Skip to main content

“የአቤል ደም” እና “አብረን ሰው እንሁን”

“የአቤል ደም” እና “አብረን ሰው እንሁን”

መግቢያ
   የ“አቤል ደም” ጸሐፊ አባ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑ ፤ የ”አብረን ሰው እንሁን” ጸሐፊ ደግሞ ሰለሞን ጥላሁን (ፓስተር) የኢትዮጵያ ወንጌል አማኝ ነው።

    የ"አቤል ደም" በእጄ የገባው በመሸጪያ ድንኳኑ ፊት ለፊት ሰልፍ አይቼ ፣ “ምን ቢሆን ነው” በማለት ሰልፉን ተቀላቅዬ ነው (በአትላንታው በአሜሪካ የኢትዮጵያውያን እስፖርትና ባህል በዐል ላይ ማለት ነው)።“አብረን ሰው እንሁን”ን ያገኘሁት አንድ ወዳጄ ልኮልኝ ነው (በዚህ አጋጣሚ ፓስተር ሰለሞንን አንድ ቅጂ ደርሶኛል አመሰግናለሁ ማለት እወዳለሁ)።

      የአቤል ድምጽ እጄ ከመግባቱ ከሁለት ሳምንት ቀደም ብዬ “አብረን ሰው እንሁን”ን አንብቤው ነበር። የጽሑፌ ርዕስ ይኸንኑ የንባቤን ቅደም ተከተል (ከፊት ወደ ኋላ) የሚያንጸባርቅ ነው።

        የመጽሐፍ ሐያሲ አይደለሁም። የምጽፈው ለማሔስ አይደለም፣ የተጻፈው ሁሉ ገብቶኛል፣ ዘልቄዋለሁ ብዬም አይደለም።ለወገኑና ለአገሩ ችግር መፍትሔ ተገኘ ብሎ ሰፍ እንዳለ ሰው በ"ፈጣን ንባቤ" ከመጽሐፎቹ የጨበጥኩትን ያህልና የተሰማኝን ለማካፈል ነው። በሳትሁትና በተሳሳትሁት ለመታረምና ለመማር ዝግጁ ነኝ

ከመጽሐፍቱ የተማርኩት

     ሁለቱም መጽሐፎች በርካታ ገጾች በመያዛቸውና ዐሳቦቹም ለእኔ አዲስ በመሆናቸው በማነብበት ወቅት በማስመር፣ በማድመቅ፣ በማክበብና በጥያቄ ምልክት ሞልቼአቸዋለሁ።

      ያለጥርጥር እጅግ ብዙ የተደከመባቸው ናቸው።በንባቤ እንደተረዳሁት ከሆነ ሁለቱም ጸሐፊዎች “እኛን ኢትዮጵያውያንን ሰው እንሁን” ብለው ጋብዘውናል። የአቤል ደም ጸሐፊ “ሰው” የሚሉት አስተሳስቡና አካሄዱ በገነት ከመውደቁ በፊት ወደ ነበረው ክብሩ የተመለሰውን እንደሆነ ተሰምቶኛል።“አብረን ሰው እንሁን” ደግሞ “ ሰው” ማለቱ በንኡስ ማንነት (ጾታ፣ ቀለም፣ ብሔር ወዘተርፈ) ከመውረድ ወጥቶ ትልቅ ማንነቱ ማለትም “”መለኮት ሰጥ” የሆነ ክብር ያለውን ማለቱ እንደሆነ ተሰምቶኛል።

     የአቤል ደም ጸሐፊ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የደረሰው ጉስቁልና ፣ ግፍ፥ ሰቆቃና መሪር ጩኸት እንዳመመው፣ እንደ አስለቀሰውና እንዳሳስበው እረኛ የጻፋት ነው።በለቅሶ ስሜት ታጭቋል።የአብረን ሰው እንሁን ጸሐፊ ግን ስለ ግጭቶች ያለውን ሳይንሳዊ ዕውቀት የተነተነበት ነው።

