Skip to main content

ለፓስተር ግርማ ቤካ



ለፓስተር ግርማ ቤካ

ይህ የመጀመሪያው ጽሑፌ በዩ ትዩብ ለማቅረብ እንዲስማማ የተደረገ ነው።
አድማጭ ተመልካቾቼ እንደምን ሰነበታችሁ? እኔ ቸርነቱ የበዛ አምላክ ይመስገንና ደህና ነኝ። የዛሬ ዝግጅቴ አንድ ፓስተር ወንድሜ ለተናገረው ምላሸ የሚሰጥ ነው።
    የአርሲ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች የደረሰባቸውን ግፍ ከኦርቶዶክሳውያኑ ጎን በመሆን ያወገዙ የወንጌል አማኞች ነበሩ። ይኸንን የወንጌል አማኞች ድርጊት “አታሽቃብጡ” በማለት ይኸው ወንድማችን ተቃውሞታል።የተቃወባቸውን ስምንት ምክንያቶች ነጥብ በነጥብ እያነሳሁ የራሴን አጭር ምላሽ የምሰጥባቸው ይሆናል። ከአጭር ምላሹ በኋላም ማብራሪያን አስከትላለሁ። በመጨረሻም ሐሳቤን አጠቃልላለሁ።በስፋት ከተደመጠ ቀና ውይይት ይከፍታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
    በዚህ አጋጣሚ ቤተሰብ የተገደለባቸውን እግዚአብሔር አምላክ ያጽናናችሁ ለማለት እወዳለሁ። ያፈሩትን ሐብትና ንብረት በትነው፣ ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ እንዲሰደዱ ለተገደዱት ወገኖችም ስቃያችሁን እግዚአብሔር “ሕይወትን ለማዳን” ያድርግላችሁ እላቸዋለሁ።

አሁን ወደ ምላሹ፡
    የተወደድክ ፓስተር ወንድሜ: ለጤናህ እንደምን አለህ? እኔ ቸርነቱ የማያልቅበት እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን ደህና ነኝ።
    በአርሲ ግፍ ለተቀበሉት ኦርቶዶክሳውያን ድምጽ ላሰሙቱ የወንጌል አማኞች “አታሽቃብጡ" በሚል ሐሳብ ዙሪያ የተናገርከውን በአንክሮ አዳምጬ ከጨረስኩ በኋላ ግልጽነትህንና ስሜትህን ለመግለጥ መድፈርህን አድንቄአለሁ።ይኸው ድፍረትህ እኔንም እንድናገር አነቃቅቶኛል። ወንጌላዊ አማኝ ብሆንም በአርሲ ኦርቶዶክሳውያን የደረሰውን ግፍ ካወገዙት ጋር እንደምቆም በአክብሮት ለመግለጥና ምክንያቴን ለማብራራት ተነሳሳሁ። በገሐድ ምላሽ መስጠቴም መልዕክትህ ገሐድ ስለነበረ ነው።

“እንደ እኛ መከራን በፀጥታ ይቀበሉ” ከሚለው እጀምራለሁ።


ፍትሕ በጎደለበት ላይ ዝም ማለት ጨቋኙን ከመርዳትና በደልን ከማጽደቅ ተለይቶ የሚታይ አይደለም። እውነት ነው ፥ እንደ ክርስቲያን መከራን መቀበል ይጠበቅባቸዋል። በትእግስትም መቀበል ይገባቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ማለት ፍትሕን ከመፈለግ ጋር ይጋጫል ማለት አይደለም። ስለዚህ ኦርቶዶክሳውያኑ ፍትሕን መጠየቃቸው አግባብነት አለው። “ጸጥ ብላችሁ ፍዳውን ተቀበሉ” አንበላቸው። በማገዛችን እኛም ልንወቀስ አይገባም።

