"የሚቀጠቅጥ በእኛ ላይ ወጥቶአል"
የቀን እንቅልፍ ለምዶብኛል።እንደ ወትሮዬ ምሣዬን ከበላሁ በኋላ ድንክ አልጋዬ ላይ ጋደም አልኩ። ወዲያው እንቅልፍ አሸለበኝ።እንደ ሌላው ጊዜ አጭርና ጣፋጭ ሆኖ አልተሰማኝም። ህልም አይሉት፣ ቅዠት- ብቻ ቆየሁበት።አንድ ሰው ጎራዴውን ታጥቆ በግራጫ ፈረስ ላይ ጉብ ብሏል። ጀርባውን ለእኔ ሰጥቶ ስለነበር ፊቱ አልታየኝም።ማን እንደሆነ አልለየሁትም። ለምን እንደሆነ አላውቅም፤ ገና ሳየው “ፈረሱስ፣ ጎራዴውስ የራሱ ይሆን?” ብዬ ጠየቅሁ።
ትንሽ ጊዜ ትክ ብዬ እንዳየሁት፦ «በዕቅዳችን መሠረት ኢምፓየራችንን ለመመሥረት እንፍጠን። ብዙ ሕዝብ ሊያልቅ ይችላል፣ ምንም ማድረግ አንችልም። ለመመሥረቱ ግን መፍጠን አለብን» ሲል ሰማሁት።
ቀጥሎም፦ «ኢምፓየሮቻችንን ለመገንባት እንቅፋቶችን የምናስወግድበት ዘዴ አግኝቼአለሁ!»አለ ጮክ ባለ ድምጽ።
እኔም:-«መጀመሪያ ኢምፓየር ሲል የሰማሁት መስሎኝ ነበር። አሁን ደግሞ ኢምፓየሮች ይላል።ምን ማለቱ ነው? አልዘባረቀም? ለመሆኑ የሚናገረው ለማንነው?» አልኩ። ወደ ቀኝ፣ ከቀኝ ወደ ግራ፣ ከዚያ ወደፊት አማትሬ ተመለከትሁ።ጥቋቁር ፈረሶቻቸውን ሽምጥ ለመጋለብ አቆብቁበው ያሉ ሦስት ሰዎችን ከፊት ለፊቱ አየሁ።ለካንስ የሚናገረው በተጠንቀቅ ለሚጠብቁት ለእነዚያ ሰዎች ኖሯል። አለቃቸው መሆኑ ይሆን?
ለመጀመሪያው ሰው ተናገረ፦ «ወደ ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ውጣ ! ነገዶቿንና ጎሳዎቿን ሁሉ በጎጥ ፣ በቀበሌ ከፋፍላቸው፣ ክተፋቸው።እርስ በእርሳቸው እንዳይዳረሱ አድርጋቸው። ለመሰልቀጥና እንደፈለግን ለመጥረብ የሚመቸን እንደዚያ ሲሆኑ ነው። የሚቋቋሙበት አቅም ያጣሉ።ዳግመኛ የሚሰባሰቡበት 'ቡረሌ' እንዳያገኙም ነቅንቃቸው። ፍጠንና ይኸንኑ አድርግ»ሲል ሰማሁት።የመጀመሪያው ሰውዬም ይኸንኑ ለማድረግ ከመቅጽበት ሸመጠጠ።
የመጀመሪያው ሰውዬ ብዙም ሳይርቅ ሁለተኛውን ደግሞ አለው፡- <<አንተ በሃይማኖት ተቋማት ላይ እንድትሠራ ነው የምልክህ።ለእኛም ዕቅድ መሳካት በየመንገዱ ድንጋይ እንዳያስቀምጡብን ጠንክረህ መሥራት አለብህ። እነዚህ ሕዝብን የማስተባበር አቅም ስላላቸው፣ ካስተባበሩም እኛ ለምንፈልገው ዐላማ ብቻ እንዲሆን ማድረግ አለብህ። ፕሮቴስታንቶቹ በአንድ ላይ ባለመሆናቸው አይመቹም ነበር። አሁን ግን በአንድ ድርጅት ጥላ ሥር ስለተደራጁልህ ነገሩ ቀላል ሆኖልሃል። ሃይማኖቶቹ ሦስት ዋና ሥፍራ ተገኝተውልሃል።ሁሉንም ትቀርባለህ።ወዳጅ ታደርጋለህ።