Skip to main content

ሥርዐት

ሥርዓቶች

1. የመስቀሉ አከባበር 

2. ፊትን ወደ ምሥራቅ ስለማዞር   

3. መቅደሱና መሠዊያው 

4. ዕጣን   

5. መብራትና ጧፍ   

6. ሥዕሎችና ምስሎች (አርማዎች) 

(1) መስቀሉን ማክበር

በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት አማኞች መካከል ካሉት ልዩነቶች አንደኛው በኦርቶዶክስ ያለው አስደናቂ የመስቀል አከባበር ነው።ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ከመጸለያቸው በፊትም  ሆነ ከጸለዩ በኋላ “በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም” እያሉ  ራሳቸውን በመስቀሉ ምልክት አያማትቡም፣ ከመመገባቸው በፊትም በምግቡ ላይ የመስቀሉን ምልክት አያሳዩም። እንዲሁም ሰውንም ሆነ አልባሳትን  ለመባረክ በመስቀሉ ምልክት አይጠቀሙም።

ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን መስቀሉን በልባቸው በማመናቸው ብቻ ሳይሠሩበት ረክተዋል። እስከቅርብ ጊዜ ድረስ መስቀልን በቤተክርስቲያናቸው ላይ ከፍ አድርገው (በቅርጽ ወይም በሥዕልም ቢሆን) አያሳዩምም ነበር። ብዙዎቹ መስቀሉን አያደርጉትም፤ አንዳቸውም መስቀሉን በእጃቸው አይዙም። የመስቀሉንም በዓላት አያከብሩም።  መስቀሉን በመያዝ እየዘመሩና እያወደሱ  ሰልፍን አያደርጉም። መስቀሉንም አይሳለሙም፤ በእርሱም በረከትን አይቀበሉም። 

አሁን ኦርቶዶክስ ለምን ለመስቀሉ ትልቅ ሥፍራ እንደምትሰጥ፣ በመስቀሉ ማማተብ እርባናና ጥቅም ያለው እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትን መሠረት ያደረገ መሆኑን ለማስረዳት እንሞክራለን።  

(1) ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ አፅንኦት ማድረጉ 

ጌታ አገልግሎቱን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሚያስተምርበትም ጊዜ፣ ከስቅለቱም በፊት ለመስቀሉ ትልቅ አፅንኦት ሰጥቷል። እንዲህም አለ፦“መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።” (ማቴ 10÷ 38)። “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” [(ማቴ 16÷24) (ማር 8÷34)] ።ከእርሱ ጋር በነበረው ንግግር  ወጣቱን ሐብታም እንዲህ አለው፦ “ሂድ፥ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ --- መስቀሉንም ተሸክመህ ና፥ ተከተለኝ አለው” (ማር 10÷21)። ደግሞም እንዲህ አለ፦ “ማንም መስቀሉን ተሸክሞ በኋላዬ የማይመጣ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም” (ሉቃ 14÷27) ።

(2) መስቀሉ የመላእክቱና የሐዋርያቱ አገልግሎት ማዕከል ነበር 

ስለጌታ ከሙታን መነሣት ለሴቶቹ ያበሰረው መልአክ የተናገረው ዋና ነጥብ እንዲህ ያለው ነው÷ “እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፤ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም” (ማቴ 28÷5፣ 6)።   ምንም እንኳ ከሙታን ተነስቶ ያለ ቢሆንም ከዚህ እንደሚታየው መልአኩ ጌታን ‘የተሰቀለው’ ብሎ ጠርቶታል። ‘የተሰቀለው’ የሚለው አጠራር ለጌታ መታወቂያ ሆኖ ኖሯል። 

ሐዋርያት አባቶቻችን በስብከታቸው ሁሉ ለስቅለቱ አፅንኦት ሰጥተውታል። ቅዱስ ጴጥሮስ ለአይሁድ ሲሰብክ እንዲህ አለ፦“እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ” (ሐዋ 2÷36) ። ቅዱስ ጳውሎስም እንዲህ ብሏል፦“እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” (1 ቆሮ 1÷23) ፣ ምንም እንኳ የጌታ ስቅለት “ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት” ሆኖ ቢቆጠርም።  

ሐዋርያው መስቀሉን የክርስትና ‘ፍሬ ነገር’ እንደሆነ ቆጥሮታል። እንዲህ ሲል “በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና” (1 ቆሮ 2÷2) ። እንዲህ ሲል ለማወቅ የሚፈልገው ጉዳይ መስቀሉን ብቻ ነበር ማለት ነው። 

(3) መስቀሉ የሐዋርያቱ የክብር ዕቃ ነበር

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ” (ገላ 6÷14) ብሏል ። ከነዚህ ቃላት በስተኋላ ያለውን ምስጢር ብንጠይቀው“ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት” (ገላ 6÷14) ነው በማለት መልሱን ይቀጥልበታል። 

(4) የመስቀሉን ምልክት ስናማትብ ብዙ መለኮታዊና መንፈሳዊ ትርጉሞቹን እናስታውስበታለን

እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር ማለትም ለእኛ ድኅነት ሲል ሞትን ስለመቀበሉ “እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ” (ኢሳ 53÷6) የሚለውን እናስታውስበታለን። የመስቀሉን ምልክት ስናደርግ“የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።” (ዮሐ 1÷29)ና “እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ” (1 ዮሐ 2÷2) የሚለውን እናስታውሳለን።

(5) የመስቀሉን ምልክት ስናማትብ ፣ ከ’ተሰቀለው’ ጋር መቆጠራችንን እንገልጻለን

የሚገለጥበትን አንዳች ምልክት ሳያሳዩ መስቀሉን  በልባቸው በሚኖረው መንፈሳዊ ትርጉም ብቻ  የሚወስኑቱ ምልክቱን በማመሳቀል፣ መስቀሉን በሁሉ ፊት በመያዝና በመሳለም (በመሳም) ፣ በእጃችን ላይ በመነቀስ፣ በአምልኮ ሥፍራችንም ከፍ አድርገን በማሳየት፣ እኛ እንደምናደርገው ከጌታ ጋር መቆጠራቸውን  በግልጽ አያውጁትም። እነዚህን ሁሉ ማድረጋችን እምነታችንን በግልጽ ማስታወቃችን ብቻ ነው። በክርስቶስ መስቀል በሰዎች ፊት አናፍርም፤ ይልቁንም እንመካበታለን፤ በእርሱ ተጠርተናል፤ በዓሉን እናከብራለን፤ቃል እንኳ ሳንተነፍስ  በምናሳየው እምነታችን እንዲገለጥ መስቀሉን ከእጃችን አንለይም። 

(6) ሰው መንፈስና አእምሮ ብቻ ሳይሆን አካላዊ ስሜቶችም አሉት። እነዚህ አካላዊ ስሜቶች ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች መስቀሉ ሊሰማቸው (ሊረዱት) ይገባል። 

ሰዎች ሁሉ በተመሳሳይ መንፈሳዊ እድገት ላይ ያሉና ለመንፈሳዊ ተመስጦ የስሜት ህዋሳቶቻቸው የማያስፈልጓቸው አይደሉም። የስሜት ሕዋሳቶች ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች ሁሉ ይመገባሉ፤ በዚህ ያገኟቸው ለውጦችም (መልዕክቶችም) በራሳቸው ውስጥ ተገድበው አይቀሩም። ይልቁንም ለውጦቹን ለአእምሮና ለመንፈስ ያስተላልፋሉ። አእምሮ በራሱ መስቀሉን ጨርሶ ላያስታውስ ወይም በበቂ መጠን ላያስታውስ ይችላል። ነገር ግን ሰው መስቀሉን በፊት ለፊቱ በስሜት ሕዋሳቶቹ ሲያይ ከመስቀሉና ከ’ተሰቀለው’ ጋር የተገናኙትን መለኮታዊና መንፈሳዊ ስሜቶች (መልእክቶች) ሁሉ ያስታውሳል።  በዚህ መንገድ እግዚአብሔርን በመንፈስ ፣ በአእምሮና በአካል እናመልከዋለን ማለት ነው። እነዚህ ሁሉ ይደጋገፋሉ።

(7) መስቀሉን የምናማትበው በጸጥታ (ቃል ሳናሰማ) አይደለም፤ ነገር ግን “በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ አሜን” እያልን ነው።

በመሆኑም ምልክቱን ባማተብን ቁጥር ለዘለዓለም አንድ አምላክ በሆነው በቅድስት ሥላሴ ማመናችንን እንገልጻለን። አሜን! ቅድስት ሥላሴን  በተከታታይ ለማስታወስም ይህ መልካም አጋጣሚ ይሆንልናል።  

(8) የመስቀል ምልክቱን ባማተብን ቁጥር ቃል ሥግው ስለመሆኑና (በሥጋ መገለጡንና) ስለቤዛነት ያለንን እምነት እናስታውቃለን

የመስቀሉን ምልክት የምናማትበው ከላይ ወደ ታችና ከግራ ወደ ቀኝ ነው ። በዚህ እግዚአብሔር ከሰማይ ወደ ምድር መውረዱን፣ እንዲሁም ሰዎችን ከግራ ወደ ቀኝ ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ሕይወት ማፍለሱን እናስታውሳለን። ባማተብን ቁጥር በአእምሮአችን የምናስባቸውና በልባችን የሚሰሙን ተመስጦዎች ምንኛ የበዙ ናቸው!

(9) መስቀሉን ማማተብ ለልጆቻችንና ለሌሎችም ሃይማኖታዊ ትምህርት ነው

በሚጸልይበት ጊዜ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን በተገባ ቁጥር ፣ በሚበላበት ሰዓት ፣  በሚተኛበት ጊዜ የመስቀሉን ምልክት የሚያማትብ ሰው እርሱ መስቀሉን የሚያስታውስ ሰው ነው። መስቀሉን እንዲህ ማስታወስ መንፈሳዊ ጠቀሜታ ያለውና በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠየቀም ነው።  ሰዎችን ሁሉ በተለይም ልጆችን ክርስቶስ እንደተሰቀለ ያስተምራል። 

(10) በምናማትበት ጊዜ እንደታዘዝነው እስከሚመጣ ድረስ ክርስቶስ ለእኛ መሞቱን መናገራችን ነው።

እስከሚመጣ ድረስ ሞቱን እንድናውጅ (ያም ቤዛችን ነው) ጌታ ያዘዘው ነው። “ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና” (1ቆሮ 11÷26) ። የመስቀሉን ምልክት በምናማትብባት በእያንዳንዲቷ ጊዜ ሞቱን እንናገራለን ፤ እናም እስኪመጣ ድረስ እርሱን እናስባለን። 

ጌታን በቅዱስ ቁርባኑም እናስታውሰዋለን። ነገር ግን ይህ ምስጢረ ቤተ ክርስቲያን  ያለማቋረጥ የሚከበር አይደለም። ማማተብ ግን ሁል ጊዜም የሚደረግ በመሆኑ የጌታን ሞት ሁልጊዜም  ያስታውሰናል።

