Skip to main content

መንፈሳዊ ስጦታዎችና በልሳኖች የመናገር ስጦታ

መንፈሳዊ ስጦታዎችና በልሳኖች የመናገር ስጦታ

1. ለድኅነትህ ከመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ይልቅ  የመንፈስ ፍሬዎች የበለጠ ጠቃሚ ናቸው

2. ስጦታዎች በአንተ ምስጉንነት የሚሰጡ አይደሉም፤ ስለዚህ ለእነዚህ ሽልማት የላቸውም

3. ስጦታዎቹ ይሰጣሉ ወይስ ይጠየቃሉ?

4. የጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴና በልሳኖች የመናገር ስጦታ

5. በልሳን መናገር በስጦታዎቹ ቅደም ተከተል የመጨረሻው ነው

6. በልሳን መናገር የሁሉ ስጦታ አይደለም

7. በልሳን መናገር ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ መሆን አለበት

8. በልሳን መናገር መተርጎም አለበት

9. የ‘ራሱን ያንጻል’ ትርጕም ምንድነው?

10. ሐዋርያው በልሳን መናገርን በተመለከተ የሚደረግን ስህተት አጥብቆ ይዋጋል

11. በልሳን መናገር ለማያምኑ ምልክት ነው


መንፈሳዊ ስጦታዎችና  በልሳኖች የመናገር ስጦታ

ከፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን አንዳንዶቹ የመንፈስ ስጦታዎችን አጥብቀው ይይዛሉ። እንደ እግዚአብሔር ልጆችነታቸውና ወራሽነታቸው ልዩ መብታቸው አድርገው በማሰብ ሊያገኙትም ይጣጣራሉ። “ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ” (1 ቆሮ 12÷31) የሚለውን የጥቅሱን መጨረሻ አብረው ሳያገናዝቡ በፊታቸው “የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ” (1 ቆሮ 12÷31) የሚለውን ጥቅስ ያኖራሉ። 

በልሳን መናገርን እጅግ አስፈላጊ አድርገው ሲወስዱ ወዲያውኑ አስከትሎ ሐዋርያው ጳውሎስ “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ” (1 ቆሮ 13÷1) በማለት የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ቸል ይሉታል። ሐዋርያው ከሁሉም ስጦታዎች ይልቅ ፍቅር እንዴት እንደሚመረጥ ያስረዳውን ይተዉታል።

ለድኅነትህ ከመንፈስ ስጦታዎች ይልቅ የመንፈስ ፍሬ የበለጠ አስፈላጊ ነው

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው” (ገላ 5÷22፣ 23) በማለት ስለመንፈስ ፍሬዎች ተናገረ።ሐዋርያው ጳውሎስ የመንፈስ የመጀመሪያው ፍሬ የሆነው ፍቅር ተራራን ከሚነቀንቅ እምነትም ይልቅ ይበልጣል አለ። “ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ” (1 ቆሮ 13÷2)። ጌታ ስለፍቅር እንዲህ ብሏል፦ “በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል” (ማቴ 22÷40) ።   

ደቀ መዛሙርቱ በስጦታው ደስ ተሰኝተው ወደ ጌታ በተመለሱ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦“ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፥ ስማችሁ ግን በሰማያት ሰለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ” (ሉቃ 10÷20) ።

ምንም   እንኳ  የመንፈስ ስጦታዎችን  የተቀበሉ ቢሆንም ብዙ ሰዎች ድኅነታቸውን አጥተዋል፤ ጠፍተዋልም

ስጦታዎቹ አልረዷቸውም፤ አላዳኗቸውም። ጌታም “በዚያ ቀን ብዙዎች። ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም። ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ” (ማቴ 7÷22፣ 23) የሚለውን ጥቅስ ያስተውሏል።

ስጦታዎቹ በምስጉንነታችሁ የምታገኟቸው አይደሉም። ስለዚህ ለእነዚህ ሽልማት የላችሁም

የመንፈስ ስጦታዎች ድኅነትን አይሰጡህም። ታዲያ ለምንድነው እነርሱን ለማግኘት የምትታገለው? ከንቱ ክብርና መገበዝ ለሚፈልጉ ሰዎች ያጓጓሉ። ትሕትናን ይወዱ የነበሩ ታላላቆቹ ቅዱሳን ግን ከመንፈስ ስጦታዎች ይሸሹ ነበር።

ከአባቶች አንዱ “እግዚአብሔር ስጦታን ከሰጠህ ስጦታውን እንዲጠብቅልህ ከትሕትና ጋር እንዲሰጥህ ለምነው፤ አለበለዚያም ደግሞ  ስጦታውን ከአንተ እንዲወስድ ለምነው” ብለዋል።