የሚሠሩልህን ታማኝና የማይታወቅባቸውን ሰዎች በሁሉም ተቋማት ውስጥ ቁልፍ ሥፍራ ላይ ታኖራለህ። በእነዚህ ሰዎች አማካኝነት የሃይማኖት ተቋማቱ እኛ ከምንላቸው ውጭ ማድረግ እንዳይችሉ እርስ በእርሳቸው እንዲጠባበቁ ታደርጋለህ። እንደ ጊዜው ሁኔታ ለእኛ በሚጠቅመን አኳያ ታሰልፋቸዋለህ። ሲያስፈልግ ጠንካራ፣ ሳያስፈልግ ደካማ፣ ሲያስፈልግ የተስማሙ፣ ሳያስፈልግ የተጣሉ ታደርጋቸዋለህ።አንደኛው ከቁጥጥራችን ሥር ቢወጣ የተቀሩትን ሁለቱን ታስነሳበታለህ።>>ንግግሩን ቆም አደረገ።
የተነገረው ሰው ወደ ሃይማኖት ተቋማቱ ሊቻኮል ነው ብዬ ስጠብቅ እርሱም እየተቁነጠነጠ ሳለ፦ «ቆይማ አልጨረስኩም» አለው። «አይታወቅም ኦሮቶዶክሶቹና ሙስሊሞቹ እኛ በማንፈልገው መልክ ሊተባበሩብን ይችሉ ይሆናል።የዚያን ጊዜ ፕሮቴስታንቱን ሚዛን እንዲጠብቁልህ ማድረግ ያስፈልግሃል»አለው።
ከፕሮቴስታንቱ ወገን እንደምቆጠር ትዝ አለኝና ስለ እኔ ሊያወራ ነው ብዬ ከፊት ይልቅ ጆሮዬን አቁሜ አዳመጥኩት።እናንተዬ በህልም ሲሆን ለካ ጆሮ መቆም ይችላል።
ያ ሁለተኛው ሰው «እንዴት?» ብሎ ጠየቀ፡፡ በመጠየቁ ወደድኩት። መውደድ እንኳ በህልም ይቻላል፤ አልተደነቅሁም።
«ኦርቶዶክሳውያኑም ሙስሊሞቹም ፕሮቴስታንቶቹን 'ስማችንን በበጎ አያነሱንም' ይሏቸዋል። ደግሞ ሁል ጊዜ 'ነፍሳቸውን የማዳን ኅላፊነት አለብን' ስለሚሉ ከእነርሱ ዘንድ ሰዎቻቸውን ወደ ፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን ለማፍለስ ይሠራሉ።እምቢ አንሰማም ቢሏቸውም አይፋቷቸውም። ከዚህ የተነሳ ኦሮቶዶክሶችና ሙስሊሞቹ ባይጠጓቸው ነው ፍላጎታቸው።እነርሱም ወንጌላቸውን ለመንገር ካልሆነ በስተቀር አይቀርቧቸውም።ይኸንን ሁኔታ እንደማያቋርጥ ማኳረፊያ አድርገህ መጠቀም ትችላለህ። ደግሞም ልብ በል! ፕሮቴስታንቶቹ 'የዳኑትን ነፍሳት'ይቆጥራሉ።እኛ ግን ከሁለቱ ትልልቅ ሃይማኖቶች ያስወጧቸውን ሰዎችና በዚህም ኅይላቸውን መቀነሳቸውን እንቆጥራለን።ደግሞም አስተውል! ሁለቱ ሃይማኖቶች በዚህ ምክንያት ሲበሳጩ ትኩረታቸው ተቀፈደደልን ማለት ነው።እኛ ሥራችንን እንሠራለን።» መልሱ ነበር።
እኔ ቆሽቴ አረረ።በውስጤ ተንጨረጨርሁ። «የሚገርም ተንኮል ነው! እንዴት እኛን እንደዚህ መሣሪያ ታደርገነናለህ? ምን በደልንህ?» ለማለት ፈልጌ አፌን ግን መክፈት አቃተኝና አለቀስሁ።በእንባ ብዛት ዐይኖቼ ቀሉ፣ ዐበጡም። ቆይቼ ግን «መጨረሻውን ማየት እንጂ አሁን ማልቀስ ምን ይፈይዳል?» ብዬ እንባዬን ጠራርረግሁና አፍጥጬ ማየቴን ቀጠልሁ።
በዚህ መኻል ሁለተኛው ሰውዬ ሌላ ጥያቄ ጠየቀ፡- «እንዴ እነርሱም እኮ የተቋቋሙት ለራሳቸው ዐላማ ነው። ከእኛ ዐላማ ጋር የማይሄድ ነገር ሊሠሩ ቢችሉስ?»