     “የአቤል ደም” ጸሐፊ አግባብ ባለው ሥፍራ ሁሉ “ቃየል” በሚሏቸው (የመንግስት፣ የፖለቲካ እና የቤተክርስቲያን ኅላፊዎች) ላይ ብስጭታቸውንና ወቀሳቸውን ሳያሰሙ አያልፉም። እንዲሁም እንደ “አቤል ደም” ጩኸታቸው ወደ እግዚአብሔር ወጥቷል ለሚሏቸው በከንቱ ደማቸው ለፈሰሰውና ለሚጎሳቆሉት (ለግፉአን) ምስኪን ኢትዮጵያውያን ሃዘነቴያቸውን፣ ርኅራኄያቸውን፣ ቁጭታቸውንና ዕንባቸውን ሳያፈሱ አያልፉም።

       የሰላም መንገዱ (ከጉዳት መውጨያው)፦- ንስሐ መግባት (በንባቤ እንደገባኝ  ኃጢአትን/በደልን /ጉዳትን ማወቅ ማለት ነው፟)--- መናዘዝ (ሰበብ ሳያበዙ ስለበደሉ ኅላፊነትን መውሰድ ማለት ነው)-ኃጢአቱን መተው/መመለስ----ይቅርታን ማግኘትና መስጠት (ቂምን፣ በቀልን መተው ማለት ነው)- እርቅ ማውረድ (የሁለት ወገን መስማማት ማለት ነው) እንደሆነ አስምረውበታል። እነዚህ ምን ማለት እንደሆኑና እንዳልሆኑ ፣ዐይነታቸውን፣ እንዴት እንደሚከናወኑ፣ ተግዳሮቶቻቸው ምን እንደሆኑ ፣ እንዴት እንደሚሰላሰሉ ወዘተርፈ ዝርዝር ዕውቀት አካፍለዋል።

       በማሳያነት፣ በማረሚያነት፣በማበረታችነት፣ በአስረጂነት፣ በአርአያነት ከመጽሐፍ ቅዱስ በርካታ ታሪኮችን እንደ አገባቡ እየጠቀሱ የንስሐ፣ የይቅርታና የእርቅ ጉድዮችን ያፍታታሉ፣ ያብራራሉ። በመስኩ የስመጥር ጸሐፊዎችን ዕውቀትም (ለጸሓፊዎቹ እውቅና በመስጠት) ከመጽሐፍ ቅዱስ ካገኙት ትምህርት ጋር በማዛመድ መልዕክታቸውን አጠንክረው ገምደውታል።አልፎ አልፎ የተረኩት ዛሬ ላይ የሚታወቁ ሰዎች ታሪኮችም የግል ሕይወትን ይበረብራሉ።ለንስሐችን፣ ለይቅር መባባላችንና ለዕርቃችን ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ የተሠራው ሥራና ትምህርቱ መሠረታችንና ምሳሌያችን መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውታል።

      ለዘለቄታዊ ሰላም ማንኛውም ወገን ሥርዐተ እምነቱን (value system) እግዚአብሔርን ማዕከል ያደረገ (theocentric) ፣ ፈሪሐ እግዚአብሔር ያለው (እንደገባኝ በእግዚአብሔር መታመንና እግዚአብሔር የሚደሰትበትን ፈቅዶ ማድርግ፣ የማይደሰትበትን ከማድረግ ቆርጦ መራቅ ነው) ወደ ማድረግና መሆን እንዲመለስ ይመክራሉ።

       አብረን ሰው እንሁን ጸሐፊ ደግሞ ግጭት ልውጠታዊ (ከአባ ኮስኳሴ ቢራቢሮ እንደሚወጣ እንዳለው) ሊሆን እንደሚችልና እንዴት እንደሚደረግ፣ ሰላምም የሚገነባ ጉዳይ እንደሆነና እንዴት እንደሚገነባ እንዲሁም ስለ ግጭት ተያያዥ ጉዳዮችን አሳምሮና ከሽኖ ተንትኗል፣ አስተምሯል። በየሥፍራው የሰጠው ዕጣሬና የግንዛቤ ጥያቄ (አንዳንዴ ለአንዱ ምዕራፍ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ለሁለት ምዕራፎች አያጣመረ) መጻፉ ዐሳቡን ለመከለስና ለማሰላሰል የሚጋብዝ ነው። አንባቢዎቹ ዐሳቡን እንደተረዱለት እርግጠኛ ለመሆን ያደረገው ጥረት ሆኖ ተሰምቶኛል። ጥንቅቅ ያለ አቀራረብ ነው።

