ብፅዕት ማርያምን የማክበር ጉዳይ ማወኩ?
በባንቱ ገብረማርያም
አድማጭ
ተመልካቾቼ፡ እንደምን አላችሁ? ክብሩ ይስፋ የመድኃኒዓለም! እኔ ደህና ነኝ
ሰሞኑን
የማርያም ሥዕል መቀደዱን ከማህበራዊ መገናኛ ተመለከትኩ። ስለዚያ ያለኝን አስተየየት እንደሚከተለው አቀርባለሁ። እንድትከታተሉት በታላቅ ትህትና እጋብዛችኋለሁ።
በመጀመሪያ ስለ ማርያም ሥዕል ያለኝን ትውስታ ልንገራችሁ። በጎባ/ባሌ የአዝማች ደግልሃን ት/ቤት ተማሪ ነበርኩ(ስሙ ተቀይሯል)። ይህ ታሪክ የሆነ ጊዜ የስንተኛ ክፍል ተማሪ እንደነበርኩ አሁን ተዘንግቶኛል። የዘጠነኛ ወይም የአሥረኛ ክፍል ተማሪየነበርኩ ይመስለኛል። በዚያን ዐመት በትምህርት ቤቱ የተማሪ ክበቦች ተቋቁመው ነበር።ታዲያ እኔም ከተቋቋሙት አንዱ ከነበረው ከመጽሐፍ ቅዱስ ክበብ ገባሁኝ። የክበቡ
መሪ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ዩኒቨርስቲ (ስሙ ተቀይሯል) በብሔራዊ አገልግሎት የመጣ የኬሚስትሪ አስተማሪ ነበር።
አንዱን ቀን መጽሐፍ ቅዱስን ሊያስተምረን አባላቱን ሚካኤል ጋራ
ላይ ይዞን ወጣ(አካባቢውን ለማታውቁት ሚካኤል ጋራ ከትምህርት ቤቱ ጀርባ የተቆለለ ጋራ ነው)። እዚያ ስብሰባ ላይ ነበር የማርያምን ሥዕል ያደለን።የሥዕሉ ትልቅነቱ የኪስ ቦርሳ
ውስጥ ለማስገባት የሚያስቸግር ያህል ነበር።እጅግም ትልቅ አልነበረም ለማለት ነው። ት/ቤት ለዕረፍት በተዘጋበት
ጊዜ ያንን ሥዕል
ይዤ ጎሮ ወረድኩ።ለእናቴ ሰጠኋት። እጅግ በጣም ደስ አላት። እያገላበጠች ሳመቻት። በኋላም የክት ልብስ በሚቀመጥበት ሳጥን ውስጥ ሥዕሏን በጥንቃቄ አስቀመጠችው። መረቀችኝ። ያ
ቀን እናቴን ደስ ያሰኘሁበት የማይረሳኝ አንዱ ቀን ነበር። በነገራችን ላይ ብርቅ በነበረበት በዚያን ዘመን እናቴ የእኔን ጨምሮ የልጆቿን ፎቶ ግራፍ ስታገኝ የሚሰማትና የምታደርገው ተመሳሳይ ነበር።
ይህን
ትውስታዬን የቀሰቀሰው ሰሞኑን የማርያም ሥዕል በአደባባይ መቀደዱ ነው።እናቴ ዛሬ በሕይወት ኖራ፣ የማርያም ሥዕል ተቀደደ መባልን ብትሰማ፣ ምን ያህል ታዝን እንደነበር ታየኝ። የመደባደብም ሆነ የመሰዳደብ ነገር የማይታይባት ስለነበረች፣ ምናልባት የቀደደችው ሰው ትደብደብ አትልም ይሆናል። ነገር ግን በጣም እንደምታዝንና በነጠላዋ ጫፍ
እንባዋን እየጠራረገች እንደምታለቅስም ታየኝ። የብዙ እናቶች ስሜትም ተመሳሳይ የሚሆን ይመስለኛል።
ታዲያ
ይህን አስቤ፦ “የማርያምን ሥዕል የቀደደችዋ ልጅ ምነው ይህን ዐይነት ደስታ ለመስረቅ ምክንያት ባልሆነች? ምን ረብ ኖሮት ቀደደች? እናቶችን የሚያሳዝን
ነገር ምነው ባልመረጠች” ብያለሁ። “እንዳው ለመሆኑ ለምን አደረገችው?” ፦ ያስከተልኩት ጥያቄ ነበር።በዚህ ድርጊቷ ሥዕሉ አንዳች የማድረግ ኃይል የለውም ብላ መልዕክት ለማስተላለፍ ፈልጋ ከነበረ መልዕክቱ ለማነው? ኃይል የለውም
