መካከለኛነት /ምልጃ
1. በክርስቶስ መካከለኛነት (አስታራቂነት)ና በቅዱሳን ምልጃ (አማላጅነት) መካከል ያለው ልዩነት
2. የቅዱሳኑ ምልጃ ለእኛ መጸለይ ብቻ ነው
3. እግዚአብሔር ሰዎች የጻድቅንን ምልጃ እንዲለምኑ ይጠይቃል
4. መላእክትና ቅዱሳን በምድር ላይ ያለንበትን ሁኔታ ያውቃሉን?
5. የቅዱሳኑ ታላቅነት፣ ዕውቀታቸውና አገልግሎታቸው
6. ስለ ቅዱሳን ታላቅነት ሌሎች ምሳሌዎች
7. በሞት የተለዩቱ ቅዱሳን አሁንም ቢሆን በሕይወት ናቸው
8. የመላእክት ምልጃ ምሳሌዎች
9. በጌታ ፊት የቅዱሳን ሞገስ
10. ተቃውሞዎችና ምላሾቻቸው
11. የቅዱሳንን ጸሎት መጠየቅ መንፈሳዊነቱ
12. ምልጃ በየዕለቱ የምናየው እውነታ ነው።
ምልጃ
ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን የድንግል ማርያምን ወይም የመላእክትን ወይም የቅዱሳንን ምልጃ (አማላጅነት) አይቀበሉትም ። ለተቃውሞአቸውም መሠረቱ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ “ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” (1 ዮሐ 2÷1) ና ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” (1 ጢሞ 2÷5) በማለት የጻፉት ነው።
(1) በእርግጥ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነትና (አስታራቂነትና) በቅዱሳን ምልጃ (አማላጅነት) መካከል መሠረታዊ ልዩነት አለ
የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት የ‘‘ማስተሰረይ’ ሥራ ነው፤ ያም ማለት በምትካችን ዕዳችንን የከፈለ ‘ማስተሰረያ’ ሆኖ የኃጢአትን ይቅርታ እንድናገኝ ያስታርቀናል ማለት ነው። እርሱ በመካከለኛነት ለአባቱ ለአብ “ኃጢአታቸውን አትቁጠርባቸው። ምክንያቱም እኔ በደላቸውን ተሸክሜላቸዋለሁና” (ኢሳ 53÷ 6) ይላል ማለት ነው። እንደዚህ በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል መካከለኛ ሆኖ ይቆማል፣ ኧረ እንዲያውም እርሱ ብቻ ነው በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል ያለ መካከለኛ። የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ፍትሕን ፈጽሞ (አሟልቶ) ለእነርሱ በመሞት ለሰዎች የኃጢአትን ይቅርታ አስገኘ።
ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ይህንኑ ማለቱ ነው እንዲህ ሲል፦“ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ” (1 ዮሐ 2÷1፣2)። እዚህ ላይ የማስተሰረይ መካከለኛነት መሆኑ ግልጽ ነው። ለኃጢአተኛው የሚደረግ መካከለኛነት ነው። “ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ” ይህ ኃጢአተኛ ማስተሰረያ ያስፈልገዋል። ይህንን ‘ማስተሰረያ’ ያቀረበ ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ስለዚህ ስለእኛ ባፈሰሰው ደሙ በኩል ክርስቶስ ስለ እኛ መካከለኛ ሆኖ ሊቆም ይችላል።
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለ ብቸኛ መካከለኛ መሆኑን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውም ቢሆን ይኸው ትርጉም ነው የሚሰጠው። እንዲህ ይላል፦“አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ፤ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ፥ ይህም በገዛ ዘመኑ ምስክርነቱ ነበረ” (1 ጢሞ 2÷5፣ 6) ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን መስዋዕት ያደረገ፣ የኃጢአትን ዋጋ የከፈለ አዳኝ ሆኖ ያስታርቀናል።
ይህ ዓይነቱ መካከለኛነት ጨርሶ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። ይህ ለክርስቶስ የብቻው ባህርይ (መለያው) ነው። የቅዱሳን ምልጃ (አማላጅነት) ግን ከማስተሰረይ ወይም ከመቤዠት ጋር ግንኙነት የለውም። ስለ እኛ ወደ ራሱ ወደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በምልጃ መቅረብ ነው።
(2) የቅዱሳን ምልጃዎች ስለእኛ የሚጸልዩአቸው ጸሎቶች ብቻ ናቸው፤ የተማጽኖ ዓይነት ናቸው፤ ከክርስቶስ የ‘ማስተስረይ መኻከለኛነት’ (አስታራቂነት) ፍጹም የተለዩ ናቸው።
ይህ “እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ” (ያዕ 5:16) በሚለው በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል የተፈቀደ ነው። ቅዱሳን ራሳቸው ሰዎችን እንዲጸልዩላቸው ይጠይቁ ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች በጻፈው መልእክት “ስለ እኛ ጸልዩ” (2 ተሰ 3÷1) ብሏል። ዕብራውያንንም እንዲዚሁ“ጸልዩልን” (ዕብ 13÷18) በማለት ጠይቋል። ለኤፌሶን ሰዎችም “በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ--ና ---- ስለ እኔ ለምኑ” (ኤፌ 6÷18 ፣ 19) ብሏል።
አንዳችን ለሌላችን እንድንጸልይ ያለው ጥያቄ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰበት ሥፍራ ቁጥር ሥፍር የለውም። ቅዱሳኑ ስለእነርሱ እንድንጸልይላቸው ከጠየቁ እኛ እነርሱ እንዲጸልዩልን አንጠይቅምን? እንደ እኛው መንፈሳዊ ውጊያ ያልተለያቸውንና ለመከራ የተጋለጡትን ጸልዩልን ብለን ከጠየቅን ተጋድሏቸውን ጨርሰው ወደ ገነት የሄዱትንና ከክርስቶስ ጋር የሚኖሩትን መጠየቅ የለብንምን? ወይስ እነዚህ ቅዱሳን ከምድር ወደ ገነት ከሄዱ በኋላ ከማዕረጋቸው ዝቅ ተደርገዋል? እንዲጸልዩልን መጠየቅ የሚፈቀድልን በምድር ሳሉ ብቻ ነውን? ለእግዚአብሔር ቅርብ በሆኑበት በገነት ሲሆኑ እንከለከላለንን? የሰው ልጆችን ጸሎት ከጠየቅን ከመላእክት መጠየቅ የበዛ ነገር መሆኑ ነውን?
