Skip to main content

ልቡን ለሕዝብ የሚያዘነብል መሪ ፍለጋ

 ልቡን  ለሕዝብ የሚያዘነብል መሪ ፍለጋ

ለዚህ ሐተታዬ መነሻ የሆኑኝ የብጹእ አቡነ ኤርምያስ፣ የብጹእ አቡነ ሉቃስ እና የብጹእ  አቡነ አብርሃም  ንግግሮች ናቸው። እንደ ራሴ ግንዛቤ ከንግግሮቹ  ባገኘኋቸው ሦስት የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ እይታዎች (እሴቶች) ላይ አትታለሁ። 


መጀመሪያ ስለ ብጹኣን ጳጳሳቱ የተሰማኝን ልጻፍ፦


  1. ሦስቱም ብጹአን አባቶች በንግግራቸው የብሔር ማንነታቸውን ሲገልጡ አልሰማሁም። ምናልባት መነኩሴ ማለት ለዚህ ዐለም ነገር የሞተ ማለት ሆኖባቸው ምድራዊውን የነገድ ነገር ስለማያስቡት ሊሆን ይችላል። ወይም ራሳቸውን ለኦርቶዶክሳውያንና እድል ፈንታው ከኦርቶዶክሳውያኑ ጋር ለሚወሰን ሕዝብ ሁሉ አባት አድርገው ስለሚያዩ ሊሆን ይችላል (የዐሳባቸውን መድረሻ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ማድረጋቸው  ለዚህኛው ምክንያት ክብደት ይሰጣል)።

  1. ሦስቱም ብጹአን አባቶች ለኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንና  ምዕመናኑ የሚገዳቸው ናቸው። በአቡነ ኤርምያስ በኩል የላሊበላ አብያተክርስቲያናት ጉዳት እንዳይደርስባቸው ብልሃት ያሉትን መምከራቸውና በሰበካቸው ስለሚገኘው ምእመናቸው  ችግር መጨነቃቸው ማሳያ ነው። አቡነ ሉቃስ ደግሞ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ስለመቃጠላቸው፣ ገደማውያንና መነኮሳቱ ስለመገደላቸውና ፣ በአጠቃላይ ስለ ኦርቶዶክሳውያኑ መጨፍጨፉ ያሰሙት የቁጭት ቃል ይመሰክራል። አቡነ አብርሃም ከሕግ ውጭ የታሠሩ ኦርቶዶክሳውያን እንዲፈቱ ፣በሕግ አግባብ የታሠሩ ካሉም ፍትሕን  እንዲያገኙ መጠየቃቸው (ይፋ ባልሆነ መንገድ) ይኽንኑ ያሳያል።  በቀኖናዋ መሠረት እንጂ በሌላ ወገን ተጽዕኖ  ቤተክርስቲያን እንደማትሠራ ማረጋገጫ መስጠታቸውም ለቤተክርስቲያን የመቆማቸው የመጨረሻው መገለጪያ ነው። 

  1. ሦስቱም ብጹአን አባቶች ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚገዳቸው እንደሆነ ይታያል።  መነሻቸው ፊት ለፊት የሚያዩት የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ እልቂት እንደሆነ ቢታይም ለመላ ኦርቶዶክሳውያን እንዲሁም እድል ፈንታቸው ከኦርቶዶክሳውያኑ ጋር ለሚወሰን  ሁሉ መቆርቆራቸውን መገንዘብ አይከብድም።

  2. ከንግግራቸው እንደተረዳሁት ሦስቱም የመንግሥት ሠራተኛነት (ካድሬነት) ወይም የመንግሥት ጠላትነት የሚታይባቸው አይደሉም።አገሪቷ የገባችበትን ችግር የምትወጣበትንና ወደ ሰላም የምትመለስበትን መንገድ በየራሳቸው መረዳት በቅንነት ያቀረቡ ብቻ ሆነው ነው የታዩኝ (በዚህ ዐሳቤ የማይስማሙ ሊኖሩ መቻላቸውን  እገነዘባለሁ። ስሜታቸውን አቅልዬ አላየውም)።


ታዲያና ይኸውላችሁ ከንግግራቸው ሦስት የዐማራ ሕዝብ እይታዎችን (እሴቶችን) አግኝቼባቸዋለሁ።እነርሱን  ለማሳየት እሞክራለሁ። 


የመጀመሪያው  የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ እይታ (እሴት)

የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ በመንግሥት ሥርዐት መኖርን የለመደ እንደመሆኑ መጠን መንግሥትን እንደ ጠባቂው አድርጎ ይመለከታል። መንግሥትን በታማኝነት ማገልገል ተገቢ እንደሆነም ያምናል።አቡነ ኤርምያስ የተናገሩት ይኸንኑ  ነባር የዐማራ ሕዝብ እሴትን/ልማድን ያስታወሰ ነው (በነገራችን ላይ  ሚሊሺያውና አድማ ብተናውም በዚህ አስተሳሰብ የሚሠራ ሳይሆን አልቀረም። በብዙዎች ዘንድ ያ መንግሥት በምናባዊ ዐለም እንጂ ዛሬ መሬት ላይ የሌለ መሆኑ ይታመናል።ይኸንን  በቶሎ ተረድቶ ሚሊሺያውና አድማ በታኙ ለዐማራ ሕዝብ ነጻነት ከሚዋደቁት ጋር ቢሰለፍ መልካም ይሆናል። የተሻለውን ለማስላትም የሚሳነው አይመስለኝም)።


ወደ አቡነ ኤርምያስ ንግግር ልመለስና፡- በነባሩ እይታ መሠረት አቡነ ኤርምያስ ስለውይይትና ምክክር ያነሡት ትክክልና ተገቢ ቢሆንም  የጦርነቱ አቅጣጫ ካልለየ በስተቀር ይህን የሚቀበል ወገን ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም። በተጀመረ ጦርነት መኻል አንደኛው ወገን የተሸናፊነት  ስሜት ካልተሰማው ወይም ሁለቱም ወገኖች መሸናነፍ  እንደማይኖር ካልታያቸው  በስተቀር የተሳካ ውይይት ማድረግ መቻሉም ያጠራጥራል። የወደፊቱ ባይታወቅም ለጊዜው ግን የሚሆን አይመስልም።ጦርነቱ ሳይነሳ ቀድሞ ቀረ።ስለዚህ  ስለ መከላከያና ስለፋኖ የሰጡትን ምክር የዐማራ ሕዝብ ለነጻነቱ ከሚያደርገው ተጋድሎ ጋር  እንዲቃኙት  እመኛለሁ።ለመምከር እየቃጣሁ አይደለም።እስከዚህም ያለ አቅሜ የምንጠራራ አይደለሁም።ሕልውናን የሚፈታተን በመሆኑ የአቋም ለውጥ /ማቋረጥ አስፈለገና ነው  እንጅ መንግሥትንና መከላከያን ማክበር  ነባር የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ እሴት መሆኑ ግን አይካድም።


ሁለተኛው የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ እይታ

    የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ  ከበርካታ ዐመታት መከራው በመማር መንግሥት ጥበቃ እንደማያደርግለትና እንዳውም ከአጥፊዎቹ ጋር እንደሚተባበርበት አይቷል። ለሌሎች ወገኖችም ቢሆን  መንግሥት የሚጠቅም ስለመሆኑ ጥርጣሬ አለው።በእመዛኙ በ "ዐማራ ክልል" አሁን ላይ የሚዋጋውን መከላከያም ወራሪ ኅይል አድርጎ ያየዋል። ከዚህ  የተነሳ የአሁኑ መንግስት በማንኛውም መንገድ መወገድ አለበት ብሎ ፋኖ በሕዝቡ ትብብር ለዚሁ ግብ እየተጋደለ ይገኛል። የዐማራ ሕዝብ  (ሁሉም ማለት በሚቻልበት ደረጃ) ስለመንግሥት ያለው የአሁኑና ገዢ  እይታ ይህ ነው።


