እግዚአብሔር የጠላቶቼ ጠላት አይደለም!
በባንቱ ገብረማርያም
አድማጭ ተመልካቾቼ ፡ እንደምን ሰነበታችሁ? እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ። እንደገና ብቅ ብያለሁ። ዛሬ የምናገረው መምህር በጋሻው ሰሞኑን የተናገሩት መነሻ ሆኖኝ ነው። ርዕሱም "እግዚአብሔር የጠላቶቼ ጠካት አይደለም" የሚል ይሆናል። እንደ ተለመደው በጽሞና እንድትከታተሉኝ ላስቸግራችሁ እወዳለሁ። አሁን ወደ አስተያየቴ፦
ከዚህ ቀደም በኦርቶዶክሳውያን ስለሚደርሰው መከራ የደረስኩበትን ግንዛቤ “መከራው እስካለ” በሚል ርዕስ ጽፌ ነበር። ማንበብ ለሚፈልግ ሊንኩ ይኸው። You searched for መከራው እስካለ - Hintset ። መምህር በጋሻው ሰሞኑን በተናገሩት መነሻ የጻፍሁት ይኸኛው ጽሑፍ ከዚያ የተከተለ አድርጎ መውሰድ ይቻላል።
“እግዚአብሔር የጠላቶቼ ጠላት አይደለም” የሚለው ሐረግ የተነገረው በማርቲን ኒሞለር (Martin Niemöller") የሉተራዊ ነገረ መለኮት አዋቂ በነበረው ጀርመናዊ ነበር። ማርቲን መጀመሪያ የሂትለር ደጋፊ ቢሆንም በኋላ ላይ አጥብቀው ከሚቃወሙት አንዱ ሆኗል።
“የእግዚአብሔር ፍቅርና ምህረት በወገን/ በቡድን የሚታጠር አይደለም። ጠላት ለሚባሉትም እንኳ የተዘረጋ ነው ። የእዚአብሔር ፍቅር የግል ቂም በቀልን ትክክለኛነት ለማጽደቅ ወይም የበቀል መሣሪያ ሆኖ ሊያገለግል አይገባውም” ብሎ የሚሞግት ሰው ነበር።
ናይጄራዊቷ ጸሐፊና ተናጋሪ ቺማማንዳ ንጎዚ አዲሼ (Chimamanda Ngozi Adichie) ይኸንን አተያየት በሕይወት ጉዞዋ ደርሳበታለች። ነገር ግን ጊዜ እንደወሰደባት በተለያዩ አጋጣሚዎች ስትናገር ተደምጣለች። የካቶሊክ አማኝ የሆነችዋ ይኽች ሰው አንድ ጊዜ ራሷንና የእርሷ የሆኑትን የሚተናኮሉትን እግዚአብሔር እንደሚቀጣላት ታስብ ነበር። ነገር ግን በጊዜ ሂደት እግዚአብሔር ወገን እንደማይለይ ተረዳች። አሁን ላይ “እግዚአብሔር የጠላቶቼ ጠላት አለመሆኑን ለመረዳት ጊዜ ወስዶብኛል” እያለች ታወሳለች። ይህንን ሰፋ ያለ አተያየት እንድትጨብጥ የረዳት ስለ እምነት፣ ስለ ርኅራኄ እና በሰው ልጅ መኻል ስለሚኖር ጠብ ውስብስብነት በጊዜ ሂደት የተማረችው ነው ። (ስለ ማርቲንና ስለ አዲሼ የወሬ አባቴ AI ነው።)
ይኸን ሐሳብ ባሰላሰልኩት ጊዜ እኔም ታዲያ “ጠላቶቼን/አሳዳጆቼን ተበቀለልኝ“ የሚለውን ሐሳብ ለመለወጥ “ማደግ ያስፈልግ ይሆን?” ብያለሁ።
ብቻ ይህ “እግዚአብሔር ጠላቶቼን ተበቀለልኝ” የሚለው ሐሳብ ለጊዜው የፎከረውን ሰው ደስ ሊያሰኘው ቢችልም ከጀርባው ሦስት አደገኛ ሐሳቦች እንዳዘለ ግን ማየት ይቻላል።
- እግዚአብሔርን የግል ቂምን መበቀያ መሣሪያ አድርጎ ያሳንሰዋል።
- ተናጋሪውን በሞራል እንከን የለሽ ወይም ከተፎከረበት ወገን የበለጠ አድርጎ ያመጻድቀዋል/ያስታብየዋል።