           ሁለቱም ጸሐፊዎች (በተለይ የ”አብረን ሰው እንሁን፡ ጸሐፊ”) ለመዳበሩ እንዲሆን ዐማርኛ ቋንቋን ሆን ብሎ ዐልሚ ምግብ መግቦታል።

የራሴ ድምዳሜ፦ የአቤል ድምጽ ማዕከሉ (በአመዛኙ ለማለት ነው) ለልባችን፣ የ"አብረን ሰው እንሁን” ደግሞ ማዕከሉ ለአእምሯችን መናገር ሆኖ ከሚታይ በስተቀር ሁለቱም ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው መሆኑ በግልጽ ይነበባል። ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳሰቡለት «እግዚአብሔር ያስብላቸው ፣ ሰሚ ይስጣቸው!»እላለሁ።፣

በተያያዘ፦ በወንጌላውያን የተጻፋትን ኦርቶዶክሳውያን ፥ በኦርቶዶክሳውያን የተጻፋትን ወንጌላውያንን ቢያነቡ ይጠቅም ይሆን? በዚህ ርዕስ ላይ ከሙስሊም ወገኖች የተጻፈ ካለ ለማንበብ አልቦዝንም።

እግዚአብሔር ይስጥልኝ። ቸር እንሰንብት

ባንቱ ገብረማርያም

ይህን ከለጠፍኩ በኋላ የ"አብረን ሰው እንሁን" ጸሐፊ ከዚህ ዓለም ድካም ማረፉን ሰምቼ አዝኛለሁ። ለመላው ቤተሰቡ መጽናናትን ይስጥልኝ።

Comments

Popular posts from this blog

Comparative Theology የነገረ መለኮት ንጽጽር (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት)/ በብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሲኖዳ ሳልሳዊ

 የነገረ መለኮት ንጽጽር  (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት): የወደደ  ሁሉ በነጻ እንዲጠቀምበት ተፖስቷል። ይሁን እንጂ መብቱ በሕግ የተጠበቀ ስለሆነ በየትኛውም መልኩ ለንግድ እንዲውል አልተፈቀድም። ልዩ ልዩ መግቢያ የሚለውን መጀመሪያ ካነበቡ በኋላ የተቀረውን በተመረጠው ቅደም ተከተል ማንበብ ይቻላል። ልዩ ልዩ መግቢያ   ጥምቀት   ትውፊት (ወግና ልማድ)   መካከለኝነት   ጾም የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ መንፈሳዊ ስጦታዎችና በልሳኖች የመናገር ስጦታ   ሥርዐት ንስሐ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ (1)  ድንግል ማርያምን ስለማክበር (2) ለጥያቄዎች መልስ (ሀ) ድንግሊትን ‘የወይን ግንድ (ተክል)’ና የ ‘ሕይወት በር’ የሚል ማዕረግ  ለምን እንሰጣታለን? (ለ) ወደ ድንግል ማርያም መጸለይ ትክክል ነው ወይ? (3) የድንግል ማርያም ድንግልና ዘላለማዊነት (4) ለተቃራኒ አስተያየቶች መልስ (ሀ) “የመጀመሪያ ልጇን” የሚለው ሐረግ (ለ) “ሚስትህ” የሚለው ሐረግ (ሐ) “አብረው ከመሆናቸው በፊት ጸንሳ ተገኘች” (መ) “የመጀመሪያ ልጇን እስክትወልድ አላወቃትም” (ሠ)  “ወንድሞቹ” የሚለው ሐረግ   የቅድስት ድንግል ማርያም  ክብሯ (1) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ድንግል እመቤታችንን አያከብሩም፤ ደግሞም እንድታማልድላቸውም (እንድትማልድላቸውም)  አይጠይቋትም።ከእነርሱ ወገኖች አንዳንዶቹ እንዲያውም ጫጩቱ ከተፈለፈለ በኋላ ዋጋ ከሌለው የዶሮ እንቁላል ቅርፊት ጋር እስከሚያመሳስሏት ይደርሳሉ።ይህ የተጋነነ ማቃለል የመጣው ምናልባት ሮሜዋውያን ካቶሊኮች የተጋነነ ማክበር ስለሚያከብሯት ለዛ ተቃርኖ ከማሳየት አዝማሚያ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን አንዱንም የእርሷን በዓል አያከብሩም።  (2) አንዳንዶቹ የፕሮቴስታንት ወገኖች ድንግል ማርያምን “እህታችን” ይሏታል። (3) በተጨማሪ አንዳንዶቹ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ጌታ ኢየሱስን በድንግልና ከወለደች በኋላ ከዮሴፍ ጋር ጋብቻዋን ፈጽማለች፤ የ‘ኢየሱስ ወንድሞች’  ወይም የ’ጌታ ወንድሞች’ ተብለው የተጠሩ ልጆችን ወልዳለች ይላሉ።  (4) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ቤተክርስቲያናችን ለድንግል እመቤታችን የሰጠቻቸውን አንዳንድ የማዕረግ ስሞችም ይቃወማሉ።  (5) ድንግልን ያለማክበራቸው አንዱ...