(11) በማማተባችን የኃጢአት ቅጣቱ ሞት መሆኑን እናስታውሳለን

ክርስቶስ የሞተው ለዚያ ነበር።“በበደላችን ሙታን” (ኤፌ 2÷5) ነበርን።ነገር ግን ክርስቶስ ስለእኛ በመስቀል ላይ ሞቶ ሕይወትን ሰጠን። በመስቀል ላይ ዋጋን ከፈለና ለአባቱ እንዲህ አለ÷- “አባት ሆይ ይቅር በላቸው”  

(12) መስቀሉን በማማተብ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር እናስታውሳለን

መስቀሉ የፍቅር መስዋዕት መሆኑን እናስታውሳለን።“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” (ዮሐ 3÷16) ። “ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል።--- ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን” (ሮሜ 5÷8፣10) የሚለውንም እናስታውሳለን። በመስቀሉ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር እናስታውሳለን ምክንያቱም “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም”ና (ዮሐ 15፥ 13) ። 

(13) የመስቀሉን ምልክት እናማትባለን፤ ምክንያቱም ኃይል ይሰጠናል 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመስቀሉ ኃይል ተሰምቶት እንዲህ አለ፦ “ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ” (ገላ 6፥ 14) ። “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና” (1ቆሮ 1:18) ። እዚህ ላይ ልብ እንበል፦ ‘ስቅለቱ’ ነው የእግዚአብሔር ኃይል” አለማለቱን፣ ‘መስቀል’ የሚለውን ቃል ብቻ የእግዚአብሔር ኃይል ማለቱን ። 

ስለዚህ የመስቀሉን ምልክት ስናማትብና ‘መስቀል’ የሚለውን ቃል ስንናገር በኃይል እንሞላለን፤ ምክንያቱም ጌታ በመስቀሉ በኩል ሞትን መርገጡንና ሕይወትን ለሰው ሁሉ መስጠቱን፣ ሰይጣንን መርታቱንና ማሸነፉን ያስታውሰናልና። ስለመሆኑም

(14) የመስቀሉን ምልክት የምናማትብበት ምክንያት ሰይጣን ይፈራዋልና ነው

ከአዳም መፈጠር ጀምሮ የዘመን መጨረሻ ድረስ ያለው የሰይጣን ልፋት ከንቱ ሆኖ የቀረው ‘መስቀሉ’ ላይ ነው። እግዚአብሔር ዋጋውን በደሙ ከፈለ። በእርሱ የሚያምኑትንና የሚታዘዙትን ሁሉ ኃጢአታቸውን በደሙ አስወገደው። ስለዚህ ሰይጣን መስቀሉን ሲያይ ታላቅ ሽንፈቱንና የልፋቱን ሁሉ መና መቅረት በማስታወስ ይንቀጠቀጣል፤ ይዋረዳል፤ ያፈገፍጋልም። 

ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጆች የመስቀሉን ምልክት ይጠቀማሉ፤ ምክንያቱም የድልና የእግዚአብሔር ኃይል ምልክት ነው። በውስጣቸው በኃይል ይሞላሉ፤ ጠላትም በውጭ ሆኖ ይንቀጠቀጣል። 

በቀደመው ጊዜ የእባቡ ከፍ መደረግ ለሕዝቡ ፈውስና ከሞት መትረፊያ ነበረ። ይህ የክብር ጌታ በመስቀል ላይ ከፍ ከመደረጉ ጋር ይመሳሰላል። በፍቱንነቱ (በውጤማነቱም) የመስቀሉን ምልክት ይመስላል (ዮሐ 3፥ 14) ። 

(15)የመስቀሉን ምልክት በማማተብ በረከትን እንቀበላለን።

 ዓለሙ ሁሉ ተረግሞ በሞት ቅጣት ሥር ነበር። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር የመታረቅን በረከት (ሮሜ 5:10) ፣ አዲሱን ንጹህ የሕይወት በረከት፣ የአካሉ ብልት የመሆን በረከት ሊሰጠን በመስቀሉ ላይ ጌታ እርግማናችንን ሁሉ ተሸከመ። የአዲስ ኪዳን ጸጋዎች ሁሉ የተገኙት ከመስቀሉ ነው። ካህናቱ በረከትን ለማስተላለፍ በመስቀል ይጠቀማሉ። ይህን የሚያደርጉት በረከት የሚገኘው ቡራኬ እንዲሰጡበት አደራ ከተቀበሉበት ከጌታ መስቀል እንጂ ከእነርሱ አለመሆኑን ለማሳየት ነው።  ደግሞም ሥልጣነ ክህነታቸው የተገኘው ‘ከተሰቀለው’ ክህነት ነውና መስቀልን ይጠቀማሉ።  የአዲስ ኪዳን በረከቶች ሁሉ የተገኙት ከጌታ መስቀልና ከእርሱ (ከመስቀሉ) ፍቱንነት የተነሳ ነው። 

(16) በክርስትና የተቀደሱት ምስጢራት ሁሉ ሲካሄዱ መስቀሉ ጥቅም ላይ ይውላል

ምስጢራት ሁሉ የመነጩት ከክርስቶስ የመስቀሉ ደም ሥራ ነው። ስለ መስቀሉ ባይሆን ኖሮ እግዚአብሔርን በምስጢረ ጥምቀት እንደ ልጅ ለመቅረብ ፈጽሞ ባልቻልን ነበር፤ በቅዱስ ቁርባን የሥጋውና የደሙ ተካፋይ ለመሆን ምንጊዜም ባልተገባን ነበር (1ቆሮ 11:26) ። ማናቸውንም ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ምስጢራት ጸጋዎችንም ልንካፈል ባልቻልንም ነበር። 

(17) ከመስቀሉ ጋር ያለንን ኅብረት ለማስታወስ  መስቀሉን  ከፍ ከፍ እናደርጋለን 

“ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል” (ገላ 2፥ 20)ና “እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ” (ፊል 3፥ 10) የሚሉትን የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ቃሎች እናስታውሳለን። እዚህ ላይ ራሳችንን እንጠይቃለን፤ መቼ ነው የጌታን መከራ ወደ መካፈል (ኅብረት) ልንገባና ከእርሱ ጋር ልንጸለይ የምንችለው? 

ንስሐ የገባውንና ከጌታ ጋር የተሰቀለውን በኋላም በገነት ከእርሱ ጋር ሊገባ የተገባውን ሌባ  እናስታውሳለን። ምናልባት በገነት ሆኖ “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ” የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስን መዝሙር እየዘመረ ይሆናል።

ምኞታችን ከክርስቶስ ጋር ወደ መስቀሉ መውጣት ነው። ከስሜት ሕዋሳቶቻችን ጋር በተገናኘ ቁጥር መስቀሉ ክብራችን ይሆናል። 

(18) መስቀሉን እናከብራለን ምክንያቱም እርሱ የአባታችን ደስታ ነው 

በመስቀል ላይ የዋለውን ክርስቶስን አባቱ ደስ የሚያሰኝ የኃጢአት መስዋዕትና የሚቃጠል መስዋዕትም አድርጎ ተቀብሎታል። እርሱ “በእግዚአብሔር ዘንድ ጣፋጭ ሽታ” ነበር (ዘሌ 1፥ 9፣13፣17) ። ይህን በተመለከተ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ” (ኢሳ 53፥ 10) 

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረው ሕይወቱ ሁሉ አባቱን ደስ አሰኝቷል። ይሁን እንጂ ደስታውን ሙሉ ያደረገው በመስቀሉ ላይ “ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ” ጊዜ ነው (ፊል 2፥ 8) ።

እኛም ክርስቶስን እንደዚሁ እስከሞት ድረስ በመታዘዙ እንድንመስለው መስቀሉን ባየን ቁጥር የክርስቶስን ፍጹም መታዘዝ፣ ፍጹም መገዛት እናስታውስበታለን። 

መስቀሉ አብ የሚደስትበት ዕቃ ነው፣ የ‘ተሰቀለው’ ልጁም የሚደሰትበት ዕቃ ነው፣ እንዲህ ተብሎ የተጻፈለት ልጁ፦“እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና” (ዕብ 12፥ 2) ።በእዚህ ዓይነት የክርስቶስ ፍጹም ደስታ በመስቀሉ ነው። እኛም እንደ እርሱ እንሁን።

(19) በመስቀሉ ነቀፌታውን እየተሸከምን ወደ እርሱ ወደ ሰፈሩ ውጭ እንወጣለን (ዕብ 13፥13)

የክርስቶስ ነቀፌታ ስቅለቱና መከራው ነው። መስቀሉን በማማተብ የህማማት ሳምንቱን ስሜት ስንካፈል ስለነቢዩ ሙሴ የተባለውን እናስታውሳለን። “ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና” (ዕብ 11፥ 26)

(20) የክርስቶስን መስቀል እንሸከማለን፤ ምክንያቱም ዳግም መምጣቱን ያስታውሰናል።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዓለም መጨረሻና ስለጌታ መምጣት እንዲህ ይላል፦“በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤” (ማቴ 24 ፥ 30) ። ስለዚህ በኋላ በሰማይ ደመና በታላቅ ክብር መገለጡን እስከጠበቅን ድረስ ‘የሰው ልጅ’ ምልከት የሆነውን መስቀሉን አሁን በምድር ሳለን እናክብረው። 

(2) ፊትን ወደ ምሥራቅ ስለማዞር

የቤተ ክርስቲያን ሕንጻዎች ሁሉ ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ አዙረው ነው የሚታነጹት። ስንጸልይም ፊታችንን ወደ ምሥራቅ አዙረን ነው፤ ምክንያቱም ምሥራቅ ለእኛ ‘ምልክት’ ነው ። ልቦቻችንን ውድ ወደሆኑ በርካታ አሳቦች (ተመስጦዎች) ያቀናቸዋል። በእግዚአብሔር ሃሳብም ትልቅ ሥፍራ አለው። እግዚአብሔር ለምሥራቅ ትልቅ ሥፍራ ሰጥቶታልና እኛም እንስጠው። 

(1) እግዚአብሔር ሰውን ከመፍጠሩ በፊት ምሥራቅን ለራሱ የብርሃን ምንጭ አድርጎ ፈጠረው። ያን ብርሃንም መልካም እንደሆነ እግዚአብሔር አየ። “እግዚአብሔር ፀሐይን በአራተኛው ቀን ፈጠረ፤ ሰውን ደግሞ በስድስተኛው ቀን (ዘፍ 1) ።  

የፀሐይ መውጣት የክርስቶስና የእርሱ ብርሃን ምሳሌ ነው።ጌታ ‘የጽድቅ ፀሐይ’ ተብሎ ተጠርቷል፤ እንዲህም ተጽፏል፦ “የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች፥ ፈውስም በክንፎችዋ ውስጥ ይሆናል” (ሚልክያ 4፥ 2) ።

(2) እግዚአብሔር ሰውን ከመፍጠሩ በፊት የኤደን ገነትን ለሰው በስተምሥራቅ ተከለለት። ከዚያም እርሱን በዛ አኖረው። ኃጢአትን እስካደረገበት ጊዜ ድረስ ሰውን ባኖረበት በዚያ በገነት  የ’ሕይወትን ዛፍ’ም ተከለው። የኤደን አትክልት ሥፍራ ልንደርስበት የምንናፍቀው የገነት  ምልክት ነው (ዘፍ 2፥ 8) ። ሰው ፊቱን ወደ ምሥራቅ ማዞሩ የተከለከላትን ገነት የመጓጓቱ ምልክትና የሕይወትን ዛፍ የመመኘቱ ምልክት ነው።  