ብዙ ስጦታዎችን ከጌታ የተቀበለው ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ አለ፦“ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው” (2 ቆሮ 12÷2) ። ይህ ታላቅ ሐዋርያ፣ ጸጋ የበዛለት ሰው፣ እስከ ሦስተኛው ሰማይ የተነጠቀ ሰው (2 ቆሮ 12÷7) ከስጦታዎቹ (የተነሳ) አደጋ ላይ ነበር! በመንፈስ ስጦታዎቹ ሐዋርያ ጳውሎስ ፍርሃት ከነበረው የዛሬዎቹ ምስኪን ወጣቶች መብታችን ነው በማለት ስለመንፈስ ስጦታ ሲጸልዩ፣መንፈሳዊ መካሪዎቻቸውም  እጃቸውን በራሳቸው ላይ ጭነው የመንፈስ ስጦታን እንዲቀበሉ ሲጸልዩላቸው የቱን ያህል መፍራት ይገባቸው?

ያዕቆብ አባታችን መንፈሳዊ ስጦታዎችን ተቀበለ፤ የብኵርና መብትን አገኘ፣ የጌታ መላእክት ሲወጡበትና ሲወርዱበት ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ መሰላልን ተመለከተ፤ እግዚአብሔርን ራሱን አየ፤ ከእርሱም ጋር ተነጋገረ፤ከእግዚአብሔር ከሰውም ጋር ታግሎ አሸነፈ (ዘፍ 32÷ 28) ። ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ያዕቆብን ከስጦታዎቹ ሊታደገው እግዚአብሔር የጭኑን ሹልዳ ነክቶ አደነዘዘው። “ያዕቆብም የጭኑ ሹልዳ ደነዘዘ” (ዘፍ 32÷28)፤  ከስጦታዎቹ የተነሳ እንዳይታበይ ሊረዳው  እግዚአብሔር ለያዕቆብ  ይህን ዓይነት ድካም በአካሉ አደረሰበት። 

ዛሬ ጊዜ ላይ ከስጦታዎች የበለጠ አደገኛው ነገር አንድ ሰው ለሌላው ሰው “ና ስጦታን አስተላልፍልሃለሁ፤ ወይም ልምምዱን ትቀበላለህ” ብሎ እጁን ጭኖ በመጸለይ መንፈስ ቅዱስን ወይም ሙላቱን እንዲቀበል ሲፈቅድ ነው። እንግዳ የሆነው ነገር ደግሞ አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር የመፈወስ  ስጦታን ለሴቶች ስለሚሰጣቸው ሴቶችም እንኳ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ በሰዎች ላይ እጃቸውን የመጫናቸው ነገር ነው። 

ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ማሰጠት የካህናት ተግባር ነው፤ መጀመሪያ በሐዋርያቱ እጅ በመጫን ተደረገ፤ ከዚያም በካህናቱ በ‘ሚስጢረ ሜሮን’   

መንፈስ ቅዱስን ከምስጢረ ጥምቀት በኋላ በ’ምስጢረ ሜሮን’ (ኮንፎርሜሺን ክርስትናን በሚቀበልበት ሥርዓት)  እንቀበላለን። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚሁ ቅባት በ(1ኛ ዮሐ 2÷20፣ 27 ) ይናገራል። በሐዋርያቱ ስለተደረገ እጅ መጫን ደግሞ በ(ሐዋ 8÷14-17) ተጠቅሷል። 

የሐዋርያቱ ቀጥሎም የተተኪዎቻቸው የነበረውን ሰዎች መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ የመጸለይ ሥልጣን  ዛሬ ወጣቶችና ምዕመናን የእኛ ነው ይላሉ። ወጣቶችና ምዕመናን መንፈስ ቅዱስን ሌሎች እንዲቀበሉ፣ እንዲሞሉና በልሳን እንዲናገሩ ይጸልያሉ።   

በእኛ በኦርቶዶክስ ነገረ መለኮት የመፈወስ ስጦታ የነበራቸው ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ‘ሴራብዮን’ ና ሌሎችም በርካታ ቅዱሳን እንዳደረጉት ሁሉ የመፈወስ ስጦታ የተቀበሉ እንታይ አላሉም።  

ለመሆኑ ስጦታዎቹ ይሰጣሉ? ወይንስ ይጠየቃሉ?

እግዚአብሔር የወደደውን ዓይነት ስጦታ፣ ለፈቀደው ለማናቸውም ሰው፣ በመለኮታዊ ጥበቡ በወሰነው ጊዜ ያድላል።ቃሉ እንዳለው“የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም” (ሉቃ 17÷20)። ስጦታዎች ወደ ወደደው ሥፍራ እንደሚነፍስ እንደ ንፋስ ናቸው፣ “እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው--“(ሮሜ 12÷3) ይሆናልና። ታዲያ ለምንድነው ስለስጦታዎቹ የሚጸለየው? በተለይም ደግሞ በልሳኖች ስለመናገር ተለይቶ?

