Skip to main content

ጾም


ጾም

1. አጽዋማት ሁሉ በሚስጥር የሚደረጉ ናቸውን?

2. የማኅበር ጾም  

3. በተወሰኑ ጊዜያት መጾም

4. ለተቃውሞዎች መልስ 

“ማንም አይፍረድባችሁ” ለሚለው

አትክልት ብቻ የመብላት ጾም ለሚለው 

ከተወሰኑ ምግቦች መከልከል ለሚለው

5. አምልኮን ስለ ማደራጀት የቤተ ክርስቲያን ሥልጣን

ጾም

በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጾም ምሳሌ ሳይሆን ትዕዛዝ እንደነበር እጅጉን ግልጽ ነው።ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ጾምን ጨርሰው አይክዱም። በተግባር ግን ትተውታል ማለት ይቻላል። በዚህ ሥፍራ የጾም አስፈላጊነቱን፣ ጥቅሙን ፣ መንፈሳዊነቱን በአጠቃላይ መልኩ አልጽፍም። እነዚህ ሁሉ “የጾም መንፈሳዊነት” (“The spirituality of fasting”) በሚለው በሌላው መጽሐፋችን ሊነበቡ የሚችሉ ናቸው። 

የልዩነት ነጥቦች

(1) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ጌታ በተራራው ስብከቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት (ማቴ 6:17፣ 18) ጾም በእግዚአብሔርና በጿሚው መካከል በሚስጢር መደረግ አለበት ይላሉ።

(2) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ለአማኞቻቸው ሁሉ የተወሰነ ቋሚ የጾም ቀን ወይም በመነሻ ምክንያት የሚደረግ ጾም የላቸውም።ነገር ግን ከጾማቸው አብዛኛው የየግል ልምምድ ነው። ይህም ግለሰቡ በፈለገው ቀን ወይም በፈለገው መልክ የሚያደርገው ነው።ቤተ ክርስቲያን በጿሚው ላይ ሥልጣን የላትም፣ ጣልቃም አትገባም። 

(3) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን “እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ። እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው።” (ቆላ 2÷16፣ 17) ለሚለው ሐረግ የስህተት ትርጉሙ ላይ ይመሠረታሉ።

(4) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን በአትክልት ምግቦች በመወሰናችንና ከእንስሳ አስተዋጽኦ ምግቦች በመከልከላችን ከእኛ ጋር አይስማሙም። ይህን ስናደርግ በሚቀጥለው ጥቅስ ቢያንስ የሁለተኛው ክፍል ስለእኛ እንደተናገረ አድርገው ይከሱናል።“---በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ-- መጋባትን ይከለክላሉ፥ አምነውም እውነትን የሚያውቁ ከምስጋና ጋር ይቀበሉ ዘንድ እግዚአብሔር ከፈጠረው መብል እንዲርቁ ያዝዛሉ።” (1 ጢሞ 4÷1 ፣ 3)

በምስጢር መጾምን በተመለከተ ለተሰጠ ተቃውሞ መልስ

ሁለት ዓይነት አምልኮዎች አሉ፤ የግልና የማህበር።

(ሀ)ለምሳሌ በምስጢር ለሚያይህ አባትህ በክፍልህ ዘግተህ የምትጸልየው የግል ጸሎት አለ።ይህ ግን ሁሉም የአማኞች ማህበር በአንድ መንፈስ ፣ በአንድ ነፍስና በአንድ ድምጽ ሆነው የሚጸልዩትን የማህበር ጸሎት እንዳይኖር የሚያግድ አይደለም። የዚህ ዓይነት ጸሎት ምሳሌዎች በአዲስ ኪዳን በብዛት ይገኛሉ።ከነዚህ መካከል አንዱ ጴጥሮስና ዮሐንስ ከእስር ሲፈቱ አማኞች “-- በሰሙ ጊዜ በአንድ ልብ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ድምፃቸውን ከፍ አደረጉ እንዲህም አሉ።” (ሐዋ 4÷24) የሚለው ነው።