(3) ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው በምሥራቅ አገር ነበር፣ ‘ሰብዓ ሰገል’ ኮከቡን ያዩት በምሥራቅ ነበር (ማቴ 2፥2)። ‘ኮከቡ’ የመለኮት ምሪት ምልክት ነበር። ‘ሰብአ ሰገል’ ኮከቡን ሲከተሉት ወደ ጌታ መራቸው። ይህ ለማሰላሰል እጹብ ድንቅ የሆነ ሃሳብ ነው። 

(4) ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው በምሥራቅ አገር ነው። የእርሱ ኮከብ በምሥራቅ ታየ ፤ እናቱ ድንግል ማርያምም ወደ ምሥራቅ በሚመለከት በር ተመስላለች (ሕዝ 44፥ 1፣ 2) ።

(5) ድኅነት ለዓለም የመጣው ከምሥራቅ ነው። ክርስቶስ የተሰቀለው በምሥራቅ አገር ነበር፤ በዚያም ነበር ለዓለም ሁሉ ኃጢአት ስርየት ደሙን ያፈሰሰው።  

(6) ክርስትናና ቤተ ክርስቲያን የተጀመሩት በምሥራቅ ነው። ኢየሩሳሌምም በምሥራቅ ናት። የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችበት የታላቁ ንጉሥ አገር ናት። ወንጌል በዓለም ዙሪያ የተስፋፋው ከምሥራቅ ተነስቶ ነው። የመጀመሪያው ክርስቲያን ሰማዕት ደም የፈሰሰውም በምሥራቅ ነው። 

(7) የእግዚአብሔር ክብር በምሥራቅ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ አያሌ ጊዜ ይጠቀሳል። በኢሳያስ መጽሐፍ “እግዚአብሔርን በምሥራቅ ---- አክብሩ” (ኢሳ 24፥15) ይላል። በመጽሐፈ ሕዝቅኤል ክርስቶስ በክብር ከምሥራቅ እንደሚመጣ ትንቢት አለ። እንደዚህም ተብሎ ተጽፏል፦“እነሆም፥ የእስራኤል አምላክ ክብር ከምሥራቅ መንገድ መጣ፤ ድምፁም እንደ ብዙ ውኆች ይተምም ነበር፥ ከክብሩም የተነሣ ምድር ታበራ ነበር” (ሕዝ 43፥ 2) ።

(8) ስለዚህ አብዛኞቹ የነገረ መለኮት አዋቂዎች ዳግም ምፅአቱ ከምሥራቅ እንደሚሆን ይናገራሉ።“ኢየሱስ ወደ ሰማይ እንደሄደ እንዲሁ ይመለሳል (ሐዋ 1፥11) ። በትንቢተ ዘካርያስ እንዲህ ተጽፏል፦“በዚያም ቀን እግሮቹ በኢየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረ ዘይት ላይ ይቆማሉ” (ዘካ 14፥ 4)  

(9) ምሥራቅ የሚስብና ግሩም ትዝታዎችን የሚቀሰቅስ ነው። በመጽሐፈ ሕዝቅኤል ነቢዩ በምሥራቅ ስለሚፈስ የሕይወት ውኃ ተጽፏል (ሕዝ 47፥ 1-9) ። በሁለተኛው መጽሐፈ ነገሥትም ስለ ምሥራቅ “የእግዚአብሔር መድኃኒት ፍላጻ ነው፤ (2ኛ ነገሥ 13፥ 17) የሚል ተጽፏል። በኢሳያስ መጽሐፍ ደግሞ “ስለዚህ እግዚአብሔርን በምሥራቅ፥ --- አክብሩ” (ኢሳ 24፥ 15) የሚል ተጽፏል ።

(10) ምሥራቅን ማስታወስ በልብ ትልቅ ነገር ቀስቃሽ በነፍስም መንፈስን አነቃቂ ነገር አለው። ነቢዩ ዳንኤልን አደንቀዋለሁ፤ ለአረማውያኑ አምልኮ አልተበገረም፤ ወደ ላይኛው ክፍል ገባ፤ በኢየሩሳሌም አንፃር ያለውን መስኮት ከፍቶ ለመጸለይ ተንበረከከ። እግዚአብሔር የትም መገኘቱ እውነት ነው፤ ነገር ግን ወደ ምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መዞሩ ትልቅ ትርጉም ያለውና ልብን የሚነካ ነው። አንዳንድ ሥፍራዎችን ማስታወስ የተቀደሰ ስሜትን ይቀሰቅሳል።  

(11) አምልኳችን በአእምሮ ብቻ የሚደረግ አይደለም። የስሜት ሕዋሳቶቻችንም ይነካሉ። እነርሱ ተነክተው የነፍስ ስሜትንም ይነካሉ።ይህን በምሳሌ ለመግለጽ÷ ምንም እንኳ እግዚአብሔር በየትም ሥፍራ ቢገኝም ስንጸልይ ወደ ላይ እንመለከታለን።ወደ ላይ መመልከት በልባችን የሚያሳድረው መንፈሳዊ ስሜት ለጸሎታችን የበለጠ ጥልቀት ይሰጣል። ወደ ምሥራቅ ስለመዞርም ይህንኑ ማለት ይቻላል። 

ምንም እንኳ አብ በእርሱ እርሱም በአብ ቢሆንም ጌታ ራሱ ከአንድ ለበለጠ ጊዜ ወደ ላይ ተመልክቷል። ነገር ግን ወደ ላይ መመልከት የሆነ ቁምነገር አለው።

(12) ወደ ምሥራቅ ስንዞር በእርግጥ ወደ ምሥራቅ ወደ ተዘረጋው መሰዊያ ፊት ለፊት እናያለን።ምክንያቱም መስዋዕቱ በልባችን የራሱ የሆነ መንፈሳዊ ሥፍራ አለውና። ክርስቶስ ፋሲካችን በምሥራቅ የተደረገ መስዋዕት ነው። 

(13) በጥምቀት አገልግሎት ጊዜ፣ በምሳሌነት ተጠማቂውና የክርስትና ወላጁ ሰይጣንን ለማውገዝ ወደ ምዕራብ ይዞሩና ሰይጣንን ያወግዛሉ፤ከዚያ የእምነት አቋም መግለጫ ለማሰማት ወደ ምሥራቅ ይዞራሉ። ስለዚህ የተጠመቀው ሰው በጥምቀት ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ እንደዞረ ማለትም ከጨለማ ወደ ብርሃን እንደመጣ ይሰመዋል።

(14) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችንን እንጠይቃለን፦ 

የሐሰት ትምህርት (ዶግማ) ሳይቀላቀልበት  

መንፈሳዊ ትርጉም እያለው 

ቅዱስ አሳብ (ማሰላሰል) እያስከተለ 

በመጽሐፍ ቅዱስ የጥቅስ ማስረጃ የተደገፈ ትዝታ እያመጣ 

መንፈሳዊ ቅናትን እየቀሰቀሰ  

ስለምንድነው ታዲያ ፊትን ወደ ምሥራቅ ማዞርን አብዝተው የሚቃወሙት?

(3) መቅደሱና መሠዊያው

በፕሮቴስታንቶች አብያተ ክርስቲያን መቅደስና መሰዊያ የለም። ለዚህ ምክንያቱ የበለጠ የመረረ ሲሆን ነገሩ መስዋዕት የለም (ቀርቷል) ነው። ስለመስዋዕት ምስጢረ ቁርባንን እና ክህነትን በምንወያይበት ጊዜ እናነሰዋለን። እዚህ ላይ ውይይታችንን በመሰዊያው ላይ እንወስናለን። 

(1) በብሉይ ኪዳን ስለመሰዊያ በርካታ ጽሑፎች አሉ። ነገር ግን ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን የሚያስቡት እነዚያ የክርስቶስን በመስቀል ላይ መሰዋቱን ያመለከቱ ጥላ የነበሩና አሁን ግን የቀሩ ናቸው ብለው ነው ። ስለዚህ ከእነርሱ ጋር በሚኖረን ውይይታችን ከአዲስ ኪዳን የጥቅስ ማስረጃ ማቅረብ ሊኖርብን ነው ማለት ነው።   

(2) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “መሠዊያ አለን፥ ከእርሱም ሊበሉ ድንኳኒቱን የሚያገለግሉ መብት የላቸውም” (ዕብ 13፥10) ይላል ። ድንኳኒቱን ማለት መገናኛ ድንኳን (ደብተራ ኦሪት) ወይም አሮጌው ቤተ መቅደስ (መቅደሰ ኦሪት) ማለት ነው። በዚህ ጥቅስ ላይ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል። “ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከምሳሌያዊ ትርጉም ወደ ቃል በቃል (ቀጥተኛ) ትርጉሙ ተመለሰ---- አሁን የቅዱስ ደሙ ተካፋይ ለመሆን ሥልጣን አለን፤ ያም ሥልጣን የካህኑ ብቻ የነበረው ነው”።

(3) በነቢዩ በኢሳይያስ መጽሐፍ በግብጽ ምድር መካከል ስለሚኖር መሰዊያ የተነገረ ትንቢት አለ። ነቢዩ እንዲህ ይላል፦“በዚያ ቀን በግብጽ ምድር መካከል ለእግዚአብሔር መሠዊያ፥ በዳርቻዋም ለእግዚአብሔር ዓምድ ይሆናል---- (ኢሳ19:19) ። “በዚያም ቀን እግዚአብሔር በግብጽ የታወቀ ይሆናል፥ ግብጻውያንም እግዚአብሔርን ያውቃሉ፤ በመሥዋዕትና በቍርባን ያመልካሉ” (ኢሳያስ 19÷ 19፣ 21) ።

እዚህ ላይ የተጠቀሰው መሰዊያ በእርግጥ የአዲስ ኪዳንና  የክርስትና ዘመን መሰዊያ ነው። የብሉይ ኪዳን መሆን አይችልም። ምክንያቱም አይሁድ በአህዛብ ምድር መስዋዕትን ሊሰው አይችሉም ነበር። ግብጾችም ቢሆኑ ይህን እንዲያደርጉ አይፈቅዱላቸውም ነበር። ለዚህ ነበር  በሙሴና በአሮን ጊዜ ለፈርዖን የቀረበለት አቤቱታ “እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ” (ዘጸ 8:20) የሚል የነበረው።  ፈርዖን ግን “ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ሕዝቡን ለመልቀቅ” (ዘጸ 8፥ 29) እምቢ አለ። በዝንብ ከተመታ በኋላ ፈርዖን ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጠው ተስፋ“ለእግዚአብሔር ለአምላካችሁ በምድረ በዳ ትሠዉ ዘንድ እለቅቃችኋለሁ”  (ዘጸ 8፥ 29) አለ ። ከዚህ ጥቅስ መገንዘብ እንደሚቻለው አይሁድ በግብጽ መሰዋት አይችሉም ነበር።  