(3) ጻድቃን ምልጃ እንዲያደርጉላቸው እግዚአብሔር ራሱ ሰዎችን ይጠይቃቸዋል
የጻድቃንን ምልጃ እግዚአብሔር ራሱ ይጠይቃል፣ ይቀበላል እንዲደረግም መንገዱን ያመቻቻል። ከእንደዚህ ዓይነቶች ምልጃዎች እግዚአብሔር ራሱ የተቀበላቸውን ጥቂት ምሳሌዎችን እሰጣችኋለሁ።
(ሀ) የአብርሃም የአባታችንና የንጉሥ አቢሜሌክ ታሪክ፡አቢሜሌክ ስህተትን ሠራና የአብርሃምን ሚስት ሣራን ወደ ቤተ መንግሥቱ ወሰደ። ይህን ያደረገው በንጹሕ ህሊና ነበር፤ ምክንያቱም አብርሃም እህቴ ናት ብሎ ተናግሯልና። ጌታ በህልም ወደ አቢሜሌክ መጣ፣ በሞት አስፈራው፤ እንዲህም አለው፦ “አሁንም የሰውዬውን ሚስት መልስ፤ ነቢይ ነውና፥ ስለ አንተም ይጸልያል፥ ትድናለህም” (ዘፍ 20÷7) ። እግዚአብሔር አቢሜሌክን ሣራን ለባሏ እንደመለሰ ወዲያውኑ ይቅር ሊለው ይችል ነበር።ይሁን እንጂ ይቅር መባልን ለማግኘት አስቀድሞ ሊሟላ የሚያስፈልገውን ነገር አስቀመጠ።አብርሃም ከጸለየለት ብቻ አቢሜሌክ ይቅር ሊባልና በሕይወት ሊኖር ይችላል። እግዚአብሔር እንደዚህ የአብርሃምን ምልጃ ፈለገ (ጠየቀ)። ይህንንም አቢሜሌክ ይቅርታ የሚያገኝበት ቅድመ ሁኔታ አደረገው።
(ለ) የኢዮብና የሦስቱ ጓደኞቹ ታሪክ፡ በተመሳሳይ ሁኔታ እግዚአብሔር የኢዮብን ሦስት ጓደኞች ይቅር ለማለት የኢዮብን መማለድና መጸለይ እንደ ቅድመ ሁኔታ አድርጎ እግዚአብሔር አቀረበ።ይህን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “------እግዚአብሔር ቴማናዊውን ኤልፋዝን፦እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅንን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና ቍጣዬ በአንተና በሁለቱ ባልንጀሮችህ ላይ ነድዶአል። አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደ ባሪያዬ ወደ ኢዮብ ዘንድ ሂዱ፥ የሚቃጠልንም መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ አሳርጉ፤ ባሪያዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል፥ እኔም እንደ ስንፍናችሁ እንዳላደርግባችሁ ፊቱን እቀበላለሁ---” (ኢዮብ 42÷7፣ 8)
በሁለቱም ምሳሌዎች እግዚአብሔር ራሱ ለተሳሳተው ሰው ተናገረ። ይሁን እንጂ ይቅርታን በቀጥታ አልሰጠውም። ይቅር ማለትን ቅዱሳኑ ለኃጢአተኛው በሚያደርጉት ጸሎት ላይ መሠረተው። ይህንም ያደረገው ባንድ በኩል ኃጢአተኛው ይቅርታን እንዲያገኝ፤ በሌላ በኩል ቅዱሳኑን ሕዝቡ በአክብሮት እንዲመለከታቸው ነው። ከነዚህ ከሁለቱ ምሳሌዎች መረዳት እንደሚቻለው እግዚአብሔር ምልጃውን መቀበል ብቻ ሳይሆን እንዲደረግም ይጠይቃል።
(ሐ) የአብርሃም ለሶዶም መማለድ÷ እግዚአብሔር ለአብርሃም ሳይነግረው ሶዶምን ሊቀጣ በቻለ ነበር። አብርሃም በራሱ ተነስቶ አልነበረም ስለ ሶዶም ጣልቃ የገባው። ነገር ግን ጌታ ራሱ ጉዳዩን ገለጠለት፤ በጉዳዩ አሳተፈው፤ ለሶዶም ሕዝብም እንዲለምን ዕድል ሰጠው፤ ምልጃውንም ተቀበለው። አብርሃም በሕዝቡ ሁሉ ዓይን ከብሮ እንዲታይና ፣ቅዱሳንን እርሱ እንዴት እንደሚያከብራቸው ለእኛ ሊያሳየንም እግዚአብሔር ይህን ታሪክ እንዲመዘገብ ፈቀደ። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርም አለ፦ እኔ የማደርገውን ከአብርሃም እሰውራለሁን?” (ዘፍ 18÷17) ይላል። ከዚህ በኋላ የሰዶምን ጉዳይ ለአብርሃም ነገረው። ለሶዶም ሕዝብም እንዲማልድ ዕድልን ሰጠው። አብርሃምም በሶዶም ሃምሳ ወይም አርባ ወይም ሠላሳ ወይም ሃያ ወይም አሥር ጻድቃን ቢኖሩ ስለ እነርሱ አገሩን እንደማያጠፋ ተስፋ በማድረግ ወደ እግዚአብሔር ማለደ።
በአገሩ ስለሚኖሩት ጻድቃን ሲል ጌታ አገሩን የማያጠፋው ስለአብርሃም ክብር ብቻ ሳይሆን በጌታ ፊት ጻድቃን ስለሆኑቱ ክብርም ስለመሆኑ ሃሳብ ይሰጠናል። ጌታም አለ፦ “በሰዶም በከተማይቱ ውስጥ አምሳ ጻድቃን ባገኝ ስፍራውን ሁሉ ስለ እነርሱ እምራለሁ -----ከዚያ አርባ አምስት ባገኝ አላጠፋትም ------ለአርባው ስል አላደርገውም -------ከዚያ ሰላሳ ባገኝ አላጠፋም ------ ስለ ሀያው አላደርገውም ------- ስለ አሥሩ አላጠፋትም አለ።” ( ዘፍ 18÷ 26-32)
“ስለእነርሱ እምራለሁ” የሚለው ሐረግ መለኮታዊ ዋጋ (መልእክት) አለው። እግዚአብሔር ለሌሎች ሲል ሰዎችን የሚያድን መሆኑን ያመለክታል። ይህም ስለኃጢአተኞች የሚደረግን የጻድቃንን ምልጃ የሚቀበል ለመሆኑ ግልጽ ማስረጃ ነው። ምልጃው የሚደረግላቸው ሰዎች ሳይጠይቁም (እንኳ) እግዚአብሔር የጻድቃኑን ምልጃ ይቀበላል።
(መ) ስለ እስራኤል ሕዝብ የሙሴ መማለድ
የወርቅ ጥጃን በማምለካቸው ምክንያት እግዚአብሔር ሕዝቡን ሊያጠፋ ፈቀደ። ይሁን እንጂ በቀጥታ አላደረገውም፣ ነገር ግን አስቀድሞ ለነቢይ ሙሴ ገለጠለትና ለሕዝቡ ይማልድ ዘንድ ዕድል ሰጠው፤ ምልጃውንም ተቀበለ።
ልክ አብርሃም እግዚአብሔርን “ካንተ ይራቅ” እንዳለው በተመሳሳይ ሁኔታ ሙሴም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፦“ከመዓትህ ተመለስ፥ ለሕዝብህም በክፋታቸው ላይ ራራ።ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ ይህችንም የተናገርኋትን ምድር ሁሉ ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፥ ለዘላለምም ይወርሱአታል ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ።” ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል÷- “እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ።” (ዘጸ 32÷7-14)
(ሠ) በሞት የተለዩቱ በእግዚአብሔር ፊት የበለጠ ሞገስ አላቸው÷ ከላይ የሰጠናቸው ምሳሌዎች በሕይወት ያሉ በሕይወት ስላሉ ሌሎች ሰዎች የተደረገ ጸሎት ነው። በሞት የተለዩቱ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ የበለጠ ሞገስ አላቸው። እነርሱ በእግዚአብሔር ፊት ያላቸው ሞገስ ሳይጸልዩ እንኳ (ስለእነርሱ) ምህረትን ለሰዎች እስከሚያደርግላቸው ድረስ ከፍ ያለ ነው። እነዚህ ለአንድ ሰው ከጸለዩለትማ የቱን ያህል እግዚአብሔር ምህረትን ያደርግ?
ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን ለባሪያው ዳዊት ሲል እግዚአብሔር ያደረገው የምህረትና የርኅራኄ ሥራ ነው። ሰሎሞን ኃጢአትን አደረገና እግዚአብሔር መንግስቱን ሊቀድ (ሊከፍል) ወሰነ፤ ስለሚቀደደው መንግሥት እንደዚህ አለ፦ “ነገር ግን ከልጅህ እጅ እቀድደዋለሁ እንጂ ስለ አባትህ ስለ ዳዊት ይህን በዘመንህ አላደርግም።ነገር ግን ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊትና ስለ መረጥኋት ስለ ኢየሩሳሌም ለልጅህ አንድ ነገድ እሰጣለሁ እንጂ መንግሥቱን ሁሉ አልቀድድም” (1 ኛ ነገሥ 11÷ 12፣ 13) ።
እግዚአብሔር ለኢዮርብዓም በተናገረ ጊዜ ይህንኑ ቃል ደገመው÷“እነሆ፥ ከሰሎሞን እጅ መንግሥቱን እቀድዳለሁ፥ አሥሩንም ነገዶች እሰጥሃለሁ፤ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ከእስራኤልም ነገድ ስለ መረጥኋት ከተማ ስለ ኢየሩሳሌም ግን አንድ ነገድ ይቀርለታል፤ መንግሥቱንም ሁሉ ከእጁ አልወስድም፤ ትእዛዜንና ሥርዓቴን ስለ ጠበቀው ስለ መረጥሁት ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ግን በዕድሜው ሁሉ አለቃ አደርገዋለሁ።” (1ኛ ነገሥ 11÷31፣ 32፣ 34) አለው።
በአንድ ምዕራፍ ውስጥ “ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት” የሚለውን ሐረግ ሦስት ጊዜ ደግሞታል። ለዚህ ነው መዝሙረኛው ወደ እግዚአብሔር “ስለ ዳዊት ስለ ባሪያህ የቀባኸውን ሰው ፊት አትመልስ” (መዝ 132÷10) በማለት የጸለየው።
ዳዊት እንዲህ ዓይነት ሞገስ በእግዚአብሔር ዘንድ ካለው ድንግል ማርያም፣ መላእክት፣ ከሴቶች ከተወለዱት ሁሉ የሚበልጠው መጥምቁ ዮሐንስ ፣ ለጌታ ሲሉ ስቃይ የተቀበሉትና ሞትን የቀመሱት ሰማዕታቱ የቱን ያህል ሞገስን ያገኙ ይሆኑ?
በምድር ላይ ያሉትን ጸሎታቸውን የምንጠይቅ ከሆነ “እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ” (ዳን 12÷3) የተባሉትን እንዲጸልዩልን ስለምን አንጠይቅም? ስለምን “መልካሙን ገድል የተጋደሉትን፣ ሩጫቸውን የጨረሱትንና እምነታቸውን የጠበቁትን” (2 ጢሞ 4÷7) እንዲጸልዩልን አንጠይቅም?
አንዳንድ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ጸሎት የሆነውን ምልጃ አስታራቂነት አድርገው በመቁጠርና ያለ ክርስቶስ ሌላ አስታራቂ የለም በማለት ማንኛውም አስታራቂነት ተቀባይነት የለውም ይላሉ። በዚህም መንገድ አንድ ሰው ለሌላ ሰው የሚያደርሰው ጸሎት ሁሉ ተቀባይነት የሌለው አስታራቂነት ያደርጉታል።ትክክል ግን አይደለም
“በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው ግንኙነት ቀጥታ ነው፣ ይህ መለኮታዊ ፍቅር የሌሎች ጸሎት አያስፈልገውም” በሚል ሰበብ በጸሎት ያለውን ምልጃ አለመቀበል ሐዋርያው “እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ” በማለቱ ተሳስቷል (እውነቱ ከዚህ የራቀ ነው) ማለት ነዋ (ያዕ 5÷16)።
በዚህ ዓይነት ፣ አንዱ ስለሌላው እንዲጸልይ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰው ሁሉ ትርጉም የለውም፤ ደግሞም ከመለኮታዊ ፍቅሩ ጋር አይስማማም ማለት ነዋ!
