እኔም ለሄቨን
በወገኖቻችን ሕጻናትና ሴቶቻችን ላይ የሚፈጸመው ወሲባዊ ወንጀል “ምነው ኖረ? እንዴትስ ይቆም ይሆን?” በማለት ለብቻዬ ሳወጣና
ሳወርድ የኖርኩት ጉዳይ ነው። ባሕላችን ይኸንን ጉዳይ የሚጠየፍ አድርጌ ስለምቆጥር ፤ ወንጀሉን የሚፈጽሙት የአገሬ ልጆች “ይኸንን
ባሕል እንዴት ጣሱት? እኩይ ጠባዩንስ ከየት አመጡት? ምን ነካቸው?” ስልም ቆይቼአለሁ።በሄቨን ላይ የሆነው ጉዳይ ግን ድርብርብ
ወንጀል ሆኖ ተሰምቶኛል። ከማኅበራዊ መገናኛ እንደተከታተልኩትም ታላቅና ተገቢ ቁጣን ቀስቅሷል። በተለይ ለፍትሕ ያለው ጩኸት እጅግ
በግልጽ ይሰማል። ለቤተሰቧም የሃዘኔታ መልዕክት ጎርፏል። በቀጥታ ሄቨንን የተመለከተ ጉዳይ ደግሞ አንድ ዘፈን በቴዲ አፍሮ ተዘፍኖ ሰምቼአለሁ።ድምጻዊት ቬሮኒካም (ዘፈን
ሠፈር ስለማልውል አላውቃትም ነበር) በሄቨን ላይ በተፈጸመው ግፍ ምክንያት አልበሟ የሚወጣበትን ግዜ አራዝማለች።እኔ ያልደረስኩበት ሌላም ነገር ተደርጎ ሊሆን ይችላል።ይህ
ሁሉ ሄቨንን ለማስታወስ መልካም ጅማሬ ነው። ነገር ግን የአሁኑን የሕዝብ ቁጣ ወደ ገምቢ ኃይልነት መለወጥ ይገባል እላለሁ። "በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ወሲባዊ ወንጀል ለተፈጸመባቸው
ሁለ ፈዋሽ የሆነና ለወደፊቱም ወሲባዊ ወንጀልን ለመከላከል የሚያስችል መንግሥታዊ ያልሆነ እንቅስቃሴ በስሟ ቢጀመር ስሟ ለዘላቂ
በረከት ይሆናል። አሁን የታየው ቁጣም ወደ ጠቃሚ ኃይልነት ይለወጣል።
የእርሷ ጉዳይ የአንድ ሰሞን መጯጯህ ብቻ ሆኖም አይቀርም። እንዲህ ዐይነቱ ነገር በእነርሱ ቢዘጋጅ ይሰምራልና ተጽዕኖ ፈጣሬ የሆኑ ግለሰቦች እባካቸው ተባብረው ይኸንን ዐይነት መንግሥታዊ ያልሆነ እንቅስቅሴን ያፍጥኑ" እላለሁ። ይቅርታ! ብቻ ለአዋቂ አይነግሩም፣ ለአንበሳ አይመትሩም።
Comments
Post a Comment