መቼ ነው ታዲያ ግብጾች ጌታን ያወቁት? መቼ ነው መሰዊያ የኖራቸውና ለጌታ መሰዋት የጀመሩት? ያለጥርጥር በክርስትና ዘመን ነው። በክርስትና ዘመን መስዋዕት የሚቀርብበት መሰዊያ ስለመኖሩ  ይህ የማያሻማ ማስረጃ ነው። 

(4) እግዚአብሔር ‘መሰዊያ’ የሚለው ቃል በሰው ልብና አዕምሮ ውስጥ ተተክሎ እንዲቀር ወዷል። ስለዚህ በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት መጨረሻ፤ ሐዋርያትና የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሰማዕት ከሆኑ በኋላ በጻፈው በራዕይ መጽሐፉ ወንጌላዊው ዮሐንስ ካንድ ጊዜ በላይ አንስቶታል። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ብሏል፦“ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሰዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው” (ራዕ 8፥ 3)። “አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ” (ራዕ 6፥ 9)።

(5) በመለኮታዊ እስትንፋስ የተጻፈው “የጌታ ሥጋና ደም” (1ቆሮ 11 ፥ 27) የሚለው ቃል በፊታችን እስካለ ድረስ መሰውያው መኖሩ ይቀጥላል። ደም እስካለ ድረስ ደግሞ መሰዊያ መኖር አለበት፤ ተያይዞም የግድ እርሱን የሚይዘው ቤተ መቅደስም መኖር አለበት።

እግዚአብሔር እንደሚፈቅድ ስለ ቅዱስ መስዋዕትና መስዋዕቱን ስለሚያቀርበው ካህን ስንወያይ ይህንን ርዕስ በዝርዝር እናነሰዋለን። 

(4) ዕጣን

የብሉይ ኪዳን ሥርዓተ አምልኮ አካልና ምሳሌ ብቻ ነበሩ፤ አሁን ግን ቀርተዋል ብለው ስለሚቆጥሩ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ዕጣንና ጥና አይጠቀሙም። እዚህ ላይ የጥንቱንና የአሁኑን የዕጣን ታሪክ እናሳይና ምልክት ብቻ ነው? ወይስ እውነትም ራሱን የቻለ መተግበር ያለበት መንፈሳዊ ሥራ ነው?  የሚሉትን ጥያቄዎች እንመልሳለን።

(1) ጌታ ለሙሴ አለው፦“የዕጣን መሠዊያውን ሥራ፤ ከግራር እንጨት አድርገው” (ዘጸ 30 ፥ 1) ። እዚህ ላይ ጌታ አስፈላጊ የሆነን ነጥብ ያመለክተናል። ያም ዕጣን በራሱ መሥዋዕት ሆኖ እንደተቆጠረ፣ የዕጣን መሠዊያ እየተባለ በሚጠራ መሠዊያ ላይ የሚቀርብ እንደነበረ ነው።

(2) ጌታ ለዕጣን መሠዊያ ትልቅ ቦታ ሰጥቶታል። በሁሉም ጎን በወርቅ እንዲለበጥ፣በወርቅ የተለበጡ ቀንዶች እንዲኖሩት፣ በወርቅ በተለበጡ በሁለት ቀለበቶች እንዲሸከሙትና ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን በሚያገኝበት በመጋረጃው ማለትም በምስክር ታቦቱ አጠገብ እንዲያስቀምጠው አዟል (ዘጸ 30 ፥ 3-6) ። 

(3) ዕጣኑ ጣፋጭ ዕጣን እንዲሆን ይቀመም ነበር። ጌታ እንዲህ ይላል፦“አሮንም የጣፋጭ ሽቱ እጣን ይጠንበት፤ በማለዳ በማለዳ መብራቶቹን ሲያዘጋጅ ይጠነው” (ዘጸ 30፥ 7) ። ያም ብቻ አልነበረም፦ “ይህም በእግዚአብሔር ፊት ለልጅ ልጃችሁ የዘወትር ዕጣን ይሆን ዘንድ አሮን በማታ ጊዜ መብራቶቹን ሲያበራ ያጥነዋል” (ዘጸ 30፥ 8) እንደሚል ደንገዝገዝ ሲል ይታጠን ነበር።   

ጣፋጭ ዕጣን የሚዘጋጅበት ቅመሞች በዘጸ 30፥34 ተጠቅሰዋል።ይኸው ዕጣን “በእናንተ ዘንድም ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሁን” (ዘጸ 30፥37) ተብሏልም። ከዚህም በላይ “እርሱም የቅዱሳን ቅዱስ ይሁንላችሁ። እንደ እርሱ የተሠራ ዕጣን ለእናንተ አታድርጉ” (ዘጸ 30÷36፣ 37) ።

“ጣፋጭ ዕጣን’” የሚለው ሐረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ለበርካታ ጊዜያት ተደጋግሞ ተጠቅሷል (ዘጸ 25፥6) ፣ (ዘጸ 37፥ 29) ፣ (ዘሌ 16፥ 12) ። ስለዚህ ‘ዕጣን’ ወደ ጌታ የሚያርግን ባለ መልካም መዐዛ ሽቱን ይወክላል። 

(4) አንዳንድ ሰዎች “ዕጣን ከሚቃጠለው መስዋዕት ጋር የሚቀርብ ሽታን መደበቂያ እንደሆነ ማሰባቸው ስህተት ነው። “የሚቃጠል የእንስሳ መስዋዕት አሁን የለምና” ዕጣን ቀርቷልም ይላሉ። ይህ ትርጉም ጤናማ አይደለም፤ ምክንያቱም ዕጣን በራሱ ራሱን የቻለ የተለየ የአምልኮ ዓይነት ነበር። ከሚቃጠለው መስዋዕት የተለየ የራሱ መሠዊያ ነበረው። የሚቀርብበት የራሱ ሥርዓትም ነበረው። የሌላ ነገር ምሳሌ ሳይሆን ራሱ እንደጸሎት ተቆጥሮና ተደርጎ ነበር የተወሰደው።

(5) ጌታ መቅሠፍቱን በእስራኤላውያን ላይ በላከ ጊዜ፣ ሊቀ ካህኑ አሮን፣ በሙሴ ትዕዛዝ፣ በእግዚአብሔር ፊት ስለሕዝቡ ሊማልድ ጥናውን እንደወሰደ፣ ከመሰዊያው ላይ እሳት ወሰዶ እንዳደረገበት ፣ ከዚህም ዕጣኑን እንደጨመረበት እናስተውላለን። ወደ ጉባኤው በሮጠና ዕጣኑን መስዋዕት አድርጎ ባቀረበ ጊዜ መቅሠፍቱ ቆመ። እግዚአብሔር ከአሮን ዕጣኑን እንደ ጸሎት ተቀበለው (ዘኁ 16 ፥ 44-48) ፤ እንደ መስዋዕትም ቆጠረው ። 

አሮን ዕጣኑን ብቻ እንጂ መስዋዕትን ስለ እስራኤል ሰዎች እንዳላቀረበ ልብ እንላለን። ዕጣኑ የሚቃጠለውን መስዋዕት ሽታ ለመደበቅ ሲባል አልቀረበም። ነገር ግን ለሕዝቡ ማስተሰሪያ አድርጎ አቀረበው (ዘኁ 16፥ 46፣ 47) ። 

(6)  ዕጣን ዋና ነገር በመሆኑ ምክንያት ለማቅረብ የተፈቀደው ለካህን ብቻ ነበር። ስለዚህ ዕጣን ከጸሎትም ከፍ ያለ ሥፍራ ነበረው፤ ምክንያቱም ጸሎት በአንድ ግለሰብም ወደ ጌታ ከፍ ሊደረግ ይችላል። ‘ቆሬ’ ‘ዳታን’ና ‘አቤሮንም’  ያልተፈቀደላቸውን  ዕጣኑን መስዋት ለማቅረብ የደፈሩ ጊዜ ምድር አፏን ከፍታ እነርሱንና ያላቸውን ሁሉ ዋጠቻቸው።  በሕይወታቸው ወደ ጉድጓድም   ወረዱ (ዘኁ 16፥ 31፣ 32)። ይህ የሆነው መስዋዕት ስላቀረቡ ሳይሆን ምንም እንኳ የሌዊ ነገድ ቢሆኑም ዕጣን ስላጠኑ ነበር። 

(7) ዕጣን እጅግ የከበረ ከመሆኑ የተነሳ በዕብራውያን መልእክት እንደተጻፈው ይቀርብ የነበረው በወርቅ ጥና ነበር (ዕብ 9፥4)። ስለ 24ቱ ካህናትም “ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ” ይዘው እንደነበር ተነግሮአል (በራዕ 5፥ 8 )።

(8) በነቢዩ ሚልክያስ መጽሐፍ ዕጣንን ማጠን ቀጣይ መሆኑና በአይሁድ ዘመን ተወስኖ እንደማይቀር ትንቢት አለ።“ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፤ በየስፍራውም ለስሜ ዕጣን ያጥናሉ፥ ንጹሕም ቍርባን ያቀርባሉ፤ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” (ሚል 1፥ 11)። በእርግጥ በአሕዛብ መካከል አምልኮ በክርስትና ዘመን በስተቀር በሌላ ዘመን አልሆነም። ስለዚህ ጌታ ዕጣንን በክርስቲያን አምልኮ መካከል አካቶታል ማለት ነው።

(9) ዕጣን ለመለኮት የሚገደው መሆኑን የሚያመለክቱ ሁለት ምሳሌዎች በአዲስ ኪዳን ውስጥ አሉ። ሁለቱም በራዕይ መጽሐፍ የሚገኙ ናቸው።  

(ሀ) ስለ ሀያ አራቱ ካህናት እንደዚህ ተጽፏል፦ “ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት ወደቁ፥ እያንዳንዳቸውም በገናንና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ያዙ” (ራዕ 5፥ 8)።

(ለ) ባለ ራዕዩ ቅዱስ ዮሐንስም “ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሰዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው። የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ” (ራዕ 8÷3፣4)። 

(10) “የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ።” በሚለው ላይ ሃሳባችንን ስንሰጥ የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ሁሉ ዕጣን ነው እንላለን። በመጽሐፈ መኃልየ መኃልይ ዘሰለሞን መለኮታዊ እስትንፋስ ቤተከርስቲያን በዕጣን ስለመመሰሏ እንዲህ ይላል፦“መዓዛም እንደ ከርቤና እንደ ዕጣን የሆነችው፥ ከልዩ ከነጋዴ ቅመም ሁሉ የሆነችው፥ ይህች ከምድረ በዳ እንደ ጢስ ምስሶ የወጣችው ማን ናት?” (መኃ 3÷6)።

11) በጻድቃን ሕይወት ከታዩት የዕጣን ታሪኮች መካከል አንድ አስደናቂ ታሪክ ሆኗል። ያም የእግዚአብሔር መልአክ ለካህኑ ዘካርያስ በተራው እያጠነ ሳለ የጌታ መልአክ በዕጣን መሰዊያው በስተቀኝ ቆሞ መታየቱ ነው (ሉቃ 1፥ 8-11)። ይህ ዕጣን የሚቀርብበት ሥፍራንና ዕጣን የመሰዋት አግለግሎትን ቅዱስነት የሚያረጋግጥ ነው። ይህ ቅዱስ ታሪክ በመለኮታዊ መገለጥ ውስጥ እንዲጠቀስ ተገብቶት ነበር።   