ላስረዳ፡

     ክርስትያን የሚሰደድ መሆኑን ስለማወቅ ለኦርቶዶክሳውያን መንገር ልጅ ለእናቷ ምጥ አስተማረች እንደሚሉት ይሆንብናል። ኦርቶዶክሳውያኑን የምንወቅስባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም ከነዚያ ዝርዝር ውስጥ ይህ አይገኝበትም።"ዘመነ ሰማዕታት" የተሰኘው የቀን አቆጣጠራቸው መከራን መቀበል እንዳይዘነጋቸው የሚያስታውሳቸው ነው።ሌላ አስታዋሽ አያስፈልጋቸውም። ምናልባት እኛም መጽሐፍ ቅዱስ ስላስተማረን ብቻ ሣይሆን በኅሊናችን ከአነርሱ ይዘን በመጣነው ስሜትና ባሕል ጭምር ሳይሆን አይቀርም መከራን ለመቀበል የተደፋፈርነው። ስለዚህ መከራን በትዕግሥት ስለመቀበል የምንጨምርላቸው ብዙ ዕውቀት ያለ አይመስለኝም። ይሁን እንጂ በመከራ መታገስ ማለት ፍትህን አይጠይቁ ማለት አይደለም።
    ከዚህኛው ነጥብ ጋር በተገናኘ ከተናገርከው ውስጥ “መከራ ለክርስቲያን ያለ ነገር ነውና እኛ ዝም ብለን እንደተቀበልነው ዝም ብለው ይቀበሉ” የሚለው ኅይለ ቃል ይገኝበታል። በዚህ እኛን የሞራል መለኪያ አድርገሃል። ስለ መከራችን ዝም እንዳላልን ግን የምታውቅ ይመስለኛል።በመከራችን ውስጥ እግዚአብሔር ስላሳለፈን ወይም ስለከለለን በምስክርነታችን፥ በመዝሙራችን ፥ አሁን አሁን በመጽሐፎቻችንም የምናነሳው ነው። "እንደ ሁለተኛ ዜጋ ስንታይ ኖረናል" የሚለውን ወቀሳም አንተው አንስተኸዋል። እነዚህ ሁሉ ስለመከራችን ዝም ያልን እንዳልነበረ የሚያሳዩ ናቸው። አንጩህ እንጂ ፍትህ እንፈልግ እንደነበር የሚያመለክቱ ናቸው።ስለዚህ እንደራስ ማየት ነው።በእርግጥ ስደትን አቁሙልን/አስቁሙልን ብለን ሰልፍ የወጣንበት ጊዜ አይታወስም። የቁጥር ኃይላችን (ብዛታችን) ውስን ነበረና። አንድ ላይ በሰልፍ ወጥተን "አታሳዱን" ብለን አልጮህንም። ይህንንም ቢሆን ለመጪው ዘመን ማድረግ እንድንችል አሁን እየተሟሟቅን እንገኛለን።
    “ሰርጎ ገብ ኦርቶዶክሶችን እንመነጥራለን” ያልከው ኅይለ ቃል ይኸንኑ የመሟሟቅ ሁኔታ የሚያመለክት ቀስት ነው።ስለዚህ ለ”ድምጻችን ጆሮ ያስገኝልናል ብለው ባሰቡት መንገድ ኦርቶዶክሳውያኑ አቤቱታቸውን ሲያሰሙ ፥ “አታግዟቸው ዝም ይበሉ” ማለት እኛ ያላደረግነውን አድርጉ ማለት ብቻ ሳይሆን አፈናን ማበረታታት ነው። ያልታጠቁ ዜጎች ከጥቃት ሊጠበቁ ይገባ ነበር። ስለዚህ ዝም በሉ አንበላቸው

ሁለተኛ: “አሳዳጆቻችን ነበሩ ” ስለሚለው

ያለፈ በደል የዛሬውን ግድያ ላለመቃወም ሰበብ ለመሆን አይበቃም። ከቂም የተነሣ የግድየለሽነት አዝማሚያ ማሳየት ከአርሲ ኦርቶዶክሳውያን ጨፍጫዎች ጋር ማበር ሆኖ ይታየኛል። የሲቪሎች ሕይወት ሲቀጠፍ አለመቃወም ወይም ይህን ድርጊት ክሚቃወሙ ጋር አለመተባበር ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባለው መርኅ መሠረት የሞራል ግዴታን አለመወጣት ነው። ስለዚህ አታሽቃብጡ ማለቱ ቀርቶ ግድያውን በማውገዙ መግፋት ይገባል እላለሁ።

ላብራራው፡ ኦርቶዶክሶች አሳደውናል ባልከው እስማማለሁ። የታሪክ እውነት ነው፣ አይካድም።ለብዙው ስደት የዐይን ምስክር ባልሆንም ቢያንስ ስለአንዳንዶቹ ነበርኩ። ዝርዝሩን ልተወውና (አንተም አልገባህበትም) በደፈናው ባያሳድዱን ኖሮ መልካም ነበር እላለሁ። ድርጊቱን እነርሱ ምናልባትም ማሳደድ ብለው አይጠሩት ይሆናል። ለማንኛውም የዚያ ቅያሜ ወይም ቂም ትኩሱንና ገሐድ የሆነውን የአሁኑን የአርሲ ኦርቶዶክሳውያን ግድያን ከሚያወግዙት ጋር እንዳንተባበር ምክንያት ለመሆን አይበቃም። ታዲያ የ‍ኣሁኑ ሁኔታ ቢለወጥ ኦርቶዶክሳውያን ያሳዱን ማለቴ እንዳልሆነ ትረዳኛለህ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።ይልቁንም ባለፈው ጊዜ ማሳደዳቸው፣ ወንጌላውያኑን ከማደግ እንዳላገደን በመገምገም ፣ ተባብሮ የመሥራትን መንገድ ይመርጣሉ ፣ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። እኛም "እግዚአብሔር የጠላቶቼ ጠላት አለመሆኑን" ወደ መረዳት እናድጋለን የሚል እምነት አለኝ። በአጭሩ “አሳዳጆቻችን ነበሩ” በማለት ዛሬ በእነርሱ የደረሰውን ግፍ አለመቃወም ወደ ፊት የሚያራምድ አይደለም፣ የሞራል ግዴታንም አለመወጣት ነው።

