላች  እቁብ” መሆኗን አላጣኋትም።አንበርክኮ መግዛት በአማራ ጀምሮ የት ላይ ሊያበቃ ነው? አንበርክኮ የመግዛት ጅኒ አንዴ ከጠርሙሱ ከወጣ  እንዴት ይመለሳል? ያንተው ነኝ ብሎ የሚያባብለውን ዘር እንዲሁም የራሱን ሠራተኞች ሳይቀር  አንበርክኮ እንደሚገዛ ሳይታለም የተፈታ ነው።» አልኩኝ ለረዥም ጊዜ መቀመጤ እየታወቀኝ

ብቻ  ስሜቴን መደበቅ አልተመቸኝም።በንግግሩ ምክንያት ስሜቴ ስለተጎዳ  ኡኡ ማለት አማረኝ። «ኧረ ጌታ ሆይ ይኸንን ጉዳችንን ተመልከትልንና መዳኛችንን አፍጥንልን» ብዬም ወደ  አምላኬ በውስጥ ሰውነቴ ጮኩ።  ይኸው ነው! ሌላ  ምን ላደርግ እችላለሁ?  ያው እንደ ሁልጊዜዬ  ስለአገራችን ሰላምና ለመሬዎቿ የማስተዳደር ጥበብን እንዲሰጥልን እጸልያለሁ፤ እንጸልያለን ብዬም አሰብኩ። ይሁን እንጂ ትንሽ ቆይቶ ከየት እንደመጣ አላውቅም፦  “ለምን ትጮህብኛለህ? በትርህን አንሣ” የሚል ዐሳብ እንደ መብረቅ ብልጭታ ብልጭ አለብኝ።ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘሁት ዐሳብ ነው።አስታውሰዋለሁ። እቅጩን ምን እንደሚነበብ ለማየት በጥቅስ ማውጪያ ፈልጌ  ጥቅሱን አገኘሁት። ዘጸ 14፡15፥16 “ለምን ትጮኽብኛለህ? እንዲጓዙ ለእስራኤል ልጆች ንገር አንተም በትርህን አንሣ” ነው የሚለው። የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ቀደም ሲል ይኸንን ድምጽ ሰምቶ መሆን አለበት። መሪዎቹ በትሮቻቸውን አንስተዋል።ልጆቹም ማርና ወተት የምታፈሰውን አገራቸውን ለመውረስ እየተጓዙ ነው።[እነርሱ የሚከላከሉና ለኢትዮጵያውያን ኃላፊነት የሚሰማቸው ብሔርተኞች ናቸው።ለኢትዮጵያውያን ሁሉ በረከት ይዘው ይመጡ ይሆን?]


ተጻፈ  4/26/2023 (በአውሮፓውያኑ) በዳላስ::በዚህ [ ] ምልክት ያሉት በመጀመሪያው ጽሑፍ አልነበሩም።


Comments

Popular posts from this blog

Comparative Theology የነገረ መለኮት ንጽጽር (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት)/ በብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሲኖዳ ሳልሳዊ

