ደግሞ ባንዳ /ሆዳም በሉኝ አሉ!
ማህበራዊ አንቂ አይደለሁም። ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ግን ተቆርቋሪ ነኝ። እንዳውም ለዘለቄታው ይጠቀምበታል ያልኩትና እያስተዋወቅሁት ያለ የራሴ ዐሳብ አለኝ። በመቀጠል የምጽፈው ስለ ዐማራና ዎገኖቹ ነው። ዐማራ ነኝና። ስለ ሌሎች ነገዶችና ጎሳዎች የሚፈቀድልኝ ስላልመሰለኝ አልጽፍም። ታዲያ ባንጠቀምባቸው ወይም እጅግ በተመጠነ ልክ ብቻ ብንጠቀምባቸው የምላቸው ሁለት ቃላት (ከእነርሱ ተቀራራቢ የሆኑቱን ሁሉ ማለቴ ነው) አሉ። እነርሱም “ባንዳ” ና “ሆዳም“ የሚሉት ናቸው።የምጽፈው እነርሱን የታከከ ነገር ነው።
ከጠላት ጋር በማበራቸው ምክንያት በታሪክ ባንዳ ተብለው የሚጠሩ መኖራቸውን አላጣሁትም። የወገኑን ነጻነት የማረጋገጥ ሥራን አሳንሶ፣ የአጭር ጊዜ የግል ጥቅም ማግኘትን አግዝፎ መያዝና ለተጋድሎው እንቅፋት መሆን ሆዳም ሊያሰኝ እንደሚችልም እረዳለሁ።ስንጠቀምባቸው ምናልባት በዚህ እሳቤ ቃኝተን እንደሆነም እገምታለሁ።
ይሁን እንጂ አንድ ዎገን በዐሳብ ሊለይ ይችላል።ተቀባይነት ያለውን ዐሳቡን ተቀባይነት ወደ ሌለው ሊለውጥም ይችላል። ተቃራኒ የሆነ ዐሳቡን ትቶ የሚቃረነውን ዐሳብ ሊቀበል ይችላል። በርካታ ሰው “ዐማራ” ነኝ የሚለውን ማንነት ለማስታወስ ወይም ለመቀበል እንኳ ምን ያህል ጊዜ እንደፈጀበት ልብ ይሏል። ሁሉም የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ በአንድ ጊዜ በአንድ መስመር ላይ ይገኛል ለማለት ትልቅ ድፍረትን ይጠይቃል። ስለዚህ የራስን ዎገን እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ አድርጎ ባንዳ/ሆዳም እያሉ ፈርጆ ስብዕናውን መግደል - ባንዳ በሚለውና በሚባለው መኻል ያለውን ልዩነት ያሳይ እንደሆነ እንጂ - ለዐማራው ምን ይጠቅመዋል? በተለይም በሰፊው የዐማራ ሕዝብ በመሪነት የመመረጥ ውድድር በሌለበት ሁኔታ።
የሚፈለገውን ነገር ማሳየት አይበቃም ወይ? ባንድ/ሆዳም ከማለት ይልቅ ሌሎች ቃላትን መጠቀም ቢመረጥ እላለሁ።
ለምሳሌ፦ ዐሳቡ ወይም ሥራው እየተጨመረ፦
- “ለጊዜው ከእኔ ዐሳብ በተቃራኒ የቆምከው ወንድሜ/ የቆምሽው እህቴ"
- ”ዐሳብክን እንድትለውጥ ተስፋ የማደርገው ወንድሜ/እንድትለውጭ ተስፋ የማደርግሽ እህቴ”
- “የዐማራን ሕዝብና ዎገኖቹን ሕልውናና ነጻነት እየጎዳህ ያለኸው ወንድሜ/ እየጎዳሽ ያለሽው እህቴ”
- "በጨዋ አንደበት ብትናገር የማደንቅህ ወንድሜ/የማደንቅሽ እህቴ
- "የዐማራን ሕልውና ከሚጻረር ጋር የምትሠራ ወንድሜ/የምትሠሪ እህቴ"
- "ዐማራን የሚጎዳ ዐሳብ የያዝከው ወንድሜ/የያዝሸው እህቴ
- "ዐማራን የሚጎዳ ሥራ እየሠራህ ያለኸው ወንድሜ/ ያለሽው እህቴ ወዘተርፈ የመሳሰለውን ለማለት ነው
በእርግጥ "ባንዳ"ን/"ሆዳም"ን በኃይለ ቃል (በቁጣ) ለመናገር መጠቀም “ፍላጎትንና ግብን ለማስተላለፍ ዐይነተኛ ዘዴ የሚሆንበት ጊዜ እንዳለ አልስተውም። የኃይለኝነት ስሜትም ሳይሰጥ አይቀርም።የሁል ጊዜ ልማድ ማድረግ ግን በድምር ውጤቱ ለዐማራ ለበረከት የሚሆን አይመስለኝም።