ሦስተኛ፡ “ለእኛ ድምጽ ሆነው አያውቁም” ስለሚለው

ያለፈው አልፏል፣ ባለፈው አለመረዳታችን ስለዛሬዎቹ ተገዳዮች ዝም ለማለት በቂ ምክንያት አይሆነንም። የመኖር መብታቸው ሲገፈፍ ከተጎዱት ጋር መቆም የሚገባን ፣ እነርሱ በፊት ከኛ ጋር ቆመው ስለነበር ወይም ሁኔታው ተስማሚ ስለሆነ አይደለም። ከተበደሉት ጋር መቆም በራሱ ትክክል ስለሆነ እንጂ።

ላፍታታው፡ ለእኛ ድምጽ ሆነው አለማወቃቸው እውነት ነው። መከራ በደረሰብን ጊዜ ኦርቶዶክስውያን ስለ እኛ ተሟግተው የሚያውቁ አይመስለኝም።በበኩሌ “ፕሮቴስታንቶችን አታሳዷቸው፣ መከራ አታምጡባቸው” ብለው ሲጮሁልን ሰምቼ አላውቅም። ብድር በምድር ይጽና ካላልክ በስተቀር በእኔ በኩል የብድራት ቀለበትን መስበር እመርጣለሁ። ለማንኛውም ዛሬና አሁን እልቂት እየደረሰበት ያለ የኦርቶዶክስ ማህበረሰብ አትግደሉኝ ብሎ ድምጹን ሲያሰማ ማገዝ ተገቢ ነው።አቅዶ ዝምታን መምረጥ እንዲያውም ሌሎችንም አትተባበሯቸው ብሎ መምከር ግን የሰውን መብት ከሚጥሱ ጋር መተባበር ሆኖ ይታየኛል። እንዲህ ዓይነቱ ነገር ተገቢ አይደለም።

አራተኛ: “ኦርቶዶክሳውያኑ መጥፋታችንን ይወዳሉ” ስለሚለው

ኦርቶዶክሳውያኑ እምነታችንን እንጂ የእኛን መጥፋት አይመስለኝም የሚወዱት። የሰው ሕይወት ደግሞ ከእዚህ ዓይነቱ የሃይማኖት ክርክር በላይ ነው። ግፍ ለተፈጸመባቸው ከሚጮሁ ጋር ልንተባበር የሚገባው በነገረ መለኮት መመሳሰል ላይ ተንተርሰን አይደለም፤ በሞራል ትክክል ስለሆነ ብቻ እንጂ። ስለዚህ የአርሲ ኦሮቶዶክስ ክርስቲያኖች መገደልን ካወገዙት ጋር መቆም ሊያስወቅስ አይገባም።

ላስፋፋው፡ መጥፋታችንን ይወዳሉ የሚለው ኅይለ ቃል ቢስተካከል ስለ ኦርቶዶክሳውያን የተናገርከው እውነት ነው።ያልተስተካከለው አባባል ኦርቶዶክሳውያኑ እንድንጠፋላቸው ይፈልጋሉ የሚለው ነው። እንዲጠፋ የሚፈልጉት እኛን ሳይሆን እምነታችንን ነው። እኛን በተመለከተ የሚፈልጉት ወደ እነርሱ መመለሳችንን ሊሆን ይችላል።መስተካከል ያለበትም ይህ ነው። የእምነት ውድድር እንጂ ፍላጎታቸው በአካል መጥፋታችን አይመስለኝም። ልክ እኛ “የኦንሊ ጂሰስ” እና “የይሖዋ ምስክር” ትምህርት እንዲጠፋ ፥ ሰዎቹም ወደ እኛ እንዲመለሱ እንደምንፈልገው ማለት ነው።በአካል የመጠፋፋቱን መንገድ እኛም ፣ኦርቶዶክሳውያኑም የማናስበው ብልሆች ነን ለማለት እደፍራለሁ።ለጊዜው አልታይ ብሎን እንጂ በምሥራቅ አፍሪካ ዕጣችን አንድ ነው። የማድመጥ ፣ የገርነትና የመተባበር ዕድል በፊታችን አለ።ለማንኛውም ሕልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርምና ገና፥ ለገና ወደ ፊትም ሊያጠፉን ይችላሉ በሚል ከወዲሁ ይጥፋ ብሎ ዝም ማለት በረከት የለበትም።የበቀል የቅድሚያ ክፍያ ከእኛ ይራቅ። የሰላማዊ ሰው ሕይወት ከሃይማኖት ክርክር በላይ ነው። በሰላም በሚኖር ሕዝብ ላይ ግፍ ሲፈጸምበት፣ መጨፍጨፉን እየሰሙ ዝም ለማለት በቂ ምክንያት አይሆንም።