በእርግጥ በምስጢር እንዲጸለይ ያለው የጌታ ትዕዛዝ ለዚህ ዓይነት ጸሎት ሊጠቀስ አይገባውም (ማቴ 6÷6) ።

ለ) እንደዚሁም ሁሉ የቀኝ እጅ የምትሠራውን ግራህ እንዳታውቅ የሚሆንበት፣ በምስጢር የሚደረግ የግል ልግስና አለ (ማቴ 6÷3)። ይህ ግን ከሰው ሁሉ የሚሰበሰበውን አጠቃላይ ልግስና ለምሳሌ ንጉሥ ዳዊት መቅደሱን ለመሥራት ከሕዝቡ ገንዘብን በሰበሰበ ጊዜ ያለውን ዓይነት የሚከለክል አይደለም። ራሱ ምን ያህል እንደሰጠ በዝርዝርና ከአባቶች ቤት አለቆች ፣ ከእስራኤል ነገድ አለቆች፣ ከሺህ አለቆችና  ከመቶ አለቆች እንዲሁም በንጉሡ ሥራ ላይ ከነበሩ ሹሞች ምን ያህል እንደተዋጣ መዝግቧል (1ኛ ዜና መዋ 29÷3-9)።

በሉቃስ ላይ መባቸውን የጣሉት ባለጠጎችና ሁለት የመዳብ ሣንቲም የጣለችው ድሃ መበለት መጠቀሳቸው ሌላ ምሳሌ ነው (ሉቃ 21÷ 1፣2) ።

(ሐ) ልክ እንደዚሁ ባጠቃላይ በአማኞች ማህበር በጋራ የሚደረገውን ጾም የማይሽር በግል በምስጢር የሚደረግ ጾምም አለ።  

የማህበር  ጾም  መጽሐፍ  ቅዱሳዊ  አስተምህሮ  ነው ወይስ አይደለም? ለሚለው ቅዋሜ መልስ

የማህበር ጾምን በተመለከተ በርካታ ምሳሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል፦

(ሀ) በአስቴር ዘመን የሕዝብ ጾም 

ሁሉም ሰዎች በአንድ ጊዜ፣ ለአንድ ዓላማ፣ አንድ ጥያቄ ለጌታ አቅርበዋል። ጌታም ጾማቸውን ተቀብሎ የጠየቁትን መልሶላቸዋል (መጽሐፈ አስቴር 4) ።

(ለ) የነነዌ ሰዎች ጾም

ሁሉም በአንድ ላይ ጾመዋል፤ ይህም በሚስጢር አልነበረም፤ ጌታም ጾማቸውን ተቀብሏል፤ ኃጢአታቸውንም ይቅር ብሏል (ዮናስ 3) ።

(ሐ) በነህምያና በዕዝራ ጊዜ  የሕዝብ ጾም

ነህምያ እንዲህ ይላል፦“በዚህም ወር በሀያ አራተኛው ቀን የእስራኤል ልጆች ጾመው፥ ማቅም ለብሰው፥ በላያቸውም ትቢያ ነስንሰው ተከማቹ” (ነህ 9:1) ። ዕዝራ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “በአምላካችን ፊት ራሳችንን እናዋርድ ዘንድ፥ ከእርሱም የቀናውን መንገድ ለእኛና ለልጆቻችን ለንብረታችንም ሁሉ እንለምን ዘንድ በዚያ በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም አወጅሁ” (ዕዝራ 8÷21) ።

(መ) በኢዮኤል ጊዜ የነበረው ጾም

መጸሐፍ ቅዱስ “አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። ጾምንም ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፥ ሕዝቡንም አከማቹ፥ ማኅበሩንም ቀድሱ፥ ሽማግሌዎቹንም ሰብስቡ፥ ሕፃናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ፤ ሙሽራው ከእልፍኙ፥ ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ” (ኢዮኤል 21÷2-17) ይላል።

(ሠ) በአዲስ ኪዳን  የሐዋርያቱ ጾም

ደቀመዛሙርቱ ስለምን እንደማይጾሙ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠየቀ ጊዜ ይህን መለሰ፦ “ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ በዚያ ጊዜም ይጦማሉ” (ማቴ 9÷15) ። ሐዋርያቱም በምስጢር ሳይሆን በአንድ ላይ ጸለዩ፣ ጌታም ጾማቸውን ተቀበላቸው። 

ስለ ሐዋርያቱ ጾም ጥቂት ምሳሌዎች፤ “እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ፦ በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ። በዚያን ጊዜም ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው።” (ሐዋ÷13 2፣ 3)

(ረ) ቅዱስ ጳውሎስ በመርከቡ ከነበሩት ጋር ለረዥም ጊዜ ጾመ (ሐዋ 27÷

21)።

ስለዚህ የማህበር  ጾም ተቀባይነት  ያለውና መጽሐፍ  ቅዱሳዊ አስተምህሮ ነው። በአምልኮና ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ ያለን የነፍስ አንድነት ማረጋገጫ ነው። በተለይም ጾሙ ማህበሩን በመላው በሚመለከተው ጉዳይ ላይ ከሆነ ወይም ሁሉም ማህበረሰብ የሚካፈልበት ማለትም በጸሎት እንደሚያደርጉት በአንድ ነፍስ ከሆነ ተቀባይነት ያለው ነው ።   

