Skip to main content

የአማሮች አባት ኑዛዜ

 

 

የያን ሰሞኑ የጋዜጠኛ መዐዛ መሐመድና የመምህር ፋንታሁን ዋቄ ቃለ መጠይቅ ቀሰቀሰኝና ጻፍሁት። (share or forward)

የአማሮች አባት ኑዛዜ

               ዘመኑ ቆይቷል። የሚሆነው ነገር አይታወቅም በማለት ትልቁን-ዋርካ አባታቸውን- የአማሮቹን አባት- ተቀጣጥረው ሊጎበኙት  ሄደው ነበር።ታዲያ እነዚያ ሊጠይቁት የሄዱት ተወላጆቹ ዋርካውን ቀድሞ ያዩት እንደነበር ሆኖ አላገኙትም። ለወትሮ ደጅ ደጅ ሲል ፣ሲንጎራደድ ነበር የሚያገኙት።ያን እለት ግን አልጋ ላይ ውሏል። ሲያያቸው ደስ አለው።ሰላምታ ተለዋወጡ። ተነቃቅቶም  ቀና ለማለት ሞከረ። በወጉ ተቀምጦ ሊያጫውታቸው ፈለገና  ወገብ ከየት ይምጣ? ደጋግፈው  አስቀመጡት። ከዚያም ጉሮሮውን አጥርቶ ያናገራቸው ጀመር።እነርሱም ጸጥ ብለው ሊያዳምጡት ገቡ።

ዕድሜ ጠገብኩ አይባልም እንጂ ብዙ ዘመን ኖሬአለሁ።ይህን ያህል ዘመን እኖራለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር።ብዙ ትውልድ አሳለፍኩኝ። እንደ እኔ በዕድሜ የጠገቡ ያሉ አይመስለኝም አሁን ግን ክፉ ሰው - እርጅና መጥቶብኛል። አልጋ ላይ ከዋልኩ ሰነባበትኩ። ሕልፈተ ሞቴም  የደረሰ ይመስለኛል።የአብራኬ ክፋዮች፣ ልጆቼ፣ ዝርያዎቼ አስታውሳችሁኝ ልትጠይቁኝ ስለመጣችሁ ተባረኩ።ምሩቅ ሁኑ። ዳግመኛ ላታዩኝ ትችላላችሁና ዛሬ ትዝታዬንም ትውስታዬንም ላውጋችሁ። ኑዛዜ ብትሉትም ይሆናል አደራዬንም አሸክማችኋለሁ።አለ

"እሺ እናዳምጥሃለን!አባታችን። ንገረን አለ-ከመኻላቸው አንደኛው ልጅ።" ታላቃቸው መሆኑ ነው መሰለኝ።

አባትም ቀጠለ፦

«በልጅነቴ ዘመን የማደሪያና የመተዳደሪያ  ነገር አያሳስብም ነበር። መብል አይቸግርም። የዱር እንስሳ አድኖም ይበላል። ከዛፋም ፍሬ ለቅሞ በልቶ ጠግቦ ማደር ይቻል ነበር።መሬቱን ጫር ጫር አድርገው ቢዘሩትም እህል ይሆናል። እንስሳ ቢያረቡ መስኩ ሰፊም ለምለምም ስለነበር የሚግጠው ሞልቶለታል።የጣፈጠ ነገር ቢያምር ወደ ጫካ ወጣ ብሎ ማሩን ቆርጦ ማምጣት ነው።መድኀኒቱም ቅጠል በጥሶ ሥር ምሶ ይገኛል። ዋናው የሚፈለገው  ዘር  መተካትና ማብዛት ከጠላት የሚከላከልልህ ጋሻ ፣መመኪያ፣ መኩሪያ ወንድ ልጅ መውለድ ወይም  አማች ማምጣት ነበር።እኔም ታዲያ ያንን ብዬ በልጅነቴ ነበር 'ምሽት' ያገባሁት። ያገባኋት ልጅ ማህጸነ ለምለም ነበረች። ልጆችን ወለደችልኝ።በላይ በላዩ ወለደችልኝ። ጅግና ጅግና የሆኑ ወንዶችን፣ በቁንጅናቸውና በደም ግባታቸው  ከሰው ዐይን ያውጣችሁ  የተባሉ ሴቶች ልጆችን ወለደችልኝ።ሴቶቹን ሙያም ልቅም አድርጋ አስማረችልኝ። አጎቶቼ፣ አክስቶቼ ወንድሞቼና እህቶቼም አልቦዘኑ። እነርሱም ተራብተዋል።ግና ምን ያደርጋል (እናንተ እልደረሳችሁባትም) ክፉን ደጉን አብራኝ ያየች የልጆቼ እናት ጥላኝ አረፈችብኝ/ሞተችብኝ።"