ስጦታዎቹ አንዱ ሰው  በሌላ ሰው ላይ የሚያሳርፋቸው አይደሉም÷ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ የሚሰጡ ናቸው። የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎችም ናቸው።

ከንቱ ክብርን ለሚፈልጉ፣ በልሳን የመናገር ስጦታን ለማግኘት በሚጸለይላቸው ጊዜ የትምክህት ልባቸውን ሊያረካ ይችል ይሆናል። ለአሮጌው ሰዋችን የሚያጓጓ ስጦታ ነው። ለመንፈሳዊ ሰው ግን የሚማርክ አይደለም። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ በልሳን የመናገር ስጦታ ለሁሉም ነው አይልም (1 ቆሮ 14)። ከዚህም ይልቅ የሚከፋው በልሳኖች የመናገር ስጦታ ያላቸው የሌላቸውን ሲንቁና ዝቅ አድርገው ሲመለከቷቸው፣ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ብለው ሲናገሩባቸው ነው። ይህ ንቀታቸው ስጦታው አለን የሚሉትን ወደ መጠራጠር አያመራንምን? 

አንድ ሰው መጥቶ “ይህን ልምምድ እንድታገኝ  እለምንልሃለሁ (እጸልይልሃለሁ)” ቢላችሁ “እነዚህ ስጦታዎች አይገቡኝም” ብላችሁ መልሱለት። “እነርሱን ለመሸከም የሚችል የልብ ትህትና የለኝም። እግዚአብሔር ስጦታን ሊሰጠኝ ቢፈልግ ሳልጠይቀው ሊሰጠኝ ይችላል። ከዚያ በኋላ በዚህ እንዳልታበይ እንዲጠብቀኝ እጸልያለሁ” በሉት። “እግዚአብሔር ስጦታውን ከሰጠኝ ስለዚያ አላወራም። ለሰዎችም አላውጅም ካቅሜ በላይ ለሆነ መንፈሳዊ ውጊያ ራሴን እንዳላጋልጥ” በሉት። 

“ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ” የሚለው ሐረግ ስጦታዎችን እንጠይቅ ማለት ሳይሆን ለመቀበል ልባችንን በንጽህናና በትህትና እናዘጋጅ ማለት ነው።ይህም ታምራዊ ኃይልን ማየት ብቻ ሳይሆን ሐዋርያው እንዳስተማረው ጥበብን መናገር፣ ዕውቀትን መናገርና እምነትን ያካትታል (1ቆሮ 12÷8፣9)። 

እግዚአብሔርን መልካም ስጦታ ለመጠየቅ ከፈለጋችሁ ጌታ ምንን መጠየቅ እንዳለባችሁ ያስተምራችኋል። በተራራው ስብከቱ እንዲህ አለ፦ “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” (ማቴ 6÷33) ። ጌታ ባስተማረን በዚህ የጸሎት ምሳሌ ውስጥ ልብ እንደምንለው ስጦታዎችን አንጠይቅም።

የጴንጤ ቆስጤ እንቅስቃሴና በልሳኖች የመናገር ስጦታ

የጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ ጎልቶ የሚታወቅበት ባህርይ ጴንጤ ቆስጤዎቹ በመንፈስ ቅዱስ በመጠመቅ (በውሃና በመንፈስ ከመጠመቅ ሌላ ማለት ነው) ማመናቸው ነው። በግብጽ የሚገኙት የጴንጤቆስጤዎችና ተከታዮቻቸው የሆኑቱ የካሪዝማቲክ ወገኖች ማወጅም ሳያስፈልጋቸው የሚያስተምሩት ይህ መሆኑ ከመጽሐፎቻቸው ግልጽ ሆኖ ይታያል። ይህንኑ ጉዳይ የ‘መንፈስ ቅዱስ ጥምቀት’ ወይም የ‘መንፈስ ቅዱስ መሞላት’ ብለው ይጠሩታል። 

የጴንጤቆስጤና የካሪዝማቲክ ወገኖች  በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ፣ የመንፈስ ቅዱስ መውረድና  ሙላት  የሚታወቅበት ዋንኛ መለያ በልሳኖች መናገር እንደሆነ ያስባሉ። እንደነርሱ አመለካከት በመንፈስ ቅዱስ መሞላት የመጀመሪያው ምልክት በልሳኖች መናገር ነው። በዚህ ምክንያት አዲስ አባል ሲቀላቀላቸው ልክ በጴንጤ ቆስጤ ቀን በሐዋርያት የታየውን እንዲመስል በልሳን እንዲናገር ለማድረግ እነዚሁ ወገኖች በብዙ ይደክማሉ። 