በማህበር ጾም ግብዝነት የለበትም

በማህበር ጾም በአንዱ ሰውና በሌላው መካከል ልዩነት አይደረግበትም። በርግጥ የጾሙ ደረጃና ጥልቀት  ለእያንዳንዱ ምስጢር ሆኖ ይቀራል። በአዲስ ኪዳን የማህበር ጾምን የሚከለከል አንድም ጥቅስ የለም።   

በተወሰነ ጊዜ ስለመጾም ላለው ተቃውሞ መልስ

ጌታ በነቢዩ ዘካርያስ መጽሐፍ “የአራተኛው ወር ጾም የአምስተኛውም የሰባተኛውም የአሥረኛውም ወር ጾም” (ዘካ 8÷19) በማለት እንዳስረዳው በተወሰነ ጊዜ መጾምም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ነው። ጾም የሚደረግበትን የተወሰነ ቀን መደንገጉ የማህበር አምልኮውን ሥርዓት ለማስያዝ ይሆናል። የእያንዳንዳቸው ወቅታዊ የክርስቲያን ጾሞች ክርስቲያናዊ ትርጉም አላቸው። እያንዳንዱ ጾም የየራሱ የሆነ ዓላማ፣ ውጤትና ምክንያት አለው።

“ማንም አይፍረድባችሁ”  ለሚለው ሐረግ መልስ

ሐዋርያው “በመጾም ማንም አይፍረድባችሁ” አላለም። ነገር ግን “በመብል ወይም በመጠጥ ማንም አይፍረድባችሁ” (ቆላ 2÷ 16) ነው ያለው። ይህን ሲል ለአይሁድ የተከለከሉትን ንጹህ ያልሆኑ ምግቦችንና እነርሱም ንጹህ አይደሉም ብለው የሚቆጥሯቸውን ምግቦች ማለቱ ነው።

ይህ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከቆርኔሌዎስ ጋር ተያይዞ ያየውን ራዕይ ያስታውሰናል። ሐዋርያው የምግብ ዓይነቶችን ሁሉ የያዘ ታላቅ ሸማ አየ፣ ደግሞም አርዶ እንዲበላ ድምፅን ሰማ ። ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ፥ አይሆንም፤ አንዳች ርኵስ የሚያስጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅምና አለ። ደግሞም ሁለተኛ። እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ” (ሐዋ 10÷ 14፣ 15) ።

ሐዋርያው÷ “በመብልና በመጠጥ ---ማንም አይፍረድባችሁ” ሲል ስለነዚህ ንጹህ ያልሆኑ፣ የሚያስጸይፉና  ርኩስ የተባሉ ምግቦች ማለቱ ነው። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች አይሁድ ስለነበሩ ክርስትናን ‘ይሁዲነት’ ለማድረግም ይሞክሩ ነበር። ያም ማለት የአይሁድ ልማዶችን ሁሉ የሚያስጸይፍ ምግብን ያለመብላት ልማድን፣ መንጻትን፣ ሰንበት ማክበርን፣ የጨረቃ በዓልን፣ የወር መባቻን፣ የአይሁድ በዓሎችን (ፋሲካ ፣ ያልቦካ ቂጣን፣ የጥሩምባ ፣ የድንኳንና የማስተሰርያ ቀን የመሳሰሉትን ወደ ክርስትና ሊያስገቡ ይፈልጉ ነበር። ጳውሎስ ክርስትናን ይሁዲነት ማድረግ ሊቃወም ፈልጓል። ለዚህ ነው “እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ። እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና” (ቆላ 2÷16፣ 17) በማለት የጻፈው።

በመሆኑም ይህ ስለጾም አውስቶበት የነበረበት አጋጣሚ ሳይሆን የተለወጡቱ አይሁድ ወደ ክርስትና ይዘው ሊገቡ አስበውት ስለነበረው ልማድ የተናገረበት አጋጣሚ ነበር። 