አምስተኛ: “የግብጽና የኤርትራ አጀንዳ ተሸካሚ ቢሆኑስ” ስለሚለው

ስለ ጠላት አጀንዳ የሚኖር ክስ ለተበዳዮች ድምጽ መሆንን አይደፈጥጥም። የሰላማዊ ዜጎች ሕይወት ከፓለቲካ አጀንዳ በላይ ስለሆነ በዚህ ሰበብ አቤቱታን ካሰሙ ጋር ትብብርን መንፈግ ትክክል አይደለም። ካስፈለገ ፖለቲካውን በሌላ መንገድ መከታተል ይቻላል።

ዝርዝሩን ላቅርብ ፡ የግብጽና የኤርትራ አጀንዳ ተሸካሚ መሆን አለመሆናቸውን ሙሉ ሰው ስለሆኑ ራሳቸው ኦርቶዶከ‍ሳውያኑ ይናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትርም ቢሆኑ የኢምሬተስን ፈቃድ፥ ምክርና ሁለንተናዊ ድጋፍ ተከትለው ነው የሚሠሩት ይባላል። እርሳቸውም ይህን ሲያስተባብሉ አልሰማሁም፡፡ የምታውቀው ካለ ስለዚህም የተጣራውን ወሬ ብትነግረን የተሟላውን ሥዕል ለማየት ይረዳናል።
    ለማንኛውም መልስ እንድሰጥበት የሚመለከተኝ “የኤርትራና የግብጽ አጀንዳ ተሸካሚ ሊሆኑ ስለሚችሉ አትጩህላቸው” የሚለው ሐሳብ ስለሆነ “ክሱ” የመኖር መብታቸዉን በግፍ ለተቀሙት ድምፅ ከሆኑ ጋር እንዳልተባበራቸው ለምክንያትነት አይበቃም እላለሁ። የሰው ሕይወትን እና ሰብአዊ ክብርን የላቀ ዋጋ መስጠት ተገቢ ነው።

የአሰብ ወደብ ጉዳይን ላንሳ
ስለኤርትራና ግብጽ ያነሳኸው የአሰብን ወደብ ከማስመለስ ጋር አያይዘህ ሳይሆን አይቀርም። እነዚህ አገሮች የሚነሱት ከዚያ ጋር ተያይዞ ነውና። የወደቡ ነገር ከተነሣ አይቀር እኔም ጎራ ልበልበት።ኢትዮጵያ ወደብ ያስፈልጋታል። ነገር ግን “ከወደቡ በፊት ከኤርትራ ሕዝብ ጋር ስለመቀራረብ/ አንድ ስለመሆን መነጋገሩ አይሻልም?” እላለሁ። ከኤርትራ ጋር የሚያስማማ ነገር ቢኖር ይመረጣል ባይ ነኝ። በጦርነት ማስመለስ ይሻላል ብለው ካደረጉት ውሣኔው የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ነው። በብሔር በተሸነሸነች ኢትዮጵያ ወደቡ ሲመለስ ከሚገኘው በረከት ይልቅ የሚከተለው ሻሞና ፥ ከተመለሰ በኋላ በእጅ ለማቆየት የሚማገደው የአገሬ ድሀ የሚያሳስበኝ መሆኑን ግን መሸሸግ አይቻለኝም።
    በእርግጥ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በታሪክ አሰብን ያስመለሱ ጀግና” ለመባል ልባቸው ሳይመኝ ስለማይቀር በባሌም ሆነ በቦሌ ይሞክሩት ይሆናል።ከተነሣ አይቀር ይህ ለኢትዮጵያ በመቆርቆሬ በእግረ መንገድ ያቀረብኩት የግል አስተያየቴ እንጂ የፖሊሲ ምክር አይደለም። ሙያዬ አይደለም። ለማንኛውም ክግብጽና ከኤርትራ ጋር አያይዘህ ለኦርቶዶክሳውያኑ ከሚጮሁ ጋር አትጩሁ ላልከው ከላይ መልስ ሰጥቼአለሁ።