ይኸን ሲናገር ሃዘን ተቀሰቀሰበት።አለቀሰ።ጠያቂ ተወላዶቹንም አስለቀሳቸው። ይሁን እንጂ የሚለውን ለመስማት ስለጓጉ ራሳቸውን አረጋግተው እርሱንም አረጋጉት።

ትንሽ ቆይቶም

"እኔም ብሆን እንግዲህ ወደ እርሷው መሄጃዬ ደርሷል" ብሎ ተከዘ። ጨዋታውን ለመቀጠል ፈልጎ ሊያወራ ቢሻ የት ላይ እንደነበረ ጠፋበት።ተደነጋገረው።

"የት ላይ ነበርኩ? ልጆቼአለ።

አንደኛው ስለ ትዳሩ ትዝታ እያወራ እንደነበር አስታወሰው።

"ጎሽ ልጄ " አለው ያስታወሰውን ልጅ እያየው።

"አዎ የትዳሬ ትዝታ ላይ ነበርኩ። ታዲያ ይኸውላችሁ እርሷን ወስዶ እኔን ግን ለጉድ አስቀምጦኛል፥ ጎልቶኛል ብል ይሻላል።አገር አልገዛሁም። ለዘመቻም ጋሻና ጦር አላነሳሁም። ግን ብዙ ነገር አይቻለሁ።

ከሚታወሰኝ አንዱ የማክዳ ነገር ነበር። ንግሥታችን በጣም ልባም ነበረች።የንጉሥ ሰለሞንን ዝና ትሰማ ኖሮ ኢየሩሳሌም ሄዳ ጥበቡን ቀስማ ተመለሰች።የሰለሞንን ጥበብ ጨምራ  በመመለሷ ደስ አለን። ይልቁንም በኋላ ምኒልክ ከእርሱ የወለደችው መሆኑን ያወቅን ጊዜ ደስታችን እጥፍ ድርብ ሆነ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኦሪት ሕግና ወግ ዘለቀን በቃ ምን አደከማችሁ፣ የእኛን ሰው እግሩን ከኢየሩሳሌም የሚያቆመው ጠፋ። የእኔ ልጆች ወደ ኢየሩሳሌም  ሲሄዱ ወደ ሁለተኛ ቤታቸው እንደሄዱ እየተሰማቸው ነበር። እንዳውም ራሳቸውን  እንደ እስራኤላዊ የቆጠሩም አልጠፋ።"

ሁለተኛው ልጅ ማክዳ በርካታ እስራኤላውያንና ታቦቱን ይዛ ነው የተመለሰችው የሚለውስ ወሬ እውነት ነው እንዴ? ብሎ ሊጠይቅ ፈለገና የአባቱን ጨዋታ ማደነጋገር እንዳይሆን ፈርቶ ተወው።

"ወደ እየሩሳሌም መሄድ እንዲህ  የተለመደ ሆኖ ስለነበር ነው  ከብዙ ዐመታት በኋላ ጃንደረባው ወደዚያው ተሻግሮ ሲመለስ የምሥራችን ይዞልን የመጣው። ክርስቶስ በስቅላት ሞቶ ከሙታን ስለ መነሳቱ ይህንንም ያደረገው ሊያድነን ስለመሆኑ  በንጉሡ ቤት ለነበሩት ተረከላችው። ለጊዜው ያመኑትና የተጠመቁት በዚያው  አካባቢ የነበሩ ልጆቻችን ነበሩ። ዘመን እየተቆጠረ ሲሄድ  ከሮማ ሕዝብ ጋር መናገድን ተከሎ  ተስፋፋና ይኸው ከእናንተ የምትበዙት ክርስቲያኖች ናችሁ።"

"የሚገርም ታሪክ ነው፣ አባባ! ታዲያ እስልምና ደግሞ እንዴት ገባ?” ብሎ ሦስተኛው ልጅ ጠየቀ። ጭውውቱን አደናግራለሁ ብሎ አልሠጋም።