‘አትክልት ብቻ’  በመብላት መጾምን  በተመለከተ ስላለው ተቃውሞ መልስ

(ሀ) በመጀመሪያ ደረጃ በእኛ ቤተ ክርስቲያን ጾም ‘አትክልትን ብቻ’ መብላት ሳይሆን መጀመሪያ ለተወሰነ ጊዜ ሳይበላ ይቆይና ከዚያ  ‘አትክልትን ብቻ’ (የእንስሳ ተዋፅኦ ሳይጨመርበት) መብላት ነው ለማለት እንወዳለን። 

(ለ)እግዚአብሔር መጀመሪያ ለአዳምና ለሔዋን በገነት (ዘፍ 1÷29)ና ኃጢአት ከተደረገም በኋላ (ዘፍ 3÷18) ያቀረበው የ’አትክልት ብቻ’ ምግብ ነበር ። እንስሳ ሁሉ የሚመገበው የ’አትክልት ምግብ’ ያም ማለት ሣር ነበር (ዘፍ 1÷30) ።

(ሐ) የኖኅ መርከብ እስካበቃበት ጊዜ ድረስ ማለትም ዓለሙ ሁሉ ተበላሽቶ የጥፋት ውኃን እግዚአብሔር ያወረደበት ጊዜ እስካለፈ ድረስ ሰው ሥጋን እንዲበላ መጽሐፍ ቅዱስ አልፈቀደም። (ዘፍ 9÷3) ።

(መ) እግዚአብሔር ሕዝቡን በሲና በረሐ ሲመራ የመገባቸው ‘አትክልት ብቻ’ ማለትም መና ነበር (ዘኁ 11÷7 ፣ 8)። ምርር ብለው እስከጮሁበት፣ እስካጉረመረሙበትና መንፈሳቸውን እስካወኩበት ጊዜ ድረስ ሥጋን (ድርጭትን) እንዲበሉ አልፈቀደላቸውም። ሥጋንም በሰጣቸውም ጊዜ በታላቅ መቅሠፍት እጅግ መታቸው፣ ይህም ለብዙዎቹ መሞት ምክንያት ሆነ (ዘኁ 11÷33) ። የተቀበሩበትም ሥፍራ የ‘ምኞት መቃብር’’ (ትርጓሜውም የመጎምዠት መቃብር ነው) ተብሎ ለመጠራቱ ምክንያቱ ሥጋን በመጎምጀታቸው ነበር። 

(ሠ) ዳንኤልና ሦስቱ ወጣቶች የተመገቡት አትክልት ብቻ (ጥራጥሬ) እንደነበር ልብ እንላለን። ጌታም መብላቸውንና ጤንነታቸውን ባረከና ከንጉሱ አሽከሮችም ሁሉ ይልቅ የተሻሉ ነበሩ (ዳን 1÷12፣ 15) ። 

‘አትክልት ብቻ’ የሚበላበት ምክንያት ቀለል ያለ ምግብ በመሆኑ ነው። የሰውነት ምኞትን አይቀሰቅስም። እግዚአብሔር ለሰው የሰጠው የመጀመሪያው ምግብም ነበር።

ከአንዳንድ  የምግብ ዓይነቶቹ  መከልከልን  በተመለከተ ላለው ተቃውሞ መልስ

ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን የሚመረኮዙበት ሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ስለ ቤተከርስቲያን ሥርዓት የሚያወራ አይደለም፤ ነገር ግን ይላል፦ “---አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ----፤ መጋባትን ይከለክላሉ፥ አምነውም እውነትን የሚያውቁ ከምስጋና ጋር ይቀበሉ ዘንድ እግዚአብሔር ከፈጠረው መብል እንዲርቁ ያዝዛሉ” (1 ጢሞ 4:1-3) ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እዚህ ላይ የሚያወሳው ምናልባት ጋብቻን፣ ሥጋንና ወይንን ይከለክሉ ስለነበሩት ስለ ‘ተረፈ ማኒዎች’ና ስለ‘መንድያኖች’  ይሆናል። እነዚህን ቤተ ክርስቲያን አውግዛ መናፍቃዊ ጽሑፎቻቸውን ሁሉ አስወግዳለች።

ቤተ ክርስቲያን  ሥጋንና  የመሳሰሉትን ምግብ መብላትን አትከለክልም። ይሁን  እንጂ  የብህትውና  ሕይወትን  የመለማመድ  ነገር  ሆኖ  እነዚህ  በጾም ጊዜ  አይበሉም። የማይበሉት የሚያስጠይፉ ስለሆኑ ግን አይደለም። ይህ ላለመሆኑ  ጾምን  በፈቱ ጊዜ ሥጋንና አስተዋጽኦቸውን የሚበሉ በመሆኑ ይረጋገጣል።