    አቡነ ሉቃስ ካንጎደጎዱትና  ካስገመገሙት ያየሁት ይኸኛውን ስሜቱንና ቁጣውን ማስጋባታቸውን ነው።ሚሊሺያውም፣ አድማ ብተናውም ፣መከላከያውም በኢትዮጵያ  ላይ በተለይም  በኦርቶዶክሳውያን ላይ ያስከተለውን ሰቆቃ ተረድቶ በመንግሥት ላይ እንዲነሳና ለነጻነት ከሚዋደቀው ጎን እንዲሰለፍ የተናገሩትም ለዚህ ይመስለኛል። ከዚህ የማይገጥመውንም ረግመዋል (መንግሥትን የማይሰማ፣ የማይለወጥ፣ አታላይ  ፣ አውዳሚ፣  ጨፍጫፊና አስጨፍጫፊ ሆኖ  ካገኙት አባት  በመፍትሔነት ከቀረበው ሌላ ምን እንዲቀርብ ይጠበቃል?)። ለማንኛውም እርሳቸው የአሁኑን ትኩስ  የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹን እይታ ማንጸባረቃቸውን ተገንዝቤአለሁ።


ሦስተኛው  የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ እይታ(እሴት)

    የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ያከብራል። ሌላውም እንዲያከብራት ይጠብቃል። ማለትም ዶግማዋንና ቀኖናዋን ጠብቃ እንዳትሠራ የሚያውካት እንዳይኖር ይጠብቃታል። ከመንግሥት ጋር ተቀራርባ መሥራቷንም የለመደው ነው። የሚያምጹን ከመንግሥት ጋር ለማስማማት ታማኒነት አላት  ብሎም ያምናል። የአቡነ አብርሃም ንግግር ደግሞ በዚህ እይታው (እሴቱ) ዙሪያ የሚያጠነጥን ሆኖ አግኝቼዋለሁ።


    እርሳቸው እንዳሉት  ቤተክርስቲያን የሰላም መንገድንና ፍቅርን  እንዲከተሉ መንግሥትንም ሆነ ሕዝብን ታስተምራለች፣ ትገስጻለች። ጠብ ሲኖርም ታስታርቃለች።  ፍሬያማነቱ ግን የሚወሰነው  በሁሉም ወገን አመኔታ በማግኘቷ ልክ ነው። ምዕመናኑና እድል ፈንታው ከኦርቶዶክሳውያኑ ጋር የተቆራኘው ሕዝብ መንግሥትን አታላይ አይደለም ብሎ በሚያምነው ልክ የማስታረቁ ሥራ ቀና ይሆንላታል። መንግሥት ደግሞ ለቤተክርስቲያኒቷ በሚሰማው (በሚያስበው) የልጅነት ስሜትና ወሳኙን የምርጫ ድምጽ ልታሳጣኝ ትችላለች ወይም በማስተዳደሩ ልታውከኝ ትችላለች ብሎ በሚሰማው ሥጋት ልክ ለአስታራቂነቷ ጆሮዋን ይሰጣል። ለጊዜው ውጤታማ ሥራ ልትሠራ ያልቻለችው በሕዝብና በመንግሥት መኻል መተማመን በመጥፋቱ ነው። እንዳውም ራሷ በመንግሥት ተጠቂ ሆናለች።ብጹዕ አቡነ እብርሃም እንደገለጹት እስካሁን አላደረገችውም እንጂ መንግስት በጉዳይዋ እየገባ ማስቸገሩን ካበዛው መናኑ ለመንግሥት እንዳይታዘዝ በማድረግ ነጻነቷን ታስጠብቃለች። ምእመናንና ምዕመናት የሃይማኖታቸው ጉዳይ ነውና ለትእዛዙ ይገዛሉ። ይህም የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ የሚቀበለው እይታ ነው።


የራሴ መደምደሚያ ፡


    ለዐመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሲከማች የኖረው ጉስቁልናና አበሳ የዐማራ ክልል እየተባለ በሚጠራው ውስጥ በተከፈተው ጦርነት የመጨረሻ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ይኸው ሁኔታ ብጹአን አባቶችን ያናግራቸው የጀመረ ይመስላል። እኔንም ስለዚሁ ጦርነት ሎ በሰማሁ ቁጥር ያሳዝነኛል። ልቤን ያመኛል፣ ያጥወለውለኛል። ይኼ ሁሉ እልቂት ለማንና ለምንድነው? እላለሁ።ደግሞ እልቂቱ በአንድ አገር ልጆች መኻል መሆኑ የበለጠ ያሳዝናል።የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ግን ምርጫ እንደሌለው እገነዘባለሁ።የሚያደርገው ራስን የማዳንና የመከላከል ተጋድሎ ነውና ይኸንኑ በአንድ ልብ ሆኖ ይቀጥላል።