ስድስተኛ: “ የአሁኑን ማለትም የብልጽግና መንግሥትን ይጠላሉ” ስለሚለው

መንግሥት የዜጎችን የመኖር ዋስትና ማረጋገጥ ሕጋዊ ግዴታ አለብት።የተፈጸመውን ግድያ እውቅና መስጠትና በደሉን መመርመርም ኃላፊነቱ ነው። እነዚህን መሠረታዊ ሥራዎቹን ሳይሠራ ሲቀር በኃላፊነት መጠየቅ እርሱን መጥላት አይደለም።

የአያያዝካቸውን ጉዳዮችም ላንሳ፡ 
    ከዚህኛው መንግሥት በፊት የነበሩትን ሳይቃወሙ ይህንን መንግሥት ብቻ ተቃውመዋል በማለት በአርሲ ስለ ተገደሉት ኦርቶዶክሳውያን የጮሁትን ለአሁኑ መንግሥት ጥላቻ ስላላቸው ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰሃል።
    ምናልባት ፓለቲካና ኮረንቲ በሩቁ እንል ከነበርነው መኻል ሆነህ ይሆናል እንጂ የቀደሙትንም መንግሥታት የሚቃወሙ ኦርቶዶክሳውያን ነበሩ።የአሁኑን መንግሥት ስለመቃወማቸው በቂ ምክንያት የላቸውም ካልክ ሞግታቸው።የሠራውን መልካም ሥራ ለማጨናገፍ ነው ካልከም ተከራከራቸው። “መገደላችንን ያስቁምልን ብለው በመጮኻቸው መንግሥትን ነክተዋል ብሎ በመቀየም የአርሲ ኦርቶዶክሳውያንን መገደል ያወገዙትን ጸጥ ይበሉ ማለት ግን አፋኝነት ነው።
    ከዚሁ ጋር አያይዘህ (ባለፈው ግዜ በነነዌ ጾም ሞዴልነት መጾማቸውንና ጥቁር መልበሳቸውን መሆኑ ነው መሰለኝ) በመንግሥት ላይ የአመጽ ቅስቀሳ አድርገዋል ብለሃቸዋል። ጾም ማወጃቸውና ጥቁር መልበሳቸውን ግን እንደ እምነታቸው ስለአገሪቷ ንስሐ መግባታቸውና መከራው እንዲቀር መጸለያቸው ነበር እንጂ አንተ እንዳስመሰልከው በመንግሥት ላይ የአመጽ ጥሪ አልነበረም።በንስሐ ሥርዐቱ ላንስማማ እንችላለን። የሥርዐታቸውን ዐላማ ማዛባት ግን አይገባም።
    እርግጥ እንዲያ እንዲሆን የሚፈልጉ የመንግሥት ተቃዋሚዎች አልነበሩም ብዬ መናገር አልችልም።ከእነዚያ ወገኖች አንዳንዶቹ ፣ "ያኔ አመጽ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ቤተክርስቲያን እስከ አሁን ከችግሯ ትላቀቅ ነበር" ብለው በቁጭት የሚናገሩ ሰምቼአለሁ። ከጥቁር መልበሱ ጋር ሌሎች የማወኪያ ዘዴዎችን የዘረዘርካቸውም የሽርደዳ ንግግር እንጂ እውነትነት ያላቸው አይመስሉም።ግራም ነፈሰ ቀኝ "በመንግሥትን ይጠላሉ ሰበብ" ግድያውን ማውገዝ ሊከለከሉ አይገባም፤ ወንጌል አማኞችም ከመተባበር።