"አይ የእኛ ነገር! መቼም በቀይ ባሕር በኩል የሚመጣ ደጉም ክፋም አያልፈንም። በአረብ አገር ነቢዩ መሐመድ ተነሳና እስልምናን ሲያሰተምር የአገሬው ሰዎች ተነሱበት።ከዚያ ሽሽት  በርከት ያሉ ቤተዘመዶቹ እኛ ዘንድ መጥተው ተጠለሉ።አንዳንዶቹማ ብዙ ዐመታት ቆይተው ነው ከነቢያቸው ጋር ተመልሰው የተቀላቀሉት።አሁን ተዘነጋኝ እንጂ የአንዳንዶችን ስም ሁሉ አውቅ ነበር። ታዲያ የአረብ ሰዎች ስደተኞቹን አሳልፎ እንዲሰጣቸው ንጉሣችንን ቢጠይቁትም እርሱ ግን እምቢ አላቸው። ያኔ ሁላችንም ንጉሡን አበጀህ አልነው። ስደተኖችን መቀበልና ማስተናገድ በጎ ተግባር አድርገን እናየው ነበርንና።ለዚህ ውለታ ነቢያቸው ተከታዮቹን'ሐበሻን በክፉ ዐይን እንዳታዩት' ብሏቸዋል ሲባል ሰምቼአለሁ።"

የእስልምና አነሳስ ሲወሳ አራተኛው ተወላጅ በሁለተኛው ሰው ጆሮ አንሾካሾከ።"ንጉሡ ሊሞት ሲቃረብ ሰልሟል ይባላል። ይህ ምን ያህል እውነት ነው ብለን እንጠይቀው?" አለ። ተጠያቂውም "ጥሩ ሐሳብ ነው! እስልምና እንዴት እንደገባ የጀመረውን ይጨርስና" አለው።

 'አማሮቹ አባት' ግን የሚያንሾካሹክትን ልብም አላላቸው።ንግግሩን ቀጥሏል።

"አያችሁ ከዚያ በኋላማ እስልምና በዐረብ አገር ተስፋፋ። እኛም ጋር  በንግድና በእጅ ጥበብ ሙያ ከአረቦቹ ጋር የመገናኘት መስመር ኖሮ ከዝርያዎቼ አንዳንዶቹ የሙስሊሞቹን ልማድና ሃይማኖት አነሡ።  በደጋው ጥቂት ሆነው በክርስቲያኖቹ መኻል ሰፈር አበጁ። ከቀይ ባህር ቅርብ በነበረው በቆላማው አካባቢ ከሰፈሩት ዝርያዎቼ ግን ከዋናዎቹ ንግድ መስመሮች በመቃረባቸው፣ አንዳንዶቹም ነጋዴዎች በመኻከላቸው በመስፈራቸው የእነርሱን ጠባይና ሃይማኖት የለመዱት በዙ። የአብርሃም ልጆች ሃይማኖት እንደዚህ ገብቶ የእኔ የአማራው ዝርያ በሃይማኖት በኩል ዥንጉርጉር ሆኗል። የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው እንደሚባለው ሆነ።"

"ታዲያ እንደዚህ ዥንጉርጉር ሲሆኑ በመኻከላቸው ግጭት ተፈጥሮ አያውቅም?" ጠየቀ ሦስተኛው። ያንሾካሾከው ግን ዝም አለ።ስለተቀደመና ይኸኛውን ወሬ መጀመርያ ልስማ ብሎ ሊሆን ይችላል። ብቻ አልጠየቀም።

"የዩዲት ጉዲት ነገር ብቻ አይነሣ።ከዚያ በስተቀር ከእኔ ከአማራው ተወላጅና ከቅርብ ዘመዶቼ በሃይማኖት የተነሣ የተጎዳዳንበት ነገር የለም። ሆኖም ውሽት ምን ያደርጋል? ነገሥታቱ ዝርያዎቼን በሃይማኖታቸው እኩል አድርገው አላዩልኝም። ከዚያ በስተቀር ዳኝነትን ስለሚሰሙ፥ ሽማግሌንም ስለሚያስገቡ፥እርቅን ስለሚያከበሩ በመልካም ጉርብትና ኖረዋል/ኖረናል። እንዳውም በየዘመኑ የነገሡትን  ነገሥታት እየተከተሉ ጋሻና ጦር ይዘው ድንበርን ከወራሪ በመጠበቅ፣ አገር በማቅናት አንድ ላይ ሲዘምቱ ኖረዋል። ከዝርያዎቼ አንዳንዶቹ ወንዶች ከዘመቱበት አካባቢው ሴቶች ልጆች እያገቡ፣ ከአካባቢው አንዳንዶቹ ወንዶችም የዝርያዬን ሴቶች እያገቡ እየተዋለዱ ተሰራጭተዋል። መሰራጨታቸውን እናንተም የምታዩት ነው።