የመካሪዎቻቸውን (የአስተማሪዎቻቸውን) ትምህርት በመከተል ጴንጤቆስጤዎችና የካርዝማቲክ ወገኖች፣ ደርሶ ሁሉንም እንደሆነ ነገር፣ ልሳኑ የሚታወቅ (የሚለይ) ሆነም አልሆነም በልሳን መናገርን ትልቅ አጽንኦት ይሰጡታል። ይሁን እንጂ አብዛኛው እንዳዉም ሁሉም ባይሆን ነው ፣ ትርጉም የሌለው  ድምጽ (ጫጫታ) ነው። 

በልሳኖች ስለመናገር መጽሐፍ  ቅዱስ የሚያስተምረው  ምንድነው?

በልሳኖች መናገር

መጽሐፍ ቅዱስን በተለይም በ‘ልሳኖች የመናገር ምዕራፍ’ ብለን ልንጠራው በምንችለው የቅዱስ ጳውሎስ የመጀመሪያው የቆሮንቶስ መልእክትን ምዕራፍ አሥራ አራትን ስናነብ የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ እንላለን። 

(1)በልሳኖች መናገር በስጦታዎቹ ቅደም ተከተል የመጨረሻው ነው

ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ስለ መንፈስ ስጦታዎች ሲናገር በልሳኖች መናገርንና ልሳኖችን መተርጎምን የጠቀሰው በስጦታዎች ዝርዝር መጨረሻ ነው። እንዲህም ይላል፦ “የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው፤ አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው፤ አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፥ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል። ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ ዕውቀትን መናገር ይሰጠዋል፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤ ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል” (1 ቆሮ 12:4-11)። እንዲህ አድርጎ ነው በልሳኖች የመናገርና የመተርጎም ስጦታን በቅደም ተከተል የመጨረሻ ያደረገው። ከእርሱ በፊት በጥበብ መናገር፣ በዕውቀት መናገር፣ እምነት፣ የመፈወስ ስጦታ፣ ተአምራትን ማድረግ፣ ትንቢትን መናገርና መናፍስት የመለየት ስጦታን አስቀድሟል። 

ደግሞም ሐዋርያው ብሏል፦ “እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛም ነቢያትን፥ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፥ ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን፥ ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ፥ እርዳታንም፥ አገዛዝንም፥ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጎአል” (1ኛ ቆሮ 12 ÷28) ። እዚህ ላይም ሐዋርያው ከመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ተራ በልሳኖች መናገርን መጨረሻ ነው ያስቀመጠው። 

ሐዋርያው “ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ።ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ” (1 ቆሮ 12 ÷31) በማለት ይኸው እጅግ የላቀው መንገድ ፍቅር መሆኑን ይገልጻል።ከትንቢትም ሁሉ፣ ከዕውቀት ሁሉ፣ ተራራን ከሚያፈልስ እምነትም ድሃን ከማሰብም፣ ከባሕታዊ አኗኗርም ይልቅ ፍቅር እንዴት ታላቅና የበለጠ ተፈላጊ እንደሆነም ያስረዳል (1 ቆሮ 13)። ፍቅር በሰውም ሆነ በመላእክት ቋንቋ ከመናገር ይልቅ - ከሰዎች ብቻ አይደለም- የበለጠ ነው። እንዲህ ይላል፦“በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ” (1 ቆሮ 13÷1 ) ።

(2) በልሳኖች መናገር ለሁሉ የሚሰጥ ስጦታ አይደለም

እግዚአብሔር”ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል” (1 ቆሮ 12÷11)። “እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፤” (ሮሜ 12÷6) “እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው” (ሮሜ 12÷3) መሆኑን ከላይ ተመልክተናል።

በልሳን የመናገር ስጦታን በተመለከተ ሐዋርያው   ጳውሎስ በግልጽ ሲናገር፦“ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን? ሁሉስ ተአምራትን ይሠራሉን?ሁሉስ የመፈወስ ስጦታ አላቸውን? ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን? ሁሉስ  ይተረጉማሉን?” (1 ቆሮ 12÷29፣30) ብሏል። ከዚህ ክፍል በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ስጦታው ለሁሉ  አይደለም። ስለዚህ በሐዋርያቱ ዘመን እንኳ ለእያንዳንዱ አማኝ በልሳኖች መናገር ስጦታን መቀበል ያስፈለገ አልነበረም። በአንድ ሰው ላይ መንፈስ ቅዱስ መውረዱን ለማረጋገጥ የግድ ተፈላጊ (መታየት የነበረበት) ምልክትም አልነበረም። በልሳኖች ባይናገርም እንኳ አንድ ሰው ‘ቅዱስ’ ሊሆን ይችላል።