“እግዚአብሔር ሰዎችን ስለሚወድ፣ ቸርነቱንና የአባትነት ፍቅሩን ለማስታወስ ስለልጆቹ ሌሎች ወደ እርሱ እንዲጸልዩ አያስፈልገውም!” ማለት ነዋ።
እንደዚህ ብለው የሚያስቡ እግዚአብሔር አቢሜሌክን አብርሃም እንዲጸልይለት ሲነግረው (ዘፍ 20÷7) ፣ ወይም ኢዮብን ለጓደኞቹ እንዲጸልይ ሲጠይቀው (ኢዮብ 42÷8) በዚያ ያለውን መለኮታዊ የአሠራር ንድፍ በተሳሳተ መንገድ ይረዱታል።
አንደኛቸው ሰዎች ለሌላኛቸው የሚያደርጓቸው ጸሎቶቻቸው (በሞት የተለዩቱ ይሁኑ ወይም በአጸደ ሥጋ እየተጣጣሩ ያሉቱ) በሰዎች መካከል ያለው የመደጋገፍ ፍቅር መገለጫ ነው። በሞት የተለዩቱ ሕያዋን መሆናቸውን ሰዎች እንደሚያምኑ ማረጋገጫ ፣ ጸሎቶቻቸውም በእግዚአብሔር እንደሚሰሙና እግዚአብሔር ቅዱሳኑንም አክብሮ እንደሚያይ የሚያመለክት ነው።
ሰዎችን እንዲጠቅም እግዚአብሔር ምልጃን ይፈቅዳል። ይህም ምልጃ በመንግሥተ ሰማይ የሚኖሩትንና በምድር ያሉትን በማገናኘት እንደድልድይ ሆኖ ያገለግላል። መንግሥተ ሰማይ ቀድሞ እንደነበረው ለሰዎች ያልታወቀናና አስደንጋጭ ሥፍራ አይደለም ፣ ነገር ግን እነርሱ (ሰዎች) በቅዱሳን ነፍሳት ሥራና ፍቅር እማመን ላይ ለመድረስ በቅተዋል።
የሚከተሉት ምልጃን በሚክዱ ተዘውትረው የሚጠየቁ ዋንኞች ጥያቄዎች ናቸው።
(4) መላእክትና ቅዱሳን በምድር ላይ ያለንበትን ሁኔታ ያውቃሉን?
የቅዱሳን ነፍሳት ያለንበትን ሁኔታ ያውቃሉን? ጸሎታችንስ ወደ እነርሱ ይደርሳልን? መልሳችን በአዎንታ ነው። ማስረጃዎቹም÷
(ሀ) በሰማይ ያለው ዕውቀት በምድር ላይ ካለው እንደሚበልጥ ምንም ጥርጥር የለውም
አንዳንዶች በመንግሥተ ሰማያት ያሉ ቅዱሳን ዜናችንና ጸሎታችንን ያውቃሉ ወይ? ብለው ሲጠይቁ ያስደንቃል። ሐዋርያው ጳውሎስ ሲመልስ እንዲህ ይላል፦“ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከዕውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደ ታወቅሁ አውቃለሁ።” (1 ቆሮ 13÷12)
ስለዚህ ነፍስን አቅፎ የያዘውን ይህን አካል ተለይተን በሚመጣው ዓለም ስንሆን ዕውቀታችን ይጨምራል፤ በርካታ ሚስጢራት ይገለጡልናል። በዚያ የነፍስ ዕውቀት ይሰፋል። ነፍስ ከውስን ዕውቀት ድባብ ተሻግራ (አልፋ) ወደ ሰፋ የዕውቀት ድባብ ውስጥ (ሰፋ ወዳለ ዕውቀት አካባቢ) ትገባለች። በዚህ ባለ ዕውቀት ላይ እግዚአብሔር ለነፍሳት የሚገልጠው ዕውቀት ይጨመርበታል። ያም ዕውቀት ማናቸውም በመለኮታዊ መገለጥ እቅፍ ውስጥ ተጠቅልሎ ያለው ዕውቀት ነው።
(ለ) የመላእክት ዕውቀት በጌታ ቃል በትክክል ተመልክቷል÷ “እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል” (ሉቃ 15÷7) በሚለው በጌታ ቃል በግልጽ ተቀምጧል።
ይህም ማለት በምድር ላይ ያለው ዜና በሰማያዊ ሥፍራ ላሉ ለመላእክቱ ሆነ ወይም ለቅዱሳኑ ነፍሳት ይደርሳል ማለት ነው። ማን ንስሐ እንደገባና ማን ንስሐ መግባት እንደሚያስፈልገው ያውቃሉ።ንስሐ በገባ አንድ ኃጢአተኛም ይደሰታሉ። በምድር ያለውን ዜና ካላወቁ እንዴት ይደሰታሉ?
(ሐ) መላእክት ጸሎታችንን ያውቃሉ፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር ዙፋን የሚያቀርቡት/የሚያደርሱት እነርሱ ናቸው። በዮሐንስ ራዕይ ለዚህ በርካታ የጥቅስ ማስረጃዎች ይገኛሉ። እንዲህም ተጽፏል፦ “ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሰዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው። የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ” (ራዕይ 8÷3፣ 4) ። በዚህ ሥፍራ የቅዱሳኑ ጸሎት ከመላእክቱ እጅና ከ‘ጥናው’ ወደ እግዚአብሔር ሲያርግ እንመለከታለን። ከሆነ ታዲያ እንዴት መላእክት ጸሎታችንን አያውቁም? አሳምረው ያውቃሉ።
እንደዚሁም 24ቱ ካህናት ጸሎታችንን ያውቃሉ፤ በእግዚአብሔር ፊት ከፍ ያደርጉታልና። በራዕይ መጽሐፍ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፦“መጽሐፉንም በወሰደ ጊዜ አራቱ እንስሶችና ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች (ካህናት) በበጉ ፊት ወደቁ፥ እያንዳንዳቸውም በገናንና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ያዙ” (ራዕ 5÷8) ። ካህናት በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርቡትን ጸሎቶች ስለማወቃቸው ይህ ማስረጃ ነው።
በተመሳሳይ መንገድ “ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና” (ማቴ 18÷10) ብሎ ጌታ የተናገረላቸው የሕጻናት መላእክቶቻቸውም እንዲሁ ናቸው።
(መ) የአብርሃም፣ የሀብታሙ ሰውና የአልዓዛር ታሪክ (ሉቃስ 16) ÷ አብርሃም አባታችን ለባለጸጋው ሰው እንዲህ አለው፦“ልጄ ሆይ፥ አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም እንደ ተቀበልህ አስብ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ” (ሉቃ 16÷25) ። አባታችን አብርሃም እንዴት አድርጎ ነው አልዓዛር የታገሠውን ክፉ ነገር ያወቀ? ባለጸጋው የተቀበለውን መልካም ነገርስ እንዴት አወቀ? ሙሴና ነብያት የኖሩት አብርሃም ከምድር ከተለየ ከብዙ መቶ ዐመታት በኋላ ሆኖ ሳለ የሐብታሙ ዘመዶች “ሙሴና ነቢያት” እንዳሏቸውስ በምን አወቀ? ያንን ሁሉ እንዴት አወቀ? “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ፥ አየም ደስም አለው” (ዮሐ 8÷56) በማለት የተነገረለት አብርሃም ይህንን እንዴት አያውቅም?