ከሌሎች ምግቦች ሁሉ ታቅቦ ዳንኤል ጥራጥሬን ብቻ በላ፣ ያም ሆኖ ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች  እንደሚያሳዩት አልተነቀፈም። እንደዚሁም ሁሉ መጥምቁ ዮሐንስ ከተወሰኑ ምግቦች ተከልክሎ ነበር። በየትም ሥፍራ፣ በየትኛውም ዘመን ባሕታውያን እንደዚሁ የተወሰኑ መብሎችን አይመገቡም።

ለተወሰነ ጊዜ የብሕትውናን ኑሮ መለማመድ አንድ ነገር ነው። የተወሰነ መብልን ጨርሶ መከልከል ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነው። አንድ በጣም አስፈላጊ ነጥብ መግለጽ ይቀረናል። 

አምልኮን ለማደራጀት የቤተ ክርስቲያን ሥልጣን 

ቤተ ክርስቲያን አጽዋማትን ደንግጋለች፤ መንፈሳዊ ደምቦችንም አውጥታላቸዋለች፣ እንደ የመንፈሳዊ መነሻቸው ጊዜንም ወስናላቸዋለች። እንደዚህ አድርጋ ቤተ ክርስቲያን ጾምን በሚገባ ጠብቃለች።በቤተ ክርስቲያን አስፈላጊና ምትክ የማይገኝላቸው መንፈሳዊ ልምምዶች ሆነውም ቆይተዋል። 

አባላቶቿ በአንድነት እግዚአብሔርን ማምለክ ይችሉ ዘንድ መንፈሳዊ ጥቅም የሚያገኙበትን ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ልምምዶችን ለማደራጀት ቤተ ክርስቲያን መብት፤ እንዳውም ግዴታ አለባት። እዚህ ላይ ለመሪዎቿ በጌታ የተሰጣቸውን አደራ ማለትም “-- በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።” (ማቴ 18÷18) የሚለውን ነው ሥራ ላይ የምታውለው። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነው።

ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ጾምን በግልና በየጉባኤው የመወሰን አካሄድን በመምረጣቸው ምክንያት ጉባኤአቸውን ከጾም የሚገኘውን በረከት አሳጥተውታል። በእነርሱ  ዘንድ ጾም ጨርሶ የቀረ ያህል መሆኑ ያስቆጫል። የጾም ሥርዓት ለግለሰቡ ባብዛኛው ጊዜ ጠቃሚ ነው።  ነጻነቱን አይጋፋም። ስለአጠቃቀሙ መመሪያ ያስገኝለታል  እንጂ።


Comments

Popular posts from this blog

Comparative Theology የነገረ መለኮት ንጽጽር (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት)/ በብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሲኖዳ ሳልሳዊ

 የነገረ መለኮት ንጽጽር  (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት): የወደደ  ሁሉ በነጻ እንዲጠቀምበት ተፖስቷል። ይሁን እንጂ መብቱ በሕግ የተጠበቀ ስለሆነ በየትኛውም መልኩ ለንግድ እንዲውል አልተፈቀድም። ልዩ ልዩ መግቢያ የሚለውን መጀመሪያ ካነበቡ በኋላ የተቀረውን በተመረጠው ቅደም ተከተል ማንበብ ይቻላል። ልዩ ልዩ መግቢያ   ጥምቀት   ትውፊት (ወግና ልማድ)   መካከለኝነት   ጾም የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ መንፈሳዊ ስጦታዎችና በልሳኖች የመናገር ስጦታ   ሥርዐት ንስሐ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ (1)  ድንግል ማርያምን ስለማክበር (2) ለጥያቄዎች መልስ (ሀ) ድንግሊትን ‘የወይን ግንድ (ተክል)’ና የ ‘ሕይወት በር’ የሚል ማዕረግ  ለምን እንሰጣታለን? (ለ) ወደ ድንግል ማርያም መጸለይ ትክክል ነው ወይ? (3) የድንግል ማርያም ድንግልና ዘላለማዊነት (4) ለተቃራኒ አስተያየቶች መልስ (ሀ) “የመጀመሪያ ልጇን” የሚለው ሐረግ (ለ) “ሚስትህ” የሚለው ሐረግ (ሐ) “አብረው ከመሆናቸው በፊት ጸንሳ ተገኘች” (መ) “የመጀመሪያ ልጇን እስክትወልድ አላወቃትም” (ሠ)  “ወንድሞቹ” የሚለው ሐረግ   የቅድስት ድንግል ማርያም  ክብሯ (1) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ድንግል እመቤታችንን አያከብሩም፤ ደግሞም እንድታማልድላቸውም (እንድትማልድላቸውም)  አይጠይቋትም።ከእነርሱ ወገኖች አንዳንዶቹ እንዲያውም ጫጩቱ ከተፈለፈለ በኋላ ዋጋ ከሌለው የዶሮ እንቁላል ቅርፊት ጋር እስከሚያመሳስሏት ይደርሳሉ።ይህ የተጋነነ ማቃለል የመጣው ምናልባት ሮሜዋውያን ካቶሊኮች የተጋነነ ማክበር ስለሚያከብሯት ለዛ ተቃርኖ ከማሳየት አዝማሚያ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን አንዱንም የእርሷን በዓል አያከብሩም።  (2) አንዳንዶቹ የፕሮቴስታንት ወገኖች ድንግል ማርያምን “እህታችን” ይሏታል። (3) በተጨማሪ አንዳንዶቹ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ጌታ ኢየሱስን በድንግልና ከወለደች በኋላ ከዮሴፍ ጋር ጋብቻዋን ፈጽማለች፤ የ‘ኢየሱስ ወንድሞች’  ወይም የ’ጌታ ወንድሞች’ ተብለው የተጠሩ ልጆችን ወልዳለች ይላሉ።  (4) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ቤተክርስቲያናችን ለድንግል እመቤታችን የሰጠቻቸውን አንዳንድ የማዕረግ ስሞችም ይቃወማሉ።  (5) ድንግልን ያለማክበራቸው አንዱ...