እግዚአብሔር መቼ ስጦታን እንደሚሰጥና የሚሰጥበትንም ምክንያት እርሱ ያውቃል። ስብከት በተጀመረበት በዚያን በሐዋርያትም ዘመን በልሳኖች መናገር ተትረፍርፎ ለማነጽ ተሰጥቶ ነበር። በዚያን ዘመን ያስፈልግ ነበርና። 

በልሳኖች መናገር በሁሉ ዘመን አያስፈልግም። ይህን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ” (1 ቆሮ 13÷8) ። በሐዋርያትም ዘመን እንኳ በልሳኖች ለመናገር መሟላት የሚገባቸው ነገሮች ነበሩ። ከእነዚህ አንዳንዶቹ ሁኔታዎች ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው በመጀመሪያ ደብዳቤው በምዕራፍ አሥራ አራት እናነባለን።

(3) በልሳኖች መናገር ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ መሆን አለበት

በልሳኖች ስለመናገር የሚያወሳው ምዕራፍ (1 ቆሮ 14ን ማለት ነው) ተለይቶ የሚታወቅበት ዋና ቃል ‘ለማነጽ’ የሚለው ቃል ነው።ሐዋርያው ይኸንኑ ቃል ደጋግሞና አስረግጦ ይናገራል፤ በአጽንኦትም እንዲህ ይላል፦ “ሁሉ ለማነጽ ይሁን።” (1 ቆሮ 14÷26)ና  “እንዲሁ ደግሞ እናንተ መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ የምትፈልጉ ከሆናችሁ ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ እንዲበዛላችሁ ፈልጉ” (1 ቆሮ 14÷12) ።

ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ ሐዋርያው እንዲህ ይላል፦“በልሳኖች ከሚናገር ትንቢትን የሚናገር ይበልጣል።” (ቍ 5) ምክንያቱም በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል፤ ትንቢት የሚናገር ግን ማሕበሩን ያንጻል” (ቍ 4) ። “ትንቢትን መናገር’ ማለት በዚያን ጊዜ ማስተማር ማለትም ነበር።  ሐዋርያው ‘ትንቢት መናገርን’ ይመርጣል። ምክንያቱም “ትንቢትን የሚናገር ግን ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም ለሰው ይናገራል”ና (ቍ 3)።

(4) በልሳን የተነገረው መተርጎም አለበት

ሐዋርያው እንዲህ ይላል፦ “ስለዚህ በልሳን የሚናገር እንዲተረጉም ይጸልይ” (1 ቆሮ 14÷13) ። በማከልም፣“የሚተረጉም ባይኖር ግን በማኅበር መካከል ዝም ይበል” (ቍ 28) ይላል ። የሐዋርያው ምክንያት ግልጽ ነው፤ የቤተ ክርስቲያን መታነጽ ነው።እንዲህ ይላል፦“ማኅበሩ ይታነጽ ዘንድ ንግግሩን ባይተረጐም በልሳኖች ከሚናገር ትንቢትን የሚናገር ይበልጣል” (ቍ 5) ። መታነጽ የማይኖር ከሆነ ዝም ይበል። ‘ዝም ይበል’ የሚለው ሐረግ ሐዋርያዊ ትዕዛዝ ነው። ስለዚህ በልሳን የሚናገር ወይ ለማነጽ መናገር አለበት ወይም ዝም ማለት አለበት።  

የሚተረጉም መኖሩ በልሳን የተነገረው ጤናማ ለመሆኑ ይመሰክራል።ስለዚህ በልሳን የመናገር ስጦታ በአንድ ጊዜ (ላይ) ለሁለት ሰው ይሰጣል። አንደኛው የሚናገር ሲሆን ሌላውኛው የሚተረጉም ነው። ይህ ሲሆን ሁሉ “ነገር በሁለትና በሦስት ምስክር አፍ ይጸናል” (2 ቆሮ 13÷1) የሚለው ሥራ ላይ ዋለ ማለት ነው። በልሳን መናገር ያለ ተርጓሚ ከሆነ ጥቅሙ ምንድነው? በሥፍራው የተገኙት ሁሉ የማይረዱት ከሆነ ምን ፋይዳ አለው?

(5) ‘ራሱን ያንጻል’ የሚለው ትርጕሙ ምንድነው?