በሃይማኖተኞች  መኻል ያለው ግብብነት ይህ ሲሆን መደበኛውና ትልቁ ችግር ግን በአልጋ ወራሾቹ መኻል የሚኖረው ግብ ግብ ነው። በውጊያ አሸንፎ ንጉሡ እስኪታወቅ ድረስ በልጆቼ መኻል የሚኖረው ጦርነት ከቤቷ ባለቤት ጋር ሁልጊዜም እንቅልፍ እናጣበት ነበር። በዚያ ፍልሚያ የራሴ ዝርያዎች፣ የአጎቶቼ፥ የአክስቶቼ ፥የወንድሞቼና የእህቶቼ ዝርያዎች ሁሉ መፈጀታቸው ሁልጊዜም ይቆጨኛል። ብልሃት ያጣ ነገር ነው። ንጉሥ በሞተ ቁጥር እርሱን ለመተካት ውጊያ ተለይቶን አያውቅም።ይኸን ሳነሳው ራሴን ያመኛል። ስለዚህ ባላወራ ይሻለኛል። እንዳውም ይኸን ልተውና አደራዬን ልንገራችሁ።" አለ ወሬውን ለመቀየር።

ጠያቂዎቹም ምንም እንኳ ስለ አልጋ አወራረሱ ምሳሌ እያነሳ መተረኩን እንዲቀጥልላቸው ቢፈልጉም መንገሽገሹን አይተው እሺ አደራውን እንስማ አባባ ቀጥል አሉት። ስለ ንጉሡ መስለም ሊጠይቁ ተስማምተው የነበሩቱም ሁኔታውን አይተው ይመስላል መጠየቁን ተውት።

"በንግግሬ መነሻ እንደነገርኳችሁ ትዳር የመሠረትኩበትን ምክንያት አውቃችኋል። እኔን የሚገደኝ ዝርያዬ እንደ ምድር አሸዋ እንደ ሰማይ ክዋክብት በዝቶ ብርቱና ራሱን የቻለ ሕዝብ ሆኖ እንዲወጣና እንዲኖር ነው። ስለዚህ ይኸን ምኞቴን ፈጽሙልኝ። እስካሁን እኔ በሕይወት ስላለሁ ተወላጆቼ ዝርያዎቼ በየቦታው ብትበታተኑም እኔን ለመጠየቅ ስትመጡ እርስ በእርሳችሁም ትገናኙ ትጠያየቁ ነበር።  ወሬያችሁንም ትሰማሙ ነበር። እኔ ከሞትኩም በኋላ ቢሆን ይኸንኑ አድርጉ። በልዩ ልዩ ምክንያት በአካል የበለጠ እየተበተናችሁ፥ እየተሠራጫችሁ መሄዳችሁም አይቀርም።ያን ጊዜ በሥፍራ ስለተራራቃችሁ ተለይይታችሁ ቅሩ ማለት አይደለም።ተገነኛኙ።ተሰማሙ።

ኑሯችሁንና  ሥራችሁን  የሚያቀል ብልሃት ፈልጉ፣ ፈልስሙ። ሥራን ከመሥራት አትለግሙ። አንድ የምጠላባችሁ ነገር አለ።  በሚሠራው የሥራ ዐይነት መነሻነት መናናቃችሁን አልወድላችሁም። ዝርያዬ ብርቱና ራሱን የቻለ እንዲሆን ሁሉም የሥራ ዐይነት ያስፈልገዋል። ስለሆነም የትኛውንም ዝርያዬን በሚሠራው ሥራ ዐይነት ሰበብ አትናቁ።

በመኻከላችሁ ያሉትን ድሆች አታጎሳቅሉ። በእነርሱ ላይ የትዕቢትን ነገር አታስቡ። ይልቁንም ራሳቸውን እንዲችሉ አግዟቸው። ዝርያዎቻችሁ ናቸው። እነርሱም ምክንያት ሳያበዙ ጠንክረው ይሥሩ።