- ይቅር መባባልን፣ ምህረትንና እርቅን ገሸሽ የማድረግ ቂም ቋጥሯል
በአጭሩ፦ ሳይታወቀው ፎካሪው እውነትንና ፈውስን ከሚፈልግ ይልቅ በተፎከረባቸው ወገኖች በደረሰው ሃዘንና ሰቆቃ የሚደሰት “ተሳላቂ” ሆኖ እንዲያርፈው ያደርገዋል።
ታዲያ መምህር በጋሻው ብቻ ሳይሆን ነገር ላለመፈለግ ብለው አያውጁትም እንጂ በእኛ ሰፈርም “እግዚአብሔር ጠላቶቼን ተበቀለልኝ" የሚለው እምነት ለበርካታ ዐመታት ሰፍኖ የቆየ ነው። በተቃወሙን ላይ መከራ ሲመጣ እግዚአብሔር ስለእኛ ለመበቀል እንዳደረገው የምናምን ብዙ ነን። ዛሬ ለአቅመ አሳዳጅነት ደርሰንም እንኳ ይኸንኑ ሐሳብ ያልለቀቅን እንገኛለን።
በአርግጥ እግዚአብሔር ለቡድን ወይም ለግለሰቦች ፍርድን አያደርግም፣ ፍትሕን አይሰጥም ብሎ መናገር አይቻልም። ነገር ግን ፎካሪው "ተበቀለልኝ" ብሎ ከመናገሩ አስቀድሞ ጥያቄዎችን ቢጠይቅ ማስተዋል ይሆንለታል።
- በደሉ እውነት ተፈጽሟል ወይ?
- ከተፈጸመስ በደሉን እግዚአብሔር የሚያየው ፎካሪው እንደሚያየው ነው ወይ?
- ለመሆኑ ፎካሪው ክበደሉ ፍጹም ነጻ ነው? ድርሻ የለውም ወይ?
- በእውኑ እግዚአብሔር ከአንዱ ይልቅ ለሌላው ያደላል? አንዱን ለይቶ የሚያግዝበት እውነት በፎካሪው የተለየ ጽድቅ አይቶበት ነው?
- በተመሳሳይ ሁኔታ እግዚአብሔር የተፎከረባቸውንስ ይወድ አይደለምን?
- እግዚአብሔር ቅጣትን ያደረገው ፎካሪው ለፎከረበት በቀል ነው ወይስ ለሌላ የላቀ ዐላማው ነው?
"መለኮት ተበቀለልኝ" ከማለት አስቀድሞ ለእነዚህ የጠራ መልስ ማግኘት የቸርነትን መንገድ መከተል ነው።
ለማንኛውም በዚህ ዙሪያ የቱንም ያህል የነገረ መለኮት አተያየት ልዩነት ይኑር ኦርቶዶክሳውያኑ መገደላቸው ጥፋት በመሆኑ ላይ ግን የምንስማማ ይመስለኛል። ሰላማዊ ሰው መግደል በባሕላችንም ጥዩፍ ነው። ለዚህም ይመስለኛል ባለፈው ኦርቶዶክሳውያኑ እንዳይገደሉ ባወቁት ዘዴ ሁሉ ሙስሊም ጎረቤቶቻቸው የተከላከሉላቸው።
በኦርቶዶክሳውያኑ መገደል ሁላችንም የተቃውሞ ድምጻችንን ማሰማት አለብን እላለሁ። አዎ ከኦርቶዶክዳውያኑ ጋር ልዩነት አለን። ይህ አይካድም። ነገር ግን ኦርቶዶክሳውያኑ የሥጋ ዘመዶቻችን እንዳልሆኑና ስለ እነርሱ ኃላፊነት እንደሌለብን ነገር አንደበታችንን መያዝ የለብንም። አሸዋ ውስጥ አንገቷን ስለቀበረች የተደበቀች እንደሚመስላት ሰጎን አንሁን! ከእርቶዶክሳውያኑ ጋር በአንድ ጀልባ እንዳልተሳፈርን ሊመስለንም አይገባም። መምህር በጋሻውን ስለማላውቃቸው ስለ ስብዕናቸው ልናገር የምችለው ክፉም፣ ደግሞ የለኝም።ነገር ግን በተናገሩት ውስጥ የሚባርክ ነገር አላየሁበትም።ስለእርሳቸው በዝቶ መወራቱም ዋናውን ነገር ለመሸፈን ምክንያት ሆኗል።