አሁን ባለበት ደረጃ ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ የመጋደሉ ጉዳይ ቀልድ እንዳልሆነ ለማንም ግልጽ ነው።ሕልውናንና ነጻነትን የማረጋገጡ ተጋድሎ የምር፣ የመረረና አጣዳፊም ነው። በብዙ መቶ ሺህ ወይም ሚሊዮን ወገኖቻችን ነፍሳቸውን አስይዘው እየታገሉበት ያለ ሥራ ነው። ሲቪሉ የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹም በብዙ ጉስቁልናና ሥጋት ውስጥ ነው።እየሞቱ ያሉት ነጻነትን በማፈን ዐላማ ቢሆንም፤ የመከላከያና የሚሊሽያ አባላትም ዎገኖቻችን መሆናቸውና ጦርነቱ እንዲያጥርላቸው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ከማንም የተደበቀ አይመስለኝም። ስለሆነም በገሀድም ሆነ በስውር ለተጋድሎው የለየለት እንቅፋት የሚሆንን ዎገን ለማስታመም የሚበቃ ጊዜ እንደሌለ የማይታየኝ አይደለሁም። እንዲህ ዐይነቱን እንቅፋት፣ ተሰሚነት እንዳይኖረው ማድረጉ ወይም ማግለሉ ቀን የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑ ይገባኛል።
በስተቀረ ግን የግራውንም የቀኙንም ሁሉ ባንዳ /ሆዳም ማለት የሰውን የመለወጥ ዕድል፣ የመሥራት ፍላጎት እንዲሁ አስተዋጽኦውን የሚያቀጭጭ እንጂ የሚያበረታታ አይመስለኝም።
በተያያዘ፦ ለረዥም ጊዜ (ቢያንስ ላለፋት አምስት ዐመታት) ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ሕልውናና ነጻነት ሳያወላውሉ በጽናት የታገሉን በአመራር ከፊት እንዲቆዩ ወይም እንዲመጡ መርዳት ለእኔ ለፖለቲካ መሃይሙ ለጥንቃቄ የሚረዳ ሆኖ ይሰማኛል።
ገባ ወጣ ያሉትንና የሚሉትን ወይም ዐማራን ለመምራት ዕድሉን አግኝተው ከጉዳት ያልታደጉትን ፊት ለፊት በአመራርነት አለማምጣት ብልህነት እንደሆነ ይታየኛል። እነርሱም ቢሆኑ እውነት ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ የሚቆረቆሩ ከሆነ ለተጋድሎው ማዋጣታቸውን እየገፉበት ለአመራር ሥፍራው ከሚያስተማምኑት ጋር መጋፋቱን ቢተውት እላለሁ።አዳዲስ ወጣት መሪዎችንም ወደፊት ማምጣት የሚበጅ ሆኖ ይሰማኛል። ይገባኛል፣ ይህ ዐሳብ ገራ ገር እንዳውም የቂላ ቂል ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ ዐሳብ ነው።
ለመደምደም፦የዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ታማኝነቱ ከተጋድሎው ግብ እንጂ ከመሪው/መሪዋ አለመሆኑን ልብ ማለቱም ይበጃል።ማንም መሪ የዐማራን ሕዝብና ዎገኖቹን ሕልውናና ነጻነት በስውርም በግልጽም ከማገልገል ዞር ቢል ወይም ቢጠለፍ የተቆረበው ከተጋድሎው ግብ እንጂ ከእርሱ/ ከእርሷ ጋር አለመሆኑን መረዳት ለመሪውም ለተመሪውም በረከት ይሆናል።
ስለ አነበባችሁልኝ አመሰግናለሁ።
ደግሞ ባንዳ /ሆዳም በሉኝ አሉ!
Comments
Post a Comment