ሰባተኛ: “ የኦሮሞ ሕዝብን ስም ያጠለሻሉ” ስለሚለው

ግፍ የፈጸሙት ግለሰቦች ናቸው እንጂ የኦሮሞ ሕዝብ አይደለም።የአርሲ ኦርቶዶክሳውያን ግድያ የኦሮሞ ሕዝብን ስም ከማጠልሸትም ሆነ ከመሸላለም ጋር ግንኙነት የለውም። ከማጠልሸት ጋር ማገናኘቱ ጭፍጨፋው እውቅና እንዳያገኝና ግፍ እንዳይጋለጥ አቅጣጫ ማስቀየስ ሆኖ የሚታይ ነው ።
ስለአቆላለፍከው ጉዳይ ላትት፡ መንግሥትን ከመጠየቅ ይልቅ ግድያዉን መቃወምን ሕዝብን ወደማነካካት አዞርከው። የኢትዮጵያ መሪዎቹ የወጡበትን የከበረውን የኦሮሞ ሕዝብ ስሙን ያጠለሻሉ በማለት አደገኛ ነገር አደረግህ። አርሲን የምታውቀው ከሆነ በዚያ ያሉ ኦርቶዶክሳውያን አማራ ተብለው ስለሚጠሩና (እስከማውቀው ድረስ) ገዳዮቹም አማራን ገደልን ሰለሚሉ ኦሮሞ ተወቃሽ እንደተረገ መስሎህ ይሆናል።ወይም ነገሩን እያወቅህ በተንኮል አገናኝተኸው ይሆናል።
    በእርግጥ ኦርቶዶክሳውያኑ አማራ ተብለው እስከተጠሩ ፣ የሚገደሉትም አማራ ተብለው እስከሆነ ድረስ ከአማራ ተጋዳዮች ጋር እንዲሰለፋ የሚቀሰቅሱ አሉ። እነዚያ ኃይሎች አማራ በሃይማኖት ፥ በመኖሪያ አካባቢና በመሳሰለው ውስጥ የመጋደል አቅሙን ከሚበታትን፣ ኃይሉን በአንድ ላይ በአንድ አማራነት ከረጢት ቢያስቀምጥ ተቃውሞው ውጤታማ ይሆናል ብለው ይወተውታሉ።

መንግሥትም በበኩሉ እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም።አብረውት ከሚሠሩ ጋር በመሆን ይህ እንዳይሆን አስከሬን ቆጠራውን በዘር እየሽነሸነ ያቀርባል ። የሌሎች ሃይማኖት ሰዎችም ተገድለዋል በማለት ጥያቄውን ለማፋዘዝ ይተጋል። "ግድያው ከሃይማኖት ጋር ግንኙነት የለውም ብሎም ነገርን ለማስቀየስ ይሞክራል።ታዲያ በዚህ መኻል ከፍትህ ጠያቂዎቹ ኦርቶዶክሳውያን የኦሮሞን ማሕበረሰብ የሚወቅስ ምን ንግግር ተሰማህ? የኦሮሞ ማኀበረሰብን የሚነካ ነገር የለበትም። ሊነካም አይገባም።

ባይሆን ጉዳዩ የተፈጸመው በኦሮምያ ክልል ስለሆነ የኦሮሚያ ስሙ ጠፋ የሚለው ወቀሳ ያስኬዳል። ለዚህ መድኅኒቱ "በጎ ነገር ሲደረግ ኦሮምያ ክልል፥ "ክፋ ሲደረግ ግን ክልል 4" እያሉ መናገር ይሻል ይሆን? እላለሁ።

ለማንኛውም በአርሲ ኦርቶዶክሳውያን ላይ የደረሰባቸው ግድያ መሠረታዊ የመኖር መብትንና የሰውነት ክብርን የሚዳፈር ጉዳይ ስለሆነ መቃወምን ትቶ በሕዝብ ጉያ መሸሸግ አይገባም።

ስምንተኛ: “ሰርጎ ገብ ኦርቶዶክሳውያኑን እንመነጥራቸዋለን” ስለሚለው:

    ውድ ወንድሜ፡ ይህ ጫፍ ረገጥና አደገኛ ንግግር ነው። ደግነቱ የክርስቶስ ሃሳብ ስለሚገባህ ለመታረም የሚከብድህ አይመስለኝም።

የተደነቅሁበትን ላክል፡ የኦርቶዶክሶች ወንጌል አማኞች ዘንድ ሠርገው መግባታቸውን አላውቅም ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት ከአንተ ነው። እኛ እነሱጋ ሰርገን ገብተናል ሲባል ሰምቼ አውቃእለሁ። እንዳውም በእቅድ ይህንን የሚያደርጉ እንዳሉ ተረድቼአለሁ። ምክንያታቸውም ነፍሳትን ለማዳን ነው። የኦርቶዶካሳውያን እኛጋ ሰርጎ መግባት ግን እንግዳ ነገር ሆኖብኛል፣ አስደንቆኛልም። እውነት ከሆነም “ሰርጎ ገብ ኦርቶዶክሳውያንን እንመነጥራለን" የሚለውን ቃል ምን አመጣው? አስጨናቂ ሆኖ ተሰምቶኛል። ውድ ወንድሜ እንዲህ ዐይነት ሐሳብ ወደየት እንደሚያመራ ይታወቅሃል? ይህ ክፋ ሐሳብ ካንተ ይራቅ። መቼም ከክፋት ለመራቅ የልብ ትህትና እና ቅንነት እንዳለህ ባምን ቂላቂል የምባል አይመስለኝም።