‘ራሱን ያንጻል’ ማለት ስጦታውን የተቀበለው ሰው ለግሉ ለመታነጽ በሚጠቅመው፤ መንፈስ በወረደበት ልዩ መንፈሳዊ ሁኔታ (ተመስጦ) ውስጥ ይገባል ማለት ነው። ስለዚህ ሁኔታ በቅዱስ ጳውሎስ የተሰጡ ሁለት ማስታወሻዎች አሉ።  እነርሱም፦

(ሀ)በግሉ በሚጸልይበት ጊዜ በእርሱና በእግዚአብሔር መካከል እንደሚኖረው መንፈሳዊ ሁኔታ (ልክ እንደዚያ) ያ ሰው ጸጥ ማለት አለበት። ሐዋርያው እንዲህ ይላል፦“የሚተረጉም ባይኖር ግን በማኅበር መካከል ዝም ይበልና ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር።” (1 ቆሮ 14÷28) ። በልሳን መናገሩ በእርሱና በእግዚአብሔር መካከል ያለ ነገር ነው። በልሳን ሲናገር በቤተ ክርስቲያን ሰው ሁሉ እያየው ሳይሆን እልፍኙን ዘግቶ በግሉ እንደሚጸልይ ሰው መሆን ማለት ነው። ስለዚህ በልሳን መናገር የጸሎት ዓይነት ይሆናል። ያም ሲሆን፦ 

(ለ) አእምሮ ፍሬያማ አይሆንም፣ የመንፈስ ሥራ ብቻ ነው። ሐዋርያው ይህን ይላል፦ “በልሳን ብጸልይ መንፈሴ ይጸልያል አእምሮዬ ግን ያለ ፍሬ ነው” (1 ቆሮ 14÷14)።  ሐዋርያው ይህንን የጸሎት  ሁኔታ በአዕምሮ በመረዳት እንዲሟላ ነው የሚፈልገው።  ሰውዬው በመንፈስ ሆኖ መጸለይ ይገበዋል፣ ደግሞም በአእምሮውም በመረዳት፣ በመንፈስ ሆኖ መዘመር ይገበዋል፣ ደግሞም በአዕምሮውም በመረዳት።ምንም እንኳ ሐዋርያው እጅግ በጥንቃቄ ልብ እንዲባል የሚፈልገውን  በማከል፣ መታነጹ የተሟላ እንደማይሆን አመልክቶ “በልሳን የሚናገር ራሱን ያንጻል” (1 ቆሮ 14:4) የሚለውን ቢጠቅስም ስለመታነጽ እንዲህ ይላል፦“---ከሁላችሁ ይልቅ በልሳኖች እናገራለሁና እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ ነገር ግን ሌሎችን ደግሞ አስተምር ዘንድ በማኅበር እልፍ ቃላት በልሳን ከመናገር ይልቅ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ልናገር እወዳለሁ” (1 ቆሮ 14:18፣ 19) ።

ስለዚህ ትልቅ ነገር ማግኘት እንደሆነ በማመን ሰዎች ባለ በሌለ ኃይላቸው በልሳን ለመናገር መጣጣር አያስፈልጋቸውም። 

እንደ መንፈስ ቅዱስ ስጦታ በልሳን የመናገር ጉዳይ እንደዚህ ከሆነ ታዲያ አንዳንድ ሰዎች በልሳን እንናገራለን ስለሚሉትና ስለቃላቸው እውነተኛነት እርግጠኛ ካልሆንን ምን እንበል? 

(6) ሐዋርያው በልሳን መናገርን በተመለከተ የሚደረጉ ስህተቶችን ይዋጋል

ለማነጽ ያልሆኑ ልሳኖችንና ስጦታውን ያገኘውን ሰው ዝም አለማለት ሐዋርያው አጥብቆ ተዋግቷል። 

እንዲህ ይላል÷-

(ሀ) ልሳኖች የሚጠቅሙ አይደሉም። “አሁን ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ መጥቼ በልሳኖች ብናገር፥ በመግለጥ ወይም በዕውቀት ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኋችሁ ምን እጠቅማችኋለሁ?” (ቍ. 6)። እንደዚህ ዓይነቱን ልሳን ድምፅ ሲሰጥ የድምፁን ልዩነት እንደማይገልጥ፣ ድምፁ እንደማይታወቅና የማይገባ የሙዚቃ መሣሪያ አድርጎ ይገልጠዋል (ቍ. 7ና 8) ።

(ለ) ልሳኑ ለነፋስ የሚነገር ይሆናል። ሐዋርያው ይላል፦“እንዲሁ እናንተ ደግሞ የተገለጠውን ቃል በአንደበት ባትናገሩ ሰዎች የምትናገሩትን እንዴት አድርገው ያስተውሉታል? ለነፋስ የምትናገሩ ትሆናላችሁና” (1 ቆሮ 14:9) ።