(ሠ) ምስክርነት ከሰማዕታት ነፍሳት፤ ቅዱስ ዮሐንስ በራዕይ መጽሐፉ እንዲህ ይላል፦ “አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ።በታላቅ ድምፅም እየጮኹ። ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ። ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፥ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው” (ራዕ 6÷ 9-11) ። ስለዚህ ሰማዕታት ከሞታቸው በኋላ ጌታ ገና ደማቸውን እንዳልተበቀለላቸው ያውቃሉ።ወደ እግዚአብሔር ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እስከ መቼ ክፉው በምድር እንዲሰለጥን ትፈቅዳለህ? እስከ መቼ ነው በጉልበታቸው የበረቱ ልጆችህን የሚያጠፉት? እስከ መቼ ነው ደምን በማፍሰስ የሚኖሩት?” ይላሉና። እነዚህን ሁሉ ነገሮች እንዴት አድርገው ነው የሚያውቁት? አዎ እነዚህን ሁሉ ያውቃሉ። የባሪዎች ባልንጀራዎቻቸው ቁጥር ሲፈጸምም ያውቃሉ።
(ረ) ስለነቢዩ ኤልያስ አስደናቂ ታሪክ (2ኛ ዜና መዋዕል 21) ፤ በዜና መዋዕል መጽሐፍ እንደዚህ ተጽፏል። ንጉሥ ‘ኢዮራም’ ወንድሞቹን ሁሉ ገደለ፣ በንጉሥ ‘አክዓብም’ መንገድ ሄደ፣ በይሁዳ ተራራ መስገጃዎችን ሠራ፣ የኢየሩሳሌንም ሰዎችን እንዲያመነዝሩ አደረገ፣ ይሁዳን አሳተ።በዚያን ጊዜ ከብዙ ዓመታት በፊት ከምድር ተለይቶና ወደ ሰማይ አርጎ ከነበረው ከነቢዩ ኤልያስ ደብዳቤ ደረሰው። ከነቢዩ የደረሰው ደብዳቤ እንዲህ ይላል፦ ”የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በአባትህ በኢዮሣፍጥ መንገድ በይሁዳም ንጉሥ በአሳ መንገድ አልሄድህምና፥በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ግን ሄደሃልና፥--- ---ሕዝብህን-- በታላቅ መቅሠፍት ይቀሥፋል” (2ኛ ዜና መዋ 21÷12-14) ። ያ እንዴት ሊሆን ቻለ? ነቢዩ ኤልያስ ከምድር ተለይቶ ሳለ በመሆን ላይ የነበረውን እንዴት አወቀ? ለ‘ኢዮራም’ስ እንዴት አድርጎ ደብዳቤውን ላከው?
(5) የቅዱሳን ታላቅነት፣ ዕውቀትና አገልግሎት
(ሀ) በሕይወት በነበረበት ጊዜ ነቢዩ ሳሙኤል ስለጠፋ አህያ ምክር ተጠይቆ ነበር። ስለ እርሱ እንዲህ ተብሏል፦ “እነሆ፥ አንድ የእግዚአብሔር ሰው በዚህች ከተማ አለ፤ እርሱም የተከበረ ሰው ነው፥ የሚናገረውም ሁሉ በእውነት ይፈጸማል፤ አሁን ወደዚያ እንሂድ፤ ምናልባት የምንሄድበትን መንገድ ይነግረናል አለው” (1ኛ ሳሙ 9÷6) ። በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው የማይታየውን ያውቅ ከነበረ ነፍሱ በመንግሥተ ሰማያት ምን ያህል አብልጣ ታውቅ?
(ለ) ኤልሳዕ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ‘ግያዝ’ ስጦታን ከሶርያዊው ከ’ንዕማን’ በድብቅ በተቀበለ ጊዜ አወቀበት (2ኛ ነገ 5÷25-27) ።
(ሐ) ከንጉሥ አራም ሹማምንት አንዱ ስለ ነቢዩ ኤልሳዕ ለጌታው ለንጉሡ እንዲህ አለው፦ “---ነገር ግን በእልፍኝህ ውስጥ ሆነህ የምትናገረውን በእስራኤል ዘንድ ያለ ነቢይ ኤልሳዕ ለእስራኤል ንጉሥ ይነግረዋል አለ (2ኛ ነገሥት 6÷12) ።
(መ) በረሀቡ ዘመን የሚገድለውን መልእክተኛ የእስራኤል ንጉሥ እንደላከበት ነቢዩ ኤልሳዕ አወቀ ። ኤልሳዕ በሥጋ በነበረበት ጊዜ ምስጢሩን የማወቅ ስጦታ ተሰጥቶት ከነበር ሥጋውን ተለይቶ በመንግሥተ ሰማያት ከሆነ እንዴት አብልጦ ያውቅ?
(ሠ) እንደዚሁ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ሐናንያና ሳጲራ በምስጢር ያደረጉትን አውቋል። ገለጠላቸው፤ ቀጣቸውም (ሐዋ 5÷ 3፣ 9) ።
(ረ) ቅዱስ ጳውሎስም ከሄደ በኋላ በኤፌሶን ሰዎች መካከል ለመንጋው የማይራሩ ጨካኝ ተኩላዎች እንደሚገቡባቸው አወቀ (ሐዋ 20÷ 29) ።
ሐዋርያቱ ያን ያህል በአጸደ ሥጋ ሆነው አውቀው ከነበረ ጌታ በሰማይ ምን ያህል አብልጦ ይገልጥላቸው!
እነዚህ ቅዱሳን ዕውቀት አላቸው፤ ለሰዎች መልእክትም አላቸው። በምድር የጀመረው ሕይወታቸው ወደ መንግስተ ሰማይ በመሄዳቸው አላበቃም። እንደኛው በምድር ሆነው ገና በብዙ መጣጣር ላይ ያሉትንና ያልተለዩንን ከምንጠይቀው አብልጠን እነዚህን ጣልቃ እንዲገቡልን እንጠይቃቸዋለን።
(6) የቅዱሳን ታላቅነት ሌሎች ምሳሌዎች
(ሀ) የነቢዩ ኤልሳዕ አጥንቶች ታላቅ ሥራን ሰርተዋል። ሕይወት ያልነበረባቸው አጥንት ብቻ ነበሩ (2 ነገ 13÷21) ። የኤልሳዕ ነፍስ በመንግስተ ሰማይ ሆና ምን ያህል የበለጠውን በረከት ታደርግ? ያለጥርጥር ነፍሱ ካጥንቶቹ ይልቅ የበለጠ ኃይል አላት፤ የበለጠ ዕውቀትና በእግዚአብሔር ዘንድ የበለጠ ሞገስም አላት! እንደ ኤልሳዕ ያሉ የሌሎች ቅዱሳን ነፍሳት ምን ያህል የበለጠ በረከትን ያደርጉ ይሆን?
