ብፅዕት ማርያምን የማክበር ጉዳይ ማወኩ? በባንቱ ገብረማርያም አድማጭ ተመልካቾቼ፡ እንደምን አላችሁ ? ክብሩ ይስፋ የመድኃኒዓለም ! እኔ ደህና ነኝ ሰሞኑን የማርያም ሥዕል መቀደዱን ከማህበራዊ መገናኛ ተመለከትኩ። ስለዚያ ያለኝን አስተየየት እንደሚከተለው አቀርባለሁ። እንድትከታተሉት በታላቅ ትህትና እጋብዛችኋለሁ። በመጀመሪያ ስለ ማርያም ሥዕል ያለኝን ትውስታ ልንገራችሁ። በጎባ / ባሌ የአዝማች ደግልሃን ት / ቤት ተማሪ ነበርኩ ( ስሙ ተቀይሯል ) ። ይህ ታሪክ የሆነ ጊዜ የስንተኛ ክፍል ተማሪ እንደነበርኩ አሁን ተዘንግቶኛል። የዘጠነኛ ወይም የአሥረኛ ክፍል ተማሪየነበርኩ ይመስለኛል። በዚያን ዐመት በትምህርት ቤቱ የተማሪ ክበቦች ተቋቁመው ነበር።ታዲያ እኔም ከተቋቋሙት አንዱ ከነበረው ከመጽሐፍ ቅዱስ ክበብ ገባሁኝ። የክበቡ መሪ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ዩኒቨርስቲ ( ስሙ ተቀይሯል ) በብሔራዊ አገልግሎት የመጣ የኬሚስትሪ አስተማሪ ነበር። አንዱን ቀን መጽሐፍ ቅዱስን ሊያስተምረን አባላቱን ሚካኤል ጋራ ላይ ይዞን ወጣ ( አካባቢውን ለማታውቁት ሚካኤል ጋራ ከትምህርት ቤቱ ጀርባ የተቆለለ ጋራ ነው ) ። እዚያ ስብሰባ ላይ ነበር የማርያምን ሥዕል ያደለን።የሥዕሉ ትልቅነቱ የኪስ ቦርሳ ውስጥ ለማስገባት የሚያስቸግር ያህል ነበር።እጅግም ትልቅ አልነበረም ለማለት ነው። ት / ቤት ለዕረፍት በተዘጋበት ጊዜ ...