Skip to main content

ስለ "አስታዋሽ ጾምና በዐሉ" ጥያቄና መልስ

 ስለ "አስታዋሽ ጾምና በዐሉ" ጥያቄና መልስ 

ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ፦

ሕልውናችንን-ነጻነትችንን የማረጋገጥና የማስቀጠል

አንድነታችንን የመጠበቅና የማጠንከር 

በእሴቶቻችን የመደሰት፣ እነርሱን የመንከባከብና የማስተዋወቅ 

በረከታችንን የማብዛትና የማካፈል 

ኃላፊነቶቻችንን በማኅበር ፣ በማስተዋልና በትጋት እንድንወጣ “ጾሙና በዐሉ" አስታዋሽ ባሕላዊ ምልክታችን ይሁንልን  

ጥያቄ 1 አድማጭ ተመልካቾቻችን እንኳን ደህና መጣችሁ።የከበረ ሰላምታችን ይድረሳችሁ።

ዛሬ የምንወያየው ከአቶ ባንቱ ገብረማርያም ጋር ይሆናል። አቶ ባንቱ በሙያው ፋርማሲት ነው። እንደነገረኝ በእምነቱ ደግሞ ባፕቲስት ነው።ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ባሕላዊ ምልክት የሚሆን “ጾምና በዐልን” በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል። የምንወያየውም ስለዚሁ "ጾሙና በዐሉ" ምልክትነት ይሆናል። 

አቶ ባንቱ ለመወያየት  ወደ እኛ በመምጣትህ አመሰግንሃለሁ። እንኳን ደህና መጣህ። አንተ እያልኩ ልቀጥል ወይስ አንቱ?

መልስ 1፡ ዎገኔ፡  እንኳን ደህና ቆየኸኝ። ለአድማጭ ተመልካቾቻችሁም ሰላምታዬ ይድረስልኝ። አንተ በለኝ። የሚያውቀኝ ሁሉ አንተ ነው የሚለኝ።

 ጥያቄ 2 እሺ  አንተ እያልኩ እቀጥላለሁ።

አቶ ባንቱ፣ ምናልባትም ብዙ ሰው ስለማያውቅህ  እስቲ ስለራስህ በአጭሩ ንገረን። ወዲያውም መክፈቻ ይሆነናል

መልስ 2 ዎገኔ፦ አስቀድሜ ይኸን ዕድል ስለሰጠኸኝ ላመሰግንህ እወዳለሁ። አድማጭ ተመልካቾችህንም ጊዜ ወስደው  ውይይቱን  ስለሚከታተሉ ላመሰግናቸው እወዳለሁ።አዎን፣ ባንቱ ገብረማርያም እባላለሁ።እንደነገሩኝ የተወለድኩት ሽርካ በዛሬ አጠራሩ በአርሲ ዞን ነው።ነፍስ ያወቅሁትና ትምህርት የጀመርሁት ባሌ ስለሆነ ራሴን እጆሌ ባሌ እያልኩ ነው የምጠራው። በሙያዬ ፋርማሲስት ነኝ። በዚህ ሙያዬ ለ40 ዓመታት ያህል እየተዛወርኩ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ሠርቼአለሁ። አድማጭ ተመልካቾቻችን  ምናልባት ስለ ቤተ እምነቴ ለማወቅ የሚፈልጉ ቢሆን  በእምነቴ  ባፕቲስት ስሆን ወንጌላዊ አብያተ ክርስቲያናት ከሚባሉት ጋር የሚቆጠር ነው። ያም ሲሆን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስስ ልብ አለኝ። 

ጥያቄ 3፡ በጣም ጥሩ።አመሰግናለሁ። አሁን በቀጥታ ወደ "ጾሙና በዐሉ" ጉዳይ እንገባለን።

ምልክት ሆኖ የሚተከል በተለምዶ ግዑዝ ነገር ሲሆን (ለምሳሌ ሐውልት) ዐላማውም ያለፈን ታሪክ ማስታወስ ነው። እንደነገርከኝ አንተ እንዲተከል የምትፈልገው ባሕላዊ  ምልክት ግን ለየት ያለ ነው። ግዑዝ ነገርም አይደለም፣ የሚታወሰውም ነገር ያለፈ ታሪክ አይደለም። እስቲ ስላሰብከው ባሕላዊ  ምልክት በአጭሩ ንገረን

መልስ 3:

አዎን ግዑዝ ነገር አይደለም። የሚያስታውሰውም ሊሠራ (ሊፈጸም) ስለሚገባው ሥራ ነው።ባሕላዊ ዘዴ አድርጌ የምቆጥረው ይኸው ምልክት፣ ዓመታዊ "ጾምና በዐል" ሲሆን የዐማራን ሕዝብና ዎገኖቹን የጋራ የሆኑትን አራቱን ግዙፍ ኃላፊነቶቹን በማህበር፣ በማስተዋልና በትጋት እንዲወጣ የሚያስታውሰውና የሚያሳስበው ነው፣

ሁሉም ሃይማኖት ተከታዮችና የሚከተሉት ሃይማኖት የሌላችውም ይሳተፉበታል። ማለትም ኦርቶዶክሱ፣ ሙስሊሙ ፣ ወንጌላዊው፣ ካቶሊኩ፣ ይሁዲ እምነት ተከታዩ ፣ ባሕላዊ እምነት ተከታዩ፣ ምንም ሃይማኖት የሌለውም የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ በአንድነት ይሳተፉበታል።

ጥያቄ 4:

አራቱ ግዙፍ ኅላፊነቶች ስትል ምን ማለትህ ነው?

መልስ 4፡

1. ሕልውናን-ነጻነትን ማረጋገጥና ማስቀጠል

2. አንድነትን መጠበቅና ማጠንከር

3. በእሴቶቹ መደሰት፤ እነርሱን መንከባከብና ማስተዋወቅ

4. በረከትን ማብዛትና ማካፈል ናቸው።

 ጥያቄ 5; እንዴት እንዴት አድርጎ ነው ይኸን ሁሉ "ጾምና በዐል" ሊያስታውስ የሚችለው?

መልስ 5: ስለዚሁ ሙሉ አስረጂውን ማለትም

1.ጾሙና በዐሉ ከእነዚህ ጋር ምን እንደሚያገናኘውና ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ እንዴት እንዳስማማሁት፣

2. በጾሙና በዐሉ ሰሞን የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ምን ሊያከናውን እንደሚችል

3. የተለያዩ እምነት ያላቸውና እምነት የሌላቸው የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ሁሉ እንዴት አንድ ላይ ሊጾሙና በዐልን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ለማስረዳት የሞከርኩበት መሰናዶ  አለ።

4. እንዲሁም የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ  "የተወራረሱ እሴቶችና ታላሚ በረከቶች" ዝርዝር አሰናድቼአለሁ።እነዚህ ሁሉ ረዘም ያለ ጊዜ ስለሚወስዱ ምናልባት እነርሱን ዛሬ በዝርዝር ልንነጋገርባቸው አንችልም። በአዎን ድምፅ ማህበራዊ ሚዲያ  የሚቀርቡ ይሆናሉ።

 ጥያቄ 6፡ መልካም  እንዳመችነቱ የምናደርገው ይሆናል። ኅላፊነቶቹ ግን እነዚህ ናቸው ማለት ነው። ለመሆኑ "ጾሙና በዐሉ" ምን ቀን ላይ እንዲውል ነው ያሰብከው?