    መንግሥትና መከላከያ እንዲከበር እንዲሁም የኦርቶዶክስ  የሰላምና የፍቅር ሥራ ፍሬያማ እንዲሆን ከተፈለገ የሕዝብ ልብ ወደ መንግሥት ፣ የመንግሥትም ልብ ወደ ሕዝብ መዞር ያስፈልገዋልሁለቱም ዎገኖች የአባቶችንና የሽማግሌዎችን ተግሳጽና ምክር የሚሰሙ ቅኖች  ሊሆኑም ይገባል። ልብን የመመለሱ  ቅድሚያ መውሰድ ደግሞ ኃላፊነት ካለበት ከመንግሥት ይጠበቃል። መንግሥት ያን በሐቅ ቢያደርግ   የሕዝብ ልብም ለመንግሥት ያዘነብላል እላለሁ።


     ይሁን እንጂ ሕንጻና ፓርክ በመሥራቱና ዛፍ በመትከሉ ከሚያወድሱት በስተቀር መንግሥት የአመዛኙ  ሕዝብ ፍቅር ርቆታል።ልቡን ወደ ሕዝብ የሚያዞርም አይመስልም። ወደ ሥልጣን ይዞ የመጣውን እቅድ ተግባራዊ በማድረግ ልቡ ስለተነደፈ ወደ ሕዝቡ የሚመለስ ልብ አልቀረውም ተብሎ ነው የሚታመነው። ቀልቡ ወይም ከራማው ያንን እቅዱን በቶሎ እመፈጸም ላይ ተቸንክሯል።


      በተለይ  የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ እንደሚሉት ከሆነ አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ልብ ወደ ሕዝቡ ይመለሳል ብሎ መጠበቅ ተላላነት ነው። ልቡን ወደ ሕዝቡ በሚያደርግ መንግሥት መተካት  ወይም መቀየር የሚያስፈልገው ነው።ይህ እውነት ነው ብሎ ካመነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ጋር በመተባበር ልብን ወደ ሕዝቡ የሚያደርግን መንግሥት ፍለጋውን ሊያፈጥን ይገበዋል።ቢያደርግ የማይጸጸትበትን ነገር አደረገ

ቸር እንሰንብት





Comments

Popular posts from this blog

Comparative Theology የነገረ መለኮት ንጽጽር (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት)/ በብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሲኖዳ ሳልሳዊ

 የነገረ መለኮት ንጽጽር  (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት): የወደደ  ሁሉ በነጻ እንዲጠቀምበት ተፖስቷል። ይሁን እንጂ መብቱ በሕግ የተጠበቀ ስለሆነ በየትኛውም መልኩ ለንግድ እንዲውል አልተፈቀድም። ልዩ ልዩ መግቢያ የሚለውን መጀመሪያ ካነበቡ በኋላ የተቀረውን በተመረጠው ቅደም ተከተል ማንበብ ይቻላል። ልዩ ልዩ መግቢያ   ጥምቀት   ትውፊት (ወግና ልማድ)   መካከለኝነት   ጾም የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ መንፈሳዊ ስጦታዎችና በልሳኖች የመናገር ስጦታ   ሥርዐት ንስሐ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ (1)  ድንግል ማርያምን ስለማክበር (2) ለጥያቄዎች መልስ (ሀ) ድንግሊትን ‘የወይን ግንድ (ተክል)’ና የ ‘ሕይወት በር’ የሚል ማዕረግ  ለምን እንሰጣታለን? (ለ) ወደ ድንግል ማርያም መጸለይ ትክክል ነው ወይ? (3) የድንግል ማርያም ድንግልና ዘላለማዊነት (4) ለተቃራኒ አስተያየቶች መልስ (ሀ) “የመጀመሪያ ልጇን” የሚለው ሐረግ (ለ) “ሚስትህ” የሚለው ሐረግ (ሐ) “አብረው ከመሆናቸው በፊት ጸንሳ ተገኘች” (መ) “የመጀመሪያ ልጇን እስክትወልድ አላወቃትም” (ሠ)  “ወንድሞቹ” የሚለው ሐረግ   የቅድስት ድንግል ማርያም  ክብሯ (1) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ድንግል እመቤታችንን አያከብሩም፤ ደግሞም እንድታማልድላቸውም (እንድትማልድላቸውም)  አይጠይቋትም።ከእነርሱ ወገኖች አንዳንዶቹ እንዲያውም ጫጩቱ ከተፈለፈለ በኋላ ዋጋ ከሌለው የዶሮ እንቁላል ቅርፊት ጋር እስከሚያመሳስሏት ይደርሳሉ።ይህ የተጋነነ ማቃለል የመጣው ምናልባት ሮሜዋውያን ካቶሊኮች የተጋነነ ማክበር ስለሚያከብሯት ለዛ ተቃርኖ ከማሳየት አዝማሚያ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን አንዱንም የእርሷን በዓል አያከብሩም።  (2) አንዳንዶቹ የፕሮቴስታንት ወገኖች ድንግል ማርያምን “እህታችን” ይሏታል። (3) በተጨማሪ አንዳንዶቹ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ጌታ ኢየሱስን በድንግልና ከወለደች በኋላ ከዮሴፍ ጋር ጋብቻዋን ፈጽማለች፤ የ‘ኢየሱስ ወንድሞች’  ወይም የ’ጌታ ወንድሞች’ ተብለው የተጠሩ ልጆችን ወልዳለች ይላሉ።  (4) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ቤተክርስቲያናችን ለድንግል እመቤታችን የሰጠቻቸውን አንዳንድ የማዕረግ ስሞችም ይቃወማሉ።  (5) ድንግልን ያለማክበራቸው አንዱ...

