ነገረ አማት ወምራት
ትርጉም፦የባል እናትና አባት ለሚስት ዐማቶች ናቸው። አንዱን ከሌላው ለመለየት የወንድ አማቷ ወይም የሴት አማቷ ይባላሉ። የሚስት አባትና እናትም ለባል ዐማቶቹ ይባላሉ። የወንድ አማቱ ወይም የሴት አማቱ ተብለው ይለያሉ። በዚህ ጽሑፍ አማት ሲባል የባል እናትን ፥ ምራት ሲባል ደግሞ የልጁ ሚስትን ማለት ነው።
ልጆች ማንነታቸውን የሚመሠርቱበት፣ የወገንነት ስሜት የሚያገኙበት፣ ለራሳቸውም ሆነ ለወገኖቻቸው የሚኖራቸውን ኅላፊነት የሚማሩበት ማኅጸን ቤተሰብ ይባላል። ደህንነት፣ ከለላ ፣ ድጋፍና ፍቅር አግኝተው የሚያድጉትም በዚያ ነው። ቤተሰብ የሚሰፋውና ቀጣይ የሚሆነው ደግሞ በጋብቻ /በትዳር ነው። ትዳር ማለት በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መኻል አዲስን ቤተሰብ ለመመሥረት የሚገባ ቃልኪዳን ነው። ከዚህ የተለየ ትርጉም የሚሰጡት ማኅበረሰቦች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን ይህ ጽሑፍ በዚሁ ክርስትያናዊ ትርጉም የተወሰነ ነው።
በተጋቢዎቹ በራሳቸው ምርጫ ትዳር ሲመሠረት ግን ወላጆች በምርጫው ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖ እስከማይኖር ይደርሳል። ጋብቻዎቻቸውን የመመረጥ እድል አይኖራቸውም። ተከፉም ተደሰቱም ልጆቻቸው ከመረጡላቸው ጋር መዛመድ ግዴታቸው ይሆናል።
ለነገሩ በየትኛውም መንገድ የተመሠረተ ጋብቻ በጅማሮው ዘመን ላይ ድንግርግር (ሚናን ለመለየት ማስቸገሩ) ማለቱ አይቀርም። በግንኙነትም የመግባቢያው ዘዴ ግራ ያጋባል። ነጻ በመሆንና በወላጆች በመደገፍ መኻል ሚዛኑን እስኪያገኙት ድረስ ይኸ ችግር አይቃለልም።መቀራረቡ እየተጓተተ ሄዶ በመኻሉ ምራት ልጅ ከወለደች መራራቁ ሊባባስም ይችላል።
በአፍሪካውያን የተደረገ አንድ ጥናትም ከዚሁ ጋር የሚቀራረቡ አምስት ነጥቦችን ይዘረዝራል።
- ቅርበትን መፈለግ፦ ከአብራክ የተወለደ ብቻ ነው ከልብ መወደድ የሚቻለው በሚል ፈሊጥ የሌላውን ልጅነት ባለመቀበል የራስን ልጅ ብቻ ለይቶ መውደድና ሌላውን ቸል ማለት
- አማቶችን ከቤተሰቡ አለማዋሐድ፦ወላጆች በልጆቻቸው ላይ ብዙ ደክመዋልና በአዲሱ ቤተሰብ በመልካም እንዲስተናገዱ (ፊት እንዳይነሱ) ይጠብቃሉ።
- ወላጆች ሚና እንዲኖራቸው አለማድረግ፦ይኼ ጭራሽኑ በልጃቸው ቤት ገብተው አመራር ለመስጠት እስከመፈለግ ሊያነሳሳቸው ይችላል።
- ምራቶች ሥጋት ሲገባቸው፦በአማቶች እንዳልተወደዱ (ብቁ አይደላችሁም እንደተባሉ ሲሰማቸው) እስከ መበጥበጥ ይደርሳሉ፡፡ለምሳሌ ልጅ ሳይወልዱ ሲቀሩ
- ድንበር ያለፈ የወላጅ ተጽዕኖ፦ በአፍሪካ አንዳንድ ወላጆች ያበዙታል።የልጆቹን ቤት ሙሉ ለሙሉ ልቆጣጠር ይላሉ። ትርፉ የልጆቹ ሃዘን ምናልባትም የትዳሩ መፍረስ ነው።
ይህ ይባል እንጂ የሁሉ አማትና ምራት ግንኙነት በተረት እንደሚነገረው፣ በቀልድ እንደሚያስቀው፣ በዘፈን እንደሚያሳዝነው የጠለሸ አይደለም። እርስ በእርስ የሚዋደዱና መልካም ግንኙነት ያላቸው አሉ። ፍርሃት የከበበውና ጎምዛዛ ግንኙነት ያላቸውም አይጠፉም። አዎ! መወዛገብ የመላበትና ትዳርን የሚጎዳ ሊኖር መቻሉም አያጠያይቅም። በአመዛኙ ግን መኻከለኛ ሆኖ ወደ ጥሩነት ያዘነበለ ሆኖ ይገኛል ። ምናልባት ቢጠና (ተጠንቶም እንደሆን አላወቅሁም) የኢትዮጵያውያንም ተመሳሳይ ይሆናል። መቼም የኢትዮጵያ አማቶች እንደ ሕንድ አማቶች አይሆኑም የሚል የዚህ ጸሐፊ ግምት አለ። አሁን መሻሻል እያሳየ ቢሆንም በሕንድ አገር ምራት ሙሉ ለሙሉ በአማቷ ቁጥጥር ሥር ትኖራለች። ለሕክምና ወደ ጤና ድርጅት እንኳ ብቻዋን እንድትሄድ አማት አትፈቅድላትም።