መልስ 6፡ ከአድዋ ድል በዐል ጋር አያይዞ ማድረጉ ትክክል ሆኖ ስለተሰማኝ የዋዜማው ቅዳሜ ዕለት በየዐመቱ ይሆናል። 

ጥያቄ 7:ለምን ተሰማህ?

መልስ 7: እንደሚታወሰው የአድዋ ድል የዐማራ ሕዝብ እርስ በእርሱ እንዲሁም ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ዎገኖቹ ጋር አብሮና ተባብሮ ድንቅ ታሪክ የሠራበት አጋጣሚ ነው። ያንን ሁኔታ  የመናፈቄ ልክ ነው ይኸንን ጊዜ ያስመረጠኝ።

 ጥያቄ 8: ይህን ዐመታዊ "ጾሙና በዐሉ"ን እንዴት አሰብከው?

መልስ 8 የተፈናቃይን  ነገር ከተለያዩ የወሬ ምንጮች በየጊዜው  እሰማ ነበር። በሰማሁ ቁጥር ያሳዝነኝም ያሳስበኝም ነበር። የመጀመሪያው ትዝታዬ በደርግ ዘመን ከትግራይ የተፈናቀሉት ነበሩ። ያን ጊዜ ከትግራይ ልጆች ጋር ቅርበት ስለነበረኝ ምን ያህል የሚረብሽ ነገር እንደሆነ አይቼላቸዋለሁ።

የደርግ መንግሥት እንደወደቀ ስለተበተነው ሠራዊትና ቁጥሩ እጅግ የበዛ ቤተሰብ የነበረኝ ስሜት እስካሁን ትኩስ ነው።

በዚያ ጊዜ አዲስ በነበረው የኤርትራ አስተዳደር የተፈናቀሉትን /የተባረሩትን ኢትዮጵያኖች መከራም አስታውሳለሁ።

ከዚያ በኋላ ደግሞ በኢሕአዲግ መንግሥት ኤርትራውያን ከኢትዮጵያ ተፈናቀሉ/ተባረሩ። ማፈናቀል የሚሉት ነገር ማኅበራዊ ቀውስ የሚያስከትልና በጭራሽ መኖር የሌለበት ችግር መሆኑ በነዚያ ጊዜያት ተሰማኝ።

የመንግሥት አስተዳደሩ ኃላፊነት የኢሕአዲግ በነበረበት ጊዜ ሌሎችም ነገዶችና ጎሳዎች በግድ ተፈናቅለዋል። ሶማሌው፣አፋሩ፣የደቡብ ኦሞና የጋምቤላ ሕዝቦች በነባርነት ከሠፈሩባቸው መሬቶቻቸው፣ኦሮሞ ከአዲስ አበባ ዙሪያና በኋላም ከሶማሌ ክልልም እንዲፈናቀሉ ተገደዋል። ጉራጌ ከንግዱ ተነቅሏል።

መንግሥቱን የሚመሩት የኢሕአዲግ ሰዎች በተቀየሩ ጊዜና ጾሙን ካቋረጥኩ በኋላ ደግሞ የቅማንት ፣ የወላይታ፥ የኮንሶ፣ የገሙ ሰዎችም በኃይል ሥራ መፈናቀል ደርሶባቸዋል። በእነዚህ ሁሉ የደረሰው የሚያሳዝን ሲሆን ዐማሮች በብዛት የተሳተፋባቸው ድርጅቶች እና /ወይም ሌሎች ድርጅቶች በየወቅቱ ድምጻቸውን አሰምተውላቸዋል።

ዐማሮችን በተመለከተ ድግሞ  ከበደኖና ከአርባ ጉጉ ኃላፊነቱን መውሰድ በሚገባቸው ድርጅቶች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል/ተፈናቅለዋል።በጊዜው የእነዚህም ሰቆቃ ትኩረት አግኝቷል።

ከሌሎች ሥፍራዎችና ከሥራቸውም ላይ በግዳጅ የተፈናቀሉም ሲሆን ከሥፍራቸው ከተፈናቀሉት መኻል የጉራ ፈርዳዎቹ ይገኙበታል።ከጥቂት ድርጅቶችና ግለሰቦች በስተቀር አሳሳቢነቱን በሚመጥን ልክ የእነዚህ ዐማሮች ችግር የታወቀላቸው ሆኖ አልተሰማኝም። ጩኸታቸው እንደሚገባው ባለመሰማቱ አዘንኩ።ሌላ ነገር ለማድረግ ባለመቻሌ ስሜታቸውን ለመጋራት ብችል በማለት ለሁለት ዓመት ያህል በተከታታይ ቁርሴን መጾም ጀመርሁ።በዚያ ነው የመጾም ነገር የታሰበኝ። የሚያሳዝነው ግን ዐማራና ዎገኖቹን በግዴታ ማፈናቀሉ ዛሬ ላይ መባባሱና እንዳውም የጭካኔ ግድያን ሁሉ ያካተተ መሆኑ ነው።

ከባለሙያዎች እንደምሰማው ዘር ማጥራት፤ ማጽዳትም ይሉታል።

ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ አደራን የተቀበሉት የመንግሥት ዐላፊዎችም በዳዩ በይፋ እንዲታወቅ፣ ወሬውም እንዲሰማ እንኳ የማይፈለጉ ስለሚመስል የባሰውን ግራ የሚያጋባ ነው።

ጦርነቱ በግራም- በቀኝም፣ በፊትም- በኋላም ያስከተለው ማፈናቀልማ ስንቱ ይነገራል? ወደፊት የሚለወጥ ነገር ይኖር እንደሆን ነው እንጂ የእስካሁኑ ወሬው እንኳ ለመስማት የሚሰቀጥጥ ነው።

(በነገራiችን ላይ በጌታ ወንድሞቼ (በዘልማድ ፕሮቴስታንት የሚባሉት) በመንግሥታዊ አመራር ውስጥ ለመሥራት ገብተው ስመለከት የማፈናቀሉ ችግር ይወገዳል ብዬ እንደ መመካትም ቃጥቶኝ ነበር። የሆነውና እየሆነ ያለው ግን ለማመን የሚያስቸግር ነው)

ጥያቄ 9ከጉራፈርዳ ስለተፈናቀሉት የጾምከው ጾም ፥ ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ  አሁን ለምታስተዋውቀው "ጾሙና በዐሉ" መነሻ ነው ነው የምትለኝ?

መልስ 9፡ አዎን ! መነሻው እርሱ ነው።ጾም ኅላፊነቶቹን ተደጋግፎ መወጣትን እንዲያስታውስ ያስማማሁት ግን በሂደት ነው። አንድ ጊዜ ስለ ጾም የተማርኩትን በአንድ ቤተክርስቲያን አካፍዬ ነበር። ቁርሴን በምጾምበት ዘመን ያንን ትምህርት አስፍቼ ሳየው ከራሴ አልፎ ማኅበረሰቡም እንዲገለገልበት ማድረግ እንደሚቻል ታየኝ። በየጊዜው ከተከታተልኳቸው ሐተታዎችና ትንታኔዎች የማፈናቀሎቹ ሁሉ መነሻዎቹ (ምንጮቹ) ዐማራን ማግለልንና መጉዳትን ያዘሉ የትግል መግለጫዎች  መሆናቸውን እሰማ ነበር (ይህ አለመሆኑን የሚያስተባብል ታማኝነት ያለው ድምጽ እስካሁን አልሰማሁም)። "ያማ ከሆነ ለዐማራ ሕዝብ ዎገንነት መሥራት ለሁሉም ዎገን በግዴታ ከመፈናቀል መትረፊያም፣ የኢትዮጵያን ችግር መቀልበስሺያም ይሆናላ" የሚል ግምት ኖረኝ። በዚህም ምክንያት ለማኅበረሰቡ እንዲያገለግል ያሰብሁትን ጾም የዐማራ ሕዝብ ዎገንነት በሚያደምቅ መልኩ ቀረጽኩት።

 ጥያቄ 10፡ ስለ ጾሙና በዐሉ በኋላ እንመለስበታለን። የዐማራ ትርጉም ማጨቃጨቁ ስለሚሰማ ለመሆኑ ለአንተ ዐማራ ማነው?