(ሐ) በልሳን የሚናገሩ እንደ ‘እንግዳ ሰው’ ሊመስሉ ይችላሉ። ሐዋርያው እንዲህ ይላል፦“እንግዲህ የቋንቋውን ፍች ባላውቅ ለሚናገረው እንግዳ እሆናለሁ፥ የሚናገረውም ለእኔ እንግዳ ይሆናል” (1 ቆሮ 14:11) ።

(መ) በልሳን የሚናገሩ ከቤተክርስቲያኒቱ ከተገኙት ጋር ኅብረት አይኖራቸውም፤ ሌሎችንም አያንጹም። 

በልሳን የሚናገር ሰው ለመጸለይ ወይም ምስጋናን ለማቅረብ ወይም እግዚአብሔርን ለመባረክ በቆመ ጊዜ ማንም አይረዳውም (አይሰሙትማ)። ካልተረዱት ታዲያ በምን ዓይነት መንገድ ነው ሕይወትን ለአማኞች ወደ ማካፈል የሚደርሰው? ስለዚህ ሐዋርያው እንዲህ ይላል፦“እንዲያማ ካልሆነ፥ አንተ በመንፈስ ብትባርክ ባልተማሩት ስፍራ የተቀመጠው የምትለውን ካላወቀ እንዴት አድርጎ ለምስጋናህ አሜን ይላል? አንተማ መልካም ታመሰግናለህ፥ ሌላው ግን አይታነጽበትም።” (1 ቆሮ 14:16፣ 17)

(ሠ) በልሳን የሚናገሩ እብድን ይመስላሉ። “እንግዲህ ማኅበር ሁሉ አብረው ቢሰበሰቡ ሁሉም በልሳኖች ቢናገሩና ያልተማሩ ወይም የማያምኑ ሰዎች ቢገቡ። አብደዋል አይሉምን?” (1 1ቆሮ 14:23) 

(ረ) ልሳኑ አግባብ የሆነ፣ቅደም ተከተል ያለውና ግርታን የማይፈጥር ሊሆን ይገበዋል። በሐዋርያቱ ጊዜ በልሳን የመናገር ስጦታ ማንንም የሞላ ነበር። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ስጦታው በሥነ ሥርዓት እንዲያዝ አበክሮ ይናገራል። እንዲህም ይላል፦“እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና” (1 ቆሮ 14:33)ና “በልሳን የሚናገር ቢኖር ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት ሆነው በተራቸው ይናገሩ አንዱም ይተርጉም” (1 ቆሮ 14÷ 27)።

(7) በልሳን መናገር ለማያምኑት ምልክት ነው 

በሐዋርያው አስተያየት አማኞች በ‘ትንቢት’ ይጠቀማሉ። በልሳን የተነገረው ከተተረጎመ ግን ያላመኑ ያተርፋሉ። ሐዋርያው እንዲህ ይላል፦ “እንግዲያስ በልሳኖች መናገር ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፥ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም” (1 ቆሮ 14:22) ።

ስለዚህ በቤተ ክርስቲያን ያሉቱ አማኞች ከሆኑ እንደ ሐዋርያው ትምህርት በልሳን መናገር ለእነዚህ ምን ይፈይድላቸዋል? 

Comments

Popular posts from this blog

Comparative Theology የነገረ መለኮት ንጽጽር (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት)/ በብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሲኖዳ ሳልሳዊ

