ንስሐ
1. ንስሐ ምስጢር ነው
2. ንስሐና ኑዛዜ
3. ንስሐና ቤተ ክርስቲያን
4. ንስሐና ድኅነት
5. ንስሐና የጸጋ ሥራ
6. ንስሐና ልምምዶች
7. ንስሐ ፣ ደስታና ጸጸት
8. ንስሐና የሕይወት መታደስ
9. ንስሐ የሌሎች ምስጢራት ሁሉ ቀዳሚ ነው
10. ንስሐ፣ ሠናይ ጠባይና መልካም ምግባር
የንስሐ ጽንሰ ሃሳብ
የንስሐ አስፈላጊነት በሁሉም ወገን አያከራክርም፤ ነገር ግን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ንስሐ በትርጉሙ፣ በሥራው (በውጤቱ)፣ በልምምዱ (በአደራረጉ)፣ ለድኅነት በማስፈለጉ ጨርሶ ከሌሎቹ የተለየ ነው።
(1) ንስሐ ምስጢር ነው
በኦርቶዶክስ ‘ንስሐ’ ከቤተ ክርስቲያን ሰባቱ ምስጢራት መካከል አንዱ ነው። ‘ምስጢረ ንስሐ’ ይባላል። ይሁን እንጂ የፕሮቴስታንት ወገኖች በ’ምስጢረ ቤተ ክርስቲያን’ ስለማያምኑ ‘ንስሐ’ን ቅዱስ ሚስጢር እንደሆነ አይቆጥሩትም። በንስሐና በ‘ምስጢረ ንስሐ’ መካከል ልዩነት አለ። ልዩነቱንም የሚከተለው ውጤት አለ።
(2) ንስሐና ኑዛዜ
በኦርቶዶክስ ጽንሰ ሃሳብ ኃጢአትን መናዘዝ የምስጢረ-ንስሐ ዋና ክፍል ነው። መናዘዝ ስንል ለካህን መናዘዝ ማለታችን ነው፣ “ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል” (ምሳሌ 28፥ 13) ።
በብሉይ ኪዳን ሰዎች መናዘዝን ይተገብሩ ነበር። እንደዚህም ተጽፏል፦“ከእነዚህ ነገሮች በአንዲቱ በደለኛ ሲሆን፥ የሠራውን ኃጢአት ይናዘዛል። ስለ ሠራው ኃጢአት ለእግዚአብሔር የበደል መሥዋዕት ያመጣል፤ እርሱም ከመንጋው የበግ ወይም የፍየል እንስት ለኃጢአት መሥዋዕት ይሆናል፤ ካህኑም ስለ ኃጢአቱ ያስተሰርይለታል (ዘሌዋ 5፥ 5፣ 6”)።
መጽሐፍ ቅዱስ በመናዘዝ ምሳሌዎች የተሞላ ነው። ኃጢአትን መናዘዝ እስከ መጨረሻው የብሉይ ኪዳን ነቢይ ድረስ ይደረግ ነበር። በብሉይ ኪዳንና በአዲስ ኪዳን መካከል፣ ደግሞም በመጥምቁ ዮሐንስ ጊዜ “--ኢየሩሳሌም ይሁዳም ሁሉ በዮርዳኖስም ዙሪያ ያለ አገር ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፤ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር” (ማቴ 3፥ 5፣ 6) ።
በአዲስ ኪዳንም ሰዎች ይናዘዙ ነበር። እንዲህም ተጽፏል÷“አምነውም ከነበሩት እጅግ ሰዎች ያደረጉትን እየተናዘዙና እየተናገሩ ይመጡ ነበር።” ሐዋ 19፥ 18ና “እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ።” ያዕ 5 ፥ 16
ይሁን እንጂ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ኃጢአትን በመናዘዝ አያምኑም። የንስሐ አካል እንደሆነም አይቆጥሩትም።
(3) ንስሐና ቤተ ክርስቲያን
እውነት ነው፤ ንስሐ በልብ ውስጥ የሚሆን ሥራ ነው። ይህም ሥራ ኃጢአትን ከልብና በተግባር ከመተዉ በተጨማሪ መጸጸትንና ኃጢአትን ለመተው በቁርጥ መወሰንንም ያጠቃልላል። ያም ሲሆን ንስሐ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመናዘዝና በ‘ፍትሐት’ ይፈጸማል። ኃጢአተኛው ኃጢአቱን ይናዘዛል፤ ካህኑ ‘ማስተሰረያውን’ ያነብና ይቅርታን ይሰጠዋል (እግዚአብሔር ይፍታፍ ይለዋል)። ይህ የሚደረገው “ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና። መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው” (ዮሐ 20፥22፣23) የሚለውን የጌታን ቃል በመከተል ነው።
ይህም ንስሐ ገቢው ተጸጻች ሆኖ ስለሚቀጥልበት ዘዴ ከመንፈሳዊ አባቱ የሚሰጠውን ምክር በመቀበል ይከተላል።