ስለ "አስታዋሽ ጾምና በዐሉ" ጥያቄና መልስ

 ስለ "አስታዋሽ ጾምና በዐሉ" ጥያቄና መልስ  ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ፦ ሕልውናችንን-ነጻነትችንን የማረጋገጥና የማስቀጠል አንድነታችንን የመጠበቅና የማጠንከር  በእሴቶቻችን የመደሰት፣ እነርሱን የመንከባከብና የማስተዋወቅ  በረከታችንን የማብዛትና የማካፈል  ኃላፊነቶቻችንን በማኅበር ፣ በማስተዋልና በትጋት እንድንወጣ “ጾሙና በዐሉ" አስታዋሽ ባሕላዊ ምልክታችን ይሁንልን   ጥያቄ 1 ፡ አድማጭ ተመልካቾቻችን እንኳን ደህና መጣችሁ።የከበረ ሰላምታችን ይድረሳችሁ። ዛሬ የምንወያየው ከአቶ ባንቱ ገብረማርያም ጋር ይሆናል። አቶ ባንቱ በሙያው ፋርማሲት ነው። እንደነገረኝ በእምነቱ ደግሞ ባፕቲስት ነው።ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ባሕላዊ ምልክት የሚሆን “ጾምና በዐልን” በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል። የምንወያየውም ስለዚሁ "ጾሙና በዐሉ" ምልክትነት ይሆናል።  አቶ ባንቱ ለመወያየት  ወደ እኛ በመምጣትህ አመሰግንሃለሁ። እንኳን ደህና መጣህ። አንተ እያልኩ ልቀጥል ወይስ አንቱ? መልስ 1፡ ዎገኔ፡   እንኳን ደህና ቆየኸኝ። ለአድማጭ ተመልካቾቻችሁም ሰላምታዬ ይድረስልኝ። አንተ በለኝ። የሚያውቀኝ ሁሉ አንተ ነው የሚለኝ።  ጥያቄ 2 ፡ እሺ  አንተ እያልኩ እቀጥላለሁ። አቶ ባንቱ፣ ምናልባትም ብዙ ሰው ስለማያውቅህ  እስቲ ስለራስህ በአጭሩ ንገረን። ወዲያውም መክፈቻ ይሆነናል መልስ 2 ዎገኔ ፦ አስቀድሜ ይኸን ዕድል ስለሰጠኸኝ ላመሰግንህ እወዳለሁ። አድማጭ ተመልካቾችህንም ጊዜ ወስደው  ውይይቱን  ስለሚከታተሉ ላመሰግናቸው እወዳለሁ።አዎን፣ ባንቱ ገብረማርያም እባላለሁ።እንደነገሩኝ የተወለድኩት ሽርካ በዛሬ አጠራሩ በአርሲ ዞን ነው።ነፍስ ያወቅሁትና ትምህርት ...