ንቄው ነበር!
የገጠመኝን ታሪክ ላውጋችሁ። ከ30 ዓመት በፊት የሆነ ነው። የትምህርት ቤት ጓደኞቼ ሦስት ወጣት ፍልስጤማውያን ነበሩ። ከአንደኛው ጋር እንዳውም አንድ ሪደር (ፕሮፌሰር) ነበረን።ታዲያ ወንድማቸው ስለሆነው የአይሁድ ሕዝብ ባወራን ጊዜ
<<ልታስተናግደው መኝታ ቤት የሰጠኸው ሰው ቤትህን ሲቀማህ ዝም ብለህ ታየዋለህ እንዴ? እኛም አይሁዶችን የምናያቸው እንደዛ ነው። ምኞታችን ሁሉ ትምህርታችንን ጨርሰን እነርሱን መውጋት ነው >>
ብለውኝ ነበር።
የተላኩ(ህ)በትን ትምህርት እንደምንም ጨርሼ ትምህርት ቤቱን ከተለየሁ ወዲህ ግንኙነት ስለሌን ያድርጉት ፥ አያድርጉት አላውቅም። ሁላችንም “የሰው አገር ሰው” መሆናችን አቆራኝቶን ነበርና በጊዜው ግን እንቀራረብ ነበር።ታዲያ ከዕለታት አንዱን ቀን፥ የጾም ፍቺያቸው ጊዜ ይመስለኛል (አሁን ተዘንግቶኛል) ልጎበኛቸው እቤታቸው ሄድኩ። አንድ “የታላቁን የዐረብ ኢምፓየር” ካርታ እስቲከር በቤታቸው ግድግዳና በብዙ ሥፍራ ተለጥፎ አየሁ።ተገረምኩም። ኢትዮጵያ ጭምር “የአፍሪካ ቀንድ” አገሮች በዚያ ካርታ ተጨምረው ነበርና።
<<ይህ ደግሞ ምንድነው? ኢትዮጵያ እዚህ ውስጥ እንዴት ተጨመረች?>>
ብዬ ጠየቅኋቸው።ተደናገጡ። ሊያስረዱኝም ሞከሩ።
<<የነቢያችን ተከታዮች ዐበሻ አገር በተጠለሉ ጊዜ ነጋሻቸው ሙስሊም ሆኖ ነበር>>
አሉኝ። ሆኖም ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያን በዐረብ አገር ለማካተት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አልታየኝም። አፈጣጠራቸውም ታሪካችውም ለየቅል ነውና።ይሁን እንጅ አልተንጨረጨርኩም።
<<ምንም አይደለም፥ ይህን ኢምፓየር ንጉሥ ሆና ኢትዮጵያ እስከገዛች ድረስ አያጣላንም>>
ብዬ ቀልጄ አለፍኩ። የዚያ አካባቢ ልጆች ምን እየተነገራቸው እንደሚያድጉም በእግር መንገዴን ገመትሁ።የሄድኩበትን ትምህርት እስከምጨርስ ድረስ ወዳጅነታችን አልተቋረጠም ነበር። ይህ ገጠመኝ ሰሞኑን ትዝ አለኝ። ንቄ ትቼው የነበረውን ይህን አስታውሼ:-
<<የመጀመርያው የታላቁ ዐረብ ኢምፓየር ንጉሥ ለማድረግ አስቀድሞ ዐረባዊ መልክ ለማልበስ ይሆን እንዴ ከኢምሬት በሚገኝ ሁለንተናዊ ድጋፍ ኢትዮጵያ እንዲህ የምትመሰቃቀለውና ከመሠረቷ የምትናደው?>> ብዬ መጠርጠር ጀመርሁ።
Comments
Post a Comment