በጎውን ወግና ልማዳችሁን እትልቀቁ።ይልቁንም ከጎረቤቶቻችሁ በጎ ወግና ልማድ ጋር አወራርሱ።

ዝርያዬ ብርቱና ራሱን የቻለ እንዲሆን ያለኝን ምኞት የሚያጨናግፍ እንዳይሳካለት በራችሁን ጠርቅሙ። ተመቻችታችሁ አትገኙ።በመኻከላችሁ ንፋስ አታስገቡ።

የሚበጅ ወዳጅነትን አጥብቁ። ጠላት ሆነው የሚነሱባችሁን ከተቻላችሁ ወገን አድርጉ።ነጣጥለውም ሆነ በጅምላ እስኪውጧችሁ ድረስ ግን አትዘናጉ፣ አትበለጡ።በየሰበቡ አትደንዝዙ።ንቁ ሆናችሁ ኑሩ። ብርታትንና ራስን መቻል ፊት ለፊታችሁ እዩ! እየሰማችሁኝ አይደል ልጆች?” አለ በመኻሉ እያዳመጡት መሆኑን ለማረጋገጥ

አዎ እየሰማንህ ነው፤ አባታችን ቀጥልልጆቹም ተጯጯሁ።

"አዎ አትበለጡ! በመኻከላችሁ ጠብ የሚያስነሳንና የሚዘራን አሸኩሻኪውንና መልቲውንም ፊት አትስጡት። ወደቤታችሁ አታስገቡት። ከእንደዚያ ዐይነቱ ጋር አብራችሁ አትቀመጡ።በእውነተኛው ተጸጽቶ ይቅርታ ቢጠይቅ ግን ከማኅበሩ ከመደባለቅ አትከልክሉት።

እግርና እግርም ይጋጫልና አንዳንድ ጊዜ ስትቃቃሩም ከጥንት ጊዜ አንስቶ እንደምናደርገው በሽምግልና፣በ እርቅና በዳኝነት ጨርሱ።

ወገኖቼ አይደሉም ብለው ለማጥቃት ከሚነሳባቸው ጋር ሙስሊሞች ሲጋጠሙ ክርስቲያንኖች አግዟቸው። እንዲሁም ወገኖቼ አይደሉም ብለው የሚነሳባቸውን ሲመክቱ ክርስቲያን ወንድሞቻችሁን ሙስሊሞች አግዙ።

ወገኖቼ ናችሁ ብለው ከክርስቲያን ወንድሞቻችሁ ነጥለው የሚያዩዋችሁን ሙስሊሞች አትስሙ። ወገኖቼ ናችሁ ብለው ከሙስሊም ወንድሞቻችሁ ጋር ሊነጥሉዋችሁ ለሚፈልጉ ከርስቲያኖች ጆሮ አትስጡ።

ማንኛችሁም ለበረከታችሁ ስትሉ ዝርያዬ ካልሆነ ጋር ብትተባበሩ የሚጎዳችሁ ካልሆነ በስተቀር ሌሎቻችሁን ቅር አይበላችሁ። ለእኔ አደራ ተጻራሪ ሲሆኑ ብቻ እንደ አራስ ነብር ሆናችሁ ሁላችሁም በአንድነት ተነሱ። ክርስትያን ወይም ሙስሊም ያልሆናችሁም በዚሁ ሐሳብ ኑሩ።አንዱ ሌላውን ያበረታታው እንጂ አይዘርጥጠው።

በመዘናጋታቸው ወንድሞቻችሁ በጠላት ቢማረኩ ሰውኑም እንስሳውንም አስመልሱ።ወገን መውደድን፥ ጀግንነትን ታሪክን አትጣሉ።

አንዱ ለሌላው ሃይማኖቱን ሲያስረዳና ሲያብራራ  ወይም የሌላውን ሃይማኖት ጉድለት ሲያመለክት በትህትና ያድርግ።ነገር ፈላጊ አይምሰል።