ቀደም ሲል በሻሸመኔና በሌሎች አካባቢዎች ከዚያም ወዲህ በተለያዩ ጊዚያት በአርሲ ሰላማዊ ኦርቶዶክሳውያን መገደላቸው ወንጀል ነው-አሰቃቂ ነው- አውሬነት ነው። (ጭካኔውን ለመግለጽ ምንም ዓይነት ቃል ሊገልጸው የሚችል አይመስለኝም)። ወንጀልን መከላከል ፣ ወይም ማስቆም፣ በተደረገም ጊዜ ተጠርጣሪውን አፈላልጎ ይዞ ለፍርድ ማቅረብ የመንግሥት ኃላፊነት ነው። ምናልባትም ከሌላው የሚቀድም ኃላፊነቱ ነው። ያቃተውም ከሆነ ሕዝብ ራሱን እንዲከላከል ማስቻል ይጠበቅበታል።ስለዚህ መንግሥትን በኃላፊነት መጠየቅ ተገቢ ነው። ይህ እንዳይሆን ይመስለኛል በመምህር በጋሻው ንግግር ላይ ርብርቡ - አዎ ትኩረትን ለማስቀየስ። ዋናው ትኩረት መሆን ያለበት መንግሥት ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ተጠያቂ ማድረግ ላይና ኃላፊነቱን እንዲወጣ ግፊት ማድረግ ላይ ሊሆን ይገበዋል። ከመንግሥት ፍጹምነትን መጠየቄ አይደለም። እንዲህ ዐይነት ነገር የታየው ተደጋግሞ ስለሆነና ይህ በቂ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስለሆነ ፣ በእኔ አተያየት መንግሥት በአርሲም ሆነ በሌላ ሥፍራ ሰላማዊ ዜጎች እንዳይገደሉና እንዳይጠቁ የሚጠብቅ ሥርዐት ላለመዘርጋት ሰበብ የለውም።
በጌታ ወንድማቸው የሆናችሁና የምትቀርቧቸው የእኛ ሰፈር ሰዎች በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ይኸንኑ ኃላፊነት እንዲያስፈጽሙ በጆሮአቸው ሹክ ብትሏቸው ምናልባት እናንተን ይሰሙአችሁ ይሆናል።
ተሳስቼ ሊሆን ይችላል፣ እንደ እኔ ማስተዋል የተሄደ እንደሆነ ግን የሕዝብን ጩኸት የሚሰሙ ሆነው አልታዩኝም።ምናልባት የጩኸቱ ሞገድ በኪሎ ኸርዝ ሲለካ ሊደመጥ ከሚችለው ዞን ውጭ ሆኖባቸው ሊሆን ይችላል። ወይም በሕዝብ ጩኸት አዋኪ ሞገድ እየተለቀቀበት ሊሆንም ይችላል። ምክንያታቸውን እንጃ ፤ ብቻ የማይሰሙ እንደሆነ ተሰምቶኛል።
በነገራችን ላይ ነገሮች ቢለዋወጥ ኦርቶዶክሳውያኑ በእኛ በሚደርሰው ነገር ድምጻቸውን ያጠፉ ይሆናል። ለዚያም ሁኔታ ቢሆን አስተያየቴ አይለወጥም። በምሥራቅ አፍሪካ ተሆኖ ወንጌልን ለጎረቤቶቻችን ለማድረስ እኛና እነርሱ ማለት የሚበጅ ስላይደለ ድልድይ በማበጀቱ ላይ ማተኮሩ ይመረጣል እላለሁ።
“እግዚአብሔር የጠላቶቼ ጠላት አይደለም”! የሰላማዊ ኦርቶዶክሳውያንና የሌሎችንም ሰላማዊ ዜጎች ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት የመንግሥት ነው።
ቸር እንሰንብት!
ሁሉ ቀን መልካም ቀን ይሁንላችሁ።
የሰማና የወደደ ላልሰማ ያሰማ!
ያየና የወደደ ላላየ ያሳይ!
ያነበበና የወደደ ላላነበበ ያስነብብ
ሰብስክራይብ ፣ሼር፣ ላይክ ፣ ደወሏን ይጫኑ እንዲሉ
ባንቱ ገብረማርያም
Comments
Post a Comment