 የነገረ መለኮት ንጽጽር  (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት): የወደደ  ሁሉ በነጻ እንዲጠቀምበት ተፖስቷል። ይሁን እንጂ መብቱ በሕግ የተጠበቀ ስለሆነ በየትኛውም መልኩ ለንግድ እንዲውል አልተፈቀድም። ልዩ ልዩ መግቢያ የሚለውን መጀመሪያ ካነበቡ በኋላ የተቀረውን በተመረጠው ቅደም ተከተል ማንበብ ይቻላል። ልዩ ልዩ መግቢያ   ጥምቀት   ትውፊት (ወግና ልማድ)   መካከለኝነት   ጾም የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ መንፈሳዊ ስጦታዎችና በልሳኖች የመናገር ስጦታ   ሥርዐት ንስሐ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ (1)  ድንግል ማርያምን ስለማክበር (2) ለጥያቄዎች መልስ (ሀ) ድንግሊትን ‘የወይን ግንድ (ተክል)’ና የ ‘ሕይወት በር’ የሚል ማዕረግ  ለምን እንሰጣታለን? (ለ) ወደ ድንግል ማርያም መጸለይ ትክክል ነው ወይ? (3) የድንግል ማርያም ድንግልና ዘላለማዊነት (4) ለተቃራኒ አስተያየቶች መልስ (ሀ) “የመጀመሪያ ልጇን” የሚለው ሐረግ (ለ) “ሚስትህ” የሚለው ሐረግ (ሐ) “አብረው ከመሆናቸው በፊት ጸንሳ ተገኘች” (መ) “የመጀመሪያ ልጇን እስክትወልድ አላወቃትም” (ሠ)  “ወንድሞቹ” የሚለው ሐረግ   የቅድስት ድንግል ማርያም  ክብሯ (1) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ድንግል እመቤታችንን አያከብሩም፤ ደግሞም እንድታማልድላቸውም (እንድትማልድላቸውም)  አይጠይቋትም።ከእነርሱ ወገኖች አንዳንዶቹ እንዲያውም ጫጩቱ ከተፈለፈለ በኋላ ዋጋ ከሌለው የዶሮ እንቁላል ቅርፊት ጋር እስከሚያመሳስሏት ይደርሳሉ።ይህ የተጋነነ ማቃለል የመጣው ምናልባት ሮሜዋውያን ካቶሊኮች የተጋነነ ማክበር ስለሚያከብሯት ለዛ ተቃርኖ ከማሳየት አዝማሚያ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን አንዱንም የእርሷን በዓል አያከብሩም።  (2) አንዳንዶቹ የፕሮቴስታንት ወገኖች ድንግል ማርያምን “እህታችን” ይሏታል። (3) በተጨማሪ አንዳንዶቹ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ጌታ ኢየሱስን በድንግልና ከወለደች በኋላ ከዮሴፍ ጋር ጋብቻዋን ፈጽማለች፤ የ‘ኢየሱስ ወንድሞች’  ወይም የ’ጌታ ወንድሞች’ ተብለው የተጠሩ ልጆችን ወልዳለች ይላሉ።  (4) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ቤተክርስቲያናችን ለድንግል እመቤታችን የሰጠቻቸውን አንዳንድ የማዕረግ ስሞችም ይቃወማሉ።  (5) ድንግልን ያለማክበራቸው አንዱ...

ስለ "አስታዋሽ ጾምና በዐሉ" ጥያቄና መልስ

 ስለ "አስታዋሽ ጾምና በዐሉ" ጥያቄና መልስ  ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ፦ ሕልውናችንን-ነጻነትችንን የማረጋገጥና የማስቀጠል አንድነታችንን የመጠበቅና የማጠንከር  በእሴቶቻችን የመደሰት፣ እነርሱን የመንከባከብና የማስተዋወቅ  በረከታችንን የማብዛትና የማካፈል  ኃላፊነቶቻችንን በማኅበር ፣ በማስተዋልና በትጋት እንድንወጣ “ጾሙና በዐሉ" አስታዋሽ ባሕላዊ ምልክታችን ይሁንልን   ጥያቄ 1 ፡ አድማጭ ተመልካቾቻችን እንኳን ደህና መጣችሁ።የከበረ ሰላምታችን ይድረሳችሁ። ዛሬ የምንወያየው ከአቶ ባንቱ ገብረማርያም ጋር ይሆናል። አቶ ባንቱ በሙያው ፋርማሲት ነው። እንደነገረኝ በእምነቱ ደግሞ ባፕቲስት ነው።ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ባሕላዊ ምልክት የሚሆን “ጾምና በዐልን” በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል። የምንወያየውም ስለዚሁ "ጾሙና በዐሉ" ምልክትነት ይሆናል።  አቶ ባንቱ ለመወያየት  ወደ እኛ በመምጣትህ አመሰግንሃለሁ። እንኳን ደህና መጣህ። አንተ እያልኩ ልቀጥል ወይስ አንቱ? መልስ 1፡ ዎገኔ፡   እንኳን ደህና ቆየኸኝ። ለአድማጭ ተመልካቾቻችሁም ሰላምታዬ ይድረስልኝ። አንተ በለኝ። የሚያውቀኝ ሁሉ አንተ ነው የሚለኝ።  ጥያቄ 2 ፡ እሺ  አንተ እያልኩ እቀጥላለሁ። አቶ ባንቱ፣ ምናልባትም ብዙ ሰው ስለማያውቅህ  እስቲ ስለራስህ በአጭሩ ንገረን። ወዲያውም መክፈቻ ይሆነናል መልስ 2 ዎገኔ ፦ አስቀድሜ ይኸን ዕድል ስለሰጠኸኝ ላመሰግንህ እወዳለሁ። አድማጭ ተመልካቾችህንም ጊዜ ወስደው  ውይይቱን  ስለሚከታተሉ ላመሰግናቸው እወዳለሁ።አዎን፣ ባንቱ ገብረማርያም እባላለሁ።እንደነገሩኝ የተወለድኩት ሽርካ በዛሬ አጠራሩ በአርሲ ዞን ነው።ነፍስ ያወቅሁትና ትምህርት ...