በሚስትና በእናቷ መኻል እንዲሁም በባልና በሚስት ወላጆች መኻል ውጥረት ሊኖር ቢችልም ጥናቶች እንደሚያሳዩት ቅድሚያ ተከሳሽ አማት (የባል እናት) ስትሆን ለጣቂዋ ምራት (የልጁ ሚስት) ናቸው።በባልና በሚስት ወላጆች መኻል ውጥረት የሚኖረውም በአመዛኙ በትዳሩ ጣልቃ የሚገቡ ሆኖ ሲሰማው ነው።
በአማትና በምራት መኻል ግንኙነቱን ሰላማዊ ቢያደርጉ የመጀመሪያ ተጠቃሚዎች እነርሱ ራሳቸው ይሆናሉ። አማት ከልጇ ጋር መገናኘት፣ የልጅ ልጆቿን አግኝታ አብራ ጊዜ እንድታሳል፣ ፍቅርን እንድትለዋወጥ፣ ስታረጅም እንድትጦር ይረዳታል ። ለምራት ደግሞ ከውኃ አጣጭ ጋር ያለውን ግንኙነት በጎ ያደርግላታል ። ልጆቿን በመንከባከቡ እርዳታ ታገኛለች፣ የገንዘብ አቅም ካላቸው በዚያም በኩል ርዳታ ልታገኝ ትችላለች። እርሷም በተራዋ አማት ስትሆን የሚረዳትን ንድፍ ታገኝበታለች ። እናት የሞተባት ወይም የእናት ፍቅር ያላገኘች ደግሞ ያንን ጉድለቷን ልትሞላላት ትችላለች።
ሴቶች ማኅበራዊ ግንኙነትን በመምራቱ ዋና ተዋናይ እንደመሆናቸው መጠን የሁለቱ ግንኙነት የቤተዘመዱን መተሳሰር ይወስነዋል ። መተባበሩ ወይም መከፋፋቱ ለምራትና ለአማት ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይሆንም። ለሦስቱም ቤተሰቦችና ባጠቃላይ በጋብቻ ለሚዛመዱት ሰፊ ማኅበረሰብ የመትረፍ ዕድል አለው። ማኅበረሰቡ ላለበት ቤተክርስቲያንም አይደርስም አይባልም። ስለዚህ ቤተክርስቲያን ለዚህም ጉዳይ ትኩረት ልትሰጥ ያስፈልጋታል።የንግድና መሰል የሥራ ሽርክና በቤተሰብ መኻል ሲኖርም የአማትና የምራት ግንኙነቱ እንደ አገባቡ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል። ይኸንን “በቀንድ ከብት ልማት” በተሠማሩ የተደረገውን አንድ ጥናት መሠረት አድርጎ መገመት ይቻላል።እንደተጋቡ ቅድሚያ ታማኝነታቸው ለመሠረቱት ለራሳቸው ቤት መሆኑን ማረጋገጡ የአማት-ምራት ችግርን ለመቅረፍ ዐይነተኛ መፍትሔ ነው።
የአማትና ምራት ጉዳይ አትድረስብኝ-አልደርስባትም ማለት የሚቻልበት አይደለም። ለሁለቱም መገናኘት ምክንያት የሆነው ልጁ/ባሉ በመኻከላቸው እስካለ ድረስ ሊዳረሱ የሚችሉበትና ሊጋጩ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው።
ደግነቱ ከግጭት የመራቅ አቅጣጫም አለ።ምራት በእናትና በልጁ መኻል በተፈጥሮ (በመውለድ/በመወለድ)፣ አብሮ ታሪክን በመካፈል ውስብስብና የማይበጠስ የነገረ ልቡና ግንኙነት እንዳለ መገንዘብ ያሻታል። የአማትን ጥበቧን፣ ልምዷን ፣ጠቃሚነቷንና ሥጋቷን ልብ ማለት አማትን ሰላማዊ ያደርጋታል። አማት ደግሞ ለልጇ የአካልና የስሜት ፍላጎቱን ለቀሪው ዘመኑ ሁሉ የምትሞላለት፣በልጁ ሕይወት ዋናዋ ሴት ተዋናይ መሆኗን በመቀበል ከምራት ጋር ከመፎካከርና እርሷን በነገር ከመንካት ትራቅ።ሁለቱም ባልን በእናቱና በሚስቱ መኻል እንዲመርጥ የሚያስገድድ ሁኔታ ውስጥ አያስገቡት።አንደኛዋን እንዲመርጥ ሲገደድ ባልተመረጠችው ላይ ጉዳትና ቁጣ ያስከትላልና። ልጅ/ባልም ቢሆን አይፋዘዝ፣ እናቱን ያላገለላት (ያልረሳት) እንደሆነ እንዲሰማት በማድረግ ቅርበቱን/ቅድሚያ ታማኝነቱን ከሚስቱ ጋር ማድረግን ይማር።
ይህን በመግቢያነት ካተትኩ በኋላ ’ሪይል ሲምፕል’ የተሰኘ መጽሔት ካቀናበረው የተወሰደ የአማትና ምራት ግንኙነትን የሚያሳየውንና ሰላማዊ የማድረጊያ ስልቱን የሚያስረዳውን ጽሑፍ አቀርባለሁ። ጌታ ቢፈቅድ ብኖርም በሌላ ጊዜ ደግሞ ታሪኮቻቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ስለሚገኙ አማትና ምራት እጽፋለሁ።
ዋቢ
ATTITUDE OF MOTHER-IN-LAW TOWARDS DAUGHTER-IN-LAW AS A DETERMINANT FAC... (iproject.com.ng)