ከቄስ ( ዶ/ር ) ቶሎሳ ይልቅ

 አድማጭ ተመልካቾቼ አንደምን ከረማችሁ? የአብርሃም አምላክና አምላካችን የተመሰገነ ይሁንና እኔ ደህና ነኝ።"ከቄስ (ዶ/ር ) ቶሎሳ ይልቅ" በሚል ርዕስ ያዘጋጀሁትን  የሚከተለውን መልዕክቴን እንድትከታተሉልኝ በታላቅ አክብሮት እጠይቃችኋለሁ። ባንቱ ገብረማርያም ነኝ ከቄስ (ዶ/ር) ቶሎሳ ይልቅ           ቄስ (ፓስተር) ዶ/ር ቶሎሳ  ጉዲና የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን በአትላንታ/ጆርጂያ ፓስተር መሆናቸው በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ይመስለኛል። በበኩሌ የማከብራቸውም ሰው ናቸው። በወንጌላውያን መኻል ለበርካታ ዐመታት ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የተናገሩ፣ ያሳሰቡና የጸለዩ መሆናቸውን ሰምቼአለሁ።በነገዳቸው የተደራጁትን የወንዛቸው ልጆችን ወቀሳ ተቋቁመው ለመላው ኢትዮጵያዊ ሲጮኹ የኖሩ ናቸው።           ስለ እሬቻ የሰጡት ትምህርት እስከዛሬ እንደሞዴል የማየው ነው። እሬቻን እንዳይከተሉና እንዳያስፋፉ የአሁኖቹን የመንግሥት ዐላፊዎች የመከሩበትንም ጊዜ አስታውሳለሁ።           የወንጌላውያን ሽማግሌ ብቻ ሳይሆኑ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌ አድርጌ አያቸዋለሁ። ይህን መደላድል የማስቀምጠው ስለእርሳቸው ያለኝን አስተያየት ለማስታወቅና ይኸው ሐሳቤ የጸና መሆኑን ለማስጮህ ነው።አስተያየቴን አልጠየቁኝም፣ የሚጨምርላቸውም ሆነ የሚቀንስባቸው ነገር እንደማይኖርም ጠንቅቄ አውቃለሁ። መደላድሉን አስቀድሜ  ማስቀመጤ ወንድሞችንና እህቶችን “አይዟችሁ አትደንግጡ” ለማለት ያህል ነው። ...