መልስ 10፡ አንድ ሰው ዐማራ ነኝ እስካለ ያ ይበቃል። ቀድሞ ባያስበውም እስካሁን ዐማራነቱን ለይቶ ያላወቀ ያለ አይመስለኝም።ሲገደል/ሲጠቃ/ሲገለል/ ሲፈናቀል ዐማራ ተብሎ ከሆነ ያ ሰው አማራ ነው።

ጥያቄ 11:እንደዚያ ከሆነ ከዚህ ቀደም መዐሕድ እንዳለው መላው ዐማራ ሕዝብ ማለት አይቻልም ኖሯል? ዎገኖች የሚለው ለምን አስፈለገ?

መልስ  11: "መዐሕድ" ን ካነሳኸው አይቀር ለመላው የዐማራ ሕዝብ የቆረጠ ተጋድሎ ያደረገ የመጀመሪያው ድርጅት መሆኑን ማስታወስ እወዳለሁ። በእኔ ዕይታ ምናልባትም እስካሁን ምትክ ያልተገኘለት ድርጅት ነው ማለት ይቻላል። መሥራቹና መሪው ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ስለሥራቸው ሲመሰገኑ ይኖራሉ። ታዲያ እንደገባኝ መላው ዐማራ የሚለው የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ንዑስ ስብስብ (subset) ተደርጎ ሊታሰብ የሚችል ነው። አፉን በአማርኛ ቢፈታም ዐማራ መባል የማይፈልገውን ምርጫ ማክበርም አለ። ዎገንነቱን ግን ማመን ይቻላል።

የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ያልኩበት መነሻ ምክንያት በተመለከተ ግን

1. ከላይ እንደገለጽኩልህ የዐማራ ሕዝብን ዎገንነት ማድመቅ ማለት በግዳጅ ማፈናቀልን ማስቀረት፣ የኢትዮጵያን ችግር መፍቺያ አቅጣጫም ማለት ሆኖ ተሰምቶኛል።

2. የዐማራ ሕዝብ ሁሉንም የኢትዮጵያና የኤርትራ ነገዶችና ጎሳዎች እንዲሁም ውሕድ ሕዝብ ሁሉ ዎገኔ ነው ብሎ ነው የሚያምነው። እያንዳንዱን እየጠራሁ ማስቀመጥ ስለማይመች በጥቅሉ ዎገኖች ማለት ተገደድኩና ነው እንጂ "የዐማራ ሕዝብና እከሌ ነገድ/ ጎሳ ዎገኑ" እያልኩ አንድ በአንድ ብጠራ ደስ ባለኝ። እኔ በዐማራው ሕዝብ መኻል አንደቆመ ሰው ዎገኖቼ ማለቱ አልከበደኝም።

3. የዐማራ ሕዝብ ማንነቱ ራሱ የተወሳሰበ ነው። የዎገኖቹን ማንነት የማይጋራ ማንነቱ አይታሰብም። በሃይማኖት ከተለያየ ወገን ነው። ስለተዋለደም የተዋለዱትን ማንነት ያነሳል፣ ይይዛል። በቋንቋም እንደተወለደበትና እንዳደገበት አካባቢ አማርኛ ሳይሆን ሌሎች ቋንቋዎችን ወይም ቋንቋንም  ይናገራል። የራሴን ቤተሰብ ጨምሮ ብዙ ቤተሰብ ውስጥ አማርኛ የማይናገር ይገኛል።

ስለዚህ ነው ማንነቱን የዐማራ ሕዝብ ብቻ ከማለት የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ የሚለው የተሻለ የሚገልጠው ሆኖ የተሰማኝ።

ይኼ ሁሉ የመከራ ዶፍ እየወረደበት ሳለ ስለሚወስደው እርምጃ የዐማራ ሕዝብ ግራ የተጋባውም ሁሉ ዎገኑ በመሆኑና በተወሳሰበ ማንነቱ ምክንያት ይመስለኛል።በኃይል እመከላከል ውስጥ ቢገባ እጁን በእጁ መቁረጥ ይሆንበታል። ዝም ቢልም ይጠፋል ። ዎገኖቹም ውሎ አድሮ እንደማይተርፉ ያታየዋል። አዎ ራሱንም ማዳን ማለት ዎገኖቹንም ማዳን እንደሆነ ቢረዳም በዚህ አጣብቂኝ ተይዞ ይዋዥቃል 

የዐማራ ሕዝብ ሲጎዳ ዎገኖቹ ሁሉ ጉዳቱ የራሳቸው መሆኑን ቢገነዘቡትና በሙሉ ልብ ቢያግዙት ግን መዋዠቁም ይገታል፣ ሁሉም ይተርፋሉ። ውጤቱ መልካም ይሆናል ማለት ነው።

አንዳንድ ጊዜ ሳስበው ምናልባት የእነርሱም የተወሳሰበ ማንነት ይሆን ለመደገፍ ችግር የሆነባቸው እላለሁ? ብቻ ይዋል ይደር እንጂ አስበውበትና አስልተው ዎገኖቹ (ነገዶችና ጎሳዎች ውህዶቹም) በሙሉ ልብ የዐማራ ሕዝብን ማገዛቸው አይቀርም ብዬ አምናለሁ።በዚህ አጋጣሚ እስካሁንም በኣስቸጋሪ ሁኔታ ሆነው ይኸንኑ ላደረጉለት አድናቆት እንዳለኝ መግለጥም እወዳለሁ።

ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ልመለስና ተረድቼአቸዋለሁ ብዬ ባሰብኳቸው በሦስቱ ነጥቦች ላይ ቦግ አድርጎ እንዲያበራባቸው ነው የዐማራ ሕዝብ ከማለት ይልቅ የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ማለትን የመረጥኩት።

ጥያቄ 12: ከዚህ ዐሳብህ ጀርባ ያለው እውነተኛ ዐላማ ዐማሮችን ማትረፍ እንጂ ውሎ አድሮ ማፈናቀልን ጨምሮ ዎገኖች የሚላቸውን ጥፋታቸውን ለማስቀረት አይደለም የሚሉ ተቺዎች ቢነሱስ ምን ትመልሳለህ?