ባለ ግራጫ ፈረሱ ለማሰብ እንኳ ጊዜ አልወሰደም፤ መለሰ፦«ያ እንኳ ቀላል ነው። በመኻከላቸው በርካታ ልዩነቶች አሉ። እነዚያ ደግሞ ከልባቸው የሚያምኑባቸው ልዩነቶች ናቸው።አሁን እነርሱን ወደ ጎን ያደረጓቸው የጋራ ችግር ላይ አናተኩር ብለው ነው። ነገራቸው አላምር ካለን ያንን ልዩነታቸውን እናስጮሀለን። በሌላ በኩል ሌሎቹን መሸርሸራቸውን እንዳያቋርጡ 'የወንጌል አገልግሎት' በሚሉት እንደግፋቸዋለን።በዚህ መንገድ በአንድ በኩል አመኔታቸውን እንዳናጣ በሌላ በኩል ሁለቱን ሃይማኖቶች የመሸርሸር አገልግሎታቸው እንዳይቋረጥብን እናደርጋለን። ለእኛ የሚያገለግሉንን ቁጥርም ይጨምሩልናል። በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ መግደል ይሆንልናል።»
ቆም አለና ቀጠለ፦ «እንዳውም ሁለቱ ሃይማኖቶች እንደሚነሱባቸውና ጠባቂያቸው እኛ እንደሆንን እንዲሰማቸው አድርጋቸው። እኛ ከሌለን ጉዳቸው እንደሚፈላ አሳምናቸው። ምን ጊዜም ከእኛ ሥር እንዳይወጡ አገልጋዮቻችን ሆነው እንዲቆዩ ሥራ። አንድ ኅይል ሆነው ከእኛ ማፈንገጥ ሲያስቡ ልዩነታችውን ታጫጭሰዋለህ። ለእኛ እስካገለገሉ ብቻ ነው አንድነታቸውን የምትደግፈው።ተግባባን?»አለው።
ይኸኛው ነገር እኔን በቀጥታ የሚመለከተኝ ስለሆነ አስቆጨኝ።ዋይ ነዶ! በማለት በትልቁ ተነፈስኩ። ከንፈሬንም በጥርሴ ሳላደማው አልቀረሁም። ብቻ አሁን አልታወስህ አለኝ።
ሁለተኛው ሰው ከዚያ በኋላ ጊዜም አላጠፋ በተሰጠው መመሪያ መሠረት ሊሠራ ሸመጠጠ።
ለሦስተኛው ሰው ደግሞ ምን መልእክት ይኖረው ይሆን? ብዬ በመገረም ስጠባበቅ ሳለሁ እርሱንም ጠራው፦
«ይኸውልህ የአንተ ሥራ ደግሞ» ብሎ ለማሰብ ይመስል ቆም አለ።በረዥሙ ከተነፈሰ በኋላ፦
«ያንተ ሥራ በእሬቻ ዙሪያ ነው። እሬቻ የጣዖት አምልኮ እንዳልሆነ፣ ይልቁንም ለአምላክ ምሥጋና የማቅረብ መልካም ባሕል እንደሆነ በማኅበረሰቡ ውስጥ ከሚያሰርጹት ጋር ሥራ። የእሬቻ ልማድ የእኛን ዐሳብ ተሸካሚና መሣሪያችን ልናደርገው የምንችለው ነው። ይዋል ይደር እንጂ የክርስትናም የእስልምናም ሃይማኖቶች የማስተባበር ሃይላቸውን እንዲያጡ ልንገዳደርበት እንችላለን።
ኦርቶዶክሶቹም ሙስሊሞቹም 'የጣዖት አምልኮ ነው ከእሬቻ ተጠበቁ' ብለው መስበክ እንዳይችሉ በራሳቸው የውስጥ ጉዳይ እንጠምዳቸዋለን። ተልዕኳችን ወንጌልን መናገር ነው የሚሉት ፕሮቴስታንቶች እንኳ በዚህ በኩል ጠንክረው አይሠሩም። ሰዎችን በእሬቻ ልማድ ውስጥ እንዳይገቡ፣ የገቡትም ወደ ክርስትና እንዲመለሱ በማድረግ ሰማዕት እስከመሆን ድረስ ለመሥራት አይነሳሱም።
ሚሲዮናውያን በ'ዶክትሪናቸው ስለሚኖር ክርክር’ና ‘የሶሺያሊዝምን እግዚአብሔር የለም ትምህርት’ በመከላከል ብልሃት አስክነዋቸዋል። ነገር ግን እሬቻን ለመቋቋም የሚያዘጋጅ ነገር የላቸውም። በዚህ በኩል የሚያግዟቸው አይሆንም። እንዳውም ድንቅ ባሕል እንደሆነ በማስረዳት ከሚሲዮናዊዎቹ ድጋፍ የሚያገኙት ‘ለእሬቻ ተሟጋቾቹ’ ሊሆኑ ይችላሉ» አለው። ይኼ ሦስተኛው ሰውዬ ጋልቦ የታዘዘውን ለመፈጸም ይሂድ አይሂድ አላወቅሁም።
«ወዮልን! ለሃይማኖት ተቋማት፣ ለነገዶችና፣ ለጎሳዎች ድብልቆችም አይተርፏትም፤ 'የሚቀጠቅጥ በሁላችን ላይ ወጥቷል’- ሁላችንም ነጻነታችንን ለማስጠበቅ የምንችልበትን ዘዴ እንፈልግ፣ እንፍጠን፣ እናምልጥ» እያልኩ በሲቃ እየጮህኩ ባነንኩ። ስባንን የሠራ አካላቴ ሲንዘፈዘፍ አገኘሁት። በኢየሱስ ስም ልበል ፣ ወይም በስመ አብ ወወልድ መንፈስ ቅዱስ ልበል ወይም ብስሚላሂ አላወቅሁትም! ብቻ የሆነ ነገር አጉተመተምሁ።ረዥም የመሰለኝ ለካንስ አሥር ደቂቃ ብቻ ነው የተኛሁት! (ወገኖቼ ምናባዊ ህልም ነው።)
ባንቱ ገብረማርያም
ተጻፈ 12/15/2022
Comments
Post a Comment