ፋኖ ፡ በኢትዮጵያ የሃያ አንደኛው ምዕተ ዐመት ልዩ ክስተት
የኢትዮጵያን ሁኔታ ከዜና አቅራቢዎች እንደሚከታተል ሰው በዚችው ጥቂት ዕድሜዬ በርካታ ፓለቲከኞች ተነስተው አይቼአለሁ። አስተዋጽኦዋቸውን በጓዳዬ ያደነቅኋቸው ብዙ ናቸው። ከእነዚህ መኻል ባስቀመጥኳቸው ሥፍራ ያላገኘኋቸው አሉ።ድርጅቶቻቸውም እንደዚያው የሆኑባቸው። ያዘንኩላቸውም ያዘንኩባቸው ይኖራሉ። ችግራቸውንና ፈተናቸውን እነርሱ ያውቃሉ። እኔ በሩቅ ሆኜ የምከታተል ስለሆንኩ እሳቱ ምን ያህል እንደፈጃቸው ልረዳላቸው አልታደልኩም።
አሁን ላይ ከእነዚህ መኻል የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹን ለማዳን ኃላፊነቱን በሚገባ እየተወጣ ያለውን ፋኖ፣ ለመለወጥ ወይም ለማደናቀፍ ወይም ጠልፎ ለመጣል የሚሠሩትን ግን ተቀይሜአቸዋለሁ። የዐማራ ስቃይን ለዘለቄታው ማስወገድ እስከቻለ ድረስ ማንስ ፋኖን ቢመራው ምን ቸግሯቸዋል? ቀጥታ በተጋድሎው ሥፍራ ላይ ያሉት የፋኖ መሪዎች ያጎደሉት ምን ኖሮ ነው? እንደ እኔ ዐሳብ ይህን ትተው በመተባበሩ ላይ ቢያተኩሩ ለሁላችንም ድንቅ ይሆናል እላለሁ። ደግሞ ይኸንን ያጡታል ብዬ አላስብም። መተባበሩን ይመርጣሉም ብዬ አምናለሁ።
ለማንኛውም በስፋት ሲዘገብ እንዳገኘሁት ፋኖዎች
ሞትን ሳይፈሩ፥ ደፍረው ፥ በነፍሳቸው ቆርጠው
ጉልበታቸውን በደሊላዎች ሳያደክሙ
ገንዘብንም ሎሌያቸው እንጂ ገዥያቸው ሳያደርጉ
በቅርብም በሩቅም ባሉ ወንድሞቻቸው የሸፍጥና የኅይል ሥራ ሳይርዱ
የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ እንዳይጐዳ እየተጠነቀቁለትና እርሱም እየደገፋቸው
አብዛኞቹ መሪዎቹ ለዐማራ ሕዝብ በረከት ሲሉ የግል ኢጎአቸውን በመዋጥ ወደ መተባበርና ማበር እየተመነደጉ
የፊት ለፊት አጥፊዎችንና አጥቂዎችን ሁሉ ተቋቁመው ተገዳዳሪ ኅይል ሆነው ወጥተዋል። ይህ በኢትዮጵያ የ21ኛው ምዕተ ዐመት ልዩ ክስተት ነው እላለሁ። ፋኖዎች እዚህ ላይ በመድረሳቸው እጄን በአፌ ላይ አስጭነውኛል። እንዳውም መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ሳያግዛቸው አልቀርም እላለሁ።
(ነፍሳቸውን ይማርና) ፕሮፌሰር መስፍን ያኔ ጎንደር -ጎጃም -ወሎ -ሸዋ እየተባለ ይጠራ ስለነበረው አካባቢ በአንድ የጥናት ጉባኤ ላይ የተናገሩትን አስታውሳለሁ። “አገሪቷ ያሏት ምርጥ ተዋጊዎች የሚገኙበት አካባቢ ነው” ሲሉ ሰምቼአቸው ነበር። ታዲያ ያንን ሰምቼ “ዐማራው ይኽን ያህል መከራ ሲያይ፣ በሥጋት ታጥሮ እየተዋከበ እያዩት ፥የተባሉት ተዋጊዎች የታሉ”? እያልኩ እኖሮ ነበር። የዐርበኛ ጎቤ ብቅ ማለት ለመጀመሪያ ጊዜ ለዚህ ጥያቄዬ መልስ ሆነኝ። “ጀግና ሸክላ ነው” ማለት እውነት ነው መሰለኝ ብዙም ሳይቆዩ ተሰውተዋል (በወቅቱ የቅርብ ዘመዴ የሞተ ያህል ሃዘን ተሰምቶኛል)። ‘በአምላኩ ተሰማ’ የሚል ቅጽል ስም ለራሴ እንዳወጣ ምክንያት ሆነውኝ አልፈዋል። ለካንስ እነሻለቃ መሳፍንትም ኖረዋል (የለውጥ በሩ ተበርግዶ ከተጋድሎው ሥፍራቸው ብቅ ያሉ ጊዜ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌቪዥን መስኮት ያየኋቸውና ያወቅኋቸው)። እነዚህ ፈር የቀደዱለት የመሰለኝ አዲሱ ፋኖነት ዛሬ እልፍ አእላፋትን ማርኳል።የአብርሃም አምላክና አምላካችን ለመጨረሻው ድል ያብቃው።
አዎን በልጅነቴ እንዳየሁት ኢትዮጵያውያን በፍቅር መኖር እንድንችል በሩን ለመክፈት ያብቃው።
ቸር እንሰንብት!
ዎገናችሁ ነኝ
Comments
Post a Comment