መልስ 12 በእርግጥ ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ምሰሶ ነው የምለውን የዐማራውን ሕዝብ የማትረፍ ፍላጎት እንዳለኝ ድብቅ አይደለም።ባለቤቱ ካልጮኸ ጎረቤት አይረዳም እንዲሉ ዎገኑ እንዲደርስለት መጮኼ መሆኑ ምስጢር አይደለም። በምልክቱ በማስተላልፈው መልዕክት ለዐማራው ብቻ መጨነቅ መስሎ ቢታይብኝ አያስደንቅም። ነገር ግን እውን የዐማራ ሕዝብ ለራሱ እንዲሆንለት የሚፈልገውን በጎ ነገር ሌሎቹ በተለይም ዎገኔ ለሚላቸውና ለሚሉት እንዲሆንላቸው አይፈልግም? ታሪኩ የሚያሳየውስ ምንድነው? ዛሬ በተለየ ሁኔታ ተገመገመ እንጂ ያለፈውና በማለፍ ላይ ያለው ትውልድ ለኢትዮጵያ (ለሁሉም ነገድና ጎሳ) ይጠቅማል ብሎ ባሰበው ጎራ ሆኖ ሕይወቱን ያለማመንታት እስከመገበር አልደረሰም? ያ እራሱ ከባድ መሥዋዕትነት ነው። ከዛም አልፎ በራሱ ዘመዶች  ጥፋት ሳይቀር አልተባበረም? ዛሬስ ቢሆን ለኢትዮጵያም ለኤርትራም በጎ ማሰቡን መች ተወ? የዐማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያውያንና ለኤርትራውያን ባለመዋደቅ አይታማም። ለማንኛውም  የዐማራ ሕዝብ ራሱን ከጥቃት ለማዳን የቻለ ጊዜ ዎገኖቹንም አዳነ ማለት ነው። 

ጥያቄ 13: እንደዚያ ከሆነ ለምን የኢትጵያ ባሕላዊ ምልክት አላልከውም?

መልስ 13:አጀማመሪ እንደነገርኩህ (መልስ 9ን ለማለት ነው) ስለሆነ ነው። የዐማራ ዎገን አይደለሁም የሚል ኢትዮጵያዊ እስከሌለ ድረስ፣ ማለትም ሁሉም የዐማራ ሕዝብ ዎገን ነኝ ፣ እንደ አንድ ዎገን ከዐማራ ሕዝብ ጋር አብረን እንኖራለን እስካለ ድረስ አሁንም ቢሆን ምልክቱ የኢትዮጵያ የማይሆንበት ምክንያት አይታየኝም።ለጊዜው ግን በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሲባል የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹን ህመምና ስቃይ ስለሚያድበሰብስና ስለሚደብቅ አልመረጥኩትም። 

ጥያቄ 14፡ ከላይ በሰጠኸኝ መልስ የኢትዮጵያን ልጆች ሁሉ ለዐማራ ሕዝብ ዎገን አድርገሃል። ታዲያ ማን ነው ዎገን ያልሆነ? ማን ቀረ?

መልስ 14፡ እንደ ሕዝብ ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች የዐማራ ሕዝብ ዎገን ናቸው። በእርግጥ ዐማራውን መስዋዕትነት እስከመክፈል በሚደርስ  እርዳታ ቢረዱት ዎገንነታቸው  ከዐማራው ሕዝብ ጋር የመዋሐድ ያህል ይሆናል።የድርጅት አባልን በተመለከተ ግን ያንን ማለት የሚቻል አይመስለኝም። በእኔ ዕይታ ሁለት ሥፍራ እመድባቸዋለሁ። አንደኛው “የዐማራ ሕዝብ ዎገን”  ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “የዐማራ ሕዝብን ዎገኔ ለማለት እያሰበበት ያለ" ነው።

እንደ እኔ አስተያየት ከድርጅት አባል መኻል 

“ዎገን” ብሎ ለመፈረጅ ማሟላት ያለበት መለያ (ማንጠሪያ ) መሥፈርቱ

1. ለራሱ ነገድ ቢቋቋምም ሌላውን ለመጉዳት ያልሆነ ድርጅት አባል ወይም

2. የዐማራ ሕዝብን ሌሎቹንም ሳያማርጥ ዎገኔ የሚል ድርጅት አባል ወይም

3. የዐማራ ሕዝብንም ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችንም ሳያማርጥ (ሁሉንም ማለት ነው) ጠላቴ የማይል ድርጅት አባል መሆኑ ሲሆን

“እያሰበበት ያለ” ብሎ ለመፈረጅ መለያ (ማንጠሪያ) መሥፈርቱ ደግሞ

1.ለራሱ ብሔረሰብ ሲሠራ ሌሎችንም እየጎዳ የሚሠራ ድርጅት አባል ወይም

2. በአንደኛው ብሔረሰብ ላይ ጉዳት ለማስከተል ሲል ሌላውን መርጦ ዎገኔ የሚል ድርጅት አባል፣

3. ዐማራውንም ሆነ ሌላውንም መርጦ ወይም ሁሉንም ጠቅልሎ ጠላቴ የሚል ድርጀት አባል መሆኑ ይሆናል።

ጥያቄ 15 እንዳንተ ሃሳብ “እያሰበበት ያለ” ተብለው የሚፈረጁት አሁን ከሚታወቁት የየትኞቹ ድርጅቶች አባላት ናቸው? ለምን ደፍረህ ጠላት አትላቸውም?

መልስ 15፡ የዐማራን ሕዝብና ዎገኖቹን በመጉዳት በሰፊው የሚከሰሱ ድርጅቶች አሉ።"ዎገኑ"ንና "እያሰበበት ያለውን" ማንጠሪያ (መለያ) መስፈርቱን አስቀምጬ ብቻ ማለፉ ይበቃኛል።

 ጥያቄ 16፡ “ዎገኖቹ” የሚለው ቃል ወላዋይ ያደርጋል ፣ የዐማራን ሕዝብ በራሱ ቁርጥ አድርጎ እንዳይሠራ “ዎገን”ን መጨመር ማዘናጋት ይሆናል ብለው ለዐማራ የተቋቋሙ ድርጅቶች ቢቃወሙህስ? ደግሞም ለሰርጎ ገቦች ቀዳዳ መክፈት ነው ብለው ቢከራከሩህስ?

መልስ 16፡ ስሜቸውን እረዳለሁ። ነገር ግን ዐማራ ዎገኖቹን የመዘንጋት ባሕል አልነበረውም። ወደፊትም የሚኖረው አይመስለኝም። ስለዚህ ለእነርሱም ጭምር መጋደሉ አይቀርም። ይሁን እንጂ የዐማራ ሕዝብ ራሱ ለመጥፋት ወይም ዝንተ ዐለም ለመጎዳት ይመርጣል፣ ይፈቅዳልም ብዬ አላስብም። ምንም ቢሆን ለራሱም መሥራቱ አይቀርም። ወላዋይነቱ ይቀራል።እንደዚያም እናድርግ እላለሁ። (ዛሬ ላይ ይህ እየሆነ ያለ ይመስላል)። ዐማራ ብቻ ብልም  ልዩነት የሚያመጣ አይመስለኝም። ክፋት ያሰበ ሠርጎ በመግባት ዐማራን የሚጎዳበት ብልሃት አያጣም። ዎገንነትን ከመጣል ባይሆን  ዎገን የተባለው የሚሠራው ሥራ የዐማራን ሕልውናና በረከት የሚጎዳ ነው ወይ ብሎ በመጠየቅ ማጥራቱ የሚሻል ይመስለኛል።ስሜቱንና ሥጋቱን ግን እገነዘባለሁ።

 ጥያቄ 17 ከሃይማኖትህ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ልጠይቅህ።ባዘጋጀኸው ምልክት የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ሃይማኖቶችን ሁሉ (ኦርቶዶክስን፥ እስልምናን ፥ ፕሮቴስታንትን እና ሌሎችንም) እኩልና አንድ አድርጎ ያያል እንደሚል መግለጽህን ተረድቼአለሁ። እንዲህ የሚለው የራሱን የጴንጤ ሃይማኖት ዕውቅና ለማሰጠትና ከሌሎቹ ለማስተካክል ነው እንጂ ሁሉን ሃይማኖት እኩል አድርጎ ማየት የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ እሴት ሆኖ አይደለም የሚሉ ቢነሱ ምን ትላቸዋለህ?