(ለ) የጳውሎስን ገላ የነካ ጨርቅ ወይም ልብስ ብዙ ድውያንን የፈወሰና በአጋንንት የተያዙን ነጻ ያወጣ በረከት ነበረ (ሐዋ 19:12) ። የጳውሎስ ነፍስና እርሱን የሚመስሉ የቅዱሳን ነፍሶች በመንግሥተ ሰማያት ሆነው ምን ያህል በረከትን ያስገኙ?
(7) በአጸደ ሥጋ የተለዩ ቅዱሳን አሁንም ሕያዋን ናቸው
ይህንን እውነት ጌታ እንዲህ ሲል አስረድቷል፦““እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም” (ማቴ 22÷31፣32) ። ስለዚህ እነዚያ ቅዱሳን ሕያዋን እንጂ ሙታን አይደሉም። ታዲያ ስለምንድነው ሙታን አድርገን የምንቆጥራቸውና እንዲጸልዩልን የማንጠይቃቸው?
የጌታ የፊቱ መልክ በተለወጠበት ተራራ ላይ ሙሴና ኤልያስ ከጌታ ጋር መታየታቸውንም መዘንጋት የለብንም። ሙሴ ደግሞ የሞተው ጌታ ከመወለዱ ከ14 ምዕተ ዓመቶች በፊት ነበር። ይሁን እንጂ ልክ ወደ ሰማይ እንደተወሰደው እንደ ኤልያስ በሕይወት አለ። ነፍሶቻቸው አልሞቱም፤ በገነት ይገኛሉ፤ እኛ ከምናየው በላይ ያያሉም።
(8) የመላእክት የመማለድ ምሳሌ
በነቢዩ በዘካርያስ መጽሐፍ ውስጥ ሁለት ምሳሌዎች ይገኛሉ፤
(ሀ) የመልአኩ ምልጃ ስለ ኢየሩሳሌም፡ መልአኩ እንዲህ ሲል ጸልዮአል፦ “አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ እነዚህ ሰባ ዓመት የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው? “(ዘካ 1÷12) ። እግዚአብሔር ሳይጠይቀው ስለ ኢየሩሳሌም ከማለደ እንዲጸልይላችሁ ከጠየቃችሁትማ መልአኩ የቱን ያህል አብልጦ ይማልድ?
(ለ)የጌታ መልአክ ምልጃ ስለ ታላቁ ካህን ስለ ኢያሱ፤ በኢያሱ ላይ ክስ ሊያመጣ የነበረውን ሰይጣንን በመቃወም መልአኩ ሰይጣንን ተቃውሞ ቆሞ፦“ኢየሩሳሌምን የመረጠ እግዚአብሔር ይገሥጽህ፤ በውኑ ይህ ከእሳት የተነጠቀ ትንታግ አይደለምን?” (ዘካ 3÷1፣ 2) አለው ።
(ሐ) ሌላም ምሳሌ በዘፍጥረት ላይ ይገኛል፤ የጌታ መልአክ ያዕቆብን ጠበቀው፣ አዳነውም። ያዕቆብ ይህን የተናገረው ኤፍሬምንና ምናሴን በባረከ ጊዜ ነው። እንዲህም አለ:- “ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ፥ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ” (ዘፍ 48÷16) ።
(መ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መላእክት “ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?” (ዕብ 1÷14) በማለት የተናገረውንም መዘንጋት የለብንም። ይህም ማለት በምድር ላይ ስላሉ ስዎች መላእክት የሚያከናውኑት ሥራ አላቸው ማለት ነው።
(9) ቅዱሳን በጌታ ፊት ሞገስ ስለማግኘታቸው፤
(ሀ) የቅዱሳንን ምልጃ የምንጠይቀው በሚወዳቸውና ስለሰዎች በሚደረግ የምህረት ሥራ ላይም ባሰማራቸው ጌታ ፊት ካላቸው ታላቅ ሞገስ የተነሳ ነው። ያም ብቻ ሳይሆን ከሥጋዎቻቸው ከተለዩ በኋላ ነፍሶቻቸው ስላገኙት የላቀ ዕውቀትና የሰፋ ችሎታም ጭምር ነው።
(ለ) መላእክት በጌታ ፊት ሞገስ ያላቸው መሆኑን ስንናገር እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ስሙን ከስሞቻቸው ጋር አያይዞ መጥራቱን እንጠቅሳለን። እንዲህ አለ፦“እኔ የአባትህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ አለው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ያይ ዘንድ ፈርቶአልና ፊቱን ሸፈነ” (ዘጸ 3÷6) ።
(ሐ) የቅዱሳንን ስም ሲሰማና የገባላቸውን ቃል ኪዳን ሲያስታውስ የርኅራኄና የምህረት ልቡ ወዲያውኑ ስለሚላወስ ነበር ቅዱሳን የቅዱሳንን ስም ለጌታ ያስታውሱ የነበረው። የእስራኤል ሕዝብ እንዳይጠፋ በማለደበት ጊዜ ነቢዩ ሙሴ ለጌታ እንዲህ አለ፦ “ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ--- ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ” (ዘጸ 32÷13)።
(መ) የሶርያው ንጉስ ‘‘አዛሄል’ እስራኤላውያንን ባስጨነቀ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ግን ራራላቸው፥ ማራቸውም፥ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ስላደረገውም ቃል ኪዳን እነርሱን ተመለከተ፤ ሊያጠፋቸውም አልወደደም፥ ፈጽሞም ከፊቱ አልጣላቸውም” (2ኛ ነገሥ 13÷23) ያለውን እናስታውሳለን።