በዚህ በዘካርያስ በክፍሉ ተራ የሚቃጠል ዕጣንን በመሰዋቱ አጋጣሚ ዕጣን  ከሌላው መስዋዕት የተለየና ራሱን የቻለ እንደነበረ ግልጽ ሆኖ ይታያል።ከመስዋዕት ወይም ከሚቃጠለው መስዋዕት ከማቅረብ ጋር ግንኙነት አልነበረውም።

12) በክርስትና ዕጣን አስፈላጊ የመሆኑ አንዱ ምክንያት ሰብአ ሰገል ለጌታ ካመጡለት ስጦታ መካከል ዕጣን መገኘቱ ነበር። ወርቅ የመንግስቱ ከርቤው ደግሞ የመከራው ምልክት እንደነበረ ሁሉ በተመሳሳይ ሁኔታ ዕጣኑ ለክህነቱ ምልክትና ሰብአ ሰገሉ ክህነቱን የመሰከሩበት ስጦታ ነበር ።

(13) ዕጣን የስሜት ሕዋሳቶቻችንን የሚያረካበትና ነፍሳችንን የሚመግብበት በርካታ ትርጉሞች አሉት። ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ ሁሉ የጠለቀ መንፈሳዊ እርከን ላይ የደረሱና የጠለቀ ግንዛቤም አላቸው ማለት አይቻልም። ለምሳሌ አብዛኛውን ስብከት ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ወይም ጸሎት የማይረዱቱ ልጆች በስሜት ሕዋሳቶቻቸው በኩል ዕጣኑ፣ ጧፉና አርማዎቹ በመንፈሳዊ ረገድ ይነኳቸዋል፤ መንፈሳዊ ትምህርት ለማግኘት ይረዷቸዋል። ከፍ ወዳለ መንፈሳዊ ድባብም (መንፈሳዊ ከፍታም) ይወስዷቸዋል። በቂ መረጃና ጥልቅ እምነት ለሌላቸው አማኞች ማለትም የጠለቀ ዕውቀት ለሌላቸውና የነገረ መለኮት መጻሕፍትን ላልተማሩ ይኸንኑ ማለት ይቻላል።

የእጣን መንፈሳዊ ትርጉሙና ጥልቅ አሳቡ 

14) ከዕጣን የምንማረው የመጀመሪያው ትምህርት “ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል።” (ማቴ 10 ፥ 39) የሚለውን የጌታን ትምህርት ነው። ለዚህ አንድ ምሳሌ የዕጣን ቅንጣት ነው። ይቃጠላል፤ አሁንም ይቃጠላል፤ ባለ መልካም ሽታ የጭስ አምድ እስከሚሆን ድረስ ይቃጠላል። በጥናው ውስጥ የዕጣኑን ቅንጣት ብትፈልጉ አታገኙትም፤ ምክንያቱም ራሱን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መስዋዕት አድርጎ አቅርቧል። 

የሚቃጠል መባ ከመስዋዕቶች ብቻ ሳይሆን ከዕጣኑም ነው።መጽሐፍ ቅዱስ ዕጣንን በራሱ መሰዊያ ላይ የሚቀርብ መስዋዕት አድርጎ ይቆጥረዋል። ዕጣን የሚያስተምረን ትልቅ ትምህርት አለ።ሰው ራሱን የሚቃጠል መስዋዕት አድርጎ ለጌታ ሲያቀርብ እንዴት ቆንጆ ነገር ነው! ማንኛውም መስዋዕት ከራስ ውጭ ነው። ነገር ግን ራስን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ ከሁሉ የበለጠ ነው። ራስን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ በዕጣን ተመስሏል። “እግዚአብሔር አምላክህ የሚበላ እሳት ነው” (ዘዳ 4፥ 24) ተብሎ እንደተጻፈው ቅዱሳን በመለኮታዊ ማዕጠንት ተጨምረው በእግዚአብሔር ፍቅር የተቃጠሉ የዕጣን ቅንጣት ነበሩ። 

(15) በዕጣን ያለው ሁለተኛው ትምህርት ደግሞ ያለማቋረጥ ማረግ ማለትም ወደ ላይ መውጣት ነው። የሚቃጠል ዕጣን እታች መቅረትን አይቀበልም። ይልቁንም ወደሰማይ ያርጋል፤ ይስፋፋል፤ ይሰራጫል። መውጣቱንና መስፋፋቱን አያቋርጥም። ብትወዱም ባትወዱም የዕጣኑን ጪስ ስታዩትና ስትከተሉት ዓይናችሁን ወደ ሰማይ ማቅናታችሁ አይቀርም። ለዚህ ነው ልክ ያለማቋረጥ ወደ መንግስተ ሰማይ እንደሚያመለክት ቀስት ሆኖ ዕጣን ሁልጊዜ የሰውን ስሜት ወደ ላይ የሚስበው። 

(16) በዕጣን ያለው ሦስተኛው ትምህርት ደግሞ ጣፋጭ መዐዛን መምሰሉ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ዕጣን ጣፋጭ እንዲሆን ይቀመማል ይላል። ዕጣኑን የሚያሸት ሁሉ የሰው ሕይወት በእግዚአብሔር ፊት የሚያውድ ሽቶ እንዲሆን ያስታውሳል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “---በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ” “---- ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና” (2ቆሮ 2÷ 14፣ 15)። 

(17) በዕጣን ካሉት እጹብ የሆኑና የጠለቁ አሳቦች ውስጥ አንዱ ጌታ የታየበትን ደመና፣ ወይም ጥቁር ደመና የሚያስታውሰን ነው። ጌታ እንዲህ ይላል፦“እኔ በስርየቱ መክደኛ ላይ በደመናው ውስጥ እታያለሁና” (ዘሌ 16፥ 2) ። ደግሞም በመጽሐፈ ዘሌዋውያን  ‘የጢሱ ደመና” (ዘሌ 16፥ 13) ተብሏል። ስለ ሊቀ ካህን አሮን እንደዚህ ተብሏል፦ “በእግዚአብሔርም ፊት ካለው መሠዊያ ላይ የእሳት ፍም አምጥቶ ጥናውን ይሞላል፥ ከተወቀጠውም ከጣፋጭ ዕጣን እጁን ሙሉን ይወስዳል፤ ወደ መጋረጃውም ውስጥ ያመጣዋል።እንዳይሞትም የጢሱ ደመና በምስክሩ ላይ ያለውን መክደኛ ይሸፍን ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣኑን በእሳቱ ላይ ያደርጋል” (ዘሌ 16፥  12፣ 13) ።

እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ሕዝቡን በመራ ጊዜ በመገናኛ ድንኳኑ ቢሆን፣ በቤተ መቅደሱ ቢሆን ወይም በሲናይ ምድረ በዳ ቢሆን በደመና ወይም በጭስ ተገልጦ ነበር። በሲናይ ምድረ በዳ ሕዝቡን ሲመራ በቀን ደመናን በላያቸው በማድረግ ነበር። ደመናው እግዚአብሔር የሚጋርዳቸው መሆኑን ያመለክት የነበረ ሲሆን ሲነሣ እግዚአብሔር መነሣቱን ያውቁና ይጓዙ ነበር። ደመናው ከቆመ ይቆሙ ነበር (ዘኁ 9÷ 17) ። ስለዚህ እንዲህ ተብሎ ተጻፈ፦ “ከሰፈራቸውም በተጓዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ደመና ቀን ቀን በላያቸው ነበረ።” (ዘኅ 10 ፥ 34)  

(18) ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ግብጽ በመጣ ጊዜ በደመና መጣ ተብሏል (ኢሳ 19፥ 1)። ደመናው ወደ ላይ የሚያርግ ባለመልካም መዐዛ ዕጣን የነበረችው የድንግል ምሳሌ ነበር። ክርስቶስ በዳግም ምፅዓቱም ከደመና ጋር ይመጣል (ማቴ 24 ፥ 30)። ስለዚህ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ደመና የእግዚአብሔርን መገኘት ይወክላል።  

(19) የፊቱ መልክ የተለወጠበት ጊዜ በደመና የእግዚአብሔር መገኘት ምሳሌ ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስት ደቀ መዛሙርት ጋር እየተነጋገረ ባለበት ሰዓት እንዲህ ተብሎ ተነግሯል፦“ይህንም ሲናገር ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ሳሉ ፈሩ። ከደመናውም። የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።” (ሉቃስ 9 ፥ 34፣ 35)

(20) እግዚአብሔር ለሙሴ በደመና ተናገረው። እግዚአብሔር ለሙሴ ሲናገር መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሙሴም ወደ ተራራ ወጣ፥ ደመናውም ተራራውን ሸፈነው። የእግዚአብሔርም ክብር በሲና ተራራ ላይ ተቀመጠ፥ ደመናውም ስድስት ቀን ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን ከደመናው ውስጥ ሙሴን ጠራው።” (ዘጸ 24፥ 15፣ 16) ። ጌታ ለእስራኤል ልጆች ከመገናኛ ድንኳኑ ሲናገርም የሆነው ይኸው ነበር። ደመናና ጪስ የመገናኛ ድንኳኑን ይሸፍኑ ነበሩ። 

(21) በሰሎሞን ቤተ መቅደስ ምረቃ በዓል ላይም ተመሳሳይ ነገር ነበር የሆነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦“ካህናቱም ከመቅደሱ በመጡ ጊዜ ደመናው የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው። የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶ ነበርና ካህናቱ ከደመናው የተነሣ ለማገልገል ይቆሙ ዘንድ አልቻሉም። ሰሎሞንም “እግዚአብሔር በጨለማው ውስጥ እኖራለሁ ብሎአል” (1ኛ ነገሥ 8፥ 10-12) ።

(22) ዕጣን ደመናን ወይም ጥቁር ደመናን የሚወክል ነው። ይህም የእግዚአብሔር መገኘትንና ክብርን ያስታውሰናል። “ደመና ጭጋግም በዙሪያው ናቸው፤ ጽድቅና ፍርድ የዙፋኑ መሠረት ናቸው” (መዝ 97፥ 2) ተብሎ ተጽፏል። ስለዚህ ከዕጣን በረከትን ለማግኘት ለሚመኝ ለማንም ሰው ዕጣን እጅግ በርካታ መንፈሳዊ ትርጉም አለው። ራሱን የቻለ አንድ የአምልኮ ዓይነት ነው። ከሌሎቹ የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች ጋር አልተገናኘም። ስለዚህ ከብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች ጋር አብሮ እንዲቋረጥ አላስፈለገውም። 

(23) በመጨረሻ ይህን እንላለን፦ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ዕጣን’ን የሚሽር ትዕዛዝ አንድም ጥቅስ አይገኝም።“መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ” (ራዕ 2፥ 7) ።

(5) የቤተ ክርስቲያን መብራትና ሻማ (ጧፍ)

የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በመብራቶቿ (በጧፎቿ) ትታወቃለች። በጸሎታችን ጊዜ መብራትን እንጠቀማለን።በጸሎት ጊዜ  በቅዱሳን ምስሎች ፊት፣ መጽሐፍን በምናነብበት ጊዜ፣ በመሠዊያውም ላይ፣  ባጠቃላይ በቤተመቅደሱና በመሠዊያው ፊት ለፊት በስተምሥራቁ መብራት ይበራል። በቤተ ክርስቲያን ያለማቋረጥ መብራት (ሻማ) ይበራል። ምሳሌያዊ ጠቀሜታ እያላቸው ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ከነዚህ አንዱንም ሥርዓት አይከተሉም። በዚህ አጭር ሐተታ በቤተ ክርስቲያን መብራትን ስለማብራት ጉዳይ እንወያያለን። ጥቅም ላይ የሚታዩበትን ምክንያትና ያዘሉትንም መንፈሳዊ ትርጉም እንቃኛለን።

(1) ቤተ ክርስቲያን ራሷ በመጽሐፍ ቅዱስ የወርቅ መቅረዝ ተብላ ተጠርታለች። ይህ በራዕይ መጽሐፍ በግልጽ ይታያል። ባለ ራዕዩ ቅዱስ ዮሐንስ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በሰባቱ የወርቅ መቅረዞች መካከል አየው፤ ጌታም እንዲህ አለው፦ “ሰባቱም መቅረዞች ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው” (ራዕይ 1፥ 20) ።

(2) ቤተ ክርስቲያን መንግስተ ሰማያትን ትመስላለች፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቤት ወይም የእግዚአብሔር ማደሪያ ናት። የመጀመሪያው የእግዚአብሔር ቤት የተገለጠበት አገላለጥ ወደዚህ የሚጠጋ ነበር። አባታችን ያዕቆብ “ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህም የሰማይ ደጅ ነው።” (ዘፍ 28፥ 17) አለ። ቤተ ክርስቲያን ‘ሰማይ’ን’ ስለምትመሰል በሰማይ ከዋክብት እንደሚያበሩ እንዲሁ በውስጧ መብራቶች ሊኖሯት ያስፈልጋል።

(3) በቤተ ክርስቲያን ያሉት መብራቶች በሰማይ የሚገኙትን መላእክት ወይም በቤቴል የእግዚአብሔር ቤት በነበረው መሰላል ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ያዕቆብ የተመለከታቸውን መላእክት ሊወክሉ ይችላሉ (ዘፍ28፥ 12)። መብራቶቹ በመላእክት ይመሰላሉ። ምክንያቱም መላእክቱ የ‘ብርሃን መላእክት’ ተብለዋል (2 ቆሮ 11፥ 14) ።  

(4) የቤተ ክርስቲያን መብራቶች የቅዱሳኑ ምሳሌ ናቸው፤ ጌታም እንዲህ ይላቸዋል፦“ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” (ማር 5፥ 16)። በዚያው አጋጣሚ ቅዱሳኑን በመቅረዙ ላይ ካለ መብራት ጋር አመሳስሏቸዋል (ማቴ 5 ፥ 15)። 

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ” (ማቴ 13፥ 43) ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ የጽድቅ ምሳሌነቱን ለአይሁድ ሲነግራቸው፦“እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፥ እናንተም ጥቂት ዘመን በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ” (ዮሐ 5፥ 35) ብሏል። ቤተ ክርስቲያን በመላእክትና በቅዱሳን የተሞላች ስለሆነ በመብራት የተሞላች ልትሆንም ያስፈልጋታል።

(5) መብራት የመሞላቷ ዐቢይ ምክንያት እግዚአብሔር በዚያ መኖሩ ነው፤“እግዚአብሔር ብርሃን ነው” (1 ዮሐ 1 ፥ 5) ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም ስለ ራሱ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” (ዮሐ 8፥ 12) ብሏል።

(6) ቤተ ክርስቲያን በብርሃን የምትሞላው የመገናኛ ድንኳኑንና የቤተመቅደሱን የመብራት ንድፍ ተከትላ ነው። በብርሃን የተሞሉ ነበሩና፣ መብራታቸው ምን ጊዜም አይጠፋም ነበር። በአሮንና ልጆቹ አሰናጅነት የወይራ ዘይት እየተጨመረበት መቅረዙ ሁል ጊዜ እንዲበራ የዘላለም ሥርዓት እንዲሆን ጌታ አዟል ። ጌታ እንዲህ ይላል፦“አንተም መብራቱን ሁልጊዜ ያበሩት ዘንድ ለመብራት ተወቅጦ የተጠለለ ጥሩ የወይራ ዘይት እንዲያመጡልህ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው። በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ታቦት ፊት ባለው መጋረጃ ውጭ አሮንና ልጆቹ ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት እንዲበራ ያሰናዱት፤ በእስራኤል ልጆች ዘንድ ለልጅ ልጃቸው የዘላለም ሥርዓት ይሁን።”  (ዘጸ 27፥  20፣ 21) ። 

ይህም በፍጥረት የመጀመሪያው ቀን “ብርሃን ይሁን ኣለ፤ ብርሃንም ሆነ። እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደ ሆነ አየ፤ እግዚብሔርም ብርሃንንና ጨለማን ለየ።’ (ዘፍ 1 ፥ 3፣ 4) ባለው በእግዚአብሔር የታዘዘ መለኮታዊ ትዕዛዝ ነው።

(7) በዘይት የሚበሩት መብራቶች መንፈሳዊ ትርጉም አላቸው። ዘይቱ የመንፈስ ቅዱስ ምልክት ነው። ለመቀባት ይጠቅም (ያገለግል) ነበር፣ መቀባቱን ተከትሎ መንፈስ ቅዱስ ይወርድ ነበር። ሳሙኤል ዳዊትን ሲቀባው የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል መጣበት (1ኛ ሳሙ 16:13) ። መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞም ከቅዱሱ ቅባት ስለመቀባት ይነግረናል (1ኛ ዮሐ 2፥ 20፣ 27) ።

በቤተ ክርስቲያን የምናበራቸው ሻማዎች እንኳ ሳይቀሩ የሚሠሩት ከዘይት ነው። ምሳሌነቱን ለመጠበቅ ሲባል የቤተ ክርስቲያን መብራትም የሚበራው በዘይት ነው። 

(8) ጌታ በቤቱ  ማለት በመገናኛ ድንኳኑ ሆነ በቤተመቅደሱ፣ መቅረዞች እንዲሠሩ ማዘዙን ልብ እንላለን። መቅረዙና ቀንዲሎቻቸው የተሠሩት ከጥሩ ወርቅ ነበር (ዘጸ 25፥  31) (ዘጸ 37፥  17) (2 ዜና መዋዕ 4፥  20)። እነዚህ ሁሉ እግዚአብሔር በቤቱ መብራት እንዲኖር የሚገደው ስለመሆኑ ማስረጃዎች ናቸው። 

(9) መብራቶቹ ሁሉ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ያለማቋረጥ ይበሩ ነበሩ። የቀንዲሉን መብራት ማጥፋት ወይም ማብራቱን ቸል ማለት በእግዚአብሔር ላይ ክህደት እንደመፈጸም ይቆጠር ነበር። ከባድ ቅጣትም ይገባው ነበር። ይህን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ “አባቶቻችን ተላልፈዋል፥ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድርገዋል፤ እርሱንም ትተዋል፥ ፊታቸውንም ከእግዚአብሔር መኖሪያ መልሰዋል፥ወደ እርስዋም ጀርባቸውን አዙረዋል፤ ደግሞም የወለሉን ደጆች ቈልፈዋል፥ መብራቶቹንም አጥፍተዋል፥ በመቅደሱም ውስጥ ለእስራኤል አምላክ አላጠኑም፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አላቀረቡም። ስለዚህም የእግዚአብሔር ቍጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ሆነ፥ በዓይናችሁም እንደምታዩ ለድንጋጤና ለመደነቂያ ለመዘበቻም አሳልፎ ሰጣቸው” (2ኛ ዜና 29፥ 6-8) ይላል።እነዚህ ሁሉ እግዚአብሔር መብራት በቤቱ እንዳይጠፋ ምን ያህል እንደሚገደው ያመለክቱናል።  

(10) መብራትን ማብራት ልዩና ጥልቅ መንፈሳዊ ትርጉም አለው። የሁል ጊዜ ዝግጁነት፣ ያለማቋረጥ ነቅቶ የመጠባበቅ፣ና የመንፈስ ቅዱስ ሥራን በልብ የመጠበቅ ምልክት ነው። ነቅቶ መጠበቅን በተመለከተ ጌታ ኢይሱስ ክርስቶስ “ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤እናንተም ጌታቸው መጥቶ ደጁን ሲያንኳኳ ወዲያው እንዲከፍቱለት ከሰርግ እስኪመለስ ድረስ የሚጠብቁ ሰዎችን ምሰሉ።” ብሏል”። “ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ የሚያገኛቸው እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው” (ሉቃ 12 ፥ 35-37) ብሏል። 

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የደናግል ምሳሌን ይነግረናል። በዚሁ ምሳሌ የአምስቱ ልባሞች ደናግል መብራታቸው ይበራ እንደነበርና የአምስቱ ሰነፍ ደናግል ደግሞ መብራታቸው እንደጠፋባቸው ይገልጥልናል (ማቴ 25፥ 1-12) ። 

በመብራቱ ያለው ዘይት መንፈስ ቅዱስ በልብ የሚሠራውን ሥራ ያመለክታል። ያለማቋረጥ መብራቱ ደግሞ በውስጡ ካለው ከመንፈስ ቅዱስ ሥራ ጋር ልብን አስተሳስሮ ለማኖር ነቅቶ መጠባበቅን  ያመለክታል።  

(11) ስለ ግለሰቦች የተባለውን በአጠቃላይ ስለቤተ ክርስቲያን አድርጎ ለመናገር ይቻላል። ሰዎች መብራትን በቤተ ክርስቲያን ሲያዩ በውስጣቸው ያለውን ብርሃን ስለመጠበቅና ብርሃናቸው ያለማቋረጥ ሁል ጊዜ እንዲበራ የማድረግ ኃላፊነታቸውን ያስታውሳቸዋል። ቤተ ክርስቲያን መብራታቸውን እያበሩ ከተገኙት ከአምስቱ ልባም ደናግልት መካከል እንደ አንዷ መሆኗን ያስታውሳሉ።

(12) ወንጌልን በማንበብ ጊዜ ጧፍን ስለማብራት በተመለከተ ደግሞ ያለጥርጥር ወንጌልን ያለ መብራት ከማንበብ ይልቅ በመብራት ማንበብ የተሻለ ነው። ይህም “ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው።” (መዝ 119÷105) የሚለውንና እንዲሁም ዓይንንም ያበራል።” መዝ 19፥ 8 የሚለውን ጥቅስ ያስታውሰናል።