መልስ 17፡ የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ በሃይማኖቴ ምክንያት በደል/ጉዳት  እንዲያደርስብኝ አለመፈለጌ  ሚስጢር አይደለም። በሌላ በኩል በእኔ ሃይማኖት ምክንያት  የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ እንዲበደል/ እንዲጎዳም አልፈልግም።ነገሩ እውቅና የማግኘት ጉዳይ አይደለም። በሌላውም ሃይማኖት ያለው ይኸው  የአለመጎዳዳት ዐሳብ   ይመስለኛል።ይህ በእንዲህ እንዳለ ሆኖ የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ በታሪኩ ከተለያዩ ሃይማኖቶች ጋር ተዋውቆ ሁሉንም አስማምቶ መኖር የለመደ ነውና የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ እሴት የሁሉንም ሃይማኖት ተከታዮች እኩል  አድርጎ ያያል መባሉ በእኔ እይታ ትክክል ይመስለኛል።  እሴቱ ባለሃይማኖቶቹን እንጂ ሃይማኖቶቹን አንድና እኩል አድርጎ ያያል ማለት ግን አይደለም።

 ጥያቄ 18: በዚህ ዓይነት (ማለትም እንደ ዐክማራ ሕዝብና ዎገኖቹነትህ) ወንድሞቼ ከምትላቸው ወንጌላውያን ያለህ ወንድምነት ወይም ግንኙነት ከሌሎች በምን ተለየ? 

መልስ 18: የወንድሞችና እህቶች ፍቅር እንዴት ይረሳል? እንዴትስ ይጣላል? አራቱን ግዙፍ ኃላፊነቶች መወጣትን በተመለከተ ግን አንዱን ከሌላው አላበላልጥም። የተለያየ ሃይማኖት የምንከተለውም የማንከተለውም እኩል ኃላፊነት አለብን።እስካሁን ባለው አስተሳሰብ በዘልማድ በጥቅሉ ጴንጤዎች እየተባልን የምንጠራው ተሳዳጆች ነበርን።አሁንም ሙሉ ለሙሉ የቀረልን ባይሆንም በግምባር ከሚታዩት (ከዋናዎቹ) ሃይማኖቶች አንዱ ሆነናል። እንደ ቀድሞው በሰፊው እንሰደዳለን ብዬ አልገምትም። የምንሰደድበት አጋጣሚ ከኖረ ግን በኢትዮጵያ በብርቱ ተሰደን በነበርንበት ጊዜ እንዳደረግነው በመረዳዳት ስሌት ለመኖር እመርጣለሁ።

ጥያቄ 19ወደ ጾሙ ጉዳይ ልመለስና እንደተለመደው ጾም ከሃይማኖት ጋር የተገናኘ ነው። ይኸ አስተዋሽ ምልክት የምትለው "ጾሙና በዐሉ" ከሃይማኖቶች ጋር አይጋጭም እንዴ? ደግሞስ ሕዝብን አንድ የሚያደርጉ በርካታ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዐሎች አሉ አይደል? ይህ ምን የተለየ ነገር ያስገኛል?

መልስ 19፡ በመልስ 9 ከላይ  እንደገለጽኩት ጾሙን ማሰቤ ከጉራ ፈርዳ ተፈናቅለው ስለነበሩት የዐማራ ሕዝብ ተሰምቶኝ በነበረው ስሜት መነሻነት ነው።

ታዲያ ይኸው ጾም በጭራሽ ከሃይማኖት ጋር እንዲጠጋጋ አልፈልግም።ሃይማኖትን የሚተካም፣ የሚያደባልቅም አይደለም። በእሳቦቱ እንደማብራራው ጾም የግድ ከሃይማኖት ጋር የሚገናኝም አይደለም።

በእርግጥ ከሃይማኖቶቹ በርካታ መርኆቹና ልማዶች ተወስደዋል።ምናልባትም የሃይማኖቶቹ ተከታዮች የረሱትን በዐዲስ መልክ ያስታውሳቸው ይሆናል።

ምን የተለየ ነገር ያስገኛል  ላልከው  በሌላ ዐይነት ሕዝባዊ በዐል የማይደረጉ ቁምነገሮች በዚህ ጾምና በዐል ይደረጋሉ።

  1. ከሁሉም ሃይማኖቶች ሊወራረሱ የሚችሉትን (የማይጣረሱትን) ልማዶችና አስተሳሰቦች አንድ ላይ ለማምጣት ሞክሬአለሁ። የትኛውንም ሃይማኖት ተከታይ እንዲሁም ሃይማኖትን የማይከተለውን የመካተት ስሜት ይሰጠዋል ብዬ አምናለሁ። በዛው መጠን በአንድ ላይ፣ በአንድ ሥፍራ ፣ በአንድ ዐላማ አብሮ እንዲውል ያደርገዋል።
  2. የጾሙ አካል የሆኑ ሌሎች ነገሮችም አሉ። ለምሳሌ በጾሙ ምክንያት ለምግብና ለመሳሰሉት ሊወጣ የነበረውን ገንዘብ በፈቃደኝነት እርዳታ ለሚያስፈልገው መስጠት አንዱ አካል ነው። ይህ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ለማሰብም ለማገዝም እንደ መልካም አጋጣሚ ሊወሰድ ይችላል። በዚህ ዎገንነትን በአንደበት ከመግለጥ አልፎ ጾምን ውሎ ገንዘብንም በመስጠት የመስዋዕት አስፈላጊነትን እንማርበታለን።
  3. የጾም ቀኑ የበዐልነት ይዘት ሲኖረው እንደተለምዶ በዐላት በዋናነት የአደባባይ ብቻ ሳይሆን በየግል ሕይወት እቤት ድረስ የሚዘልቅ ነው። እያንዳንዱ ቤተሰብ ወይም መልካም ጎረቤታሞች ማኅበራዊ ግንኙነትና ስለ አራቱ ግዙፍ ኃላፊነቶች እንደ የአቅማቸውና እንደ የአካባቢያቸው ምክክር ያደርጉበታል። የድርጊት መርሀ-ግብር ለማውጣትም እድል ይሰጣል።ሌሎችንም ቁምነገሮች ያካትታል። በእነዚህና በመሳሰሉት ምክንያቶች  ይኸ ጾምና በዐል በዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ዘንድ ዐይነተኛ ሥፍራ ይኖረዋል

ጥያቄ 20: በተጠቀሰው ጾምና በዐል ምልክትነት የተነሳ ኃላፊነቶቹን እያስታወሰ አንድ ዐማራና ዎገኑ መጾምን ባይመርጥስ/ ባይችልስ?

መልስ 20: በ"ጾሙና በዐሉ"  አስተዋሽነት ኅላፊነቶቹን በማበርና በመተባበር፣  በማስተዋልና በትጋት ለመወጣት በማቀዱ፣ በመፈጸሙ ይሳተፍ እንጂ ምርጫ ማድረግ ይችላል።ግዴታ የለበትም።

 ጥያቄ 21፡ አንተን የተመለከተ ጥያቄ ልጠይቅህ! አንተ ታዋቂ ሰው አይደለህም። ፖለቲካ ሥራም ሠርተህ አታውቅም። የፖለቲካ ዕውቀቱም ያለህ አይመስለኝም።በሃይማኖትም በኩል ቢሆን እንደዛው። የት መጤህ እንኳ ሳይታወቅ አሁን ማን ይሰማኛል ብለህ ነው የምትደክመው?