በተለይ፣ በተለይ ሲሞት ንጉሥን ለመተካት ያለውን የእልቂት ምንጭ የምታደርቁበትን ብልሃት ፈልጉ። ዘዴ አብጁ።ምከሩ። እስካሁን ያስቸገረ ነገር ቢኖር እርሱ ነው። ደግሞ የሚሰየመው ንጉሥ የእኔን ሐሳብ የሚፈጽምና እናንተንም ለዚሁ የሚያተጋ እንዲሆን አደራ! የእኔ የአንድ አባታችሁ ልጆች መሆናችሁን ለአፍታም እንኳ አትዘንጉ።ምርቃቴንና ባርኮቴን አታጥፉት።" አለ

ንግግሩን ትንሽ ቆም አደረገ። ቀጥሎም "እሺ በሉኛ" አለ።

"እሺ እንተጋበታለን።" እንዱ በሌላው ላይ እየተደረበ ልጆቹ እሺታቸውን ገለጹ።

"ይህን የምናገረው አጠገቤ ላገኘኋችሁ ለእናንተ ብቻ አይደለም። ከእኔ ልጆች ጋር ተዋልዶና ተዛምዶ ወይም መርጦ እኔን አባታችሁን ወገኔ ነው ብሎ ለሚያምነው የትም ላለውና  ለሚመጣው ትውልድ ጭምር ነው። የእኔን የአባቱን አደራ ከሚበላ በስተቀር የልጅ፥ የተወላጅና የወገን አመሳሶ የለውም። ትንሽ ሥጋ እንደ መርፌ ትወጋ ነውና። ትንሽም ዝምድና ያለ ከሆነ ያው ወገን ነው። በሥጋዎቼ መኻል ልዩነት አላደርግም። ለእኔ  ሁሎቹም እኩሎቼ ናቸው።ብቻ  አደራዬን አይብሉ።አደራዬን ከመጠበቅ ወደ ግራም ወደ ቀኝም አይበሉ። አዎ ዝርያዬ ብርቱ ሆኖና ራሱን ችሎ ሲኖር እንቅፋት አያስገቡ!"

ንግግሩን  እየቀጠለ እያለ ድንገት ጥያቄ አቃጨለብኝ። እንዴት ጥያቄዬ ዘሎ እዚህ ዘመን ላይ እንደደረሰ አልገባኝም። "የአማራ ክልል  እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ተጋድሎን ከጀመሩት ፋኖዎችና ከመሪዎቻቸው መኻል ይህን ምክሩንና አደራውን ያልሰሙ ይኖሩ ይሆን?"  የሚል ጥያቄ አስጨነቀኝ

በዚያን ቅጽበት አባትዬው በተቀመጠበት ሲያሸልበውና ጸጥ ሲል ተመለከትኩ። "ወዮ መሞቱ ነው እኮ! ይኼ ሁሉ ነገር ለካ ኑዛዜ ኖሯል በማለት በድንጋጤ ስጮህ" ከሕልሜ ባነንኩ። የማየው ሁሉ ለካ በህልሜ ኖሯል። ግና ቀን የታሰበው አይደል በህልም ደብለቅለቅ ብሎ የሚታየው? 

Comments

Popular posts from this blog

Comparative Theology የነገረ መለኮት ንጽጽር (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት)/ በብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሲኖዳ ሳልሳዊ