Curse of the Mummy-ji: The Influence of Mothers-in-Law on Women in India*Final_Manuscript.pdf (bu.edu)
Lopata, H. Z. (1999). In-laws and the concept of family. Marriage and Family Review, 28(3/4), 161-172.
Duvall, E. M. (1954). In-laws, pro and con: An original study of inter-personal relations. New York: Association Press
Allendorf, K. (2017). Like her own: Ideals and experiences of the mother-in-law/daughter-in-law relationship. Journal of Family Issues, 38, 2102–2127.
Rittenour, C. E., & Kellas, J. K. (2015). Making sense of hurtful mother-in-law messages: Applying Attribution Theory to the in-law triad. Communication Quarterly, 63(1), 62-80. doi:10.1080/01463373.2014.965837
Fischer, L. R. (1983). Mothers and mothers-in-law. Journal of Marriage and Family, 45, 187–192
Michael E. Woolley and Geoffrey L. GreifAyers, J.D., Krems, J.A., Hess, N. et al. Mother-in-Law Daughter-in-Law Conflict: an Evolutionary Perspective and Report of Empirical Data from the USA. Evolutionary Psychological Science 8, 56–71 (2022). https://doi.org/10.1007/s40806-021-00312-x
Mother-in-Law Problems: They're Worse for Women - TIME
Mother-in-Law Reports of Closeness to Daughter-in-Law: The Determinant Triangle with the Son and Husband Michael E. Woolley and Geoffrey L. Greif
(Apostolou, 2015a, Perriloux et al., 2011).*Parent–Offspring Conflict Over Mating (sagepub.com)
Prentice, C. M. (2005).
The assimilation of in-laws: The impact of newcomers on the structuration of families, Unpublished PhD thesis. Columbia: University of Missouri-Columbia.
https://www.researchgate.net/publication/365803786_The_Bible_In-Laws_and_Family_in_Africa።
(Patterson, 1978).*5448-12959-1-PB.pdf Patterson, R. P. (1978). African Studies Curriculum Unit: The Cycle of Life in the African Family. USA: Illinois Univ. Retrieved October 23, 2022, from
https://files.eric.ed.gov/fulltext/ED189006.pdf
Silverstein, J. L. (1990). The problem with in-laws. Journal of Family Therapy, 14, 399–412.
(
Comments
Post a Comment