መልስ 21፡ በእርግጥ ፓለቲከኛ አይደለሁም። በማንኛውም ረገድ የታወቅሁ ሰው አይደለሁም።ማንንም ወደ ሥልጣን ስለማምጣት ወይም ከሥልጣን ስለማውረድ እያሰብኩ አይደለም።የታየኝንና ያሰብኩትን በአደባባይ ለመግለጥ የደፈርኩ አንድ ግለሰብ ብቻ ነኝ። ነገር ግን ሥልጣን ላይ ለመውጣት የሚፈልጉትም ሆነ፣ ከሥልጣን ላለመውረድ የሚታገሉትም ፣ የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ አራቱን ግዙፍ ኃላፊነቶቹን ተደጋግፎ እንዳይወጣ እንቅፋት እንዳይሆኑ ይልቁንም እንዲያግዙ መፈለጌን ግን ለመግለጥ እወዳለሁ ፤ ለሁለቱም ቡድኖች ይጠቅማልና።

ለማንኛውም እኔ ባልታወቅም ቁምነገሩን አይተው የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ፣ የዐማራ ሕዝብ አባቶችና መሪዎች፣ የእምነት ተቋማት ይሰሙኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ይፋዊ ምልክት እንዲሆንም የየበኩላቸውን ትጋት ያሳያሉ፤ ይሳተፉብታልም ብዬ እተማመናለሁ።

በዚህ አጋጣሚ

ብጹዐን ጳጳሳት-የተከበሩ መነኮሳት፥ ካህናት-ዲያቆናት- መምህራንና ዘማርያን (የካቶሊክን ጨምሮ)

የተከበሩ ሼኾች፣ ኢማሞች፣ኡስታዞችና ሐጂዎች

የተከበሩ ቄሶች-ፓስተሮችና- የወንጌላውያን ዘማሪዎች ሌሎችም አገልጋዮች ፥

የተከበሩ ራቢዎች እንዲሁም አባቶችና እናቶች

በየሚደመጡበት ማኅበረሰብ ምልክቱና መልዕክቱ ይፋዊ እንዲሆንና እንዲያስገመግም በማድረጉ ይቸገሩልኝ ዘንድ አደራ እላለሁ።

ጥያቄ 22፡ በፖለቲካ ዐላማ የተቋቋሙት የዐማራ ድርጅቶችስ ይሰሙኛል ብለህ ታስባለህ?

መልስ 22፡

እነርሱም

1.አራቱን ግዙፍ ኃላፊነቶችን በመወጣት አኳያ ሁሉም በአንድ ዐሳብና በአንድ ላይ እንዲቆሙ

2. በሥራቸው ዎገኖችን (የኢትዮጵያንና የኤርትራን ነገዶችን ጎሳዎችን ውህዶቹን ጨምሮ ማለት ነው) እንዳይረሱ

3.ምልክቱን ሥራ ላይ ለማዋልም እንዲተባበሩ ያለኝን አደራ እንዲያውቁልኝ ቢሰሙኝ እወዳለሁ። ይሰሙኛል ብዬም ተስፉ አደርጋለሁ።በተረፈ ለዐማራ ሕዝብ ያለማወላወልና በሐቀኝነት  ለመሥራት የተነሡን  አደንቃለሁ።በእንቅፋትም ተደናቅፈው እንዳይወድቁ  ወይም እንዳይጠለፋ  ወይም በተንኮለኞች እንዳይበለጡ እመኝላቸዋለሁ።

ጥያቄ 23፡ ሌሎቹስ?

መልስ 23ሌሎችስ ስትል እነማን? 

ጥያቄ 24፡ለብሔረሰባችን ተቋቁመናል ወይም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተመስርተናል የሚሉትን ለማለት ነው።

መልስ 24፡ እነርሱም እንዲሰሙኝ ተስፋ አደርጋለሁ። የሚሰሙኝ ከሆነ ለየብሔራቸው መሥራታቸው ያው ለዐማራ ሕዝብ ዎገኖች መሥራታቸው ስለሆነ እንደዕገዛ እንደምቆጥረው ልገልጽላቸው እወዳለሁ። ይሁን እንጂ ዕቅዳቸው የዐማራን ሕዝብና ዎገኖቹን ማጥቃትን ያካተተ ከሆነ ትንሽ ማሻሻያ እንዲያደርጉ መፈለጌን መሸሸግ አልሻም። ያም የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹን በማይጎዳ መልክ ቢቻላቸው መደጋገፍ በሚያስችል መልክ እንዲያሻሽሉት ነው።በዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ በኩል መደጋገፉን እንደማያጡት ፥ የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ለዚህ ምን ጊዜም ዝግጁ እንደሆነ በድፍረት መናገር እችላለሁ። በኢትዮጵያ ስም የተቋቋሙትም ቢሆኑ የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹን ጉዳይ ግዝፈቱን አጢነው ያለማድበስበስ ትኩረት ሰጥተውና ፊት ለፊት አምጥተው እንዲሠሩ ያለኝን ምኞት እንዲያውቁልኝ ቢያዳምጡኝ እወዳለሁ።

ጥያቄ 25 ዐማራ የሠራውን ግፍ እንዴት ይረሱትና ነው በብሔር- ብሔረ ሰብ ስም የተቋቋሙት በተለይ አንዳንዶቹ ከዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ጋር መደጋገፍን የሚያስቡት?

መልስ 25፡ በአገር ግንባታ በሚደረግ ሂደት በደል ይኖራል ሲባል ነው የምሰማው። እንደተረዳሁት በአገራችን በጎ ነገር ብቻ አልተከናወነም። ግፎችም ተሰርተዋል። ይሁን እንጂ ለማስገበር የቀደሙት መንግሥታት ያደረጉት እንጂ በዐማራነት ተደራጅቶ ነገዶችን /ጎሳዎችን በማጥፋት ዐላማ የተደረገ ግን ያለ አይመስለኝም። የትኛውንም ሕዝብ ለማጥፋት ወይም ማንነት ለመለወጥ የተደረገ ክፋት ነበረ ማለት የሚቻል አይመስለኝም። ግፍ መሠራቱ ግን እርግጥ ነው።እኔ ራሴ ነፍስ ባወቅሁበት ጊዜ እንኳ ግፍ እንደሚሠራ ሰምቼአለሁ/አይቼአለሁ።በግፉ ደስተኛ አልነበርኩም። ይኼ ጉዳይ ተብሎለት ያበቃ መስሎኛል። ለማንኛውም ባለፉት ዘመናት የእኔ የሆኑቱ ተበድለው ነበር የሚሉቱ ይቅር ለማለት ይቅርታ እንዲጠየቁ የግድ አያስፈልጋቸውም። ከጥፋት ወጥቶ ወደፊት መሄጃው መንገድ ደግሞ ይቅር ማለት ነው።

 ጥያቄ 26 የአንተን አባባል ልዋስና ለአሁኑ የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ችግር "ጾሙና በዐሉ" ምን መፍትሔ ያመጣለታል ብለህ ታስባለህ?