ስለ "አስታዋሽ ጾምና በዐሉ" ጥያቄና መልስ

 ስለ "አስታዋሽ ጾምና በዐሉ" ጥያቄና መልስ  ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ፦ ሕልውናችንን-ነጻነትችንን የማረጋገጥና የማስቀጠል አንድነታችንን የመጠበቅና የማጠንከር  በእሴቶቻችን የመደሰት፣ እነርሱን የመንከባከብና የማስተዋወቅ  በረከታችንን የማብዛትና የማካፈል  ኃላፊነቶቻችንን በማኅበር ፣ በማስተዋልና በትጋት እንድንወጣ “ጾሙና በዐሉ" አስታዋሽ ባሕላዊ ምልክታችን ይሁንልን   ጥያቄ 1 ፡ አድማጭ ተመልካቾቻችን እንኳን ደህና መጣችሁ።የከበረ ሰላምታችን ይድረሳችሁ። ዛሬ የምንወያየው ከአቶ ባንቱ ገብረማርያም ጋር ይሆናል። አቶ ባንቱ በሙያው ፋርማሲት ነው። እንደነገረኝ በእምነቱ ደግሞ ባፕቲስት ነው።ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ባሕላዊ ምልክት የሚሆን “ጾምና በዐልን” በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል። የምንወያየውም ስለዚሁ "ጾሙና በዐሉ" ምልክትነት ይሆናል።  አቶ ባንቱ ለመወያየት  ወደ እኛ በመምጣትህ አመሰግንሃለሁ። እንኳን ደህና መጣህ። አንተ እያልኩ ልቀጥል ወይስ አንቱ? መልስ 1፡ ዎገኔ፡   እንኳን ደህና ቆየኸኝ። ለአድማጭ ተመልካቾቻችሁም ሰላምታዬ ይድረስልኝ። አንተ በለኝ። የሚያውቀኝ ሁሉ አንተ ነው የሚለኝ።  ጥያቄ 2 ፡ እሺ  አንተ እያልኩ እቀጥላለሁ። አቶ ባንቱ፣ ምናልባትም ብዙ ሰው ስለማያውቅህ  እስቲ ስለራስህ በአጭሩ ንገረን። ወዲያውም መክፈቻ ይሆነናል መልስ 2 ዎገኔ ፦ አስቀድሜ ይኸን ዕድል ስለሰጠኸኝ ላመሰግንህ እወዳለሁ። አድማጭ ተመልካቾችህንም ጊዜ ወስደው  ውይይቱን  ስለሚከታተሉ ላመሰግናቸው እወዳለሁ።አዎን፣ ባንቱ ገብረማርያም እባላለሁ።እንደነገሩኝ የተወለድኩት ሽርካ በዛሬ አጠራሩ በአርሲ ዞን ነው።ነፍስ ያወቅሁትና ትምህርት ...