(13) የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ከሐዋርያቱ ዘመን ጀምሮ ለመብራትና ለምሳሌያቸው ትልቅ ሥፍራ ሰጥታለች።የሐዋርያት ሥራ (መጽሐፍ) እንጀራን ከቆረሱ በኋላ ቅዱስ ጳውሎስ ስለሰበከበት ሰገነት ይነግረናል።“ተሰብስበንም በነበርንበት ሰገነት እጅግ መብራት ነበረ” (ሐዋ 20፣ 8) ይላል።

(14) ከሥዕለ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት የምናበራው ሻማ ደግሞ ቅዱሳኑ በትውልዳቸው መካከል ብርሃን እንደነበሩ የሚያስታውሰን ነው። ብርሃናቸው በሰዎች ፊት ያበራ ዘንድ እንደሚቀልጡ ሻማ ነበሩ ።

(6) ሥዕሎችና አርማዎች 

ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን በኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ባሉ ሥዕሎችና አርማዎች ወይም በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ባሉ ሐውልቶች አያምኑም። ከአሥርቱ ትዕዛዝ መካከል ሁለተኛውን ማለትም “በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም” (ዘጸ 20÷4፣ 5)ና (ዘዳ 5÷8፣ 9) የሚለውን እንደመሻር ይቆጥሩታል።

    በስምንተኛው ምዕተ ዓመት (በ726 ዓ.ም) በአፄ ሊዎ ሣልሳዊ  ጊዜ በምስሎች ላይ ጦርነት ተካሂዶ ነበር። ጦርነቱ ለጥቂት ምዕተ ዓመታት ከቀጠለ በኋላ ቀዝቀዝ አለ። ከ15ኛውና 16ኛው ምዕተ ዓመት ወዲህ በፕሮቴስታንቶቹ እንደገና አገረሸ። እስካሁን ድረስ በእምነታቸው ያለ ጉዳይ ነው። አንዳንዶቹ ፕሮቴስቴንታንት ወንድሞቻችን ምስሎችን እንደ አረማዊ (የጣዖት አምልኮ) ቅሪት አድርገው ይቆጥሩታል። ኦርቶዶክሶችንና ካቶሊኮችን ምስሎችን በማክበራቸው፣ በመሳለማቸው፣ በፊታቸው መብራትን በማድረጋቸውና በፊት ለፊታቸው በመንበርከካቸው ይወቅሷቸዋል።

የ’ምስሎችን’ (‘አርማዎችን’) መንፈሳዊ ጠቀሜታቸውን በማሳየትና፣ ቤተ ክርስቲያንም ለምን እንደምታኖራቸው በማስረዳት ለእነዚህ ሁሉ ነጥቦች መልስን ለመስጠት እንሞክራለን። 

(1) ስለምስሎች ጉዳይ መልስ ለመስጠት የሚከተሉትን ማጤን አለብን። 

(ሀ) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን የሚያነሱት ጥቅስ ምን ይላል? ይህ ጥቅስ ለምን ተባለ? ዓላማው ምንድነው? እነዚህን ጥያቄዎች እንድንጠይቅ የተደረግንበት ምክንያት“ፊደል ይገድላልና” (2ኛ ቆሮ 3፥ 6) በማለት ሐዋርያው የጻፈው ሐረግ ነው። 

(ለ) ከዚሁ ጥቅስ ጎን ቢቀመጡ ትርጉሙን የሚያሟሉ፣ የትዕዛዙን ፊደል ሳይሆን መንፈሱን እንድንረዳ የሚያደርጉ፣ ሌሎች ጥቅሶች ማንኛቸው ናቸው?  ቀደም ብለን አንድን ጥቅስ ብቻ መምዘዝ አደጋውን አስረድተናል።

(2) ምስሎችንና ሐውልቶችን እግዚአብሔር የመከልከሉ ዓላማ ምን ነበር? የጌታ ዓላማ ከቃሎቹ ግልጽ ነው። “አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውም።” ነው። የሥዕሎቹ ዓላማ እነርሱን ከማምለክ የራቀ እስከሆነ ድረስ ትዕዛዙ አልተጣሰም ማለት ነው። 

መከልከሉ ከጌታ አሥርቱ ትዕዛዛት መካከል መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ትዕዛዙ የተሰጠውም የጣዖት አምልኮ በስፋት በነበረበት ጊዜ ነበር።በዚያን ጊዜ አማኞች እምነታቸውን እንዳይተው ብዙ ጭንቀት ነበር።ስለዚህ ነበር በማንኛውም ድንጋይ ላይ በተራ ሕንጻም ሆነ መሠውያውን በመሥራት ወቅት ቅርጻ ቅርጽን ማበጀት የተከለከለው።   

(3) ብዙ እባቦችን በተመለከተው ታሪክ ላይ እግዚአብሔር ሙሴን÷ “---እባብን ሠርተህ በዓላማ ላይ ስቀል፤ የተነደፈውም ሁሉ ሲያያት በሕይወት ይኖራል አለው” (ዘኁ 21 ፥ 8) ይላል። ይህን ያዘዘውም ሰዎች ማናቸውንም ቅርጽ እንዳያደርጉ የከለከለው ጌታ ራሱ ነው። ሙሴም ይህንኑ የታዘዘውን አደረገ። በዚህም መታዘዝ ሁለተኛውን ትዕዛዝ መጣሱ አልነበረም።  

ከዚህም በተጨማሪ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህ ድርጊት የቅዱስ መስቀሉን ንድፍ የተከተለ ስለመሆኑ “ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል” (ዮሐ 3 ፥ 14፣ 15) በማለት አስተምሯል።

(4) ጌታ ሙሴን የኪዳኑን ታቦት እንዲሠራ ሲያዘው፣ ከወርቅ የተሠራ ኪሩቤል ከላይ በኩል እንዲያደርግ አዞታል። እንደዚህም አለው÷- “ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ፥ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን ታደርጋቸዋለህ። ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርገህ በአንድ ላይ ትሠራዋለህ።ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ይዘረጋሉ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፥ ፊታቸውም እርስ በርሱ ይተያያል፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ ስርየት መክደኛው ይመለከታሉ። የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ ታደርገዋለህ፤ እኔም የምሰጥህን ምስክር በታቦቱ ውስጥ ታኖረዋለህ።በዚያም ከአንተ ጋር እገናኛለሁ፤ የእስራኤልንም ልጆች ታዝዝ ዘንድ የምሰጥህን ነገር ሁሉ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል፥ በስርየት መክደኛውም ላይ ሆኜ እነጋገርሃለሁ።” (ዘጸ 25፥  18-22)። እናም እንደዚሁ ተደርጓል። 

የነዚህን የሁለቱን ኪሩቤል ቅርጽ መሥራት በላይ በሰማይ ካለው በማናቸውም በተቀረጸ ምስል ጣዖትን አታድርጉ የሚለውን ሁለተኛ ትዕዛዝ መተላለፍ አልነበረም።  ምክንያቱም ዓላማው በሁለቱ ኪሩቤል የተወከሉትን መላእክት ማምለክ አልነበረም። በተቃራኒው ልክ እባቡ በመለኮት ትዕዛዝ ተሠርቶ እንደነበረው የሁለቱ ኪሩቤል  ምስልም  የተሠራው በመለኮት ትዕዛዝ ነበር። 

(5) በተመሳሳይ መልኩ ሰሎሞንም ቤተ መቅደሱን ሠራ፤ ውስጡንም አስጌጠው። “በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው አሥር ክንድ የሆነ ከወይራ እንጨት ሁለት ኪሩቤል ሠራ። የኪሩብም አንደኛው ክንፍ አምስት ክንድ፥ የኪሩብም ሁለተኛው ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፤ ከአንደኛው ክንፍ ጫፍ ጀምሮ እስክ ሁለተኛው ክንፍ ጫፍ ድረስ አሥር ክንድ ነበረ። ሁለተኛውም ኪሩብ አሥር ክንድ ነበረ፤ ሁለቱም ኪሩቤል አንድ ልክና አንድ መልክ ነበረ። የአንዱ ኪሩብ ቁመት አሥር ክንድ ነበረ፥ የሁለተኛውም ኪሩብ እንዲሁ ነበረ። ኪሩቤልንም በውስጠኛው ቤት አኖራቸው፤ የኪሩቤልም ክንፎቻቸው ተዘርግተው ነበር፤ የአንዱም ኪሩብ ክንፍ አንደኛውን ግንብ ይነካ ነበር፥ የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ ሁለተኛውን ግንብ ይነካ ነበር፤ የሁለቱም ክንፎች በቤቱ መካከል እርስ በርሳቸው ይነካኩ ነበር። ኪሩቤልንም በወርቅ ለበጣቸው።” (1ኛ ነገሥ 6 ፥ 23-28)

(6) የሁለቱ ኪሩቤል ጉዳይ ብቻ አልነበረም። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል÷“በቤቱም ግንብ ሁሉ ዙሪያ በውስጥና በውጭ የኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸ” (1 ነገሥ 6፥29) ። ለመግቢያ ሁለት መዝጊያዎችን አደረገና “የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸባቸው፥ በወርቅም ለበጣቸው፤ ኪሩቤልናና የዘንባባውን ዛፍ በወርቅ ለበጣቸው” (1ኛ ነገሥ 6÷ 32፣ 35)። እንግዲህ የጌታ ቤት በምስሎች፣ በቅቦች፣ና በቅርጾች እንዲህ አጊጦ ነበር ማለት ነው። እንደዛም ሆኖ ሰዎች እግዚአብሔርን አምልከዋል። እነዚህን ሥዕሎችም ሆነ ቅርጾችን አላመለኩም። በዚህም ሁለተኛውን ትዕዛዝ አልሻሩም። 

(7) እንደዚሁም ሁሉ በካህናቱ፣ በሕዝቡም በነገሥታትም ይከበር የነበረው የኪዳኑ ታቦት በጭራሽ የጣዖት አምልኮን አይወክልም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን የእስራኤል ልጆች በጋይ በተሸነፉ ጊዜ የሙሴ ተተኪ የሆነው የነዌ ልጅ  ኢያሱና የእስራኤል ሽማግሌዎች  ሆነው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ተደፍተው እስከ ማታ ድረስ ወደ እግዚአብሔር ጸለዩ (ኢያሱ 7፥ 6) ። ይህን በማድረጉ ጌታ ኢያሱን “ሁለተኛውን ትዕዛዜን ተላልፈሃል” አላለውም። ነገር ግን በተቃራኒው ጌታ አናገረው፤ የ‘ከርሚ’ን ልጅ  የ‘አካን’ን ኃጢአት በመግለጽ ታዓምራዊ ምልክትን አደረገ። ‘ጋይን’ን በኢያሱ እጅ አሳልፎ በመስጠት የኢያሱን ራስ ቀና አደረገው።

ኢያሱ በኪዳኑ ታቦት ፊት በመንበርከኩ ኃጢአትን አላደረገም፤ ምክንያቱም ታቦቱን ማምለኩ አልነበረም፤ ይልቁንም ጌታን ማምለኩ ነበር። አዎ መጥቶ በኪሩቤሉ መካከል የተናገረውን ጌታን ማምለኩ ነበር። “ነቢዩ ዳዊትም ታቦቱን በመመለስ ጊዜ በታቦቱ ፊት እየዘለለና እየጨፈረ በማክበሩ ኃጢአትን አላደረገም” (2 ሳሙ 6 12-15) ። 

(8) እንደዚሁም ሁሉ እኛ ሥዕሎችንና ምስሎችን አናመልክም፤ ነገር ግን እናከብራቸዋለን እንላለን። በዚህ ዓይነት ባለ ሥዕሎቹንም እናከብራለን። ይህም “የሚያገለግለኝም ቢኖር አብ ያከብረዋል” (ዮሐ 12፥ 26) በማለት ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ በተናገረው ቃል መሠረት ነው።አብ ቅዱሳኑን የሚያከበር ከሆነ እኛ ልናከብራቸው አይገባምን?  