(ሠ) ቅዱሳን በጌታ ፊት ሞገስ ስለማግኘታቸው ለምሳሌ ያህል ሙሴን በነቀፉ ጊዜ እግዚአብሔር በአሮንና በማርያም ላይ ያሰማውን ቅሬታ እናቀርባለን። ጌታ በደመና አምድ ወረደና በሙሴ ፊት ለአሮንና ለማርያም “ቃሌን ስሙ፤ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር፥ እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ፥ ወይም በሕልም እናገረዋለሁ።፤ ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው።፤ እኔ አፍ ለአፍ በግልጥ እናገረዋለሁ፥ በምሳሌ አይደለም፤ የእግዚአብሔርንም መልክ ያያል፤ በባሪያዬ በሙሴ ላይ ትናገሩ ዘንድ ስለ ምን አልፈራችሁም? አለ።” (ዘኁልቁ 12÷6-8)
(ረ) ቅዱሳን በጌታ ፊት ሞገስን ስለማግኘታቸው ሌላው ምሳሌ ጌታ ለሐዋርያቱ÷ “የሚሰማችሁ እኔን ይሰማል፥ እናንተንም የጣለ እኔን ይጥላል፤ እኔንም የጣለ የላከኝን ይጥላል።” (ሉቃ 10÷16)ና “--የሚያገለግለኝም ቢኖር አብ ያከብረዋል” (ዮሐ 12÷26) ያለው ነው።
(10) ተቃውሞዎችና መልሶቻቸው
(ሀ) የቅዱሳንን ምልጃ ስንጠይቅ ወደ እነርሱ እየጸላችሁ ነው ይባላል። ለዚህ መልሳችን ወደ ቅዱሳኑ እየጸለይን አይደለም፤ ጸሎታቸውንና ድጋፋቸውን ብቻ ነው የምንጠይቀው የሚል ነው። ከድንግል ማርያም ጋር ስንነጋገር ጸሎትን ወደ እርሷ ማቅረባችን ሳይሆን ልጆች ከእናታቸው ጋር የፍቅር ጭውውት እንደሚጫወቱት መጨዋወታችን ነው። የልባችንን ምስጢር ለእርሷ መግለጣችን እንጂ ወደ እርሷ መጸለያችን አይደለም። በንጉሡ ቀኝ የተቀመጠች ንግሥት ናትና እንድትማልድልን በትህትና እንጠይቃታለን።
(ለ) ምልጃ ማለት የአስታራቂነት ዓይነት መሆኑ አይደለም ወይ? ነው ይባላል።ታዲያ ምናለ? በዚያ ምንም ስህተት አናይበትም። እግዚአብሔር ራሱ ምልጃን የሚጠይቀውና የሚቀበለውም ነው። አቢሜሌክን በሕይወት ይኖር ዘንድ አብርሃም እንዲጸልይለት ነግሮታል (ዘፍ 20÷7) ። ጓደኞቹ በኢዮብ ላይ በስንፍና እንዳደረጉበት እንዳያደርግባቸው ኢዮብ እንዲጸልይላቸው ነግሯቸዋል (ኢዮ 42÷8) ። አብርሃም ለሶዶም እንዲማልድ ፈቅዶለታል (ዘፍ 18) ። ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ እንዲማልድ ፈቅዷል። ምልጃቸውን ሰምቷል ተቀብሎታልም።
(11) የቅዱሳንን ጸሎት መጠየቅ መንፈሳዊነቱ
(ሀ) የቅዱሳኑን ምልጃ መጠየቅ በሚመጣው ሕይወት ማመንን፣ በሞት የተለዩቱ ሕያዋን እንደሆኑና የሚሠሩት ሥራ እንዳላቸው ማመንን፣ በምድርና በሰማይ ያልተቋረጠ ግንኙነት እንዳለ ማመንን፣ በእግዚአሔር በራሱ የተከበሩትን ቅዱሳንን በማክበር ማመንን ያመለክታል።
(ለ) ምልጃ በአንዱ አካል ብልቶች (አባላት) መካከል ያለ የፍቅር ኅብረት ነው። ቤተ ክርስቲያን አካሉ ናት።ክርስቶስ ደግሞ የሁላችን ራስ ነው።በምድር ያለነውም ሆነ በሰማይ ያሉቱ የአንዱ የአካል ብልቶች ነን። ፍቅር ፣ ጸሎትና ኅብረት የዛው የአንዱ አካል ብልቶች በሆንን መካከል ባለ ማቋረጥ የምንለዋወጠው ነው። በሞት ስለተለዩቱ በጸሎታችን ልመና እናቀርብላቸዋለን ( እንዴት እያልን??) ፤ በጸሎታቸው ስለ እኛ ምልጃ ያቀርቡልናል፤ የማይነጣጠል ግንኙነት ነው።
ምልጃን የሚቃወሙቱ ይህን ኅብረት ለማጥፋት የቆረጡ መምሰላቸው የሚያሳዝን ነገር ነው። እኛ ስለተለዩቱ፤ የተለዩቱም ስለእኛ የሚያደርጉትን ምልጃ ወይም ጸሎት ይቃወማሉ? በእግዚአብሔር አብና በልጆቹ መካከል ያለ የፍቅር ግንኙነት በእግዚአብሔር ልጆች መካከል ያለን ፍቅር ይቃረናልን? ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ አባቱን እንዲህ ብሎ አልጠየቀምን?
“----እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥” (ዮሐ 17÷21 ፣ 23)
(ሐ) ምልጃ ጠቃሚ ነው። ይህንን የሚክድ ከምልጃ የሚገኘውን ጥቅም ያጣል። በምትኩ የሚያገኘው ጥቅም የለም። በምልጃው የሚያምኑ በቅዱሳኑና በእነርሱ መካከል ካለው የፍቅር ግንኙነት ያተርፋሉ። በሞት ከተለዩቱ ነፍሳት ጋር በመገናኘታቸው ብቻ ያተርፋሉ። በእነርሱ በኩል ምንም ሳይጎድልባቸው፣ በጸሎታቸው ላይ በሚቀጥለው ዓለም ከሚኖሩቱ የበለጠውን ጥልቅና ኃይለኛ የሆነውን ጸሎት ያክሉበታል።
የቅዱሳኑን ምልጃ የሚክዱቱ ግን ይህንን ግንኙነትና ጸሎታቸውን ያጡታል። በምትኩ የሚያተርፉት ምንም ነገር የላቸውም። የቅዱሳኑን ጾም በሚያከብሩቱ፣ ቤተክርስቲያናቸውን በሚጎበኙቱ፣ ጸሎታቸውን በሚጠይቁቱ የሚታየውን ገርና ያልተወሳሰበ እምነትን ያጡታል። ሊያከብሯቸው እምቢ ሲሉና ጸሎታቸውንና ምልጃቸውን አልፈልግም ሲሉ ኖረው በሚመጣው ዓለም ከቅዱሳኑ ሲገናኙ እንዴት ይሆኑ ይሆን?