 የነገረ መለኮት ንጽጽር  (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት): የወደደ  ሁሉ በነጻ እንዲጠቀምበት ተፖስቷል። ይሁን እንጂ መብቱ በሕግ የተጠበቀ ስለሆነ በየትኛውም መልኩ ለንግድ እንዲውል አልተፈቀድም። ልዩ ልዩ መግቢያ የሚለውን መጀመሪያ ካነበቡ በኋላ የተቀረውን በተመረጠው ቅደም ተከተል ማንበብ ይቻላል። ልዩ ልዩ መግቢያ   ጥምቀት   ትውፊት (ወግና ልማድ)   መካከለኝነት   ጾም የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ መንፈሳዊ ስጦታዎችና በልሳኖች የመናገር ስጦታ   ሥርዐት ንስሐ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ (1)  ድንግል ማርያምን ስለማክበር (2) ለጥያቄዎች መልስ (ሀ) ድንግሊትን ‘የወይን ግንድ (ተክል)’ና የ ‘ሕይወት በር’ የሚል ማዕረግ  ለምን እንሰጣታለን? (ለ) ወደ ድንግል ማርያም መጸለይ ትክክል ነው ወይ? (3) የድንግል ማርያም ድንግልና ዘላለማዊነት (4) ለተቃራኒ አስተያየቶች መልስ (ሀ) “የመጀመሪያ ልጇን” የሚለው ሐረግ (ለ) “ሚስትህ” የሚለው ሐረግ (ሐ) “አብረው ከመሆናቸው በፊት ጸንሳ ተገኘች” (መ) “የመጀመሪያ ልጇን እስክትወልድ አላወቃትም” (ሠ)  “ወንድሞቹ” የሚለው ሐረግ   የቅድስት ድንግል ማርያም  ክብሯ (1) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ድንግል እመቤታችንን አያከብሩም፤ ደግሞም እንድታማልድላቸውም (እንድትማልድላቸውም)  አይጠይቋትም።ከእነርሱ ወገኖች አንዳንዶቹ እንዲያውም ጫጩቱ ከተፈለፈለ በኋላ ዋጋ ከሌለው የዶሮ እንቁላል ቅርፊት ጋር እስከሚያመሳስሏት ይደርሳሉ።ይህ የተጋነነ ማቃለል የመጣው ምናልባት ሮሜዋውያን ካቶሊኮች የተጋነነ ማክበር ስለሚያከብሯት ለዛ ተቃርኖ ከማሳየት አዝማሚያ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን አንዱንም የእርሷን በዓል አያከብሩም።  (2) አንዳንዶቹ የፕሮቴስታንት ወገኖች ድንግል ማርያምን “እህታችን” ይሏታል። (3) በተጨማሪ አንዳንዶቹ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ጌታ ኢየሱስን በድንግልና ከወለደች በኋላ ከዮሴፍ ጋር ጋብቻዋን ፈጽማለች፤ የ‘ኢየሱስ ወንድሞች’  ወይም የ’ጌታ ወንድሞች’ ተብለው የተጠሩ ልጆችን ወልዳለች ይላሉ።  (4) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ቤተክርስቲያናችን ለድንግል እመቤታችን የሰጠቻቸውን አንዳንድ የማዕረግ ስሞችም ይቃወማሉ።  (5) ድንግልን ያለማክበራቸው አንዱ...

ከቄስ ( ዶ/ር ) ቶሎሳ ይልቅ

 አድማጭ ተመልካቾቼ አንደምን ከረማችሁ? የአብርሃም አምላክና አምላካችን የተመሰገነ ይሁንና እኔ ደህና ነኝ።"ከቄስ (ዶ/ር ) ቶሎሳ ይልቅ" በሚል ርዕስ ያዘጋጀሁትን  የሚከተለውን መልዕክቴን እንድትከታተሉልኝ በታላቅ አክብሮት እጠይቃችኋለሁ። ባንቱ ገብረማርያም ነኝ ከቄስ (ዶ/ር) ቶሎሳ ይልቅ           ቄስ (ፓስተር) ዶ/ር ቶሎሳ  ጉዲና የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን በአትላንታ/ጆርጂያ ፓስተር መሆናቸው በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ይመስለኛል። በበኩሌ የማከብራቸውም ሰው ናቸው። በወንጌላውያን መኻል ለበርካታ ዐመታት ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የተናገሩ፣ ያሳሰቡና የጸለዩ መሆናቸውን ሰምቼአለሁ።በነገዳቸው የተደራጁትን የወንዛቸው ልጆችን ወቀሳ ተቋቁመው ለመላው ኢትዮጵያዊ ሲጮኹ የኖሩ ናቸው።           ስለ እሬቻ የሰጡት ትምህርት እስከዛሬ እንደሞዴል የማየው ነው። እሬቻን እንዳይከተሉና እንዳያስፋፉ የአሁኖቹን የመንግሥት ዐላፊዎች የመከሩበትንም ጊዜ አስታውሳለሁ።           የወንጌላውያን ሽማግሌ ብቻ ሳይሆኑ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌ አድርጌ አያቸዋለሁ። ይህን መደላድል የማስቀምጠው ስለእርሳቸው ያለኝን አስተያየት ለማስታወቅና ይኸው ሐሳቤ የጸና መሆኑን ለማስጮህ ነው።አስተያየቴን አልጠየቁኝም፣ የሚጨምርላቸውም ሆነ የሚቀንስባቸው ነገር እንደማይኖርም ጠንቅቄ አውቃለሁ። መደላድሉን አስቀድሜ  ማስቀመጤ ወንድሞችንና እህቶችን “አይዟችሁ አትደንግጡ” ለማለት ያህል ነው። ...