(9) መስቀሉን በተመለከተም ይህንኑ ነገር እንላለን።ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች እንዲህ አለ÷-“የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር” (ገላ 3፥ 1) ።

(10) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን የተቀረጸ ምስል እንደሆነ ሳይቆጥሩ ዛሬ ዛሬ በቤተክርስቲያናቸው አናት ላይ የመስቀል ምልክትን በማቆማቸው እግዚአብሔርን እናመሰግናለን። 

(11) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን  በእሁድ ትምህርት ክፍለ ጊዜያቸው የክርስቶስን ፣ የመላእክቱን፣ የነቢያቱን፣ የኖኅን መርከብ ከነእንስሳቱ፣ መልካሙን እረኛና በጎቹን ፣ ዳዊት በጎቹን ሲጠብቅ፣ ‘ኤልሳ’ንና ቁራዎች እርሱን ሲመግቡት፣ ድሃውን አልዓዛርን ና ቁስሉን ውሾች ሲልሱት፣ በልዓምን፣  ሰይጣን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በምድረ በዳ ሲፈትነው የሚያሳዩትን ሥዕሎች  ስለሚያሰራጩ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን ። እነዚህን ሥዕሎች ሲያሰራጩ በላይ በሰማይና በታች በምድር ሥዕልን በማድረግ ሁለተኛውን ትዕዛዝ ሻርን ብለው አይታወኩም። 

(12) በመጽሐፍ ቅዱስ የተፈጸመውን ድርጊት፣ ስለእምነት አርበኞችና ስለ ሕይወታቸው  በማስተማርና በማስረዳት በኩል የሥዕልን ውጤማነት ማናናቅ አንችልም።  ሥዕል (‘አርማ’) በሚያየው ሰው ነፍስ ውስጥ ስብከትን ከማንበብ ወይም ከመስማት የበለጠ እጅግ የጠለቀ ስሜትን ሊያሳድርበት ይችላል። ምስሎች (አርማዎች) በምድር ያሉትን አማኞች በሰማይ ካሉት መላእክትና በገነት ከሚኖሩት ቅዱሳን ጻድቃን  ጋር ያገናኛል። የሐዋርያውን ቃል እንድንፈጽም ብርቱ የውስጥ መነቃቃትን ያስከትልብናል። እንዲህ ተብሎ የተጻፈውን፦“የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው።”  (ዕብ 13÷ 7) ።

(13) ሥዕሎችን ስናከበር ሥዕሎቹ የተሳሉላቸውን ማክበራችን ነው። ወንጌልን ስንስም ለእግዚአብሔር ቃልና እንዲመራን ትዕዛዝን ለሰጠን ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር ማሳየታችን ነው። በመስቀሉ ሥር ስንጎነበስ ከአባቶቻችን አንዱ እንዳሉት “በላዩ ላይ ‘ለተሰቀለው’ ለእርሱ መስገዳችን” ነው። እነዚህን ስናደርግ “አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውም” የሚለው ትዕዛዝ  በጭራሽ እኛን አይመለከትም።  

(14) ከሐዋርያቱ ዘመን አንስቶ አርማዎች/ሥዕሎች የሚከበሩ እንደነበሩ እጅግ የታወቀ ነው። ወንጌላዊ ቅዱስ ሉቃስ ሰዓሊ ነበር ይባላል። ከአንድ በላይ የሆነ የድንግል ማርያምን ሥዕል ስሏል። የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት በመሃረብ ላይ ታትሞ እንደነበር በትውፊት ደርሶናል። 

ስለምስሎች (አርማዎች) ታሪክ ብናጠና ብርቱ እምነት የታየበት ዘመን ሰዎች ምስሎችን ባከበሩባቸው ዘመናት ነበር። ምስሎችን በመጠቀማቸው እምነታቸው አልተጎዳም እንዳውም በተቃራኒው  መልካም ሥራን አጉልተው የሚሠሩ ነበሩ። 

(15) ለምንድነው የሰዎችን መንፈሳዊ ሕይወት በሥዕላቸው እንዳያነቃቁ ሠዓሊዎችን የምንከለክለው? ሥዕሎች  ነፍስን የሚነካ መንፈሳዊ ስሜትንና የቅዱሳንን የሕይወት ታሪክ ለሰዎች አሳምረው ያስተላልፋሉ። 

Comments

Popular posts from this blog

Comparative Theology የነገረ መለኮት ንጽጽር (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት)/ በብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሲኖዳ ሳልሳዊ

 የነገረ መለኮት ንጽጽር  (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት): የወደደ  ሁሉ በነጻ እንዲጠቀምበት ተፖስቷል። ይሁን እንጂ መብቱ በሕግ የተጠበቀ ስለሆነ በየትኛውም መልኩ ለንግድ እንዲውል አልተፈቀድም። ልዩ ልዩ መግቢያ የሚለውን መጀመሪያ ካነበቡ በኋላ የተቀረውን በተመረጠው ቅደም ተከተል ማንበብ ይቻላል። ልዩ ልዩ መግቢያ   ጥምቀት   ትውፊት (ወግና ልማድ)   መካከለኝነት   ጾም የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ መንፈሳዊ ስጦታዎችና በልሳኖች የመናገር ስጦታ   ሥርዐት ንስሐ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ (1)  ድንግል ማርያምን ስለማክበር (2) ለጥያቄዎች መልስ (ሀ) ድንግሊትን ‘የወይን ግንድ (ተክል)’ና የ ‘ሕይወት በር’ የሚል ማዕረግ  ለምን እንሰጣታለን? (ለ) ወደ ድንግል ማርያም መጸለይ ትክክል ነው ወይ? (3) የድንግል ማርያም ድንግልና ዘላለማዊነት (4) ለተቃራኒ አስተያየቶች መልስ (ሀ) “የመጀመሪያ ልጇን” የሚለው ሐረግ (ለ) “ሚስትህ” የሚለው ሐረግ (ሐ) “አብረው ከመሆናቸው በፊት ጸንሳ ተገኘች” (መ) “የመጀመሪያ ልጇን እስክትወልድ አላወቃትም” (ሠ)  “ወንድሞቹ” የሚለው ሐረግ   የቅድስት ድንግል ማርያም  ክብሯ (1) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ድንግል እመቤታችንን አያከብሩም፤ ደግሞም እንድታማልድላቸውም (እንድትማልድላቸውም)  አይጠይቋትም።ከእነርሱ ወገኖች አንዳንዶቹ እንዲያውም ጫጩቱ ከተፈለፈለ በኋላ ዋጋ ከሌለው የዶሮ እንቁላል ቅርፊት ጋር እስከሚያመሳስሏት ይደርሳሉ።ይህ የተጋነነ ማቃለል የመጣው ምናልባት ሮሜዋውያን ካቶሊኮች የተጋነነ ማክበር ስለሚያከብሯት ለዛ ተቃርኖ ከማሳየት አዝማሚያ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን አንዱንም የእርሷን በዓል አያከብሩም።  (2) አንዳንዶቹ የፕሮቴስታንት ወገኖች ድንግል ማርያምን “እህታችን” ይሏታል። (3) በተጨማሪ አንዳንዶቹ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ጌታ ኢየሱስን በድንግልና ከወለደች በኋላ ከዮሴፍ ጋር ጋብቻዋን ፈጽማለች፤ የ‘ኢየሱስ ወንድሞች’  ወይም የ’ጌታ ወንድሞች’ ተብለው የተጠሩ ልጆችን ወልዳለች ይላሉ።  (4) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ቤተክርስቲያናችን ለድንግል እመቤታችን የሰጠቻቸውን አንዳንድ የማዕረግ ስሞችም ይቃወማሉ።  (5) ድንግልን ያለማክበራቸው አንዱ...

ስለ "አስታዋሽ ጾምና በዐሉ" ጥያቄና መልስ

 ስለ "አስታዋሽ ጾምና በዐሉ" ጥያቄና መልስ  ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ፦ ሕልውናችንን-ነጻነትችንን የማረጋገጥና የማስቀጠል አንድነታችንን የመጠበቅና የማጠንከር  በእሴቶቻችን የመደሰት፣ እነርሱን የመንከባከብና የማስተዋወቅ  በረከታችንን የማብዛትና የማካፈል  ኃላፊነቶቻችንን በማኅበር ፣ በማስተዋልና በትጋት እንድንወጣ “ጾሙና በዐሉ" አስታዋሽ ባሕላዊ ምልክታችን ይሁንልን   ጥያቄ 1 ፡ አድማጭ ተመልካቾቻችን እንኳን ደህና መጣችሁ።የከበረ ሰላምታችን ይድረሳችሁ። ዛሬ የምንወያየው ከአቶ ባንቱ ገብረማርያም ጋር ይሆናል። አቶ ባንቱ በሙያው ፋርማሲት ነው። እንደነገረኝ በእምነቱ ደግሞ ባፕቲስት ነው።ለዐማራ ሕዝብና ዎገኖቹ ባሕላዊ ምልክት የሚሆን “ጾምና በዐልን” በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል። የምንወያየውም ስለዚሁ "ጾሙና በዐሉ" ምልክትነት ይሆናል።  አቶ ባንቱ ለመወያየት  ወደ እኛ በመምጣትህ አመሰግንሃለሁ። እንኳን ደህና መጣህ። አንተ እያልኩ ልቀጥል ወይስ አንቱ? መልስ 1፡ ዎገኔ፡   እንኳን ደህና ቆየኸኝ። ለአድማጭ ተመልካቾቻችሁም ሰላምታዬ ይድረስልኝ። አንተ በለኝ። የሚያውቀኝ ሁሉ አንተ ነው የሚለኝ።  ጥያቄ 2 ፡ እሺ  አንተ እያልኩ እቀጥላለሁ። አቶ ባንቱ፣ ምናልባትም ብዙ ሰው ስለማያውቅህ  እስቲ ስለራስህ በአጭሩ ንገረን። ወዲያውም መክፈቻ ይሆነናል መልስ 2 ዎገኔ ፦ አስቀድሜ ይኸን ዕድል ስለሰጠኸኝ ላመሰግንህ እወዳለሁ። አድማጭ ተመልካቾችህንም ጊዜ ወስደው  ውይይቱን  ስለሚከታተሉ ላመሰግናቸው እወዳለሁ።አዎን፣ ባንቱ ገብረማርያም እባላለሁ።እንደነገሩኝ የተወለድኩት ሽርካ በዛሬ አጠራሩ በአርሲ ዞን ነው።ነፍስ ያወቅሁትና ትምህርት ...