(መ) ምልጃ የልብ የዋህነትን ይጠይቃል። ምልጃን የሚጠይቅ ሰው ትሑት ሰው ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ስላለው ግንኙነት ዕብሪት አይዘውም። ነገር ግን የሌሎችን ምልጃ የሚጠይቅን የዛን የደካማና የኃጢአተኛ ሰው ሥፍራ ይይዛል። ምልጃን የሚክድ የተገላቢጦሹን ነው የሚያደርገው። እንዲህ ብሎ በትዕቢት ይጠይቃል፦ በእኔና በቅዱሳኑ መካከል ምን ልዩነት አለ? “በእኔና በእግዚአብሔር መካከል ያለው ግንኙነት በጣም ጠንካራ ስለሆነ የሌሎች ምልጃ አያስፈልገኝም”! ራሱን ከቅዱሳኑ፣ ከሰማዕታቱና ከመላእክቱ ጋር ያስተካክላል።
እነዚህ ሰዎች “ጸልዩልን” (ዕብ 13÷8) “በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ” (ኤፌ 6÷18) በሚሉት የሐዋርያቱ ቃላት የሚወቀሱ ናቸው።
(ሠ) ምልጃ የእግዚአብሔር ፍትሕ እኩል ዕድል የመስጠት መርሕ ያለው መሆኑን ማረጋገጫ ነው። እግዚአብሔር ልጆቹን እንዲዋጋ ፣ በሃሰት ራዕይና ህልም እንዲፈትን፣ እንዲያሰቃያቸው ለሰይጣን የሚፈቅድ ከሆነ በፍትሕና እኩል ዕድል በመስጠት መርሑ መሠረት መላእክትንና የጻድቃኑን ነፍሳት በምድር ላይ ያሉትን ልጆቹን እንዲረዱ ይፈቅዳል። በሚቀጥለው ዓለም ያሉቱ በምድር ላይ ላሉ ሰዎች ጣልቃ እንዲገቡ መፍቀዱ የእግዚአብሔርን ፍትሐዊነት ያመለክታል።
እግዚአብሔር ሰይጣን ኢዮብን እንዲጎዳው ከፈቀደ መላእክትንም የተጎዳውን እንዲጠግኑ፣እነርሱም ባይጠይቁ እንኳ ልጆቹን እንዲያገለግሉ ይፈቅዳል። ልጆቹ ከጠየቁማ የቱን ያህል ያደርጉ! “ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?” (ዕብ 1÷14) መላእክት ስለዚህ ምክንያት የተላኩ እስከሆነ ድረስ ቀርበውን ሳለ ስለምን እንዲረዱን የእነርሱን ጣልቃ ገብነት አንጠይቅም?
(12) መማለድ ሕያው እውነታ ነው
የቅዱሳኑ መማለድ ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እየፈለግን በነገረ መለኮታዊ ምርምር ጽሑፎች የምናነሳው ነገር ብቻ ሳይሆን የምንለማመደው ሕያው እውነታ ነው። በተለዩቱና ገና በምድር በሕይወት ባሉቱ መካከል ያለውን አስደናቂ ግንኙነት የሚተርክ በትውልዶች መካከል ያለ ሕያው ታሪክ ነው። ስላለንበት ሁኔታ ከእኛ ይልቅ እነርሱ በእውነት ከሚያዝኑልን ቅዱሳን ጋር ያለ ሕያው ግንኙነት ነው። የማዘናቸው ልክ አንዳንዴ እኛ ሳንጠይቃቸው ወይም ሳንጸልይ እንኳ ስለ እኛ በመማለዳቸው ችግራችን መፍትሔ ያገኛል። “ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፥ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ” (ሮሜ 12÷ 15) የሚለውን እኛ ከምንረዳው በላይ ይረዳሉ። በተግባርም ያውሉታል።
ምልጃ በምድር ባሉት ቤተ ክርስቲያን አባላትና በሰማይ ባሉት ቤተ ክርስቲያን አባላት መካከል መያያዝ ለመኖሩ ማረጋገጫ ነው።አንድ ቤተ ክርስቲያን ናት፤ አንዱ ክፍሏ በምድር ያለች ‘ተዋጊ ቤተ ክርስቲያን’ የምንላት ስትሆን ሌላ ክፍሏ ደግሞ ‘ድል የነሳች ቤተ ክርስቲያን’ የምንላት በሰማይ አለች። ሁለቱም አንዳቸው ለሌላቸው ይጸልያሉ።
የቅዱሳንን ምልጃ የሚቃወሙ በበዓሎቻቸው ወቅት ወይም በቤተክርስቲያናቸውና በየገዳማቱ በቅዱሳኑ ጸሎት በኩል በእርግጥ የሆነውንና ብዙዎች የመሰከሩትን አስደናቂ ተአምር ወርውረው መጣላቸው ነው። እኔ የምለው ነው ትክክል በሚል ነገረ መለኮታዊ ክርክር የታሪክ ማረጋገጫ ያላቸውን ምስክሮችና በዕለት ዕለት ያለውን ሐቅ መካድ ይመስላል።
ለምሳሌ ድንግል ማርያም በ‘ዜይቶን’ ቤተክርስቲያኗ በገጽታዋ በመታየቷ የሆነውን ታምር መጥቀሱ ይበቃል። ይኸው ለክርስቲያን ሆነ ለእስላሙ በሰዎች የቃል ሆነ የጽሑፍ ምስክርነት ተመዝግቦ ያለ ነው። በቅዱስ ጊዮርጊስ ስም፣ በሊቀ መላእክቱ በሚካኤልና በሌሎችም ቅዱሳን የሆነውን ታምር ማንሳት ይቻላል። እነዚህ ሁሉ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችንን ከቅዱሳን ማማለድ እውነታ ጋር እንዲስማሙ ለማሳመን የሚበቁ መሆን አለባቸው።
የተለያዩ ቅዱሳንን የሕይወት ታሪክ ብታነብቡ የመላእክትንና የቅዱሳንን ለሰዎች ጣልቃ የመግባት ታሪክ ወደ ማወቅ ትደርሳላችሁ። እንዴት እንደታዩ ፣ የተናገሩትን ትንቢት፣ የሰጡትን ተስፋና መመሪያ፣ ከመካኒቷ ሴት ጻድቅ እንደሚወለድ ያመጡትን መልካም ዜና ወይም እግዚአብሔር ለአገልግሎቱ የመረጠውን ቅዱስ ሲገልጡ ታያላችሁ። እነዚህን ሰዎች በተመለከተ ከቅዱሳኑ ጋር የነበራቸው የግንኙነታቸው ነገር ያንድ ቀንና ያንድ ሌሊት ትውውቅ ብቻ ሳይሆን ዘመናትን ያስቆጠረ ነው።ልናጠፋው ከቶ የማይቻለን ግንኙነት ነው። በሰዎች፣ በመላእክትና በቅዱሳን መካከል ያለ ግንኙነት ነው። ከነዚህ ሰዎች ብዙዎች ለመረዳት ከባድ የሚሆንባቸው በምድር ባለችው ቤተ ክርስቲያንና በሰማያት ባሉ አባላቷ መካከል ያለው መያያዝ የማይነጣጣል መሆኑን የሚቃወመው የፕሮቴስታንት አቋም ነው።
Comments
Post a Comment