ሐሳቤን እንደዚህ ልቋጨው:-

    ምንም እንኳ የአርሲ ኦርቶክሳውያን መገደል ከሃይማኖትና ከዘር ያለፈ ጉዳይ ቢሆንም እንደ አንድ ማኅበርተኝነታቸው ኦርቶዶክሳውያኑ ግምባር ቀደም አውጋዥ መሆናቸው የሚያስደንቅ አይደለም። አንተም የበጎችህ ፓስተር ወይም እረኛ እንደመሆንህ ልክ (እንደ ራስህ በማየት)፣ የእነርሱን የፊት ለፊት ተቃውሞ ተገቢነት ትግነዘባለህ ብዬ አስባለሁ።ለዘመናት ያፈሩትን ሀብትና ንብረት እንዲበትኑ ተገደው ፥ ለበርካታ ትውልድ ከኖሩበት ሥፍራ የተፈናቀሉ ወገኖች (ብታስተውለው ያንተም ወገኖች ናቸው) ስቃይና ህመም ትረዳለህም ብዬ አምናለሁ።ስለዚህ የአለመተባበር ሃሳብህንና ሌሎቻችንም እንዳንተባበር መፈለግህን እንደምታነሳ ተስፋ አደርጋለሁ። በቪዲዮ እንዳየሁህ አዲስ ነገር ለመማር የሚችል ዕድሜ ላይ ያለህ ስለሚመስል ይኸንን “አታሽቃብጡ ብሎ ነገርህን” ለማረም ይሳንሃል ብዬ አላስብም። ይልቁንም ከኦርቶዶክሳውያኑ ጋር በቅንነት አብሮ ስለመኖርና ሰለመሥራት ብልሃት በማፈላለጉ ታግዛለህ ብዬ እጠብቃለሁ።
    የተወደድህ ወንድሜ ሆይ :- እኔን በተመለከተ ግን “አትግደሉን ፣ ግፍ አትስሩብን” ማለታቸውን አታስተጋቡ /አታሽቃብጡ" ያልከውን ምክር ወይም ተግሣጽ ለመቀበል ከላይ እንዳተትኩት ምክንያቶቹ ሁሉ በቂ ሆነው አላገኘኋቸውምና እምቢታዬን በታላቅ ትህትና እንድገልጽ ፍቀድልኝ።    
    በመጨረሻም የምንሰጠው አስተያየትና የምንይዘው አቋም ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ካላቸው የሞራል መርሖች ጋር የሚስማማ ሊሆን ቢችል እላለሁ። "በሰሜንም በደቡብም ላለው ፣ አድልዎ ሳናደርግ ፣ ዘርና ሃይማኖት ሳንመርጥ ፣ ለሰው በሰውነቱ ብቻ እንጮህለታለን" ብለህ የተናገርከውን ድንቅ ነገር በአርሲ ለተገደሉትና በግፍ ለተፈናቀሉት ኦርቶዶክሳውያንም እንዳፍህ ያድርገው እላለሁ።ለኦርቶዶክሳውያን እንዲሁም ለሌሎች ርኅራኄ እንዲበዛ፣ ፍትሕ እንዳይጓደልባቸው ፣ ተጠያቂነት እንዲገኝላቸው ተስፋ በማድረግ ልሰናበትህ።

ስለአዳመጥከኝ አመሰግንሃለሁ። 

አድማጭ ተመልካቾቼንም በትዕግሥት ስለተከታተላችሁኝ አመሰግናለሁ።

ሁሉ ቀን ማለፊያ ቀን ይሁንላችሁ!