የምንል እንደሆንን አለማመናችንን ለማስረገጥ ወይም ለማጽናት ይህ “ማሳያ“ አያስፈልገንም።
በ"ሥዕለ አድኖ" የሚያምኑት ኦርቶዶክሳውያኑ ደግሞ ልጅቷ ቀድዳ አንዳች ነገር ባለመሆኗ “እውነትም ማርያም ኃይል የላትም” ብለው እምነታቸውን አይጥሉም።
ታዋቂ መሆን ፈልጋ ከሆነ ብቻ ተሳክቶላታል። በአሁኑ ዘመን አንዱ የሥራ መስክ በዩትዩብና በቲክ
ቶክ የሚቀርብ ነገር ማዘጋጀት ነውና ለዚያ እንዲሆናት አስባም ሊሆን ይችላል።ብቻ ለምን ዐላማ እንዳደረገችው
የምታውቀው እርሷ ነች።
ለእኔ
ግን ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አስቸግሮኛል። ምናልባት እርሷ ወንጌላዊ አማኝ ሆና በዚህ ድርጊቷ ሰዎችን ወደ እርሷ እምነት ለመውሰድ ያሰበች ከነበረም ፣ የእምነት ምልክቱን ከመቅደድ ይልቅ “በግላችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ እመኑ፣ ከቤተሰብ በተቀበላችሁት ልማድ አትተማመኑ” ዐይነት ነገር ብትናገር የተሻለ የነበረ ይመስለኛል።
በአገራችንና
በአካባቢዋ የረዥሙን የወንጌል ተልዕኮና የክርስትያናዊ አኗኗር መቃናትን ለሚያማትሩ በኦርቶዶክሳውያንና በወንጌላውያን መኻል መፋጠጥን ሳይሆን መተጋገዝን ፣ መተንኮሰን ሳይሆን ማስረዳትን፣ መጎነታተልን ሳይሆን መቀባበልን ይመርጣሉ ብዬ አምናለሁ። አብዛኛዎቹ ወንጌላውያንም የረዥሙን መጪ ዘመን የሚያማትሩ ይመስለኛል። የልጅቷ
ድርጊት ለዚህ በጎ አስተዋጽኦ አይኖረውም።
በሌላ በኩል በድርጊቷ የተቆጡባት ብዙ ኦርቶዶክሳዉያን እንዳሉ ከማኅበራዊ ሚዲያው ተከታትዬአለሁ። አንዳንዶቹም በአካል ጉዳት ሊያደርሱባት እንደሞከሩ ሰምቼአለሁ። ለብፅዕት ማርያም ካላቸው አክብሮት የተነሳ ይህን ለማድረግ ቢነሳሱ የማይጠበቅ ዱብ ዕዳ ሆኖ የሚታይ አይደለም። በተለይ ልጅቷ ያደረገችው ዐይነት የአደባባይ አመጽ፣ የመጠቃትና የመደፈር ስሜት ስለሚያሳድርም በመቆጣታቸው አልተደነቅሁም። በተለይም በጴንጤዎች በራሳቸው ወይም በእነርሱ ስም በተደጋጋሚ ተዘልፈናል፣ ጉዳት ደርሶብናል፣ በሚሉበት ዘመን ላይ በእሳት ላይ ቤንዚን እንደማርከፍከፍ እንደሚሆን ይታየኛል። ያማል!! ያለጥርጥር ስሜት
ይጎዳል!! ያም ሆኖ በአካል መጉዳትን አስቀርተው ስለ "ስዕለ አድኖ” ለማስረዳት፣ ለማስተማርና ለመመከት አጋጣሚውን ለመጠቀም ሊመርጡ ይችላሉ።
ሐተታዬን
በአግራሞቴ ልቋጨው፦ ብፅዕት ማርያምን ማክበር ለምን ይህን ያህል እንደሚያውክ፣ ምን እንደተገኘበት አልገባህ ይለኛል።
ስለተከታተላችሁልኝ አመሰግናችኋለሁ!
ሁሉ
ቀን መልካም ቀን ይሁንላችሁ።
የሰማና
የወደደ ላልሰማ ያሰማ!
ያየና
የወደደ ላላየ ያሳይ!
ያነበበና
የወደደ ላላነበበ ያስነብብ
ሰብስክራይብ
፣ሼር፣ ላይክ ፣ ደወሏን ይጫኑ እንዲሉ
ባንቱ
ገብረማርያም
Comments
Post a Comment