 የነገረ መለኮት ንጽጽር  (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት): የወደደ  ሁሉ በነጻ እንዲጠቀምበት ተፖስቷል። ይሁን እንጂ መብቱ በሕግ የተጠበቀ ስለሆነ በየትኛውም መልኩ ለንግድ እንዲውል አልተፈቀድም። ልዩ ልዩ መግቢያ የሚለውን መጀመሪያ ካነበቡ በኋላ የተቀረውን በተመረጠው ቅደም ተከተል ማንበብ ይቻላል። ልዩ ልዩ መግቢያ   ጥምቀት   ትውፊት (ወግና ልማድ)   መካከለኝነት   ጾም የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ መንፈሳዊ ስጦታዎችና በልሳኖች የመናገር ስጦታ   ሥርዐት ንስሐ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ (1)  ድንግል ማርያምን ስለማክበር (2) ለጥያቄዎች መልስ (ሀ) ድንግሊትን ‘የወይን ግንድ (ተክል)’ና የ ‘ሕይወት በር’ የሚል ማዕረግ  ለምን እንሰጣታለን? (ለ) ወደ ድንግል ማርያም መጸለይ ትክክል ነው ወይ? (3) የድንግል ማርያም ድንግልና ዘላለማዊነት (4) ለተቃራኒ አስተያየቶች መልስ (ሀ) “የመጀመሪያ ልጇን” የሚለው ሐረግ (ለ) “ሚስትህ” የሚለው ሐረግ (ሐ) “አብረው ከመሆናቸው በፊት ጸንሳ ተገኘች” (መ) “የመጀመሪያ ልጇን እስክትወልድ አላወቃትም” (ሠ)  “ወንድሞቹ” የሚለው ሐረግ   የቅድስት ድንግል ማርያም  ክብሯ (1) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ድንግል እመቤታችንን አያከብሩም፤ ደግሞም እንድታማልድላቸውም (እንድትማልድላቸውም)  አይጠይቋትም።ከእነርሱ ወገኖች አንዳንዶቹ እንዲያውም ጫጩቱ ከተፈለፈለ በኋላ ዋጋ ከሌለው የዶሮ እንቁላል ቅርፊት ጋር እስከሚያመሳስሏት ይደርሳሉ።ይህ የተጋነነ ማቃለል የመጣው ምናልባት ሮሜዋውያን ካቶሊኮች የተጋነነ ማክበር ስለሚያከብሯት ለዛ ተቃርኖ ከማሳየት አዝማሚያ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን አንዱንም የእርሷን በዓል አያከብሩም።  (2) አንዳንዶቹ የፕሮቴስታንት ወገኖች ድንግል ማርያምን “እህታችን” ይሏታል። (3) በተጨማሪ አንዳንዶቹ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ጌታ ኢየሱስን በድንግልና ከወለደች በኋላ ከዮሴፍ ጋር ጋብቻዋን ፈጽማለች፤ የ‘ኢየሱስ ወንድሞች’  ወይም የ’ጌታ ወንድሞች’ ተብለው የተጠሩ ልጆችን ወልዳለች ይላሉ።  (4) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ቤተክርስቲያናችን ለድንግል እመቤታችን የሰጠቻቸውን አንዳንድ የማዕረግ ስሞችም ይቃወማሉ።  (5) ድንግልን ያለማክበራቸው አንዱ...

ከቄስ ( ዶ/ር ) ቶሎሳ ይልቅ

 አድማጭ ተመልካቾቼ አንደምን ከረማችሁ? የአብርሃም አምላክና አምላካችን የተመሰገነ ይሁንና እኔ ደህና ነኝ።"ከቄስ (ዶ/ር ) ቶሎሳ ይልቅ" በሚል ርዕስ ያዘጋጀሁትን  የሚከተለውን መልዕክቴን እንድትከታተሉልኝ በታላቅ አክብሮት እጠይቃችኋለሁ። ባንቱ ገብረማርያም ነኝ ከቄስ (ዶ/ር) ቶሎሳ ይልቅ           ቄስ (ፓስተር) ዶ/ር ቶሎሳ  ጉዲና የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን በአትላንታ/ጆርጂያ ፓስተር መሆናቸው በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ይመስለኛል። በበኩሌ የማከብራቸውም ሰው ናቸው። በወንጌላውያን መኻል ለበርካታ ዐመታት ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የተናገሩ፣ ያሳሰቡና የጸለዩ መሆናቸውን ሰምቼአለሁ።በነገዳቸው የተደራጁትን የወንዛቸው ልጆችን ወቀሳ ተቋቁመው ለመላው ኢትዮጵያዊ ሲጮኹ የኖሩ ናቸው።           ስለ እሬቻ የሰጡት ትምህርት እስከዛሬ እንደሞዴል የማየው ነው። እሬቻን እንዳይከተሉና እንዳያስፋፉ የአሁኖቹን የመንግሥት ዐላፊዎች የመከሩበትንም ጊዜ አስታውሳለሁ።           የወንጌላውያን ሽማግሌ ብቻ ሳይሆኑ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌ አድርጌ አያቸዋለሁ። ይህን መደላድል የማስቀምጠው ስለእርሳቸው ያለኝን አስተያየት ለማስታወቅና ይኸው ሐሳቤ የጸና መሆኑን ለማስጮህ ነው።አስተያየቴን አልጠየቁኝም፣ የሚጨምርላቸውም ሆነ የሚቀንስባቸው ነገር እንደማይኖርም ጠንቅቄ አውቃለሁ። መደላድሉን አስቀድሜ  ማስቀመጤ ወንድሞችንና እህቶችን “አይዟችሁ አትደንግጡ” ለማለት ያህል ነው። ...