መልስ 26 የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ችግር ለረዥም ጊዜ የሚቀጥል ይመስላል። መፍትሔውን ሊሰጠን የሚችል ሌላ እንደሌለ የተገነዘብንም ወይም የምንገነዘብም ይመስለኛል። መፍትሔው ተደጋግፎ፣  በማስተዋልና በትጋት አራቱን ግዙፍ ኃላፊነቶቻችንን መወጣት እንደሆነም እናጤናለን ብዬ አስባለሁ። ማንም እነዚህን ኃላፊነቶች በመወጣት  አኳያ የአቅሙንና የችሎታውን  ተባብሮ ከማድረግ ቸል  ማለት የለበትም ባይ ነኝ።፡አስተዋሽ  ምልክቱ ወይም "ጾሙና በዐሉ" እየደጋገመ  የሚያስታውሰውም ይኸንኑ ይሆናል። ያሳስበናል፣ ያነቃቃናልም።ደግሞ ጎረቤት የሚሰማው ባለቤት ሲጮህ መሆኑን ልብ ይሏል። "ጾሙና በዐሉ" ይህን ካደረገ  ቢያንስ መፍትሔውን  ጠቋሚ መሆኑ አይደለም? 

ጥያቄ 27: ለመሆኑ ዐማራ እውነት በጊዜው አንገብጋቢ የሆነውን ሕልውናውንና ነጻነቱን ለማስከበር ተደጋግፎ ይሠራል ብለህ ታስባለህ? ይህ ባሕላዊ ምልክት የምትለው ነገር ዐሳባዊ ብቻ አይሆንም? 

መልስ 27እንቅፋት የሚሆኑበት ጥቂት ግሮች አያለሁ።

የመጀመሪያው በአሁኑ ጊዜ በዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ዘንድ ለእኔ እንደሚታየኝ ግለሰባዊነት (Individualism) የተስፋፋና ሥር የሰደደ መሆኑ ነው። እስከማስታውሰው ድረስ በልጅነቴ ለአገሬ፣ ለዎገኔ፣ ለቤተሰቤና ለራሴ በረከት እሠራለሁ እያልን ነበር ያደግነው። ይኸ ለሌሎች ጥቅም በቅድሚያ የማሰብ የኢትዮጵያውያን ልማድ (Altruism) ሆኖ ነበር። የዛሬው ግለሰባዊነት በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን የዚያን ቅደም ተከተል ቀይሮታል። ይህ ተደጋግፎ መሥራትን የግድ ያስቀረዋል ባይባልም የሚያጓትተው ይመስለኛል።እንደ ዱሮው መሆን ቢያስቸግርም ግን ባለው ሁኔታ መሥራትም ይቻል ይመስለኛል።

ባለው ሁኔታም ዎገኔ ማለትን ብናስብና ጥቂትም እንኳ ብንሠራበት ተደጋግፎ ኀላፊነት መወጣት ይነቃቃል ብዬ አምናለሁ። ለምሳሌ እያንዳንዱ የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ በየቤቱ ከጊዜው፣ ከትኩረቱ፣ ከድምጹ፣ ከውይይቱ፣ ከብልሃቱና ከገንዘቡ እያሰበበት ጥቂቱን ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ በረከት ቢያዋጣ/ ቢያውል ሕይወቱን እስከመሰዋት የሚደርሰውም ይበረታታል።

ሁለተኛው ደግሞ በሌላ ጫፍ የሚገኘው ይሉኝታ ነው።ይሉኝታ ሕዝባችንን ሥርዓት በማስያዙ የጠቀመ ይመስለኛል። የማኅበረሰባችን በረከት ለማስጠበቅ ግን ጎታች መሆኑ አያጠራጥርም። የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ የኢትዮጵያ ነገር አይሆንለትም።ለራሱ ነገድ ነጥሎ ሲያስብ በነፍሱ ስለት እንዳለፈ ነገር ነው የሚሰማው።ለራሱ ሕልውና ቢሠራ «ከኢትዮጵያዊነት ወረድክ» ወይም «ዘረኛ ሆንክ» እባላለሁ ብሎ ይሉኝታ ይይዘዋል።

ይሁን እንጂ ራሱን ለማዳንና ነጻነቱን ለማረጋገጥ በመሥራቱ ምክንያት ሁለቱንም አለመሆኑን ያውቀዋል።መቼም በኢትዮጵያዊነቱ ብርቱ መሆኑን እያወቁ ሊከሱት የሚመርጡ ይኖራሉ። የእነርሱን ዐሳብ መቆጣጠር ደግሞ እንደማይችልም ይረዳል። ውሎ አድሮ «ለአቤቱታ የለው ይሉኝታ» በማለት  አብዛኛው  ይኸንን ባሕርይ ያሸንፋል ብዬ  አምናለሁ። 

በሦስተኛው  ደረጃ ደግሞ  የአንዳንድ ዎገኖች  ጊዜውን የማይጠብቅና ለዐማራ  ሕልውና ተጋድሎ መጥቀሙ ያልተረጋገጠለት  ስም መጠፋፋት ለመተባበሩ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ጥርጥር የለውም።

አራተኛ  " ዎገን ለመሆን እያሰቡበት ያሉ" ያልኳቸው  ዎገንነቱን በቁርጠኝነት እስኪቀበሉት ድረስ ማበሩንና መተባበሩን ሊያጓትቱት ይችላሉ። 

አምስተኛ-ከሁሉም በላይ ግን  "ዎገን ለመሆን እያሰቡበት ያሉ" ያልኳቸው  የሚሠሩትን  ልዩ ልዩ  የጭቆናን ስልት መረዳትና መቋቋም ባለመቻል ምክንያት ፣ ወይም ኃላፊነቱን ባለመረዳት ምክንያት ሁሉም የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ  በአንድ ጊዜ  በአንድ ላይ አለመነሳቱ ሕልውናንና ነጻነትን ማረጋገጡን ሊያዘገየው ይችላል። 

ለማንኛውም የዱላው ፅናትና አደጋው ታይቶት አዲሱ ትውልድ የራሱን ሕልውና መረጋገጥ  ማስቀደም ለዘለቄታው የሚባርክ መሆኑን በማስተዋል ፤ ይሉኝታን፣ ግለሰባዊነትንና የተቀሩትንም እንቅፋቶች ተቋቁሞና  አሸንፎ  ሁሉም በቶሎ  ተባብሮ ይነሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ (አሁን አሁን ምልክቱን እየታየ ነው)። 

አስተዋሽ  ምልክቱ ማለትም “ጾሙና በዐሉ”ም  በተቻለው ሁሉም የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ኃላፊነትን ተደጋግፎ እንዲወጣ  ደጋግሞ የሚያስታውስ እንዲሁም ስለዚሁ ለመምከርና የድርጊት መርሀ-ግብር ለማውጣት መድረክ የሚሆን ነው። ከኃላፊነቱ ቀዳሚው ደግሞ ሕልውናን ማረጋገጥና ማስቀጠል ነው። ታዲያ የ"ጾሙና በዐሉ" ምልክትነት በዚህ በኩል  አይጠቅምም ይባላል?