እንደ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን አስተያየት ንስሐ ሙሉ ለሙሉ ከቤተ ክርስቲያን ነጻ ተሆኖ የሚደረግ ነው። ከክህነት ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው የግል ጉዳይ አድርገው ነው የሚወስዱት።ምክንያቱም በክህነት አያምኑም፤ ነገር ግን በቀጥታ ከእግዚአብሔር ጋር በመገናኘት ያምናሉ።
ይህን በተመለከተ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን በሁለት ወገን የተከፈሉ ናቸው።
(ሀ) ኑዛዜንና ክህነትን በግልጽ የሚቃወመው ወገን
ይህ ደከም ያለው ወገን ነው። በጣም ግልጽ ከመሆኑ የተነሳ በእምነታቸው የሚበረቱቱ ሊለዩትና ሊጠነቀቁበት ይችላሉ። የዚህ ሃሳብ ግልጽ ስለሆነ መልስ ሊሰጥበትም አይከብድም።
(ለ) ሁለተኛው ወገን በግልጽ በኑዛዜ ላይ ወይም በክህነት ወይም በቅዱስ ቁርባን ላይ ተቃውሞ አያሰማም፤ ነገር ግን ለተከታዮቹ ስለ ‘ምስጢረ ንስሐ’ ባለማውራትና በምትኩ አማራጭ ትምህርት በማቅረብ አባላቱ የ’ንስሐን ምስጢር’ እንዲተው ያደርጋቸዋል። ይኸኛው ወገን ለምሳሌ እንደዚህ ይላል፦ “ንስሐ ያስፈልግሃል፣ ወደ እግዚአብሔርም መመለስ ያስፈልግሃል፤ እናም ሂድና በእግዚአብሔር እግር ሥር ውደቅ፤ ኃጢአትህን እርሱ በደሙ እንዲያጥብልህ ለእርሱ አስረክብ፤ ወዲያውም ከዚህ ቀደም ኃጢአትን እንዳላደርክ ያህል ያጸድቅሃል። ያጥብሃል፤ ከበረዶም ይልቅ ነጭ ትሆናለህ”።
በእዚኸኛው ወገን ያሉቱ የኑዛዜን አስፈላጊነት ወይም ስለ ኃጢአት ፍትሐት ወይም ስለ ምስጢረ ቁርባን አይናገሩም። ከትምህርታቸው እነዚህን በመተው ሰዎችን እንዲረሷቸው ያደርጓቸዋል። ይሁን እንጂ በተጓዳኝ መንፈሳዊ ቃላትን በመጠቀማቸው ብዙ የዋሆችን ያስታሉ። ይህ እውነቱን የማድበስበስ መንገድ ነው። ይህን ለሰዎች መግለጥ የእኛ ግዴታ ይሆናል።
(4) ንስሐና ድኅነት
ብዙ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ንስሐንና ድኅነትን ለመነጣጠል ይሞክራሉ። በክርስቶስ ደም ላይ ሲያተኩሩ እንደዚህ ይላሉ÷ “በክርስቶስ ደም ድነሃል። በንስሐ አይደለም። ንስሐ ከሥራዎች መካከል አንዱ ነው። በሥራ ደግሞ ድኅነት የለም”።
እኛ ድኅነት የተፈጸመው በክርስቶስ ደም መሆኑን አንክድም። ያለ ንስሐ ግን ድኅነት የለም። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳለው÷ “ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ” (ሉቃ 13፥ 3)።
ንስሐ መግባት ለድኅነት አስፈላጊ የሆነበት ምክንያቱ ማንም ያለኃጢአት አይደለምና ነው። ኃጢአት እስካለ ድረስ ለኃጢአት ቅጣት አለ። የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነው። ንስሐ ካልተገባ ከዚያ ሞት መዳን የለም። ንስሐ ነው ለክርስቶስ ደም የምንበቃ የሚያደርገን። “ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ” ይላልና ።
(5) ንስሐና የጸጋ ሥራ
ብዙ ፕሮቴስታንት ወገኖች ንስሐ ከጸጋ ሥራዎች መካከል አንዱ እንደሆነ አድርገው ያምናሉ፤ እናም የሰውን መጣጣር ዋጋ ያሳጡታል። “ከኃጢአቱ እንዲድን ሰው ራሱን በክርስቶስ እግር ሥር መጣሉ ይበቃል” ይላሉ። የኦርቶዶክስ ትምህርት (አስተምህሮ) ግን መላው የሰው መንፈሳዊ ሕይወት የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት እንደሆነ ነው የሚያስተምረው። መንፈስ ቅዱስ ያግዛል፣ ይሁን እንጂ ሰው መጣጣር አለበት። ሰው ካልተጣጣረ ሐዋርያው እንዲህ በማለት ይወቅሰዋል፦“ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም” (ዕብ 12፥ 4) ።
መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ሕይወት የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃ ሁሉ መልበስ የሚያስፈልገው የትግል ሕይወት እንደሆነ አድርጎ ነው የሚስለው። “መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ’ (ኤፌ 6 ፥ 12) ። ይህ ጦርነት ያለጥርጥር የሰውን መታገልና ማሸነፍ ይፈልጋል።
በራዕይ 2፥ 17 ላይ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት “ድል ለነሳው ------እሰጠዋለሁ” በማለት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ይህን ጦርነት ማለቱ ነው። ጸጋ ሁሉን ሥራ አይሠራም። አለበለዚያም እግዚአብሔር “ወደ እኔ ተመለሱ፥ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” (ዘካ 1÷3) ባላለም ነበር።
(6) ንስሐና ልምምዶች
ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ‘ንስሐ መግባት’ን እንደ ልምምድ ይቆጥሩታል እናም ሰዎች ንስሐ ስለገቡበት ገጠመኝ ለሰው እንዲናገሩ ያበረታታሉ። ስለዚህ “እንደዚህና እንደዚያ ነበርኩ፣ አሁን ግን እንዲህና እንዲያ ሆኜአኛለሁ” የሚለውን ንግግራቸውን ከእነርሱ ትሰማላችሁ። ኃጢአተኛው የቀደመውን ኃጢአቱን ያለሃፍረት በአደባባይ መናገሩን ይቀጥላል። አሁን ባገኘው ጸጋ ኃጢአቱ መሸፈኑንና ያገኘውን ለውጥ ያወራል።ዝም ያለ እንደሆን “እስቲ ስለ ሕይወት ለውጥህ ንገረን” ተብሎ ይጠየቃል።በኦርቶዶክስ ግን እንዲህ ዓይነቱ ትረካ ይከለከላል። ምክንያቱም ተጸጻቹ ስላደረገው ለውጥና ስለደረሰበት ሕይወት መናገር በዋናነት ጉራ መንዛት ሆኖ ይገኛል።
(7) ንስሐ፣ ደስታና ጸጸት
ኦርቶዶክስ ንስሐ የሚገባውን ሰው ተጸጻችነት አበክራ ትናገራለች።የሠራውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት እንደ ነቢዩ ዳዊት በአልጋው ላይ በዕንባ በመታጠብ ማስታወስ አለበት። የፕሮቴስታንት ትምህርት ግን ጸጸት ወደ ሌለበት ደስታ ነው የሚገፋው። አብዛኛውን ጊዜ ንስሐ የገባው ሰው አገልጋይ ነው የሚሆነው። ይህ ደግሞ በውስጡ በኃጢአቱ እንዲጸጸት ዕድል አይሰጠውም።ፕሮቴስታትንቶች ለዚህ ዝንባሌ የሚሰጡት ምክንያት ሰው ባገኘው ድኅነት ደስ መሰኘት አለበት ነው።
ለዚህ መልስ እስራኤላውያን የፋሲካውን በግ በሚበሉበት ጊዜ ያደርጉ የነበሩትን በፊታቸው እናኖራለን። እስራኤላውያን ከሞት መልአክ ሰይፍ ያመለጡበትን በማስታወስ በፈንጠዝያቸው መካከል የፋሲካ ‘በግ’አቸውን የሚመገቡት እንደ ጌታ ትእዛዝ ከመራራ ቅጠል ጋር ነበር (ዘፀ 12 ፥ 8) ። መራራው ቅጠል ኃጢአታቸውን ያስታውሳቸው ነበር፤ በፈርዖን እጅ በባርነት የነበሩበት ምክንያት ነበርና። እርግጥ ነው የፋሲካውን በግ መብላታቸው ድኅነታቸውንና ደስታቸውን ያስታውሳቸዋል። ነገር ግን በጉ ከመራራ ቅጠል ጋር መበላት ነበረበት።
እንደ ፕሮቴስታንቶቹ ሃሳብ በንስሐ ውስጥ የ’መራራው ቅጠል’ ሥፍራ ምን ሊሆን ነው? አንዱ የፕሮቴስታንት መጽሐፍ እንዳውም በጸሎታችን “ጌታ ሆይ ማረን” የምንለውን ሐረግ እስከመቃወም ደርሷል።መጸጸታችንን የሚያመለክቱትን ሐረጎች ሁሉ ተዋግቷቸዋል። የድኅነታችንን ደስታ የሚቃወም ነው በማለትም አውግዟቸዋል።
(8) ንስሐና የሕይወት መታደስ