ደህና ሰንብቱልኝ።

ባንቱ ገብረማርያም

ከአዎን ድምፅ

Comments

Popular posts from this blog

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ

የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ (1)  ድንግል ማርያምን ስለማክበር (2) ለጥያቄዎች መልስ (ሀ) ድንግሊትን ‘የወይን ግንድ (ተክል)’ና የ ‘ሕይወት በር’ የሚል ማዕረግ  ለምን እንሰጣታለን? (ለ) ወደ ድንግል ማርያም መጸለይ ትክክል ነው ወይ? (3) የድንግል ማርያም ድንግልና ዘላለማዊነት (4) ለተቃራኒ አስተያየቶች መልስ (ሀ) “የመጀመሪያ ልጇን” የሚለው ሐረግ (ለ) “ሚስትህ” የሚለው ሐረግ (ሐ) “አብረው ከመሆናቸው በፊት ጸንሳ ተገኘች” (መ) “የመጀመሪያ ልጇን እስክትወልድ አላወቃትም” (ሠ)  “ወንድሞቹ” የሚለው ሐረግ   የቅድስት ድንግል ማርያም  ክብሯ (1) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ድንግል እመቤታችንን አያከብሩም፤ ደግሞም እንድታማልድላቸውም (እንድትማልድላቸውም)  አይጠይቋትም።ከእነርሱ ወገኖች አንዳንዶቹ እንዲያውም ጫጩቱ ከተፈለፈለ በኋላ ዋጋ ከሌለው የዶሮ እንቁላል ቅርፊት ጋር እስከሚያመሳስሏት ይደርሳሉ።ይህ የተጋነነ ማቃለል የመጣው ምናልባት ሮሜዋውያን ካቶሊኮች የተጋነነ ማክበር ስለሚያከብሯት ለዛ ተቃርኖ ከማሳየት አዝማሚያ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን አንዱንም የእርሷን በዓል አያከብሩም።  (2) አንዳንዶቹ የፕሮቴስታንት ወገኖች ድንግል ማርያምን “እህታችን” ይሏታል። (3) በተጨማሪ አንዳንዶቹ ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ጌታ ኢየሱስን በድንግልና ከወለደች በኋላ ከዮሴፍ ጋር ጋብቻዋን ፈጽማለች፤ የ‘ኢየሱስ ወንድሞች’  ወይም የ’ጌታ ወንድሞች’ ተብለው የተጠሩ ልጆችን ወልዳለች ይላሉ።  (4) ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ቤተክርስቲያናችን ለድንግል እመቤታችን የሰጠቻቸውን አንዳንድ የማዕረግ ስሞችም ይቃወማሉ።  (5) ድንግልን ያለማክበራቸው አንዱ...

ጥምቀት

  ጥምቀት       (1) የጥምቀት ፍቱንነቱ (2) ማጥመቅ የካህን ተግባር ነው (3) የጥምቀት አስፈላጊነቱ (4) ጥምቀት በመንከር (በመጥለቅ) (5) የልጆች (የሕጻናት) ጥምቀትሳቦች (6) ተቃውሞዎች   ጥምቀት   በእኛ በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንቶች መኻል ጥምቀትን በተመለከተ ያሉት ልዩነቶች የጥምቀትን ትምህርት በአምስት ጉልህ   ፍሬ ነገሮች ሥር አጠቃሎ መነጋገር ይቻላል። (1)     የጥምቀት   አስፈላጊነቱ   ምንድነው? ፍቱንነቶቹስ (ጠቀሜታዎቹስ) ምንድናቸው? ኦርቶዶክስ ጥምቀት ‘ድኅነት’ን፣ ‘መንጻት’ን፣ ‘መጽደቅ’ን፣ የ‘ሕይወት መታደስ’ን እና በ’ክርስቶስ አካል አባል’ መሆን’ን መቀበያ መንገድ ነው ብላ ታምናለች። የፕሮቴስታንት ቤተ እምነቶች እንደሚሉት እነዚህን   መቀበያው “እምነት” ብቻ ነው። በ እምነት ብቻ መሆኑ ትክክል ከሆነ ታዲያ የጥምቀት አስፈላጊነቱ ምኑ ላይ ነው? የክርስትና ምልክት ብቻ መሆኑ ነውን? ወይስ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴ 28:19-20) የሚለውን የጌታን ትዕዛዝ መታዘዝ ብቻ መሆኑ ነው? (2 ) ማነው ማጥመቅ ያለበት? በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጥምቀት የሚከናወነው በካህን ብቻ ነው። ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ግን የሰውን ክህነት ጨርሶ አይቀበሉም። ስለሆነም በእነርሱ ቤተ ክርስቲያን የሚያጠምቀው ካህን ወይም ቄስ ያልሆነ አገልጋይ ነው።   ይህ አገልጋይ የቤተክርስቲያኒቷ ሽማግሌ ወይም ሴት ሽማግሌ (የሴቶችን ሽምግልና ...

Comparative Theology የነገረ መለኮት ንጽጽር (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት)/ በብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሲኖዳ ሳልሳዊ

 የነገረ መለኮት ንጽጽር  (በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት): የወደደ  ሁሉ በነጻ እንዲጠቀምበት ተፖስቷል። ይሁን እንጂ መብቱ በሕግ የተጠበቀ ስለሆነ በየትኛውም መልኩ ለንግድ እንዲውል አልተፈቀድም። ልዩ ልዩ መግቢያ የሚለውን መጀመሪያ ካነበቡ በኋላ የተቀረውን በተመረጠው ቅደም ተከተል ማንበብ ይቻላል። ልዩ ልዩ መግቢያ   ጥምቀት   ትውፊት (ወግና ልማድ)   መካከለኝነት   ጾም የድንግል ማርያም ክብሯና ዘላለማዊ ድንግልናዋ መንፈሳዊ ስጦታዎችና በልሳኖች የመናገር ስጦታ   ሥርዐት ንስሐ