 ጥያቄ 28፡ ረዥም ጊዜ ወስደን ተነጋገርን። ለዛሬው ጥያቄዎቼን ጨርሼአለሁ። የማጠቃለያ ዐሳብ ካለህ?  መድረኩ ያንተ ነው።

መልስ 28: በመደምደሚያው አራቱን ግዙፍ ኅላፊነቶቻችንን በመደጋገፍ፣ በማስተዋልና በትጋት እየተወጣን እንኑር በማለት ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ዐሳቤን አጉልቼ ለመግለጥ እፈልጋለሁ።ይህን አኗኗር የአማራ ህዝብና ዎገኖቹ ንቁ አኗኗር ማለትም አዎንአዊ (አዎናዊ) አኗኗር ብዬዋለሁ።

ለእነዚሁ ዐላማዎችና ዒላማዎች እንደ አካባቢያችንና እንደ አቅማችን በየጊዜው ብልሃትን እናመንጭም እላለሁ። “ጾሙና በዐሉ”  ለዚሁ ጉዳይ ተስማሚ አስታዎሽም መድረክም ስለሚሆነን በዚሁ እንዲሳተፍ ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ አደራዬን ማኖርም እወዳለሁ።

የመጨረሻውን ምኞቴንም ብናገር ደስ ይለኛል። ያም የድርጅቶች አባላት እንዲሁም ድርጅቶች ሁሉ የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹን ዎገኔ ነው፣ እንደ ዎገን አብረን እንኖራለን እንዲሉ ነው። ያን ጊዜ  ምልክቱ የኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ሁሉ ይሆናል።

ስለ ጥያቄህ አንተን፣ በትዕግሥት የተከታተሉንም አድማጭ -ተመልካቾችህን አመሰግናለሁ።“እግዚአብሔር ይስጥልኝ። አድማጭ ተመልካቾችህን  ስለዚሁ ምልክት የሚኖሩን ዝግጅቶች ከአዎን ድምጽ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲከታተሉም እጋብዛለሁ።

መደምደሚያ 

 አቶ ባንቱ ፦ ስለ "ጾሙና በዐሉ" ማለትም   "አስተዋሽ ምልክት" ስላደረገው ማለት ነው-ሌሎች ጉዳዮችን አንስተን እንደምንነጋገርበት ተስፋ አደርጋለሁ። ጊዜ ወስደህ ስለ "ጾሙና በዐሉ" ምልክትነት አጠቃላይ ጉዳዮችን በተመለከተ ለቀረቡ  ጥያቄዎች መልስ ስለሰጠኸኝ አመሰግንሃለሁ።

አድማጭ ተመልካቾቻችን 

እንደተከታተላችሁት ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ባንቱ ዐሳቡን አጋርቷል።

1 አራቱን ግዙፍ ኃላፊነቶቹን በማበር፣ በማስተዋልና በትጋት ለመወጣት

2. የየትኞቹም ሃይማኖት ተከታዮች የኢትዮጵያና የኤርትራ ነገዶችና ጎሳዎች ውህዶቹንም  ጨምሮ ዎገኖቹ መሆናቸውን በማስታወስ እንደ አንድ ዎገን አብሮ ለመኖር ስለማሰብ

3. በጠላትነት የሚያጠቁት ድርጅቶችም ዐሳባቸውን ቀይረው እንደ አንድ ዎገን አብሮ ለመኖር ሲመርጡ ለመተባበር ዝግጁነትና ስለመሳሰሉት ያለውን ዐሳብ አጋርቷል።

አራቱን ግዙፍ ኅላፊነቶቹን ተደጋግፎ መወጣትን ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ለማስታወስ ጾሙና በዐሉ ከተለመዱ ክብረ በዐሎች ይልቅ የተሻለ እንደሚስማማ አስረድቶ፦ ቋሚ ባሕላዊ  አስተዋሽ ምልክት እንዲሆንም የሚመለከታቸው ሁሉ በየድርሻቸው እንዲተጉ አቤቱታውን አሰምቷል። እንዲሰሙት እመኝለታለሁ።

ይኸንን ሰፊ የጥያቄና መልስ ጊዜ ወስዳችሁና ታግሳችሁ ስለተከታተላችሁ አመሰግናለሁ። ውይይቱን እዚህ ላይ እንቋጫለን።

ያነበበ ላላነበበ ያስነብብ!

የሰማ ላልሰማ ያሰማ!

ያየ ላላየ ያሳይ!

ቸር እንሰንብት! ደህና ሁኑልኝ።

አዎን ድምፅ

Comments

Popular posts from this blog

Comparative Theology የነገረ መለኮት ንጽጽር (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት)/ በብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሲኖዳ ሳልሳዊ

 የነገረ መለኮት ንጽጽር  (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት): የወደደ  ሁሉ በነጻ እንዲጠቀምበት ተፖስቷል። ይሁን እንጂ መብቱ በሕግ የተጠበቀ ስለሆነ በየትኛውም መልኩ ለንግድ እንዲውል አልተፈቀድም። ልዩ ልዩ መግቢያ የሚለውን መጀመሪያ ካነበቡ በኋላ የተቀረውን በተመረጠው ቅደም ተከተል ማንበብ ይቻላል። ልዩ ልዩ መግቢያ   ጥምቀት   ትውፊት (ወግና ልማድ)   መካከለኝነት   ጾም የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ መንፈሳዊ ስጦታዎችና በልሳኖች የመናገር ስጦታ   ሥርዐት ንስሐ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ (1)  ድንግል ማርያምን ስለማክበር (2) ለጥያቄዎች መልስ (ሀ) ድንግሊትን ‘የወይን ግንድ (ተክል)’ና የ ‘ሕይወት በር’ የሚል ማዕረግ  ለምን እንሰጣታለን? (ለ) ወደ ድንግል ማርያም መጸለይ ትክክል ነው ወይ? (3) የድንግል ማርያም ድንግልና ዘላለማዊነት (4) ለተቃራኒ አስተያየቶች መልስ (ሀ) “የመጀመሪያ ልጇን” የሚለው ሐረግ (ለ) “ሚስትህ” የሚለው ሐረግ (ሐ) “አብረው ከመሆናቸው በፊት ጸንሳ ተገኘች” (መ) “የመጀመሪያ ልጇን እስክትወልድ አላወቃትም” (ሠ)  “ወንድሞቹ” የሚለው ሐረግ   የቅድስት ድንግል ማርያም  ክብሯ (1) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ድንግል እመቤታችንን አያከብሩም፤ ደግሞም እንድታማልድላቸውም (እንድትማልድላቸውም)  አይጠይቋትም።ከእነርሱ ወገኖች አንዳንዶቹ እንዲያውም ጫጩቱ ከተፈለፈለ በኋላ ዋጋ ከሌለው የዶሮ እንቁላል ቅርፊት ጋር እስከሚያመሳስሏት ይደርሳሉ።ይህ የተጋነነ ማቃለል የመጣው ምናልባት ሮሜዋውያን ካቶሊኮች የተጋነነ ማክበር ስለሚያከብሯት ለዛ ተቃርኖ ከማሳየት አዝማሚያ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን አንዱንም የእርሷን በዓል አያከብሩም።  (2) አንዳንዶቹ የፕሮቴስታንት ወገኖች ድንግል ማርያምን “እህታችን” ይሏታል። (3) በተጨማሪ አንዳንዶቹ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ጌታ ኢየሱስን በድንግልና ከወለደች በኋላ ከዮሴፍ ጋር ጋብቻዋን ፈጽማለች፤ የ‘ኢየሱስ ወንድሞች’  ወይም የ’ጌታ ወንድሞች’ ተብለው የተጠሩ ልጆችን ወልዳለች ይላሉ።  (4) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ቤተክርስቲያናችን ለድንግል እመቤታችን የሰጠቻቸውን አንዳንድ የማዕረግ ስሞችም ይቃወማሉ።  (5) ድንግልን ያለማክበራቸው አንዱ...