ኦርቶዶክሶች ንስሐ ብለን የምንጠራውን ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ብዙ ጊዜ ‘የሕይወት አዲስነት’ ‘መታደስ’ ‘ድኅነት’ ብለው ይጠሩታል። አንዳንድ ፕሮቴስታንቶች እርስ በእርሳቸው እንደዚህ በማለት ይጠያየቃሉ፦”አዲስ ሕይወትን አግኝተሃልን? ድነሃልን? የሕይወት መታደስን ተለማምደሃልን?” በማለት አንዱ ሌላውን ይጠይቀዋል። ይህንንም አሉ ያኛውን ሁሉም ያው ንስሐ ገብተሃል ወይ? ማለት ነው። ከዚህ ያነሡም የበለጡም አይደሉም።
በኦርቶዶክስ ሃሳብ እነዚህ ሁሉ አገላለጾች÷ (መታደስ፣ አዲስ ሕይወት፣ ድኅነት ማለት ነው) በምስጢረ ጥምቀት ተፈጽመዋል። ንስሐ ግን የአኗኗር ፈሊጥን የመቀየር ሂደት ነው።
(9) ንስሐ ሌሎቹን ምስጢራት ሁሉ ይቀድማል
‘ምስጢረ ንስሐ’ ‘ምስጢረ ጥምቀት’ን ይቀድማል፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳለው÷ “ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ” (ሐዋ 2÷38)። ‘ምስጢረ ቁርባን’ንም ይቀድማል።አስተማሪያችን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው “ስለዚህ ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት። ሰው ግን ራሱን ይፈትን፥ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ፤ ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና” (1ኛ ቆሮ 11÷ 27-29)። ‘ምስጢረ ንስሐ’ ‘ቅብኣተ ሜሮን’ንም ይቀድማል። መምህራችን ሐዋርያው ያዕቆብ እንዲህ ይላል፦ “ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል” (ያዕ 5፥ 14፣ 15 ) ።
ይኸው ለተቀሩትም ምስጢራት ያገለግላል።ምስጢራት የመንፈስ ቅዱስ ጸጋዎች እስከሆኑ ድረስ ልብን በንስሐ በማንጻት መዘጋጀት ያሻል። ነገር ግን ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን በምስጢራትም ሆነ ‘ንስሐ’ን እንደምስጢር ባለማመናቸው እነዚህ ቃሎች ከእነርሱ ሃሳብ ውጭ ናቸው።
(10) ንስሐ፣ ሠናይ ባሕርይ፣ መልካም ምግባር
ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን የክርስትና ሕይወት ’ሠናይ ባህርይና መልካም ምግባር’ ማሳየት ነው ብለው አያስቡም። ‘የጸጋና የእምነት’ ነው ብለው ነው የሚያምኑት። በኦርቶዶክስም ቢሆን እምነትና ጸጋ አስፈላጊ ናቸው። ይሁን እንጂ ቤተክርስቲያናችን “እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ” (ማቴ 3 ፥ 8) የሚለውን ቀዳሚ አድርጋ ነው የምትወስደው።ኦርቶዶክስ ‘ሠናይ ባሕርይ’ (‘መልካም ጠባይ’) ለድኅነት የሚያስፈልግ ዋና ነገር አድርጋ ነው የምትይዘው።
ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን የክርስቶስን ደም ለኃጢአታችን መንጻት አስፈላጊነቱን አበክረው የሚናገሩ ከሆነ በሠናይ ጠባይና በጌታ ደም መካከል ስላለው ግንኙነት የሐዋርያውን የዮሐንስን ቃል በፊታቸው እናቀርባለን። እንዲህ ይላል፦ “ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል” (1 ዮሐ 1፥7)። በዚህ ሥፍራ እንደሚታየው ሠናይ ጠባይ እንደ ቅድመ ሁኔታ ተወስዷል። ያለንስሐ በደሙ መንጻት የለም። ንስሐ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነው።
ተፈጸመ
Comments
Post a Comment